ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል—ኒው ዮርክ
ሴሳር እና ባለቤቱ ሮሲኦ ከጥቂት ዓመታት በፊት ካሊፎርኒያ ውስጥ የተመቻቸ ሕይወት ነበራቸው፤ ሴሳር ከማሞቂያ፣ ከአየር ማናፈሻና ከማቀዝቀዣ መሣሪያዎች ጋር የተያያዘ የሙሉ ጊዜ ሥራ ነበረው፤ ሮሲኦ ደግሞ በአንድ ክሊኒክ ውስጥ የተወሰነ ሰዓት ትሠራ ነበር። የራሳቸው ቤትም ነበራቸው፤ እነዚህ ባልና ሚስት ልጆች የሏቸውም። ይሁንና ሴሳርና ሮሲኦ ሕይወታቸውን የሚለውጥ አንድ ነገር አጋጠማቸው። ምን ይሆን?
ጥቅምት 2009 የዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮ በአገሪቱ ወዳሉት ጉባኤዎች በሙሉ አንድ ደብዳቤ ላከ፤ ደብዳቤው በዎልኪል፣ ኒው ዮርክ በሚካሄደው ቅርንጫፍ ቢሮ የማስፋፋት ሥራ እገዛ ለማድረግ የሚፈልጉ ባለሙያ የሆኑ ፈቃደኛ ሠራተኞች በጊዜያዊነት በቤቴል ለማገልገል እንዲያመለክቱ የሚጋብዝ ነበር። ቤቴል ለመግባት ከሚፈቀደው የዕድሜ ገደብ በላይ የሆኑ ፈቃደኛ ሠራተኞችም እንዲያመለክቱ ተጋብዘዋል። ሴሳርና ሮሲኦ እንዲህ ብለዋል፦ “ዕድሜያችን ስለገፋ፣ በቤቴል ለማገልገል ያገኘነው ይህ አጋጣሚ የማይደገም እንደሆነ እናውቅ ነበር። በመሆኑም ይህ መብት እንዲያመልጠን አልፈለግንም!” ባልና ሚስቱ ወዲያውኑ ማመልከቻቸውን አስገቡ።
ሴሳርና ሮሲኦ ማመልከቻ ካስገቡ በኋላ ከአንድ ዓመት የሚበልጥ ጊዜ ቢያልፍም ወደ ቤቴል አልተጠሩም። ያም ቢሆን ኑሯቸውን ቀላል በማድረግ፣ ግባቸው ላይ ለመድረስ የሚረዷቸው ሌሎች እርምጃዎችን ወሰዱ። ሴሳር እንዲህ ብሏል፦ “ቤታችንን ማከራየት እንድንችል የመኪና ማቆሚያችንን አስተካክለን ባለ አንድ ክፍል መኖሪያ አደረግነው። ከዚያም በምንመኘው መንገድ የሠራነውንና ጥቂት ዓመታት ብቻ የኖርንበትን ባለ ሰባት ክፍል የሚያምር ቤታችንን ለቅቀን ባለ አንድ ክፍል ቤታችን ውስጥ ገባን። ይህን ለውጥ ማድረጋችን ምናልባት ወደ ቤቴል ብንጠራ ግብዣውን ለመቀበል እንድችል አዘጋጅቶናል።” ከዚያስ ምን ሆነ? “ወደ ትንሿ ቤታችን ከገባን ከአንድ ወር በኋላ በዎልኪል ጊዜያዊ ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆነን እንድናገለግል ተጋበዝን። ኑሯችንን ቀላል ማድረጋችን ይሖዋ እንዲባርከን የሚያደርግ አጋጣሚ ከፍቷል።”
የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ በማሳየታቸው ተባርከዋል
እንደ ሴሳርና ሮሲኦ ሁሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወንድሞችና እህቶች በኒው ዮርክ ግዛት እየተካሄደ ባለው የግንባታ ሥራ ለመካፈል ሲሉ መሥዋዕት ከፍለዋል። ከእነዚህ ወንድሞችና እህቶች መካከል በርካታዎቹ በዎልኪል ያለውን የማስፋፋት ሥራ እየደገፉ ሲሆን ሌሎች ብዙዎች ደግሞ በዎርዊክ በሚከናወነው የዋናው መሥሪያ ቤት ግንባታ ላይ የመካፈል መብት አግኝተዋል። * ብዙ ባለትዳሮች ይሖዋን ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ ለማገልገል ሲሉ የሚያምሩ ቤቶቻቸውን፣ ጥሩ ሥራቸውንና የቤት እንስሶቻቸውን ጭምር ትተዋል። ታዲያ ይሖዋ እንዲህ ዓይነቱን የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ባርኮታል? በሚገባ!
ለምሳሌ ያህል፣ የኤሌክትሪክ ሠራተኛ የሆነው ዌይ እና ባለቤቱ ዴብራ በ50ዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ላይ የሚገኙ ሲሆን በካንሳስ የሚገኘውን ቤታቸውንና አብዛኛውን ንብረታቸውን ሸጠው ወደ ዎልኪል በመዛወር በተመላላሽ ቤቴላዊነት እያገለገሉ ነው። * ይህን እርምጃ መውሰድ በሕይወታቸው ውስጥ ማስተካከያዎች ማድረግ ቢጠይቅባቸውም የከፈሉት መሥዋዕት የማያስቆጭ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ዴብራ በቤቴል የተሰጣትን የሥራ ምድብ አስመልክታ እንዲህ ብላለች፦ “በጽሑፎቻችን ላይ በሚታዩት በገነት ውስጥ የሚካሄዱ የግንባታ ሥራዎች ላይ እንደምካፈል ሆኖ የሚሰማኝ ጊዜ አለ!”
ሜልቪን እና ሻረን በዎርዊክ በሚካሄደው ሥራ ላይ ለማገዝ እንዲችሉ በደቡብ ካሮላይና የሚገኘውን ቤታቸውንና ንብረታቸውን ሸጠዋል። እነዚህን መሥዋዕቶች ማድረግ ቀላል ባይሆንም ባልና ሚስቱ እንዲህ ባለው ታሪካዊ ፕሮጀክት ላይ ተካፋይ መሆን መታደል እንደሆነ ይሰማቸዋል። “ዓለም አቀፉን ድርጅት የሚጠቅም አንድ ነገር እያከናወናችሁ እንዳላችሁ በማወቅ የሚገኘው ደስታ ወደር የለውም!” ብለዋል።
የግንባታ ሠራተኛ የሆነውና ጡረታ የወጣው ኬኔዝ እንዲሁም ባለቤቱ ሞሪን በ50ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ የሚገኙ ሲሆን ከካሊፎርኒያ መጥተው በዎርዊክ ፕሮጀክት ላይ እያገለገሉ ነው። ኬኔዝና ሞሪን ወደ ዎርዊክ ለመዛወር ሲያስቡ ቤታቸውን እንድትጠብቅላቸው ከአንዲት እህት ጋር ተነጋገሩ፤ የኬኔዝን አረጋዊ አባት ደግሞ ቤተሰቦቻቸው እንዲንከባከቧቸው ዝግጅት አድርገዋል። ታዲያ በቤቴል ለማገልገል ሲሉ በከፈሉት መሥዋዕት ተቆጭተዋል? በፍጹም! ኬኔዝ እንዲህ ብሏል፦ “እጅግ እየተጠቀምን ነው። ይህ ሲባል ተፈታታኝ ሁኔታዎች አላጋጠሙንም ማለት ነው? ተፈታታኝ ሁኔታዎች አሉ፤ ይሁን እንጂ በጣም የሚክስ ሕይወት እየኖርን ነው፤ ሌሎችም ቢሆን ወደዚህ አገልግሎት እንዲገቡ ከልባችን እናበረታታቸዋለን።”
ተፈታታኝ ሁኔታዎችን ማሸነፍ
ራሳቸውን ካቀረቡት ውስጥ አብዛኞቹ አንዳንድ መሰናክሎችን ማሸነፍ አስፈልጓቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በ60ዎቹ መጀመሪያ ላይ የሚገኙት ዊሊያም እና ሳንድራ በፔንስልቬንያ የተደላደለና አስደሳች ሕይወት ነበራቸው። የማሽን መለዋወጫ የሚሠራ አትራፊ የሆነ ኩባንያ የነበራቸው ሲሆን 17 ሰዎች ቀጥረው ያሠሩ ነበር። የሚያገለግሉት ከልጅነታቸው ጀምሮ በኖሩበት ጉባኤ ውስጥ ነበር፤ አብዛኞቹ ዘመዶቻቸውም የሚኖሩት በዚያው አካባቢ ነው። ስለዚህ በዎልኪል በተመላላሽነት የማገልገል አጋጣሚ ሲከፈትላቸው፣ ይህን ማድረግ የሚያውቋቸውን ሰዎችና የለመዱትን ነገር በሙሉ ትተው መሄድ እንደሚጠይቅባቸው ያውቁ ነበር። ዊሊያም “ለእኛ ትልቁ ፈተና የለመድነውን ሕይወትና የተመቻቸ ኑሯችንን ትተን መሄዱ ነበር” ይላል። ይሁን እንጂ በጉዳዩ ላይ ብዙ ከጸለዩበት በኋላ ባልና ሚስቱ ወደ ዎልኪል ለመዛወር ወሰኑ፤ በዚህ እርምጃቸውም አይቆጩም። “በሥራው በቀጥታ ተካፋይ መሆንና ከቤቴል ቤተሰብ ጋር አብሮ ማገልገል የሚያስገኘው ደስታ ከሌላ ከምንም ነገር ጋር ሊወዳደር አይችልም” ይላል ዊሊያም። “ሳንድራና እኔ ከምንጊዜውም የበለጠ ደስተኞች ነን!”
በሃዋይ የግንባታ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ የነበረው ሪኪ በዎርዊክ ፕሮጀክት ላይ በተመላላሽ ቤቴላዊነት እንዲያገለግል ተጋበዘ። ባለቤቱ ኬንድራ ግብዣውን እንዲቀበል ትፈልግ ነበር። ይሁን እንጂ የሚያሳስባቸው ነገር ነበር፤ ይኸውም የ11 ዓመት ወንድ ልጃቸው የጄከብ ጉዳይ ነው። ቤተሰባቸውን ወደ ኒው ዮርክ ግዛት ማዛወር የጥበብ እርምጃ መሆኑ እንዲሁም ልጃቸው ጨርሶ አዲስ ከሆነ አካባቢ ጋር መላመድ መቻሉ አሳስቧቸው ነበር።
ሪኪ እንዲህ ብሏል፦ “ቅድሚያ ከሰጠናቸው ነገሮች አንዱ በመንፈሳዊ ጥሩ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ታዳጊ ወጣቶች ያሉበት ጉባኤ ማግኘት ነበር። ጄከብ ብዙ ጥሩ ጓደኞች ማግኘት እንዲችል ፈልገን ነበር።” ቤተሰቡ የሄደበት ጉባኤ ያሉት ልጆች ጥቂት ናቸው፤ ሆኖም ብዙ ቤቴላውያን አሉ። “በዚያ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ስብሰባ ከሄድን በኋላ፣ በተለይም በጄከብ ዕድሜ የሚገኙ ታዳጊ ወጣቶች ጉባኤው ውስጥ ስለሌሉ ስለ አዲሱ ጉባኤ ምን እንደተሰማው ጠየቅሁት” ይላል ሪኪ። “እሱም ‘አትጨነቅ፣ አባዬ። ወጣት ቤቴላውያን ወንድሞች ጓደኞቼ ይሆናሉ’ አለኝ” ብሏል።
በእርግጥም ወጣቶቹ ቤቴላውያን ጄከብን ጓደኛቸው አደረጉት። ውጤቱስ ምን ሆነ? ሪኪ እንዲህ ብሏል፦ “አንድ ምሽት በልጄ ክፍል በኩል ሳልፍ መብራቶቹ እንዳልጠፉ አስተዋልኩ። የኤሌክትሮኒክ ጨዋታ እየተጫወተ እንደማገኘው ጠብቄ ነበር፤ እሱ ግን መጽሐፍ ቅዱስ እያነበበ ነበር! ምን እያደረገ እንደሆነ ጄከብን ስጠይቀው ‘እንደ ቤቴላውያን መሆኔ ነው፤ ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ዓመት ውስጥ አንብቤ እጨርሰዋለሁ’ አለኝ።” ሪኪና ኬንድራ፣ ሪኪ በዎርዊክ ባለው የግንባታ ሥራ ላይ መካፈል በመቻሉ ብቻ ሳይሆን ወደዚህ መዛወራቸው ለልጃቸው መንፈሳዊ እድገት አስተዋጽኦ እያደረገ በመሆኑም ጭምር እጅግ እንደተደሰቱ ጥያቄ የለውም።—ምሳሌ 22:6
ስለ ወደፊቱ ጊዜ አይጨነቁም
በዎልኪልና በዎርዊክ ያሉት የግንባታ ፕሮጀክቶች ውሎ አድሮ መጠናቀቃቸው አይቀርም፤ በመሆኑም በሥራው እንዲያግዙ የተጠሩት ወንድሞችና እህቶች የቤቴል አገልግሎታቸው ጊዜያዊ እንደሆነ ያውቃሉ። ታዲያ እነዚህ ወንድሞችና እህቶች ከዚያ በኋላ ወዴት እንደሚሄዱ ወይም ምን እንደሚሠሩ ከመጠን በላይ ይጨነቃሉ? በጭራሽ! ብዙዎቹ፣ ከፍሎሪዳ የመጡትን በ50ዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ባልና ሚስት ስሜት ይጋራሉ። የግንባታ ሥራ አስኪያጅ የነበረው ጆን እና ባለቤቱ ካርመን በዎርዊክ ጊዜያዊ ፈቃደኛ ሠራተኞች ሆነው ያገለግላሉ፤ እንዲህ ብለዋል፦ “ይሖዋ እስከዚህች ዕለት ድረስ በሚያስፈልጉን ጥቃቅን ነገሮች ሁሉ እንዴት እንደተንከባከበን አይተናል። ይሖዋ አሁን እዚህ አምጥቶን በኋላ ላይ እንደማይተወን ይሰማናል።” (መዝ. 119:116) የእሳት ማጥፊያ መሣሪያ ንድፍ የሚሠራው ሉዊስ እና ባለቤቱ ኬኒየ በዎልኪል ያገለግላሉ። እነሱም እንዲህ ብለዋል፦ “ይሖዋ በቁሳዊ የሚያስፈልገንን ሁሉ እጁን ዘርግቶ በልግስና ሲሰጠን አይተናል። ወደፊትም እኛን መንከባከቡን እንደሚቀጥል እርግጠኞች ነን፤ በእርግጥ ይህን የሚያደርገው እንዴት፣ መቼ ወይም የት እንደሆነ አናውቅም።”—መዝ. 34:10፤ 37:25
‘ማስቀመጫ እስክታጡ ድረስ በረከትን አፈስስላችኋለሁ’
በኒው ዮርክ ባለው የግንባታ ሥራ እገዛ ካደረጉት መካከል አብዛኞቹ ራሳቸውን በፈቃደኝነት እንዳያቀርቡ እንቅፋት የሚሆኑ ምክንያቶች ሊያቀርቡ ይችሉ ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋ “የሰማይን መስኮት የማልከፍትላችሁ፣ የተትረፈረፈ በረከትንም ማስቀመጫ እስክታጡ ድረስ የማላፈስላችሁ ከሆነ ተመልከቱ [“ፈትኑኝ፣” NW]” ብሎ ለሁላችንም ባቀረበው ግብዣ መሠረት እነዚህ ወንድሞች ይሖዋን ፈትነውታል።—ሚል. 3:10
አንተም ይሖዋን ለመፈተንና የእሱን የተትረፈረፈ በረከት ለመቅመስ ፈቃደኛ ነህ? በኒው ዮርክ እየተከናወነ ባለውም ሆነ በሌሎች ቲኦክራሲያዊ የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ በሚካሄደው አስደሳች ሥራ በመካፈል ይሖዋ እንዴት እንደሚክስህ በገዛ ዓይኖችህ ለማየት ምን ማድረግ እንደምትችል በጥሞና አስብበት።—ማር. 10:29, 30
የሲቪል መሐንዲስ የሆነው ዴል እና ባለቤቱ ካቲ የመጡት ከአላባማ ሲሆን እንዲህ ባለው አገልግሎት መካፈልን በጣም ያበረታታሉ። በዎልኪል ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆነው የሚያገለግሉት እነዚህ ባልና ሚስት እንዲህ ይላሉ፦ “የለመዳችሁትን የተመቻቸ ኑሮ ለመተው ድፍረቱ ካላችሁ የይሖዋ መንፈስ ሲሠራ የማየት አጋጣሚ ታገኛላችሁ።” አንተስ ራስህን በፈቃደኝነት ለማቅረብ የሚያስፈልግህ ምንድን ነው? ዴል እንዲህ ይላል፦ “አሁንም አሁንም ደጋግመን የምንመክረው ነገር ኑሮን ማቅለል ነው። እንዲህ በማድረጋችሁ ፈጽሞ አትቆጩም!” ከሰሜን ካሮላይና የመጣው ጌሪ በግንባታ ሥራ አስኪያጅነት የ30 ዓመት ተሞክሮ አለው። እሱና ባለቤቱ ሞሪን በዎርዊክ ካገኟቸው በረከቶች መካከል አንዱ “በቤቴል ይሖዋን ለብዙ ዓመት ያገለገሉ በርካታ ግሩም ወንድሞችንና እህቶችን ማግኘትና ከእነሱ ጋር መሥራት” እንደሆነ ይናገራሉ። ጌሪ አክሎም “በቤቴል ለማገልገል ቀላል ኑሮ መምራት ያስፈልጋል፤ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ከሁሉ የተሻለው ሕይወት ደግሞ ይህ ነው” ብሏል። ለአንድ የኤሌክትሪክ ሥራ ተቋራጭ ይሠራ የነበረው ጄሰን እና ባለቤቱ ጄኒፈር የመጡት ከኢሊኖይ ነው፤ በዎልኪል በቤቴል ፕሮጀክት ላይ መሥራት “በአዲሱ ዓለም የሚኖረውን ሕይወት ለመቅመስ ከሁሉ የተሻለ” አጋጣሚ እንደሚከፍት ይናገራሉ። ጄኒፈር አክላም እንዲህ ብላለች፦ “የምትሠሩትን ነገር ሁሉ ይሖዋ በአድናቆት እንደሚመለከተውና ሥራው ወደፊት በእሱ ዘንድ ወሮታ እንደሚያስገኝ ማወቅ በጣም ያስደስታል። ይሖዋ አትረፍርፎ ይባርካችኋል።”