ይህን ያውቁ ኖሯል?
የጥንቷ እስራኤል መጽሐፍ ቅዱስ የሚገልጸውን ያህል በደን የተሸፈነች ነበረች?
የተስፋይቱ ምድር አንዳንድ አካባቢዎች በደን የተሸፈኑና ዛፎች ‘በብዛት’ የሚገኙባቸው እንደነበሩ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (1 ነገ. 10:27፤ ኢያሱ 17:15, 18) ሆኖም በዛሬው ጊዜ አብዛኛው የአገሪቱ ክፍል የተመነጠረ ከመሆኑ አንጻር አንዳንዶች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሰው ሐሳብ እውነት መሆኑን ይጠራጠሩ ይሆናል።
ላይፍ ኢን ቢብሊካል ኢዝሬል የተሰኘው መጽሐፍ “በጥንቷ እስራኤል፣ በዛሬው ጊዜ ካለው እጅግ የሚበልጥ ሰፊ ቦታ የሚሸፍኑ ደኖች ነበሩ” ይላል። በደጋ አካባቢ የሚገኘው የተፈጥሮ ደን በዋነኝነት ጥድን (Pinus halepensis)፣ ባሉጥን (Quercus calliprinos) እና ቴረቢንዝን (Pistacia palaestina) ያካትት ነበር። በማዕከላዊው የተራራ ሰንሰለትና በሜድትራንያን የባሕር ዳርቻ መካከል ያለውን አካባቢ በሚጨምረው በሸፌላ ደግሞ የሾላ ዛፎችም (Ficus sycomorus) በብዛት ይገኙ ነበር።
ፕላንትስ ኦቭ ዘ ባይብል የተሰኘው መጽሐፍ በአሁኑ ጊዜ በእስራኤል አንዳንድ አካባቢዎች ዛፍ የሚባል ነገር እንደሌለባቸው ይናገራል። ለዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው? ይህ ቀስ በቀስ የተከሰተ ነገር እንደሆነ መጽሐፉ ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “ሰዎች በዋነኝነት የእርሻና የግጦሽ ቦታቸውን ለማስፋት እንዲሁም ለግንባታ ቁሳቁሶችና ለማገዶ የሚሆን እንጨት ለማግኘት ሲሉ የተፈጥሮውን ደን ለረጅም ጊዜ ሲጨፈጭፉት ቆይተዋል።”