ይሖዋ ሥቃያችንን ይረዳልናል
ወደ አምላክ ቅረብ
ይሖዋ ሥቃያችንን ይረዳልናል
“ራስን በሌሎች ቦታ ማስቀመጥ ማለት ሥቃያቸው በጥልቅ እንዲሰማን ማድረግ ነው።” አንድ በዕድሜ የገፉ የይሖዋ ምሥክር ሚስዮናዊ ራስን በሌሎች ቦታ ማስቀመጥ ውድ ባሕርይ መሆኑን የገለጹት በዚህ መልክ ነበር። ራስን በሌሎች ቦታ በማስቀመጥ ረገድ ዋነኛ ምሳሌያችን ይሖዋ አምላክ ነው። ይሖዋ፣ ሕዝቦቹ ሥቃይ ሲደርስባቸው ይሰማዋል። እንዲህ እንደሚሰማው እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን? ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት የተናገራቸውና ያደረጋቸው ነገሮች ይሖዋ አሳቢ አምላክ መሆኑን በሚገባ አሳይተዋል። (ዮሐንስ 5:19) ለምሳሌ ያህል፣ በዮሐንስ 11:33-35 ላይ የተገለጸውን አንድ ታሪክ ተመልከት።
ኢየሱስ፣ ወዳጁ አልዓዛር ያለ ዕድሜው በሞት በተቀጨ ጊዜ አልዓዛር ወደሚኖርበት መንደር ሄደ። የአልዓዛር እህቶች ማርያምና ማርታ በሐዘን ተደቁሰው እንደሚሆን የታወቀ ነው። ኢየሱስ ይህን ቤተሰብ በጣም ይወደው ነበር። (ዮሐንስ 11:5) ታዲያ ምን ያደርግ ይሆን? ዘገባው እንዲህ ይላል:- “ኢየሱስም [ማርያም] ስታለቅስ፣ ተከትለዋትም የመጡት አይሁድም ሲያለቅሱ ባየ ጊዜ መንፈሱ በኀዘን ታውኮ፣ ‘የት ነው ያኖራችሁት?’ ሲል ጠየቀ። እነርሱም፣ ‘ጌታ ሆይ፤ መጥተህ እይ’ አሉት። ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ።” (ዮሐንስ 11:33-35) ኢየሱስ ያለቀሰው ለምን ነበር? ወዳጁ አልዓዛር እንደሞተ እሙን ነው፤ ቢሆንም ኢየሱስ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አልዓዛርን ከሞት ያስነሳዋል። (ዮሐንስ 11:41-44) ታዲያ ኢየሱስ እንዲያዝን ያደረገው ሌላ ነገር ይኖር ይሆን?
እስቲ ከላይ የተጠቀሰውን ሐሳብ በድጋሚ ተመልከት። ኢየሱስ፣ ማርያምና አብረዋት የነበሩት ሰዎች ሲያለቅሱ ሲመለከት ‘መንፈሱ በኀዘን እንደታወከ’ ልብ በል። ይህን ሐሳብ ለመግለጽ የገባው የግሪክኛ አባባል ጥልቅ ስሜትን ያመለክታል። * ኢየሱስ ያየው ነገር በጥልቅ ነክቶታል፤ ዓይኖቹ በእንባ ግጥም ማለታቸው ለዚህ ማስረጃ ነው። በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ኢየሱስ በሰዎች ላይ ሥቃይ ሲደርስ ያዝናል። አንተስ የምትወደው ሰው ሲያለቅስ ስታይ አልቅሰህ ታውቃለህ?—ሮሜ 12:15
ኢየሱስ፣ የሌሎችን ሥቃይ እንደራሱ አድርጎ የሚመለከት መሆኑ የአባቱን የይሖዋን ባሕርያትና መንገዶች ማስተዋል እንድንችል ይረዳናል። ኢየሱስ፣ የአባቱን ባሕርያት ፍጹም በሆነ መንገድ በማንጸባረቁ “እኔን ያየ አብን አይቶአል” ለማለት እንደቻለ አስታውስ። (ዮሐንስ 14:9) እንግዲያው ‘ኢየሱስ እንባውን እንዳፈሰሰ’ ስናነብ፣ ይሖዋ እሱን የሚያመልኩ ሰዎች ሥቃይ ሲደርስባቸው እንደሚሰማው እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎችም ይህን ሐቅ አረጋግጠዋል። (ኢሳይያስ 63:9፤ ዘካርያስ 2:8 የ1980 ትርጉም) ይሖዋ እንዴት ያለ አፍቃሪ አምላክ ነው!
ሁላችንም፣ ራሱን በሌሎች ቦታ በማስቀመጥ ስሜታቸውን ለመረዳት ከሚጥር ሰው ጋር መሆን ያስደስተናል። ተስፋ ስንቆርጥ ወይም የሚያስጨንቅ ሁኔታ ሲያጋጥመን፣ ችግራችንን እና ሥቃያችንን ሊረዳ ወደሚችል አንድ ወዳጃችን እንጠጋለን። ይሖዋ ሥቃያችንን የሚረዳ እንዲሁም እንባችንን የምናፈሰው ለምን እንደሆነ የሚያውቅ አፍቃሪ አምላክ ነው፤ እንግዲያው ወደዚህ አምላክ አብልጠን እንቅረብ!—መዝሙር 56:8
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.3 “እንባውን አፈሰሰ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል አብዛኛውን ጊዜ “ድምፅ ሳያሰሙ ማልቀስን” ያመለክታል፤ ማርያምና ሌሎቹ ሰዎች ያለቀሱበትን መንገድ ለመግለጽ የገባው ቃል ግን “ድምፅ አውጥቶ ወይም እዬዬ ብሎ ማልቀስን” ሊያመለክት ይችላል።