በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታስታውሳለህ?

ታስታውሳለህ?

በቅርቡ የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች በደንብ አንብበሃቸዋል? እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር፦

መጨረሻው ሲመጣ ከሚጠፉት ነገሮች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

ከሚጠፉት ነገሮች መካከል ሰብዓዊ መንግሥታት፣ ጦርነትና የፍትሕ መዛባት፣ አምላክንም ሆነ ሰዎችን ማስደሰት ያልቻሉ ሃይማኖቶችና ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች ይገኙበታል።—5/1 ከገጽ 3-5

በሕዝቅኤል መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሰው የማጎጉ ጎግ ማን ነው?

የማጎጉ ጎግ የሚለው መጠሪያ የሚያመለክተው ሰይጣንን ሳይሆን ታላቁ መከራ ከጀመረ በኋላ የአምላክን ሕዝቦች ጠራርገው ለማጥፋት ግንባር የሚፈጥሩ ብሔራትን ነው።—5/15 ከገጽ 29-30

አንድ ሰው እንዳማረበት እንዲያረጅ የሚረዱት ስድስት ነገሮች የትኞቹ ናቸው?

መጽሐፍ ቅዱስ (1) ልካችንን እንድናውቅ፣ (2) ሚዛናዊ እንድንሆን፣ (3) አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖረን፣ (4) ለጋስ እንድንሆን፣ (5) የወዳጅነት መንፈስ እንድናሳይ እና (6) አመስጋኝ እንድንሆን ያበረታታናል። አንድ ሰው እነዚህን ባሕርያት የሚያንጸባርቅ ከሆነ እንዳማረበት ማርጀት ይችላል።—6/1 ከገጽ 8-10

ኢየሱስ የፈጸማቸው ተአምራት ለጋስ መሆኑን የሚያሳዩት እንዴት ነው?

በገሊላ በምትገኘው በቃና በተከናወነ የሠርግ ድግስ ላይ ኢየሱስ 380 ሊትር የሚሆን ውኃ ወደ ወይን ጠጅ ቀይሯል። በሌላ ጊዜ ደግሞ ከ5,000 የሚበልጡ ሰዎችን በተአምር መግቧል። (ማቴ. 14:14-21፤ ዮሐ. 2:6-11) ሁለቱንም ተአምራት ሲፈጽም እንደ አባቱ ለጋስ መሆኑን አሳይቷል።—6/15 ከገጽ 4-5

ፍጹም ባንሆንም አምላክን ማስደሰት እንደምንችል እርግጠኛ የምንሆነው ለምንድን ነው?

እንደ ኢዮብ፣ ሎጥና ዳዊት ያሉት ሰዎች ስህተት ሠርተዋል። ያም ሆኖ አምላክን የማገልገል ፍላጎት ነበራቸው፤ በፈጸሙት ድርጊት አዝነዋል፤ እንዲሁም ማስተካከያ ለማድረግ ፈቃደኞች ነበሩ። እነዚህ ሰዎች የአምላክን ሞገስ እንዳገኙ ሁሉ እኛም ሞገሱን ማግኘት እንችላለን።—7/1 ከገጽ 12-13

ታላቂቱ ባቢሎን ስትጠፋ የሐሰት ሃይማኖት አባላት የነበሩ ሁሉ አብረው ይጠፋሉ ማለት ነው?

ላይሆን ይችላል። ዘካርያስ 13:4-6 እንደሚጠቁመው አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች እንኳ ሃይማኖታቸውን የሚተዉ ከመሆኑም ሌላ የሐሰት ሃይማኖት አባል እንዳልነበሩ ይናገራሉ።—7/15 ከገጽ 15-16

ባርቅ ወደ ጦርነት የሚሄደው ዲቦራ አብራው የምትወጣ ከሆነ ብቻ እንደሆነ የተናገረው ለምንድን ነው?

ባርቅ የእምነት ሰው ነበር። ባርቅ፣ ይሖዋ ተጨማሪ የጦር መሣሪያ እንዲሰጠው ከመጠየቅ ይልቅ የአምላክ ወኪል የሆነችው ዲቦራ አብራው እንድትሆን ፈልጓል፤ ዲቦራ አብራው መሆኗ እሱንም ሆነ ሠራዊቱን ያበረታታል። (መሳ. 4:6-8፤ 5:7)—8/1 ገጽ 13

ክርስቲያኖች ሊያሰላስሉባቸው የሚችሉ አንዳንድ ነገሮች የትኞቹ ናቸው?

ልናሰላስልባቸው ከሚገቡ ነገሮች መካከል የይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች፣ በመንፈስ መሪነት የተጻፈው የአምላክ ቃል፣ የጸሎት መብታችንና ፍቅራዊ ዝግጅት የሆነው ቤዛው ይገኙበታል።—8/15 ከገጽ 10-13

ከመጥፎ ጓደኝነት መራቃችን ከመጠናናት ጋር ምን ግንኙነት አለው?

የማያምኑ ሰዎችን ደግነት በጎደለው መንገድ አንይዛቸውም። ይሁን እንጂ ራሱን ለአምላክ ካልወሰነና ለአምላክ መሥፈርቶች ታማኝ ካልሆነ ሰው ጋር የፍቅር ግንኙነት መመሥረት አምላክ ከሰጠው መመሪያ ጋር ይጋጫል። (1 ቆሮ. 15:33)—8/15 ገጽ 25

ጴጥሮስ እምነት ያጣው እንዴት ነው? እምነቱን መልሶ ያገኘውስ እንዴት ነው?

ሐዋርያው ጴጥሮስ እምነት ስለነበረው በውኃ ላይ እየተራመደ ወደ ኢየሱስ ሄዷል። (ማቴ. 14:24-32) አውሎ ነፋሱን ሲያይ ግን ፍርሃት አደረበት። ሆኖም ትኩረቱን መልሶ በኢየሱስ ላይ በማድረግ የሰጠውን እርዳታ ተቀብሏል።—9/15 ከገጽ 16-17

የሐዋርያት ሥራ 28:4 የማልታ ሰዎች ሐዋርያው ጳውሎስ ነፍሰ ገዳይ እንደሆነ አስበው እንደነበር ይገልጻል። እንዲህ የተሰማቸው ለምንድን ነው?

አንዲት እፉኝት ጳውሎስን ስትነክሰው፣ ሰዎቹ የፍትሕ አምላክ የሆነችው ዳይክ ጳውሎስን እየቀጣችው ነው የሚል የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል።—10/1 ገጽ 9

ማርታ በብዙ ሥራ ተጠምዳ ትኩረቷ መከፋፈሉ ምን ትምህርት ይሰጠናል?

በአንድ ወቅት ማርታ ትልቅ ግብዣ ለማዘጋጀት ስትል ትኩረቷ ተከፋፍሎ ነበር። ኢየሱስ፣ የእሱን ትምህርት ታዳምጥ የነበረችው ማርያም ጥሩ የሆነውን ድርሻ እንደመረጠች ተናግሯል። እኛም ያን ያህል አስፈላጊ ያልሆኑ ጉዳዮች በመንፈሳዊ እንቅስቃሴያችን ውስጥ ጣልቃ እንዳይገቡ መጠንቀቅ ይኖርብናል።—10/15 ከገጽ 18-20