ይሖዋ ባሕርያቱን ሲገልጽ
ወደ አምላክ ቅረብ
ይሖዋ ባሕርያቱን ሲገልጽ
አምላክን ይኸውም ባሕርያቱን እንዲሁም ነገሮችን የሚያከናውንበትን መንገድ እንዴት ትገልጸዋለህ? አምላክን ስለ ማንነቱ መጠየቅና ስለ ባሕርያቱ ሲያብራራልህ ማዳመጥ ብትችል የሚኖረውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ ለመመልከት ሞክር። ነቢዩ ሙሴ እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞት ነበር። የሚያስደስተው ነገር ሙሴ በአምላክ መንፈስ ተመርቶ በወቅቱ የተከሰተውን ነገር ዘግቦልናል።
ሙሴ በሲና ተራራ ላይ ሳለ ይሖዋን “እባክህ፤ ክብርህን አሳየኝ” በማለት ለምኖት ነበር። (ዘፀአት 33:18) በማግሥቱ ይህ ነቢይ የአምላክን ክብር ለቅጽበት የመመልከት መብት አገኘ። * ሙሴ በዚያ ወቅት ስለተመለከተው አስደናቂ ራእይ በዝርዝር አልጻፈም። ሆኖም ከዚያ ይበልጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውን ነገር ይኸውም አምላክ የተናገረውን ሐሳብ በጽሑፍ አስፍሮልናል። እስቲ በዘፀአት 34:6, 7 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ይሖዋ የተናገረውን ሐሳብ እንመርምር።
ይሖዋ ስለ ራሱ የገለጠው የመጀመሪያው ነገር “መሐሪና ቸር የሆነ አምላክ” መሆኑን ነው። (ቁጥር 6 NW) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር እንደገለጹት “መሐሪ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል አምላክ “አባት ለልጆቹ የሚያሳየው ዓይነት ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄ” እንዳለው የሚጠቁም ነው። “ቸር” ተብሎ የተተረጎመው ቃል ደግሞ “አንድ ሰው ችግር ላይ የወደቀ ግለሰብን ለመርዳት ሲል ከልቡ ተነሳስቶ የሚወስደውን እርምጃ” ከሚገልጽ ግስ ጋር ተዛማጅነት አለው። ከዚህ በግልጽ ለመመልከት እንደምንችለው ይሖዋ፣ ወላጆች ልጆቻቸውን በሚይዙበት መንገድ እሱም አገልጋዮቹን እንደሚንከባከባቸው እንድናውቅ ይፈልጋል። ወላጆች ለልጆቻቸው ጥልቅ ፍቅር እንዳላቸውና ልባዊ አሳቢነት እንደሚያሳዩአቸው ሁሉ ይሖዋም አምላኪዎቹን በዚህ መንገድ ይንከባከባቸዋል።—መዝሙር 103:8, 13
በመቀጠልም ይሖዋ “ለቍጣ የዘገየ” መሆኑን ገልጿል። (ቁጥር 6) በምድር ባሉ አገልጋዮቹ ላይ በቀላሉ አይቆጣም። ይልቁንም ከኃጢአት ጎዳናቸው እንዲመለሱ ጊዜ በመስጠት ድክመታቸውን ይታገሣል።—2 ጴጥሮስ 3:9
አምላክ “ፍቅራዊ ደግነቱና እውነቱ እጅግ የበዛ” መሆኑንም ገልጿል። (ቁጥር 6 NW) ፍቅራዊ ደግነት ወይም ታማኝ ፍቅር፣ በይሖዋና በሕዝቦቹ መካከል የጸና እንዲሁም ምንጊዜም የማይለወጥ ትስስር እንዲፈጠር የሚያደርግ ግሩም ባሕርይ ነው። (ዘዳግም 7:9) ከዚህም በላይ ይሖዋ የእውነት ምንጭ ነው። ይሖዋ አያታልልም፤ በሌሎችም አይታለልም። “የእውነት አምላክ” ስለሆነ ስለወደፊቱ ጊዜ የሰጣቸውን ተስፋዎች ጨምሮ የተናገራቸውን ነገሮች ሁሉ እንደሚፈጽም ሙሉ በሙሉ ልንተማመን እንችላለን።—መዝሙር 31:5
ይሖዋ ስለ እሱ እንድናውቀው የሚፈልገው ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሌላው ሐቅ ደግሞ “በደልን፣ መተላለፍንና ኃጢአትን ይቅር የሚል” አምላክ መሆኑን ነው። (ቁጥር 7 NW) ይሖዋ ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኞችን ‘ይቅር ለማለት’ ዝግጁ የሆነ አምላክ ነው። (መዝሙር 86:5) ይህ ሲባል ግን ክፋትን በቸልታ ያልፋል ማለት አይደለም። ይሖዋ ‘በደለኛውን ሳይቀጣ ዝም ብሎ እንደማይተው’ ገልጿል። (ቁጥር 7) ቅዱስና ፍትሐዊ የሆነው አምላክ ሆን ብለው ኃጢአት የሚሠሩ ሰዎችን ሳይቀጣ አያልፍም። ይዋል ይደር እንጂ የተከተሉት የኃጢአት ጎዳና የሚያስከትለውን መዘዝ ማጨዳቸው አይቀርም።
ይሖዋ ስለ ራሱ የገለጸው ነገር እሱን እንድናውቀው በሌላ አባባል ባሕርያቱንና ነገሮችን የሚያከናውንባቸውን መንገዶች እንድንረዳ እንደሚፈልግ በግልጽ ያሳያል። ይህ ዘገባ አስደናቂ ስለሆኑት የአምላክ ባሕርያት የበለጠ ለማወቅ አላነሳሳህም?
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.2 ማንም ሰው አምላክን አይቶ በሕይወት መኖር ስለማይችል ሙሴ ይሖዋን ቃል በቃል አልተመለከተውም። (ዘፀአት 33:20) ከሁኔታዎቹ መረዳት እንደሚቻለው ይሖዋ ለሙሴ በራእይ ክብሩን ያሳየው ሲሆን በመልአክ አማካኝነት አነጋግሮታል።