አምላክ ስለሚሰማቸው ጸሎቶች
ከኢየሱስ ምን እንማራለን?
አምላክ ስለሚሰማቸው ጸሎቶች
አብዛኛውን ጊዜ ኢየሱስ ለመጸለይ ጸጥ ያለ አካባቢ ይፈልግ የነበረ ሲሆን ተከታዮቹም እንዲህ እንዲያደርጉ አበረታቷቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “አንድ ቀን ኢየሱስ በአንድ ስፍራ እየጸለየ ነበር፤ ጸሎቱንም ሲጨርስ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ ‘ጌታ ሆይ፣ . . . እንዴት እንደምንጸልይ አስተምረን’ አለው። በዚህ ጊዜ እንዲህ አላቸው፦ ‘በምትጸልዩበት ጊዜ ሁሉ እንዲህ በሉ፦ “አባት ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ።”’” (ሉቃስ 5:16፤ 11:1, 2) በመሆኑም ኢየሱስ ጸሎት መቅረብ ያለበት ለአባቱ ለይሖዋ መሆኑን ገልጿል። እኛን የፈጠረንና ‘ጸሎት ሰሚ’ የሆነው አምላክ እሱ ብቻ ነው።—መዝሙር 65:2
አምላክ ሁሉንም ዓይነት ጸሎቶች ይሰማል?
የተሸመደዱ ጸሎቶችን ደጋግሞ ማቅረብ አምላክን አያስደስትም። ኢየሱስ “በምትጸልዩበት ጊዜ . . . አንድ ዓይነት ነገር ደጋግማችሁ አታነብንቡ” ብሏል። (ማቴዎስ 6:7) ለሰማዩ አባታችን የልባችንን አውጥተን መናገር ይኖርብናል። በአንድ ወቅት ኢየሱስ ሃይማኖታዊ ልማዶችን በጥንቃቄ የሚከተል ኩሩ ሰው ካቀረበው ጸሎት ይልቅ ለውጥ የማድረግ ልባዊ ፍላጎት ያለው ኃጢአተኛ ሰው ያቀረበው ጸሎት በአምላክ ዘንድ ይበልጥ ተቀባይነት እንዳገኘ ለተከታዮቹ አበክሮ ነግሯቸዋል። (ሉቃስ 18:10-14) ስለዚህ ጸሎታችን ተሰሚነት እንዲኖረው ትሑቶች በመሆን አምላክ የሚለንን ለመፈጸም ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። እንዲያውም ኢየሱስ ‘እነዚህን ነገሮች የምናገረው ልክ አብ እንዳስተማረኝ ነው። ሁልጊዜ እሱን ደስ የሚያሰኘውን አደርጋለሁ’ ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 8:28, 29) ኢየሱስ ባቀረበው ጸሎት ላይ “የእኔ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይፈጸም” ብሏል።—ሉቃስ 22:42
ስለ ምን ጉዳይ መጸለይ ይኖርብናል?
በአምላክ ስም ላይ ነቀፋ ስለተሰነዘረ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “እንግዲያው እናንተ በዚህ መንገድ ጸልዩ፦ ‘በሰማያት የምትኖር አባታችን፣ ስምህ ይቀደስ። መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየሆነ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይሁን።’” (ማቴዎስ 6:9, 10) አምላክ ለሰማይና ለምድር ያለውን ፈቃድ ለማስፈጸም የሚጠቀምበት መስተዳድር በመሆኑ የአምላክ መንግሥት እንዲመጣ መጸለይ ይኖርብናል። ኢየሱስ “የዕለቱን ምግባችንን” ለማግኘት መጸለይ እንደምንችል ተናግሯል። በተጨማሪም ሥራን፣ መጠለያን፣ ልብስን፣ ከጤንነት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችንና ሌሎች የሚያሳስቡንን ነገሮች በተመለከተ ይሖዋን መጠየቅ እንችላለን። ከዚህም በላይ ኢየሱስ፣ አምላክ ይቅር እንዲለን መጸለይ እንዳለብን ተናግሯል።—ሉቃስ 11:3, 4
ስለ ሌሎች መጸለይ ይኖርብናል?
ኢየሱስ ስለ ሌሎች ጸልዮአል። መጽሐፍ ቅዱስ “እጁን በላያቸው ጭኖ እንዲጸልይላቸው ትንንሽ ልጆችን ወደ እሱ አመጡ” ይላል። (ማቴዎስ 19:13) ኢየሱስ ሐዋርያው ጴጥሮስን “እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ ምልጃ አቀረብኩ” ብሎት ነበር። (ሉቃስ 22:32) ኢየሱስ ተከታዮቹን ስለ ሌሎች ሌላው ቀርቶ ስለሚያሳድዷቸውና ስለሚሰድቧቸው ሰዎችም እንዲጸልዩ አበረታቷቸዋል።—ማቴዎስ 5:44፤ ሉቃስ 6:28
በጸሎት መጽናት ያለብን ለምንድን ነው?
ኢየሱስ ለጸሎት ጊዜ ይመድብ የነበረ ሲሆን ተከታዮቹን ‘ተስፋ ሳይቆርጡ ዘወትር እንዲጸልዩ’ አበረታቷቸዋል። (ሉቃስ 18:1) ይሖዋ ስለሚያሳስቡን ጉዳዮች ደጋግመን በመጸለይ በእሱ ላይ እምነት እንዳለን እንድናሳይ ይፈልጋል። ኢየሱስ “ደጋግማችሁ ለምኑ፣ ይሰጣችኋል” ብሏል። እንዲህ ሲባል ግን ይሖዋ እሱን እንደ አባት ለሚወዱትና ለሚያከብሩት ሰዎች መልስ ለመስጠት ይዘገያል ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳላችሁ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጣቸውም!”—ሉቃስ 11:5-13
ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? * ከተባለው መጽሐፍ ላይ ምዕራፍ 17ን ተመልከት።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.12 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።