እምነት ምንድን ነው?
እምነት ምንድን ነው?
ለእምነት የምትሰጠው ፍቺ ምንድን ነው? አንዳንዶች እምነት ሲባል አንድን ነገር በጭፍን መቀበል ማለት እንደሆነ ይናገራሉ። መጣጥፍ አዘጋጅና ጋዜጠኛ የሆኑት አሜሪካዊው ሄንሪ ሉዊስ ሜንከን ደግሞ እምነት “አንድ ነገር እንደሚሆን ለማመን የሚያስችል ተጨባጭ ምክንያት ሳይኖር፣ ይሆናል ብሎ መጠበቅ” እንደሆነ ገልጸዋል።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ እምነት ‘አንድን ነገር በጭፍን ወይም ተጨባጭ ምክንያት ሳይኖር መቀበል’ ማለት እንደሆነ አያስተምርም። ከዚህ ይልቅ እንዲህ ይላል፦ “እምነት ተስፋ የተደረጉ ነገሮችን በእርግጠኝነት መጠበቅ ማለት ሲሆን እውነተኛዎቹ ነገሮች ባይታዩም እንኳ መኖራቸውን የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ ነው።”—ዕብራውያን 11:1
ሰዎች ስለ እምነት ያላቸው አመለካከት የተለያየ ስለሆነ ለሚከተሉት ጥያቄዎች የተሰጡትን መልሶች መመርመራችን ተገቢ ነው፦
• መጽሐፍ ቅዱስ ለእምነት የሚሰጠው ፍቺ ብዙዎች ስለ እምነት ከሚናገሩት ነገር የሚለየው እንዴት ነው?
• በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸውን ዓይነት እምነት ማዳበራችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
• ጠንካራ እምነት ማዳበር የምትችለው እንዴት ነው?
የንብረት ባለቤትነት ማረጋገጫና ጠንካራ ማስረጃ
የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የዕብራውያን መጽሐፍ በተጻፈበት ወቅት “በእርግጠኝነት መጠበቅ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል በሰፊው ይሠራበት ነበር። ይህ ቃል በአብዛኛው ይሠራበት የነበረው በንግድ ሰነዶች ላይ ሲሆን ቃሉ አንድ ሰው አንድን ነገር ወደፊት በእጁ እንደሚያስገባ የሚያረጋግጥ ዋስትና ይሰጣል። በመሆኑም አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ ዕብራውያን 11:1 “እምነት ተስፋ የተደረጉ ነገሮች እንደሚገኙ ዋስትና የሚሰጥ የንብረት ባለቤትነት ማረጋገጫ ነው” ተብሎ ሊተረጎም እንደሚችል ሐሳብ ሰጥቷል።
ጥሩ ስም ካለው አንድ ኩባንያ ዕቃ ገዝተሃል እንበል፤ ኩባንያው ዕቃውን ቤትህ ድረስ እንዲያመጣልህ እየተጠባበቅህ ነው፤ እንዲህ ባለው ወቅት ከላይ የተጠቀሰውን ዓይነት እምነት እንዳለህ በተግባር እያሳየህ ነው። የሽያጭ ደረሰኝ በእጅህ መኖሩ ዕቃውን በሸጠልህ ኩባንያ ላይ እምነት እንድትጥል አድርጎሃል። በሌላ አነጋገር ደረሰኙ፣ የገዛኸው ዕቃ እጅህ እንደሚገባ ዋስትና የሚሰጥ የንብረት ባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነድ ሆኖልሃል። ደረሰኙ ቢጠፋብህ ወይም ብትጥለው የንብረቱ ባለቤት አንተ መሆንህን የሚያረጋግጠውን ማስረጃ ጣልክ ማለት ነው። በተመሳሳይም፣ አምላክ ቃል የገባቸው ነገሮች እንደሚፈጸሙ እምነት ያላቸው ሰዎች ተስፋ የሚያደርጓቸውን ነገሮች እንደሚያገኙ ዋስትና አላቸው። በሌላ በኩል ደግሞ እምነት የሌላቸው ወይም እምነታቸው የጠፋባቸው ሰዎች አምላክ ቃል የገባቸውን ነገሮች እናገኛለን ብለው መጠበቅ አይችሉም።—ያዕቆብ 1:5-8
በዕብራውያን 11:1 ላይ “ተጨባጭ ማስረጃ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል እውነት መስሎ ከሚታየው ነገር ተቃራኒ የሆነ ማስረጃ የማቅረብን ሐሳብ ያስተላልፋል። ለምሳሌ ያህል፣ ፀሐይ በምሥራቅ ወጥታ በምዕራብ ስትገባ ስለምንመለከት ምድርን የምትዞር ትመስላለች። ይሁን እንጂ ከሥነ ፈለክ ተመራማሪዎችና ከሒሳብ ሊቃውንት የተገኙ ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት ምድር ፀሐይን ትዞራለች እንጂ ፀሐይ ምድርን አትዞርም። ይህንን ማስረጃ አንዴ ካወቅክና እውነት መሆኑን ከተቀበልክ በዓይንህ ከምታየው ነገር ተቃራኒ ቢሆንም እንኳ ምድር ፀሐይን እንደምትዞር እምነት ይኖርሃል። እንዲህ ያለው እምነት ጭፍን አይደለም። እንዲያውም ይህ እምነት እውነት መስሎ የሚታየውን ሳይሆን የአንድን ነገር ትክክለኛ ምንነት የመመልከት ችሎታ እንዲኖርህ ያደርግሃል።
ጠንካራ እምነት ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ በተጨባጭ ማስረጃ ላይ የተመሠረተ ጠንካራ እምነት እንዲኖረን ያበረታታል። እርግጥ ነው፣ እንዲህ ያለው እምነት ቀደም ሲል እናምንባቸው በነበሩት ነገሮች ላይ ለውጥ እንድናደርግ ይጠይቅብን ይሆናል። ያም ሆኖ ጠንካራ እምነት በጣም አስፈላጊ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ያለ እምነት አምላክን በሚገባ ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ምክንያቱም ወደ አምላክ የሚቀርብ ሰው እሱ መኖሩንና ከልብ ለሚፈልጉትም ወሮታ ከፋይ መሆኑን ማመን ይኖርበታል።”—ዕብራውያን 11:6
ጠንካራ እምነት ለማዳበር እንቅፋት የሚሆኑ በርካታ ነገሮች አሉ። ይሁንና ቀጥሎ በሚገኙት ርዕሶች ውስጥ የተጠቀሱትን አራት ነጥቦች ተግባራዊ ካደረግህ ጠንካራ እምነት መገንባት ትችላለህ።