“መጽናት ያስፈልጋችኋል”
አኒታ * ተጠምቃ የይሖዋ ምሥክር ከሆነች በኋላ ባሏ በጣም ይቃወማት ጀመር። “ወደ ስብሰባዎች እንዳልሄድ ሌላው ቀርቶ የአምላክን ስም እንኳ እንዳላነሳ በጥብቅ ከለከለኝ” ብላለች። “ባለቤቴ፣ ይሖዋ የሚለውን ስም ስጠራ ከሰማ በቁጣ ይገነፍል ነበር።”
አኒታን የገጠማት ሌላው ከባድ ፈተና ደግሞ ልጆቿን ስለ ይሖዋ ከማስተማር ጋር የተያያዘ ነው። እንዲህ ብላለች፦ “የይሖዋ አምልኮ በቤቴ ውስጥ እገዳ ተጥሎበት ነበር። ከልጆቼ ጋር በግልጽ ማጥናትም ሆነ እነሱን ወደ ስብሰባ መውሰድ አልችልም ነበር።”
የአኒታ ተሞክሮ እንደሚያሳየው ከቤተሰብ አባላት የሚመጣ ተቃውሞ ለአንድ ክርስቲያን ትልቅ የታማኝነት ፈተና ሊሆንበት ይችላል። ከባድ የጤና ችግር፣ ልጅን ወይም የትዳር ጓደኛን በሞት ማጣት አሊያም የቤተሰብ አባል ይሖዋን ማምለኩን መተዉም ተመሳሳይ ፈተና ያስከትላል። ታዲያ አንድ ክርስቲያን ለይሖዋ ታማኝነቱን እንዲጠብቅ ምን ሊረዳው ይችላል?
አንተ እንዲህ ያሉ ፈተናዎች ቢደርሱብህ ምን ታደርጋለህ? ሐዋርያው ጳውሎስ “መጽናት ያስፈልጋችኋል” ብሏል። (ዕብ. 10:36) ይሁን እንጂ ለመጽናት ምን ሊረዳህ ይችላል?
በጸሎት አማካኝነት በይሖዋ መታመን
ለመጽናት የሚያስፈልገንን ጥንካሬ ማግኘት ከምንችልባቸው ዋነኛ መንገዶች አንዱ በጸሎት አማካኝነት በይሖዋ መታመን ነው። አንድ ምሳሌ እንመልከት። የአና ቤተሰብ አንድ ሰኞ ቀን ከሰዓት በኋላ ከባድ ሐዘን አጋጠመው። በትዳር 30 ዓመታት አብሯት ያሳለፈው ባለቤቷ በድንገት ሞተ። አና “ሥራ እንደሄደ አልተመለሰም፤ ገና 52 ዓመቱ ነበር” ብላለች።
አና የደረሰባትን ሐዘን መቋቋም የቻለችው እንዴት ነው? ወደ ሥራዋ መመለስ ነበረባት፤ ሥራዋ ሙሉ ትኩረት የሚጠይቅ በመሆኑም እንዲህ ማድረጓ ረድቷታል፤ ይሁን እንጂ ሐዘኗን አላስወገደላትም። አና “ልቤን ለይሖዋ በማፍሰስ፣ የደረሰብኝን ከባድ ሐዘን ለመቋቋም እንዲረዳኝ ለመንኩት” ብላለች። ታዲያ ይሖዋ ጸሎቷን መልሶላታል? እንደመለሰላት እርግጠኛ ናት። እንዲህ ትላለች፦ “አምላክ ብቻ ሊሰጥ የሚችለው ሰላም ነፍሴን ያረጋጋልኝ ከመሆኑም ሌላ አእምሮዬ ጤናማ ሆኖ እንዲቀጥል ረድቶኛል። ይሖዋ ባለቤቴን በትንሣኤ እንደሚያስነሳው ቅንጣት ታክል አልጠራጠርም።”—ፊልጵ. 4:6, 7
“ጸሎት ሰሚ” የሆነው አምላክ አገልጋዮቹ ለእሱ ታማኝ ሆነው ለመኖር የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቷል። (መዝ. 65:2) ይህ ማረጋገጫ እምነት የሚያጠነክር ነው ቢባል አትስማማም? አንተም መጽናት እንደምትችል እንድታምንስ አይረዳህም?
ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች—የድጋፍ ምንጭ
ይሖዋ ሕዝቡን በክርስቲያን ጉባኤ አማካኝነት ሲደግፋቸው ኖሯል። ለምሳሌ ያህል፣ በተሰሎንቄ የነበረው ጉባኤ ከባድ ስደት ባጋጠመው ጊዜ ጳውሎስ እነዚያን ክርስቲያኖች “አሁን እያደረጋችሁት እንዳለው እርስ በርስ ተበረታቱ እንዲሁም እርስ በርስ ተናነጹ” በማለት መክሯቸዋል። (1 ተሰ. 2:14፤ 5:11) የተሰሎንቄ ክርስቲያኖች እርስ በርስ ያላቸውን ፍቅር በማጠናከርና በመረዳዳት፣ ያጋጠማቸውን የእምነት ፈተና በጽናት ማሳለፍ ችለዋል። በጽናት ረገድ የተዉት አርዓያ በዛሬው ጊዜ ላለነው ክርስቲያኖች ግሩም ምሳሌ ይሆነናል፤ በተጨማሪም ለመጽናት የሚረዳንን አንድ ነገርም ይጠቁማል።
ከጉባኤው አባላት ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት “እርስ በርሳችን የምንተናነጽበትን ነገር ለማድረግ” ያስችለናል። (ሮም 14:19) በተለይ መከራ ሲደርስ ይህ በጣም አስፈላጊ ነው። ጳውሎስ ራሱ ብዙ መከራዎች የደረሱበት ሲሆን ይሖዋም ለመጽናት የሚያስችለውን ብርታት ሰጥቶታል። አምላክ፣ ለጳውሎስ በእምነት አጋሮቹ አማካኝነት ብዙ ማበረታቻ የሰጠው ጊዜ አለ። ለምሳሌ ያህል፣ ጳውሎስ ለቆላስይስ ጉባኤ አባላት በግለሰብ ደረጃ ሰላምታ በላከበት ጊዜ “የብርታት ምንጭ ሆነውልኛል” በማለት ስለ እነሱ ተናግሯል። (ቆላ. 4:10, 11) በእርግጥም ለጳውሎስ ያላቸው ፍቅር፣ በተቸገረበት ጊዜ እንዲያጽናኑትና እንዲያበረታቱት አነሳስቷቸዋል። አንተም ከጉባኤህ አባላት እንደዚህ ያለ ማበረታቻና ድጋፍ አግኝተህ ሊሆን ይችላል።
ከሽማግሌዎች የሚገኝ ድጋፍ
አምላክ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያዘጋጀው ሌላው የድጋፍ ምንጭ ደግሞ ሽማግሌዎች ናቸው። እነዚህ በመንፈሳዊ የጎለመሱ ሰዎች “ከነፋስ እንደ መከለያ፣ ከውሽንፍር እንደ መሸሸጊያ፣ ውኃ በሌለበት ምድር እንደ ጅረት፣ በደረቅ ምድርም እንደ ትልቅ ቋጥኝ ጥላ” ሊሆኑ ይችላሉ። (ኢሳ. 32:2) ይህ እንዴት ያለ መንፈስን የሚያድስ ማረጋገጫ ነው! አንተስ በዚህ ፍቅራዊ ዝግጅት እየተጠቀምክ ነው? ሽማግሌዎች የሚሰጡት ማበረታቻና ድጋፍ እንድትጸና ሊረዳህ ይችላል።
እርግጥ ነው፣ ሽማግሌዎች ተአምር አይሠሩም። እነሱም እንደ እኛው ‘ድክመት ያለባቸው’ ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች ናቸው። (ሥራ 14:15) ያም ሆኖ ስለ እኛ የሚያቀርቡት ምልጃ ብዙ ነገር ማከናወን ይችላል። (ያዕ. 5:14, 15) በጣሊያን የሚኖር አንድ ወንድም፣ ጡንቻን የሚያዝለው መስኩላር ዲስትሮፊ የሚባል በሽታ የሚያስከትላቸውን እያደር እየተባባሱ የሚሄዱ ችግሮች ለብዙ ዓመታት በጽናት ተቋቁሞ መኖር አስፈልጎታል፤ ይህ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “የወንድሞች ፍቅርና አሳቢነት እንዲሁም አዘውትረው የሚጠይቁኝ መሆኑ እንድጸና ረድቶኛል” ብሏል። አንተስ ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ ከሰጠን ሽማግሌዎች ይበልጥ መጠቀም ትችላለህ?
ቋሚ መንፈሳዊ ፕሮግራም ይኑርህ
ለመጽናት ልንወስዳቸው የሚገቡ ሌሎች እርምጃዎችም አሉ። አንዱ እርምጃ ቋሚ መንፈሳዊ ፕሮግራም እንዲኖረን ማድረግ ነው። የ39 ዓመቱን ጆንን እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ጆን ያልተለመደ ዓይነት ካንሰር እንዳለበት ተነገረው። “ዕድሜዬ ገና በመሆኑ እንደተሰረቅኩ ያህል ተሰምቶኝ ነበር” በማለት ተናግሯል። በወቅቱ የጆን ልጅ ገና ሦስት ዓመቱ ነበር። ጆን እንዲህ ብሏል፦ “ባለቤቴ ትንሹን ልጃችንን ብቻ ሳይሆን እኔንም ጭምር መንከባከብ ብሎም ሐኪም ቤት በምሄድበት ጊዜ እኔን መርዳት ነበረባት።” ጆን የሚከታተለው የኬሞቴራፒ ሕክምና ከፍተኛ ድካምና የማጥወልወል ስሜት ያስከትልበት ነበር። የጆን ችግር ይህ ብቻ አልነበረም። አባቱም በጠና ስለታመሙ የቤተሰብ እንክብካቤ አስፈለጋቸው።
ታዲያ ጆንና ቤተሰቡ ይህን አስቸጋሪ ሁኔታ መቋቋም የቻሉት እንዴት ነው? ጆን እንዲህ ብሏል፦ “ሰውነቴ በጣም ቢዝልም ቤተሰባችን ቋሚ መንፈሳዊ ፕሮግራም እንዲኖረው አደርግ ነበር። በሁሉም ስብሰባዎች ላይ እንገኛለን፤ በአገልግሎት በየሳምንቱ እንካፈላለን፣ እንዲሁም ሁኔታው አስቸጋሪ በነበረበት ጊዜም ጭምር ቋሚ የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራም ነበረን።” በእርግጥም ጆን ማንኛውንም ተፈታታኝ ችግር በጽናት ለማለፍ ቁልፉ ምንጊዜም ጥሩ መንፈሳዊ አቋም መያዝ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። ጆን ፈታኝ ሁኔታ እየተጋፈጡ ላሉ ሰዎች የሚሰጠው ምክር ይኖራል? እንዲህ ይላል፦ “የመጀመሪያው ድንጋጤ ካለፈ በኋላ፣ የሚያስጨንቋችሁ ሐሳቦች ይሖዋ በሚሰጣችሁ ጥንካሬና በእሱ ፍቅር ይተካሉ። ይሖዋ ለእኔ እንዳደረገው ሁሉ እናንተንም ሊያጠነክራችሁ ይችላል።”
በአሁኑ ጊዜም ሆነ ወደፊት የሚያጋጥሙንን ከባድ ፈተናዎች ወይም አስቸጋሪ ሁኔታዎች በአምላክ እርዳታ በጽናት መወጣት እንደምንችል ምንም ጥርጥር የለውም። እንግዲያው በጸሎት አማካኝነት በይሖዋ እንታመን፤ በጉባኤያችን ካሉት ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንመሥርት፤ ከክርስቲያን ሽማግሌዎች ድጋፍ እናግኝ፤ እንዲሁም ቋሚ የሆነ መንፈሳዊ ፕሮግራም ይኑረን። እንዲህ በማድረግ ጳውሎስ “መጽናት ያስፈልጋችኋል” በማለት በተናገረው ሐሳብ እንደምንስማማ እናሳያለን።
^ አን.2 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።