የብሩክሊን ቤቴል የ100 ዓመት ታሪክ
ከኒው ዮርክ ሲቲ ጋር በተያያዘ 1909 ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ዓመት ነው። የኩዊንስን አውራጃ ከማንሃተን ጋር የሚያገናኘው ኩዊንስቦሮ ድልድይ እንዲሁም ማንሃተንን ከብሩክሊን ጋር የሚያገናኘው ማንሃተን ድልድይ አገልግሎት መስጠት የጀመሩት በዚህ ዓመት ነበር።
በይሖዋ ምሥክሮች ታሪክ ውስጥም 1909 ጉልህ ሥፍራ የሚሰጠው ዓመት ነው። የዎች ታወር ባይብል ኤንድ ትራክት ሶሳይቲ (የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠቀሙበት ሕጋዊ ድርጅት ነው) ፕሬዚዳንት የሆነው ቻርልስ ቴዝ ራስል፣ የአምላክን መንግሥት ምሥራች የመስበኩ ሥራ ሊስፋፋ እንደሚችል አስተውሎ ነበር። (ማቴዎስ 24:14) ወንድም ራስል ይህን ለማድረግ የማኅበሩን ዋና መሥሪያ ቤት ከፒትስበርግ፣ ፔንሲልቬንያ ወደ ብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ ማዛወር አስፈላጊ እንደሆነ ተሰምቶት ነበር። ለዚህም በ1908 ዝግጅት መደረግ የጀመረ ሲሆን በቀጣዩ ዓመት መጀመሪያ አካባቢ ማኅበሩ ወደ ብሩክሊን ተዛወረ።
ማኅበሩን ወደ ብሩክሊን ማዛወር ያስፈለገው ለምንድን ነው?
በወቅቱ የስብከቱን ሥራ በበላይነት ይመሩ የነበሩት ወንድሞች፣ ስብከቶችን በጋዜጣ ማሳተም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለማሰራጨት የሚያስችል ውጤታማ ዘዴ እንደሆነ
ተገንዝበው ነበር። በ1908 ወንድም ራስል የሚጽፋቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርቶች በየሳምንቱ በ11 ጋዜጦች ላይ ይወጡ የነበረ ሲሆን በአጠቃላይ 402,000 ቅጂዎች ይታተሙ ነበር።ይሁን እንጂ ወንድም ራስል እንደሚከተለው በማለት ጽፎ ነበር፦ “ጋዜጦች ሥራቸውን የሚያከናውኑበትን መንገድ የሚያውቁ ወንድሞች . . . እንደገለጹልን በየሳምንቱ የሚወጡት እነዚህ ስብከቶች [በትልቅ ከተማ] ውስጥ ቢዘጋጁ በመላው ዩናይትድ ስቴትስ የመታተም አጋጣሚ ይኖራቸዋል፤ በዚህ መንገድ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጋዜጦች እነዚህን ስብከቶች በቋሚነት ሊያትሙ ይችላሉ።” በዚህም ምክንያት የስብከቱን ሥራ ለማስፋፋት አመቺ የሆነ ቦታ መፈለግ ተጀመረ።
ብሩክሊን የተመረጠው ለምን ነበር? ወንድም ራስል እንዲህ ብሏል፦ “ሁላችንም በዚህ ጉዳይ ላይ መለኮታዊ መመሪያ ለማግኘት ከጸለይን በኋላ ብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ ለመከሩ ሥራ አመቺ ቦታ ነው ወደሚል ድምዳሜ ደርሰናል። ብሩክሊን . . . ብዙ ነዋሪዎች ያሉት ከመሆኑም ሌላ ‘የአብያተ ክርስቲያናት ከተማ’ በመባል የሚታወቅ መሆኑ እዚህ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ምክንያት ሆኖናል።” ከዚያ በኋላ የተገኙት ውጤቶች እንደሚጠቁሙት ይህ ውሳኔ ጥበብ የተንጸባረቀበት ነበር። በአጭር ጊዜ ውስጥ 2,000 ጋዜጦች የወንድም ራስልን ስብከት ይዘው መውጣት ጀመሩ።
ኒው ዮርክ ጥሩ ምርጫ እንዲሆን ያደረገው ሌላም ምክንያት አለ። በ1909 በታላቋ ብሪታንያ፣ በጀርመንና በአውስትራሊያ ብዙም ሳይቆይ ደግሞ በሌሎች ቦታዎች ቅርንጫፍ ቢሮዎች ተከፈቱ። በመሆኑም ዋናው መሥሪያ ቤት፣ በርካታ መንገዶችና የባቡር መስመሮች እንዲሁም የባሕር ወደብ ባለው ከተማ ውስጥ መሆኑ ምክንያታዊ ነበር።
ቤቴል የተባለው ለምንድን ነው?
በ1880ዎቹ ዓመታት የተቋቋመው የዎች ታወር ባይብል ኤንድ ትራክት ሶሳይቲ ዋና መሥሪያ ቤት የመጀመሪያ ቢሮ የሚገኘው በአሌጌኒ (አሁን የፒትስፐርግ ክፍል ናት)፣ ፔንሲልቬንያ ነበር። በዚያን ወቅት ማኅበሩ የነበረበት ሕንፃ የመጽሐፍ ቅዱስ ቤት ተብሎ ይጠራ ነበር። በ1896 በዚህ ሕንፃ ውስጥ የሚያገለግሉት ወንድሞች 12 ነበሩ።
* ቤቴል የተባለው ለምንድን ነው? ዎች ታወር ሶሳይቲ የገዛው በ13-17 ሂክስ ጎዳና ላይ የሚገኘው ሕንፃ፣ ሄንሪ ዋርድ ቢቸር የተባለው ታዋቂ ቄስ ንብረት ሲሆን ሕንፃውም የቢቸር ቤቴል ተብሎ ይጠራ ነበር። ማኅበሩ በ124 ኮሎምቢያ ሃይትስ የሚገኘውን የቢቸርን የቀድሞ መኖሪያ ቤትም ገዝቶ ነበር። የመጋቢት 1, 1909 መጠበቂያ ግንብ እንዲህ ብሏል፦ “የቀድሞውን የቢቸር ቤቴል፣ ከዚያም በአጋጣሚ ደግሞ የቀድሞ መኖሪያ ቤቱን መግዛታችን በጣም የሚያስገርም ነው። . . . አዲሱ ቤት ‘ቤቴል’ ተብሎ ይጠራል፤ አዲሱ ቢሮና አዳራሹ ደግሞ ‘የብሩክሊን የመገናኛ ድንኳን’ ይባላሉ። ‘የመጽሐፍ ቅዱስ ቤት’ የሚለው መጠሪያ በእነዚህ ስሞች ይተካል።”
በ1909 ማኅበሩ ወደ ብሩክሊን ሲዛወር ለወንድሞች መኖሪያ የተደረገው አዲሱ ቤት ቤቴል ተባለ።በዛሬው ጊዜ በብሩክሊን፣ በዎልኪልና በፓተርሰን፣ ኒው ዮርክ ውስጥ የሚገኙት የፈቃደኛ ሠራተኞቹ መኖሪያ ሕንፃዎችም ሆኑ ማተሚያዎቹንና ቢሮዎቹን የያዙት ሰፋፊ ሕንፃዎች ቤቴል ተብለው ይጠራሉ። በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ በ113 አገሮች ውስጥ የቤቴል ቤቶች ይገኛሉ። የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በማሰራጨቱ ሥራ የሚካፈሉ ከ19,000 የሚበልጡ አገልጋዮች በእነዚህ የቤቴል ቤቶች ውስጥ ይኖራሉ።
ለጎብኚዎች ክፍት ሆነ
እነዚህ ሕንፃዎች ጥር 31, 1909 ለይሖዋ አገልግሎት ተወሰኑ። ሰኞ መስከረም 6, 1909 ቤቴል ለጎብኚዎች ክፍት ሆነ። በዚያን ዕለት፣ በወቅቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው ይጠሩ የነበሩት በመቶዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ሕንፃውን ጎብኝተዋል። አብዛኞቹ ጎብኚዎች ወደ ቤቴል የመጡት ከኒው ዮርክ ሲቲ በስተ ሰሜን 320 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሳራቶጋ ስፕሪንግስ የተደረገው ትልቅ ስብሰባ እንዳበቃ ነበር። ወንድም ቻርልስ ቴዝ ራስል ጎብኚዎቹን እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ተቀብሏቸዋል። *
በአሁኑ ጊዜም ቤቴል ለጎብኚዎች ክፍት ነው። በየዓመቱ ከ40,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች በብሩክሊን የሚገኙትን ሕንፃዎች ይጎበኛሉ። የብሩክሊን ቤቴል ከይሖዋ መንግሥት ጋር የተያያዙ ሥራዎችን በማከናወን ረገድ ጉልህ ሚና የሚጫወት ሲሆን ይህም በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች በረከት አምጥቷል።