በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሰው በምግብ ብቻ አይኖርም—ከናዚ የእስረኞች ካምፕ በሕይወት ተረፍኩ

ሰው በምግብ ብቻ አይኖርም—ከናዚ የእስረኞች ካምፕ በሕይወት ተረፍኩ

ሰው በምግብ ብቻ አይኖርም—ከናዚ የእስረኞች ካምፕ በሕይወት ተረፍኩ

ዦዜፍ ሂዚገ እንደተናገረው

አንድ አብሮኝ የታሰረን ሰው “ምን እያነበብክ ነው?” ስል ጠየቅኩት። እሱም “መጽሐፍ ቅዱስ” በማለት መለሰልኝ፤ አክሎም “የአንድ ሳምንት የዳቦ ራሽንህን ከሰጠኸኝ እኔም መጽሐፉን እሰጥሃለሁ” አለኝ።

የተወለድኩት በወቅቱ የጀርመን ግዛት በነበረችው በሞዜል ሲሆን ጊዜው መጋቢት 1, 1914 ነበር። የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት በ1918 ካበቃ በኋላ ሞዜል እንደገና ለፈረንሳይ ተመለሰች። በ1940 ጀርመን እንደገና ከተማዋን በቁጥጥር ሥር አዋለቻት። ከዚያም ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በ1945 ሲያበቃ ሞዜል መልሳ የፈረንሳይ ግዛት ሆነች። በዚህ ጊዜ ሁሉ ዜግነቴ ይቀያየር ነበር፤ በመሆኑም ፈረንሳይኛም ሆነ ጀርመንኛ መናገር ቻልኩ።

ወላጆቼ አጥባቂ ካቶሊኮች ነበሩ። ሁልጊዜ ማታ ማታ ከመተኛታችን በፊት ቤተሰባችን አንድ ላይ ተንበርክኮ የመጸለይ ልማድ ነበረው። እሁድ እሁድና በበዓል ቀናት ደግሞ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንሄድ ነበር። ሃይማኖቴን በቁም ነገር እይዝ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ካቶሊኮች በሚያደርጉት በቡድን የሚካሄድ የጥናት ፕሮግራም ላይ እሳተፍ ነበር።

በሥራችን በንቃት መሳተፍ ጀመርኩ

በ1935 ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤታችን መጥተው ወላጆቼን አነጋገሯቸው። የተወያዩበት ጉዳይ ሃይማኖት በአንደኛው የዓለም ጦርነት ውስጥ ጣልቃ መግባቱን በተመለከተ ነበር። ከዚያ ወዲህ መጽሐፍ ቅዱስን ለማወቅ የነበረኝ ፍላጎት እየጨመረ ሄደ። ከዚህም የተነሳ በ1936 የቤተ ክርስቲያኑን ቄስ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሰጠኝ ጠየቅኩት። ቄሱም፣ መጽሐፍ ቅዱስን አንብቦ ለመረዳት ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት መከታተል እንደሚኖርብኝ ነገረኝ። ይሁንና የሰጠኝ መልስ የራሴ የሆነ መጽሐፍ ቅዱስ የማግኘትና መጽሐፉን የማንበብ ፍላጎቴን አሳደገው።

ጥር 1937፣ የሥራ ባልደረባዬ የሆነ አልቢን ረለቪትስ የተባለ የይሖዋ ምሥክር መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚያስተምራቸው ነገሮች ይነግረኝ ጀመር። “መጽሐፍ ቅዱስ አለህ እንዴ?” ብዬ ጠየቅኩት። እሱም መጽሐፍ ቅዱስ እንዳለው ነገረኝ። ከዚያም ብዙም ሳይቆይ በጀርመንኛ ከተዘጋጀው የኤልበርፌልደር የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ላይ ይሖዋ የሚለውን የአምላክ ስም አሳየኝ፤ መጽሐፉንም ሰጠኝ። መጽሐፉን በጉጉት ማንበብ ተያያዝኩት፤ እንዲሁም በአቅራቢያችን ባለችው በትዮንቪል ከተማ ከሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ጋር መሰብሰብ ጀመርኩ።

ነሐሴ 1937 ላይ ከአልቢን ጋር ሆኜ በፓሪስ በተደረገ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ተገኘሁ። ፓሪስ ውስጥ ከቤት ወደ ቤት መስበክ ጀመርኩ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ የተጠመቅኩ ሲሆን በ1939 መጀመሪያ ላይ ደግሞ የሙሉ ጊዜ የምሥራቹ ሰባኪ ማለትም አቅኚ ሆንኩ። እንዳገለግል የተመደብኩት ሜትዝ በምትባል ከተማ ነበር። ከዚያም ሐምሌ ወር ላይ ፓሪስ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ እንዳገለግል ተጠራሁ።

በጦርነቱ ወቅት የደረሰብኝ መከራ

ነሐሴ 1939 ላይ በፈረንሳይ የጦር ሠራዊት ውስጥ ወታደራዊ አገልግሎት እንድሰጥ ስለተጠራሁ በቅርንጫፍ ቢሮው ያገለገልኩት በጣም ለአጭር ጊዜ ነበር። ከሕሊናዬ የተነሳ በጦርነት ለመካፈል ፈቃደኛ ሳልሆን በመቅረቴ እስራት ተፈረደብኝ። በቀጣዩ ዓመት በግንቦት ወር እስር ቤት እያለሁ ጀርመን፣ በፈረንሳይ ላይ ድንገተኛ ጥቃት ሰነዘረች። ሰኔ ላይ ፈረንሳይ ድል ተደረገች፤ በዚህ ጊዜ እንደገና የጀርመን ዜጋ ሆንኩ። ሐምሌ 1940 ከእስር ቤት ከወጣሁ በኋላ ተመልሼ ከወላጆቼ ጋር መኖር ጀመርኩ።

የምንኖረው በናዚ አገዛዝ ሥር ስለሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት የምንሰበሰበው በድብቅ ነበር። መጠበቂያ ግንብ እናገኝ የነበረው ማሪዝ አናዚያክ በምትባል ደፋር ክርስቲያን አማካኝነት ሲሆን የአንድ የይሖዋ ምሥክር ንብረት በሆነ ዳቦ ቤት ተገናኝተን መጽሔቱን እቀበላት ነበር። እስከ 1941 ባለው ጊዜ በጀርመን የነበሩ የይሖዋ ምሥክሮች ያጋጥሟቸው ከነበሩት ችግሮች ማምለጥ ችዬ ነበር።

ከዚያም አንድ ቀን ጌስታፖዎች እኔ ወደምኖርበት ቤት መጡ። አዛዡ የይሖዋ ምሥክሮች የታገዱ መሆናቸውን በግልጽ ከነገረኝ በኋላ የእምነቱ አባል ሆኜ የመቀጠል ሐሳብ እንዳለኝ ጠየቀኝ። “አዎ” ብዬ ስመልስለት አብሬው እንድሄድ ነገረኝ። በዚህ ጊዜ እናቴ ስሜቷን መቆጣጠር አቅቷት ራሷን ስታ ወደቀች። አዛዡ ይህን ሲመለከት እዚያው እንድቀርና እናቴን እንድንከባከብ ነገረኝ።

በምሠራበት ፋብሪካ ውስጥ ለሥራ አስኪያጁ “ሃይል ሂትለር!” (“ሂትለር አዳኝ ነው!”) በማለት ሰላምታ አልሰጠውም ነበር። በተጨማሪም የናዚ ፓርቲ አባል ለመሆን ፈቃደኛ ሳልሆን ቀረሁ። ስለሆነም በቀጣዩ ቀን ጌስታፖዎች አሰሩኝ። በምርመራ ወቅት የሌሎች የይሖዋ ምሥክሮችን ስም ለመንገር እንቢ አልኩ። መርማሪው በሽጉጡ ሰደፍ ጭንቅላቴን በኃይል መታኝ፤ እኔም ራሴን ስቼ ወደቅኩ። መስከረም 11, 1942 በሜትዝ የሚገኘው ዞንዴርገሪኸት በሚል ስያሜ የሚጠራው ልዩ ፍርድ ቤት “የይሖዋ ምሥክሮችንና የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን ፕሮፖጋንዳ ሲያራምድ ተገኝቷል” በሚል ክስ ሦስት ዓመት እስራት ፈረደብኝ።

ከሁለት ሳምንት በኋላ በሜትዝ ከሚገኘው እስር ቤት ተነስተን ረጅም ጉዞ በማድረግ ጽፋይብሩከን ወደሚገኝ የጉልበት ሥራ የሚሠራበት ካምፕ ደረስን። በዚያም የባቡር ሐዲድ የሚጠግን ቡድን ውስጥ ተመድቤ መሥራት ጀመርኩ። ሥራችን በጣም ከባድ የሆኑ ሐዲዶችን መቀየርና ብሎኖቹን ማጥበቅ ከዚያም በሐዲዶቹ መሃል ኮረት መልሶ ማፍሰስ ነበር። የሚሰጠን ምግብ ቁርስ ላይ አንድ ኩባያ ቡናና 75 ግራም የሚመዝን ዳቦ ሲሆን ምሳና እራት ላይ ደግሞ አንድ ሳህን ሾርባ ይሰጠን ነበር። ከዚያም በአቅራቢያው በምትገኝ ከተማ ውስጥ ወዳለ እስር ቤት ተዛወርኩ፤ በዚያም በጫማ ማደሻ ክፍል ውስጥ መሥራት ጀመርኩ። ከበርካታ ወራት በኋላ ወደ ጽፋይብሩከን ተመልሼ የተላክሁ ሲሆን በዚህ ጊዜ ደግሞ በእርሻ ላይ እንድሠራ ተመደብኩ።

የምኖረው በምግብ ብቻ አልነበረም

በእስር ቤት ከእኔ ጋር በአንድ ክፍል ውስጥ የነበረው ከኔዘርላንድስ የመጣ አንድ ወጣት ነበር። የእሱን ቋንቋ በተወሰነ መጠን መናገር በመቻሌ ስለማምንባቸው ነገሮች ልነግረው ችዬ ነበር። ይህ ወጣት ጥሩ መንፈሳዊ እድገት እያደረገ መጣ፤ እንዲያውም ወንዝ ውስጥ እንዳጠምቀው ጠየቀኝ። ከውኃው ሲወጣ እቅፍ አድርጎ “ዦዜፍ፣ አሁን ወንድምህ ሆኛለሁ!” አለኝ። በሐዲድ ጥገና ላይ እንድሠራ እንደገና በተላክሁበት ጊዜ ከዚህ ወጣት ጋር ተለያየን።

በዚህ ጊዜ በአንድ ክፍል ውስጥ አብሮኝ የታሠረው ሰው ጀርመናዊ ነበር። አንድ ምሽት ላይ አንዲት ትንሽ መጽሐፍ ማንበብ ጀመረ፤ የያዘው መጽሐፍ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ነበር! መጽሐፍ ቅዱሱን በአንድ ሳምንት የዳቦ ራሽን እንድቀይረው የጠየቀኝ በዚህ ጊዜ ነበር። እኔም በሐሳቡ ተስማማሁ። የአንድ ሳምንት የዳቦ ራሽን መሥዋዕት ማድረግ ከባድ ቢሆንም ፈጽሞ አልቆጨኝም። ኢየሱስ “ሰው ከይሖዋ አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በምግብ ብቻ ሊኖር አይችልም” ሲል የተናገረው ሐሳብ ምን ትርጉም እንዳለው ይበልጥ ግልጽ እየሆነልኝ መጣ።—ማቴዎስ 4:4

መጽሐፍ ቅዱስ ያገኘሁ ቢሆንም እንኳ እንዳይወሰድብኝ ማድረግ ፈታኝ ነበር። ከሌሎች እስረኞች በተለየ ሁኔታ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ እንዲይዙ አይፈቀድላቸውም። በመሆኑም የማነበው ማታ ማታ በብርድ ልብስ ተሸፍኜ በድብቅ ነበር። ቀን ቀን ደግሞ በሄድኩበት ሁሉ ከሸሚዜ ሥር ደብቄው እዞራለሁ። ፍተሻ ሊኖር ስለሚችል መጽሐፍ ቅዱሱን ክፍሌ ውስጥ ትቼው አልወጣም ነበር።

አንድ ቀን ለስም ጥሪ ተሰብስበን ሳለ መጽሐፍ ቅዱሴን ረስቼ እንደወጣሁ ትዝ አለኝ። በዚያን ቀን ምሽት ወደ ክፍሌ በፍጥነት ተመለስኩ፤ ሆኖም መጽሐፉ ተወስዶ ጠበቀኝ። ወደ አምላክ ከጸለይኩ በኋላ ጠባቂውን ለማነጋገር ሄድኩ። አንድ ሰው መጽሐፍ እንደወሰደብኝና መጽሐፉን ፍለጋ እንደመጣሁ ነገርኩት። ጠባቂው ብዙም ትኩረት ሰጥቶ ስላልተከታተለኝ መጽሐፍ ቅዱሴን መልሼ ማግኘት ቻልኩ። በዚህ ጊዜ ይሖዋን ከልብ አመሰገንኩት!

ገላዬን ልታጠብ በሄድኩበት በአንድ ወቅት ደግሞ የቆሸሹ ልብሶቼን እያወላለቅኩ ሳለ መጽሐፍ ቅዱሴን ቀስ ብዬ መሬት ላይ ጣልኩት። ጠባቂው ወደ ሌላ ቦታ ማየት ሲጀምር መጽሐፉን ወደ መታጠቢያው ቦታ በእግሬ ገፋሁት። ታጥቤ እስክጨርስ ድረስ አንድ ጥግ ላይ ደበቅኩት። ከመታጠቢያው ስወጣ ያንኑ ዘዴ በድጋሚ ተጠቀምኩና መጽሐፍ ቅዱሱን ንጹሕ ልብሶች ወደተደረደሩበት ቦታ ገፋሁት።

በእስር ቤት ያጋጠሙኝ አስደሳችና አሳዛኝ ሁኔታዎች

በ1943 አንድ ቀን ጠዋት እስረኞች ግቢው ውስጥ ተሰልፈው ሳለ አልቢንን አየሁት! እሱም ተይዞ ታስሮ ነበር። እንዳስታወሰኝ በሚያሳይ ሁኔታ ወደ እኔ እየተመለከተ ወንድማማች እንደሆንን ለመግለጽ እጁን በደረቱ ላይ አደረገ። ከዚያም ደብዳቤ እንደሚጽፍልኝ በምልክት ነገረኝ። በሚቀጥለው ቀን በአጠገቤ ሲያልፍ አንዲት ትንሽ ወረቀት ጣል አደረገ። ይሁንና ጠባቂው ወረቀቱን አየው፤ በመሆኑም ለሁለት ሳምንት ሁለታችንም ለየብቻ ታሰርን። በዚህ ወቅት እንድንበላ የሚሰጠን የሻገተ ዳቦ ከውኃ ጋር ሲሆን የምንተኛው ደግሞ ያለ ብርድ ልብስ ጣውላ ላይ ነበር።

ከዚያ በኋላ በዚክቡርክ ወደሚገኝ እስር ቤት ተዛውሬ በብረታ ብረት መበየጃ ክፍል ውስጥ እንድሠራ ተመደብኩ። ሥራው በጣም አድካሚ ነበር፤ የሚሰጠን ምግብ ደግሞ በቂ አልነበረም። ማታ ማታ እንደ ኬክና ፍራፍሬ ያሉ ጣፋጭ ምግቦች በዓይኔ ይዞራሉ፤ ጠዋት ከእንቅልፌ የምነሳው ደግሞ ጉሮሮዬ ደርቆና ሆዴ እየጮኸ ነበር። በወቅቱ በጣም ከስቼ ነበር። ሆኖም በእያንዳንዱ ቀን ትንሿን መጽሐፍ ቅዱሴን ማንበቤ በሕይወት ለመቀጠል የሚያስችል ምክንያት እንዳገኝ አድርጎኛል።

በመጨረሻ ነፃ ወጣሁ!

ሚያዝያ 1945 አንድ ቀን ጠዋት ፈጽሞ ባልታሰበ ሁኔታ ጠባቂዎቹ በሮቹን ክፍት ጥለው ከእስር ቤቱ ሸሽተው ሄዱ። በዚህ ጊዜ ነፃ ወጣሁ! ሆኖም እስካገግም ድረስ ለተወሰነ ጊዜ ሆስፒታል መቆየት ነበረብኝ። ግንቦት ወር መጨረሻ ላይ ወላጆቼ ቤት ደረስኩ። እስካሁን በሕይወት ይቆያል ብለው አልጠበቁም ነበር። እናቴ ስታየኝ ከመደሰቷ የተነሳ አለቀሰች። የሚያሳዝነው ወላጆቼ ከዚህ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ሞቱ።

በትዮንቪል ወደሚገኘው ድሮ እሰበሰብበት ወደነበረው ጉባኤ መሄድ ጀመርኩ። ከመንፈሳዊ ቤተሰቤ ጋር በድጋሚ በመገናኘቴ ከፍተኛ ደስታ ተሰማኝ! የጉባኤው አባላት ብዙ መከራ የደረሰባቸው ቢሆንም እንኳ እንዴት በታማኝነት እንደጸኑ መስማት ያስደስት ነበር። ውድ ጓደኛዬ አልቢን ጀርመን ውስጥ በሬግንስበርግ ከተማ መሞቱን አወቅኩ። የአጎቴ ልጅ ዣን ሂሲገ የይሖዋ ምሥክር ሆኖ እንደነበረና ከሕሊናው የተነሳ የውትድርና አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ እንደተገደለ ከጊዜ በኋላ ሰማሁ። ፓሪስ በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ አብሮኝ ይሠራ የነበረው ዣን ኬራ ደግሞ በጀርመን በሚገኝ የጉልበት ሥራ የሚሠራበት አንድ ካምፕ ውስጥ አምስት ዓመት በጽናት አሳልፏል። *

ምንም ጊዜ ሳላጠፋ በሜትዝ ከተማ የስብከት ሥራዬን ማከናወን ቀጠልኩ። በዚያን ወቅት ከሚንዛኒ ቤተሰብ ጋር ብዙ ጊዜ እገናኝ ነበር። ልጃቸው ቲና የተጠመቀችው ኅዳር 2, 1946 ነበር። ቲና በአገልግሎት በቅንዓት ትካፈል የነበረ ሲሆን እኔም እየወደድኳት መጣሁ። ከዚያም ታኅሣሥ 13, 1947 ተጋባን። ቲና መስከረም 1967 የሙሉ ጊዜ የምሥራቹ ሰባኪ ሆና ማገልገል የጀመረች ሲሆን በ98 ዓመቷ ሰኔ 2003 ላይ እስከሞተችበት ዕለት ድረስ በዚህ አገልግሎት ቀጥላለች። እሷን በማጣቴ ከፍተኛ ሐዘን ይሰማኛል።

በአሁኑ ጊዜ ዕድሜዬ ከ90 ዓመት በላይ ሲሆን የአምላክ ቃል ፈተናዎችን እንድጋፈጥም ሆነ በድል አድራጊነት እንድወጣ ጥንካሬ እንደሰጠኝ ተገንዝቤያለሁ። የተራብኩባቸው ጊዜያት የነበሩ ቢሆንም ምንጊዜም አእምሮዬንና ልቤን የአምላክን ቃል ለመመገብ ስጥር ቆይቻለሁ። ይሖዋም ጥንካሬ ሰጥቶኛል። ‘ቃሉ ሕያው አድርጎኛል።’—መዝሙር 119:50

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.27 የዣን ኬራ የሕይወት ታሪክ በጥቅምት 1, 1989 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 22-26 ላይ ይገኛል።

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ውድ ጓደኛዬ አልቢን ረለቪትስ

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማሪዝ አናዚያክ

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአንድ ሳምንት የዳቦ ራሽን የሠዋሁለት መጽሐፍ ቅዱስ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1946 ከእጮኛዬ ከቲና ጋር

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዣን ኬራ ከባለቤቱ ከቲቲካ ጋር