ይህን ያውቁ ኖሯል?
ይህን ያውቁ ኖሯል?
እስራኤላውያን የኮከብ ቆጠራን ልማድ ሲከተሉ አምላክ ምን ተሰምቶት ነበር?
አንድ መዝገበ ቃላት፣ ኮከብ ቆጠራ የሚለው ቃል “የፕላኔቶች፣ የፀሐይ፣ የጨረቃና የከዋክብት እንቅስቃሴ በሰው ልጆች ሕይወት ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር በማመን በእነዚህ ግዑዝ አካላት ላይ የሚደረግ ጥናትን” እንደሚያመለክት ገልጿል። በየዓመቱ ምድር ፀሐይን ስትዞራት ከምድር ሆኖ ለሚመለከት ሰው ኅብረ ከዋክብትም አቀማመጣቸው የሚቀያየር ይመስላል። ከጥንት ዘመን ጀምሮ የሰው ልጆች በኅብረ ከዋክብት አቀማመጥ ላይ የሚታየውን ለውጥ ይከታተሉ የነበረ ሲሆን ይህም ትልቅ ትርጉም እንዳለው ይሰማቸው ነበር።
የኮከብ ቆጠራ ልማድ የመጣው ከዋክብትንና ኅብረ ከዋክብትን ያመልኩ ከነበሩት ከጥንቶቹ ባቢሎናውያን ሳይሆን አይቀርም። እስራኤላውያን ከእውነተኛው አምልኮ በራቁበት ወቅት እንዲህ ያለውን አምልኮ መከተል ጀመሩ። በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ዘመን ኮከብ ቆጠራ በእስራኤል ተስፋፍቶ ነበር። አምላክ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለው አመለካከት ግልጽ ነው። ከበርካታ መቶ ዓመታት በፊት የተጻፈው የሙሴ ሕግ፣ ከዋክብትን ማምለክ የሞት ቅጣት እንደሚያስከትል ይገልጽ ነበር።—ዘዳግም 17:2-5
ንጉሥ ኢዮስያስ፣ አይሁዳውያን ይከተሉት ከነበረው አምልኮ ጋር በተያያዘ ካካሄዳቸው ለውጦች አንዱ “ለፀሓይና ለጨረቃ፣ ለስብስብ ከዋክብትና ለመላው የሰማይ ከዋክብት ሰራዊት” ይቀርብ የነበረው መሥዋዕት እንዲቀር ማድረጉ ነው። ንጉሡ ይህንን ያደረገው ይሖዋን ‘ለመከተልና ትእዛዞቹን ለመጠበቅ’ ስለፈለገ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (2 ነገሥት 23:3-5) ይህ በዛሬው ጊዜም አምላክን “በመንፈስና በእውነት” ለማምለክ ለሚፈልጉ ሁሉ ጥሩ ምሳሌ ነው።—ዮሐንስ 4:24
በሐዋርያት ሥራ 28:11 ላይ የተጠቀሱት “የዙስ ልጆች” እነማን ናቸው?
የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ከማልታ ተነስቶ ወደ ፑቲዮሉስ የተጓዘበት መርከብ “የዙስ ልጆች” ዓርማ እንደነበረው ይገልጻል። (የሐዋርያት ሥራ 28:11) በጥንት ዘመን የነበሩ መርከበኞችና ተጓዦች እንዲህ ዓይነት ዓርማ መጠቀማቸው የተለመደ ነበር።
በግሪካውያንና በሮማውያን አፈ ታሪክ መሠረት ዙስ (ጁፒተርም ይባላል) እና ሊዳ የተባሉት አማልክት ካስተር እና ፖለክስ የተባሉ መንታ ወንዶች ልጆች ነበሯቸው። እነዚህ “የዙስ ልጆች” ብዙ ችሎታዎች እንደነበሯቸው ይነገር ነበር፤ ለምሳሌ ነፋስንና ማዕበልን መቆጣጠር የሚችሉ የተዋጣላቸው መርከበኞች እንደሆኑ ይታመን ነበር። በዚህም ምክንያት ሰዎች፣ “የዙስ ልጆች” ለመርከበኞች ጥበቃ የሚያደርጉ አማልክት እንደሆኑ በማሰብ ያመልኳቸው ነበር። ተጓዦች በባሕር ላይ ማዕበል በሚነሳበት ጊዜ ለእነዚህ አማልክት መሥዋዕት ያቀርቡ እንዲሁም ጥበቃ እንዲያደርጉላቸው ይማጸኑ ነበር። እነዚህ መንታ አማልክት ራሳቸውንም ሆነ የማዳን ኃይላቸውን የሚገልጡት በቅዱስ ኤልሞ እሳት መልክ እንደሆነ በስፋት ይታመናል፤ ይህ እሳት መብረቅ የቀላቀለ ዝናብ በሚኖርበት ጊዜ የመርከቡ ሸራ በተወጠረበት ምሰሶ ላይ የሚታየው የብርሃን ነጸብራቅ ነው።
በግሪኮችና በሮማውያን ዘንድ የካስተር እና የፖለክስ አምልኮ በጣም የተለመደ ነበር፤ አንድ ጥንታዊ ጽሑፍ በሳይሪን፣ ሰሜን አፍሪካ አካባቢ እንዲህ ዓይነት አምልኮ ይካሄድ እንደነበር ጠቅሷል። በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ የተጠቀሰው መርከብ ደግሞ ከእስክንድርያ፣ ግብፅ አቅራቢያ የመጣ ነበር።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ንጉሥ ናዚማሩታሽ በኅብረ ከዋክብት ተከብቦ የሚያሳይ የባቢሎናውያን ሐውልት
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
‘የዙስ ልጆችን’ የሚያሳይ ዲናር፣ 114-113 ከክርስቶስ ልደት በፊት
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ሐውልቱ፦ Réunion des Musées Nationaux/Art Resource, NY; ሳንቲም፦ Courtesy Classical Numismatic Group, Inc./cngcoins.com