በሕይወትህ ውስጥ የአምላክን እጅ እያየህ ነው?
“የይሖዋም እጅ በአገልጋዮቹ ዘንድ ትታወቃለች።”—ኢሳ. 66:14
መዝሙሮች፦ 65, 26
1, 2. አንዳንድ ሰዎች ስለ አምላክ ምን ይሰማቸዋል?
ብዙ ሰዎች እነሱ በሚያደርጉትና አምላክ በሚያደርገው ነገር መካከል ምንም ግንኙነት ያለ አይመስላቸውም። እንዲያውም አንዳንዶች አምላክ በሰዎች ላይ የሚደርሰው ነገር ግድ እንደማይሰጠው ይሰማቸዋል። ኅዳር 2013፣ ሃያን የተባለው ዝናብ የቀላቀለ ከባድ አውሎ ነፋስ መካከለኛውን ፊሊፒንስ ባወደመበት ወቅት የአንድ ትልቅ ከተማ ከንቲባ “አምላክ የሆነ ቦታ ሄዶ መሆን አለበት” ብለዋል።
2 ሌሎች ሰዎች ደግሞ የሚያደርጉትን ነገር አምላክ ማየት የሚችል አይመስላቸውም። (ኢሳ. 26:10, 11፤ 3 ዮሐ. 11) እነዚህ ሰዎች ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ለአምላክ እውቅና መስጠት ተገቢ መስሎ አልታያቸውም’ ብሎ የገለጻቸው ዓይነት ሰዎች ናቸው። እንዲህ ያሉ ሰዎች “በዓመፅ፣ በኃጢአተኝነት፣ በስግብግብነት፣ በክፋት” የተሞሉ ናቸው።—ሮም 1:28, 29
3. (ሀ) አምላክን በተመለከተ የትኞቹን ጥያቄዎች መጠየቅ ይኖርብናል? (ለ) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የይሖዋ “እጅ” የሚለው አገላለጽ ብዙውን ጊዜ የተሠራበት ምን ለማመልከት ነው?
3 ስለ እኛስ ምን ማለት ይቻላል? ቀደም ሲል ከተጠቀሱት ሰዎች በተለየ ይሖዋ የምናደርገውን ነገር ሁሉ እንደሚመለከት እንገነዘባለን። ይሁንና ትኩረት እንደሚሰጠንና ድጋፍ እንደሚያደርግልንስ ይሰማናል? ደግሞስ ኢየሱስ “አምላክን ያያሉ” ካላቸው ሰዎች መካከል ነን? (ማቴ. 5:8) ይህ ምን ማለት እንደሆነ ከመመርመራችን በፊት በሕይወታቸው ውስጥ የአምላክን እጅ ስላዩ ግለሰቦች፣ በሌላ በኩል ደግሞ የእሱን እጅ ማየት ስለተሳናቸው ሰዎች የሚገልጹ ምሳሌዎችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንመልከት። ከዚያም በእምነት ዓይናችን የአምላክን እጅ በሕይወታችን ውስጥ እንዴት በግልጽ መመልከት እንደምንችል እንማራለን። እነዚህን ነጥቦች ስንመረምር መጽሐፍ ቅዱስ ብዙውን ጊዜ የአምላክ “እጅ” ሲል አምላክ አገልጋዮቹን ለመርዳትና ተቃዋሚዎቹን ድል ለማድረግ የሚወስደውን እርምጃ እንደሚያመለክት ማስታወስ ይኖርብናል።—ዘዳግም 26:8ን አንብብ።
የአምላክን እጅ ማየት ተሳናቸው
4. የእስራኤላውያን ጠላቶች የአምላክን እጅ ማየት የተሳናቸው ለምንድን ነው?
4 በጥንት ጊዜ አምላክ፣ ከእስራኤላውያን ጋር በነበረው ግንኙነት ለሕዝቡ ያደረገውን ነገር ሰዎች የማየትና የመስማት አጋጣሚ ነበራቸው። ይሖዋ ሕዝቡን ከግብጽ በተአምር ያወጣቸው ከመሆኑም በላይ የተዋጓቸውን ነገሥታት ሁሉ አንድ በአንድ ድል እንዲያደርጉ ረድቷቸዋል። (ኢያሱ 9:3, 9, 10) ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ ያሉ ነገሥታት በሙሉ የተፈጸመውን ነገር የሰሙና ያዩ ቢሆንም “ኢያሱንና እስራኤልን ለመውጋት ግንባር ፈጠሩ።” (ኢያሱ 9:1, 2) እነዚህ ነገሥታት ውጊያ ከጀመሩ በኋላም እንኳ የአምላክ እጅ ከሕዝቡ ጋር እንደሆነ የማየት አጋጣሚ ነበራቸው። ይሖዋ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት “ብሔሩ ጠላቶቹን እስኪበቀል ድረስ ፀሐይ ባለችበት ቆመች፤ ጨረቃም አልተንቀሳቀሰችም።” (ኢያሱ 10:13) ሆኖም ይሖዋ የጠላቶቻቸው ‘ልብ እንዲደነድን’ ስለፈቀደ እነዚህ ብሔራት “በእስራኤል ላይ ጦርነት” ከፈቱ። (ኢያሱ 11:20) የእስራኤላውያን ጠላቶች አምላክ ለእስራኤላውያን እየተዋጋላቸው እንደሆነ ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ለሽንፈት ተዳርገዋል።
5. ክፉው ንጉሥ አክዓብ ምን ነገር ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል?
5 ከጊዜ በኋላ ደግሞ ክፉው ንጉሥ አክዓብ የአምላክ እጅ ያከናወናቸውን ነገሮች ማየት የሚችልበት ሰፊ አጋጣሚ ነበረው። ኤልያስ “በእኔ ትእዛዝ ካልሆነ በቀር በእነዚህ ዓመታት ጠል ወይም ዝናብ አይኖርም!” ብሎት ነበር። (1 ነገ. 17:1) ኤልያስ ይህን እንዲናገር ያደረገው ይሖዋ እንደሆነ ግልጽ ቢሆንም አክዓብ ማስረጃውን ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆነም። ከዚያም አክዓብ፣ ኤልያስ እሳት ከሰማይ ወርዶ መሥዋዕቱን እንዲበላው ያቀረበው ጸሎት መልስ ሲያገኝ ተመልክቷል። እንዲሁም ኤልያስ “ዝናቡ እንዳያግድህ ወደዚያ ውረድ!” በማለት ለአክዓብ የነገረው ነገር ይሖዋ የድርቁ ወቅት እንዲያበቃ የሚያደርግ መሆኑን ይጠቁም ነበር። (1 ነገ. 18:22-45) አክዓብ ግን እነዚህ ነገሮች ሁሉ ሲፈጸሙ ቢመለከትም የአምላክ ታላቅ ኃይል መግለጫ መሆናቸውን ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። ይህም ሆነ ከዚህ በፊት የተጠቀሱት ምሳሌዎች አንድ ትልቅ ቁም ነገር ማለትም የይሖዋ እጅ የሚያከናውነውን ነገር ለማስተዋል ንቁ መሆን እንዳለብን ያስተምሩናል።
የይሖዋን እጅ አይተዋል
6, 7. በኢያሱ ዘመን የኖሩ አንዳንድ ሰዎች በግልጽ ያስተዋሉት ነገር ምንድን ነው?
6 ከላይ በተጠቀሱት ተመሳሳይ ሁኔታዎች ውስጥ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች፣ ከእነዚህ ክፉ ነገሥታት በተቃራኒ የአምላክን እጅ ማየት ችለዋል። ለአብነት ያህል፣ በኢያሱ ዘመን ከእስራኤላውያን ጋር ከተዋጉት ከአብዛኞቹ ብሔራት በተለየ ገባኦናውያን ከእስራኤል ብሔር ጋር የሰላም ቃል ኪዳን ፈጽመዋል። ለምን? ገባኦናውያን “እኛ አገልጋዮችህ ለአምላክህ ለይሖዋ ስም ካለን አክብሮት የተነሳ ከሩቅ አገር የመጣን ነን፤ ምክንያቱም ዝናውንና በግብፅ ያደረገውን ሁሉ ሰምተናል” ብለዋል። (ኢያሱ 9:3, 9, 10) እስራኤላውያንን እየረዳቸው ያለው እውነተኛው አምላክ መሆኑን ተገንዝበው ነበር።
7 ረዓብም እሷ በኖረችበት ዘመን ከተከናወኑት ነገሮች በስተጀርባ የአምላክ እጅ እንዳለ መገንዘብ ችላለች። ይሖዋ ሕዝቡን እንዴት እንዳዳናቸው ከሰማች በኋላ ለሁለቱ እስራኤላውያን ሰላዮች “ይሖዋ ምድሪቱን እንደሚሰጣችሁ አውቃለሁ” ብላቸዋለች። እንዲህ ያለ አቋም መያዟ ሕይወቷን አደጋ ላይ የሚጥል ቢሆንም ይሖዋ እሷንም ሆነ ቤተሰቧን ማዳን እንደሚችል እምነት እንዳላት አሳይታለች።—ኢያሱ 2:9-13፤ 4:23, 24
8. አንዳንድ እስራኤላውያን የአምላክን እጅ ማስተዋል የቻሉት እንዴት ነው?
8 ከክፉው የእስራኤል ንጉሥ ከአክዓብ በተለየ ኤልያስ እሳት እንዲወርድ ላቀረበው ጸሎት ይሖዋ 1 ነገ. 18:39) ይህ ፈጽሞ ሊክዱት የማይችሉት ሐቅ ነው!
ምላሽ ሲሰጥ የተመለከቱ አንዳንድ እስራኤላውያን በጉዳዩ ላይ የአምላክ እጅ እንዳለበት አስተውለዋል። ከይሖዋ ዘንድ የወረደ እሳት መሥዋዕቱን ሲበላ በተመለከቱ ጊዜ “እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ነው!” በማለት በአድናቆት ተናግረዋል። (9. በዛሬው ጊዜ ይሖዋንና የእሱን እጅ ማየት የምንችለው እንዴት ነው?
9 እስካሁን የተመለከትናቸው ጥሩም ሆኑ መጥፎ ምሳሌዎች፣ አምላክን ማየት ወይም በአንድ ጉዳይ ላይ የእሱ እጅ እንዳለበት መመልከት ሲባል ምን ማለት እንደሆነ እንድንገነዘብ ይረዱናል። እኛም ይሖዋን እያወቅነው ስንሄድ ባሕርያቱንና ድርጊቱን ‘በልባችን ዓይኖች’ ስለምናስተውል በአንድ ጉዳይ ላይ እጁ እንዳለበት ማየት እንችላለን። (ኤፌ. 1:18) ይሖዋ ሕዝቡን እንደሚረዳ በግልጽ እንደተመለከቱት በጥንት ጊዜ እንደነበሩትም ሆነ በዘመናችን እንዳሉት ሰዎች መሆን እንደምንፈልግ ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁንና አምላክ በዛሬው ጊዜም ሰዎችን እንደሚረዳ የሚያረጋግጥ ማስረጃ አለን?
በዛሬው ጊዜ የአምላክ እጅ የታየበት መንገድ
10. በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ሰዎችን እየረዳ እንዳለ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለን? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)
10 ይሖዋ አሁንም ሰዎችን እየረዳ እንደሆነ እንድናምን የሚያደርገን አጥጋቢ ምክንያት አለን። መንፈሳዊ እርዳታ ለማግኘት ጸልየው ጸሎታቸው መልስ ስላገኘ ግለሰቦች የሚገልጹ ተሞክሮዎችን ብዙ ጊዜ እንሰማለን። (መዝ. 53:2) አላን የሚባል አንድ ወንድም በፊሊፒንስ በምትገኝ አንዲት ትንሽ ደሴት ላይ ከቤት ወደ ቤት እያገለገለ ሳለ ያገኛት ሴት ድንገት ማልቀስ ጀመረች። እንዲህ ብሏል፦ “ሴትየዋ የዚያን ዕለት ጠዋት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መገናኘት እንድትችል ወደ ይሖዋ ጸልያ ነበር። በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ሳለች ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ታጠና የነበረ ቢሆንም አግብታ ወደዚህ ደሴት ከመጣች በኋላ ግን ከምሥክሮቹ ጋር ተጠፋፋች። አምላክ ለጸሎቷ አፋጣኝ ምላሽ በመስጠቱ ስሜቷ በጥልቅ ተነክቷል።” ይህች ሴት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሕይወቷን ለይሖዋ ወስናለች።
11, 12. (ሀ) ይሖዋ አገልጋዮቹን የሚረዳው በየትኞቹ መንገዶች ነው? (ለ) ከይሖዋ እርዳታ ስላገኘች እህት የሚገልጽ አንድ ተሞክሮ ተናገር።
11 ብዙ የአምላክ አገልጋዮች ከዚህ በፊት ከነበሯቸው እንደ ማጨስ፣ ዕፅ መውሰድ ወይም የብልግና ምስሎችን መመልከት ካሉ መጥፎ ልማዶች መላቀቅ እንዲችሉ አምላክ እንደረዳቸው በግልጽ ማየት ችለዋል። አንዳንዶች በራሳቸው ጥረት ለማቆም በተደጋጋሚ ጊዜ እንደሞከሩና እንዳልተሳካላቸው ተናግረዋል። ሆኖም እርዳታ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ዘወር በማለታቸውና ‘ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነ ኃይል’ ከእሱ በማግኘታቸው ድክመታቸውን ማሸነፍ ችለዋል።—2 ቆሮ. 4:7፤ መዝ. 37:23, 24
12 ይሖዋ፣ በርካታ አገልጋዮቹ በሕይወታቸው ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ማሸነፍ እንዲችሉ ረድቷቸዋል። ለምሳሌ፣ ኤሚ በአንዲት ትንሽ የፓስፊክ ደሴት ላይ በመንግሥት አዳራሽና በሚስዮናውያን ቤት የግንባታ ሥራ ላይ እንድትካፈል በተመደበች ጊዜ ፈታኝ ሁኔታዎች አጋጥመዋት ነበር። “ያረፍነው አንዲት ትንሽ ሆቴል ውስጥ ሲሆን በቀን በቀን ወደ ግንባታው ቦታ ለመድረስ በጎርፍ የተጥለቀለቁ መንገዶችን በእግር አቋርጠን እንሄድ ነበር” ብላለች። ከዚህም በተጨማሪ የአካባቢውን ባሕል መልመድ ነበረባት፤ ብዙ ጊዜ ደግሞ ውኃና ኤሌክትሪክ ይቋረጥ ነበር። ኤሚ አክላ እንዲህ ብላለች፦ “ይባስ ብሎ አንድ ቀን አብራን በምትሠራ አንዲት እህት ላይ በቁጣ ገነፈልኩባት። ወደ ቤት ስመለስ ስሜቴ በጣም ተደቁሶ ነበር። በጨለማ በተዋጠው የሆቴል መኝታ ክፍሌ ውስጥ ሆኜ ይሖዋ እንዲረዳኝ በመለመን የልቤን አፍስሼ ነገርኩት።” መብራት ሲመጣ ኤሜ አንድ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት አንስታ ማንበብ ጀመረች፤ ርዕሱ ስለ ጊልያድ የምረቃ ፕሮግራም የሚናገር ሲሆን በውስጡ ኤሚ ስላጋጠሟት ፈታኝ ሁኔታዎች የሚናገሩ ሐሳቦችን ይዟል። በመጽሔቱ ላይ አዲስ ባሕልን፣ የቤተሰብ ናፍቆትንና ከዚህ በፊት ከማያውቋቸው ሰዎች ጋር ተግባብቶ መሥራትን በተመለከተ ተጠቅሷል። ኤሚ “የዚያን ዕለት ምሽት ይሖዋ እንዳናገረኝ ሆኖ ተሰማኝ። በተመደብኩበት ቦታ የመቀጠል ፍላጎት አደረብኝ” ብላለች።—መዝ. 44:25, 26፤ ኢሳ. 41:10, 13
13. ይሖዋ ሕዝቦቹ ‘ለምሥራቹ ሲሟገቱና በሕግ የጸና እንዲሆን ለማድረግ’ ሲጥሩ እንደሚደግፋቸው የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?
ፊልጵ. 1:7) አንዳንድ መንግሥታት የአምላክን ሕዝቦች ሥራ ሙሉ በሙሉ ለማስቆም ጥረት አድርገዋል። ይሁንና የይሖዋ ምሥክሮች ከ2000 አንስቶ ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ በአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት የተቀዳጇቸውን 24 ድሎችን ጨምሮ በከፍተኛ ፍርድ ቤት የታዩ 268 ጉዳዮችን ማሸነፋቸው የአምላክን እጅ መግታት የሚችል አንድም ሰው እንደሌለ በግልጽ ያሳያል።—ኢሳ. 54:17፤ ኢሳይያስ 59:1ን አንብብ።
13 የይሖዋ ምሥክሮች ‘ለምሥራቹ ሲሟገቱና በሕግ የጸና እንዲሆን ለማድረግ’ ሲጥሩ የተሳካ ውጤት ማግኘታቸው የይሖዋ ኃያል እጅ እንደሚረዳቸው የሚያሳይ ሌላ ተጨባጭ ማስረጃ ነው። (14. በስብከቱ ሥራችንም ሆነ በመካከላችን ባለው አንድነት የአምላክን እጅ ማየት የምንችለው እንዴት ነው?
14 በዓለም ዙሪያ ምሥራቹን የመስበኩ ሥራ ሊሳካ የቻለው የአምላክ እጅ ስላለበት ነው። (ማቴ. 24:14፤ ሥራ 1:8) በተጨማሪም ከሁሉም ብሔራት በተውጣጡ የይሖዋ አገልጋዮች መካከል የሚታየው አንድነት እውን ሊሆን የቻለው በይሖዋ እርዳታ ብቻ ነው። ይህ በዓለም ታይቶ የማይታወቅ አንድነት ነው! ይሖዋን የማያመልኩ ሰዎች እንኳ “አምላክ በእርግጥ በመካከላችሁ ነው” ለማለት ተገደዋል። (1 ቆሮ. 14:25) ስለዚህ ጉዳዩን ጠቅለል አድርገን ስንመለከት አምላክ ሕዝቡን እየረዳ እንደሆነ የሚያሳይ ከበቂ በላይ ማስረጃ አለን። (ኢሳይያስ 66:14ን አንብብ።) ይሁን እንጂ በግለሰብ ደረጃ ስለ አንተ ምን ማለት ይቻላል? በሕይወትህ ውስጥ የይሖዋን እጅ በግልጽ እያየህ ነው?
በሕይወትህ ውስጥ የይሖዋን እጅ እያየህ ነው?
15. አንዳንድ ጊዜ የይሖዋን እጅ በሕይወታችን ውስጥ በግልጽ ማየት የሚሳነን ለምን እንደሆነ ግለጽ።
15 በሕይወታችን ውስጥ የአምላክን እጅ በግልጽ ማየት የሚሳነን ለምን ሊሆን ይችላል? የሕይወት ውጣ ውረዶች አስተሳሰባችንን ሊቆጣጠሩት ይችላሉ። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን ይሖዋ ከዚህ በፊት እንዴት እንደረዳን ማየት ሊሳነን ይችላል። ንግሥት ኤልዛቤል፣ ነቢዩ ኤልያስን እንደምትገድለው በዛተች ጊዜ ኤልያስ፣ አምላክ ከዚህ በፊት ያደረገለትን ነገር ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ዘንግቶ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ኤልያስ “እንዲሞትም መለመን ጀመረ” ይላል። (1 ነገ. 19:1-4) ኤልያስ ያጋጠመው ችግር መፍትሔ ምን ነበር? ይሖዋ ብርታት እንዲሰጠው መጠየቅ ነበረበት።—1 ነገ. 19:14-18
16. እንደ ኢዮብ አምላክ እንዲታየን ምን ማድረግ እንችላለን?
16 ኢዮብ ባስጨነቁት ጉዳዮች ከመዋጡ የተነሳ ነገሮችን ከአምላክ አንጻር መመልከት ተስኖት ነበር። (ኢዮብ 42:3-6) እኛም አምላክ እንዲታየን እንደ ኢዮብ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ሊያስፈልገን ይችላል። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ቅዱሳን መጻሕፍት በሚፈነጥቁልን ብርሃን ተጠቅመን ባጋጠመን ሁኔታ ላይ በማሰላሰል ነው። ይሖዋ እንዴት እየረዳን እንዳለ ስንገነዘብ እሱ ይበልጥ እውን ይሆንልናል። ከዚያም ልክ እንደ ኢዮብ “ጆሮዬ ስለ አንተ ሰምታ ነበር፤ አሁን ግን በገዛ ዓይኔ አየሁህ” ማለት እንችላለን።
17, 18. (ሀ) ይሖዋ እየረዳን መሆኑን ማስተዋል የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው? (ለ) በዛሬው ጊዜ አምላክ እየረዳን እንዳለ የሚያሳይ ተሞክሮ ተናገር።
17 የይሖዋን እጅ ማየት የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው? እስቲ ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት፦ ምናልባት እውነትን የሰማህበት መንገድ በቀጥታ የአምላክ እጅ እንዳለበት እንድታምን ያደርግህ ይሆናል። በጉባኤ ስብሰባ ላይ አንድ ክፍል ሲቀርብ አዳምጠህ “ይሄ በቀጥታ እኔን የሚመለከት ነው” ያልክበት ጊዜ አለ? ወይም ደግሞ ስለ አንድ ጉዳይ ጸልየህ መልስ አግኝተህ ይሆናል። ምናልባትም አገልግሎትህን ለማስፋት ከወሰንክ በኋላ ይሖዋ ነገሮችን እንዴት እንዳሳካልህ ስታይ ተገርመህ ሊሆን ይችላል። አሊያም ለመንፈሳዊ ነገሮች ስትል ሥራህን ከለቀቅክ በኋላ አምላክ “በምንም ዓይነት አልጥልህም” ሲል የገባው ቃል ሲፈጸም ተመልክተህ ይሆን? (ዕብ. 13:5) እንግዲያው በመንፈሳዊ ንቁ ከሆንን ይሖዋ እኛን በተለያዩ መንገዶች እንዴት እየረዳን እንዳለ መገንዘብ እንችላለን።
18 በኬንያ የምትኖረው ሣራ እንዲህ ብላለች፦ “ብዙም ፍላጎት ያላት የማትመስል አንዲት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ነበረችኝ፤ እሷን በተመለከተ ጸለይኩ። ማስጠናቴን ማቆም ይኖርብኝ እንደሆነ ይሖዋን ጠየቅኩት። ‘አሜን’ ብዬ እንደጨረስኩ ስልኬ ጮኸ። የደወለችው ጥናቴ ስትሆን አብራኝ ስብሰባ መሄድ ትችል እንደሆነ ጠየቀችኝ! ይህን ስሰማ ማመን አቃተኝ!” አንተም ሁኔታዎችን በንቃት የምትከታተል ከሆነ አምላክ በሕይወት ውስጥ ብዙ ነገር እያደረገልህ እንዳለ መመልከት ትችላለህ። በእስያ የምትኖር ሮና የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ የሚሰጠንን አመራር ማስተዋል የተወሰነ ልምድ ይጠይቃል። አንዴ ማስተዋል ከጀመርን ግን ይሖዋ ምን ያህል ትኩረት እንደሚሰጠን ስለምንረዳ ሁኔታው ያስገርመናል!”
19. አምላክን ከሚያዩ ሰዎች መካከል ለመሆን የሚያስፈልገን ሌላው ነገር ምንድን ነው?
19 ኢየሱስ “ልባቸው ንጹሕ የሆነ ደስተኞች ናቸው፤ አምላክን ያያሉና” በማለት ተናግሯል። (ማቴ. 5:8) ‘ልበ ንጹሕ’ መሆን የምንችለው እንዴት ነው? ውስጣችንን ንጹሕ በማድረግና ማንኛውንም መጥፎ ምግባር በማስወገድ ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:2ን አንብብ።) መንፈሳዊነታችን ይበልጥ እየተጠናከረ ሲሄድና ትክክለኛ ምግባር ስናሳይ አምላክን ማየት ከሚችሉ ሰዎች መካከል እንሆናለን። በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይሖዋ በሕይወታችን ውስጥ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ በግልጽ መገንዘብ እንድንችል ስለሚረዳን አንድ ገጽታ ይኸውም ስለ እምነት እንመረምራለን።