ከታሪክ ማኅደራችን
በፀሐይ መውጫዋ ምድር ጎሕ ቀደደ
በዩናይትድ ስቴትስ ይኖር የነበረ ትውልደ ጃፓናዊ ፒልግሪም (ተጓዥ የበላይ ተመልካች) ሚስዮናዊ ሆኖ መስከረም 6, 1926 ወደ ጃፓን ተመለሰ። አቀባበል ያደረገለት በኮቤ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን ያስጀመረውና በአካባቢው የመጠበቂያ ግንብ ኮንትራት በመግባት ብቸኛ የነበረው ሰው ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ በዚያ ከተማ የመጀመሪያውን ትልቅ ስብሰባ ጥር 2, 1927 አደረጉ። በዚያ ስብሰባ ላይ 36 ሰዎች የተገኙ ሲሆን 8ቱ ተጠመቁ። ጅምሩ ጥሩ ቢሆንም ይህ አነስተኛ ቡድን 60 ሚሊዮን ለሚያህለው የጃፓን ሕዝብ የመጽሐፍ ቅዱስን የእውነት ብርሃን መፈንጠቅ የሚችለው እንዴት ነው?
አዲስ ነገር የመሞከር ጉጉት ያላቸው እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ግንቦት 1927 ተከታታይ የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሮችን ለማስተዋወቅ የአደባባይ ምሥክርነት ዘመቻ አካሄዱ። በኦሳካ ከተማ ለሚደረገው የመጀመሪያው ንግግር ወንድሞች በከተማዋ የእግረኛ መንገዶች ላይ የሚደረጉ ምልክቶችንና ትላልቅ ማስታወቂያዎችን ለጠፉ፤ እንዲሁም ታዋቂ ለሆኑ ሰዎች 3,000 መጋበዣዎችን ላኩ። በተጨማሪም 150,000 የጥሪ ወረቀቶችን አደሉ፤ እንዲሁም ንግግሩን በኦሳካ ዋና ዋና ጋዜጦችና በ400,000 የባቡር ቲኬቶች ላይ አስተዋወቁ። ንግግሩ በሚሰጥበት ዕለት ሁለት አውሮፕላኖች 100,000 የመጋበዣ ወረቀቶችን በከተማዋ ላይ በተኑ። የኦሳካ አሳሂ አዳራሽ “የአምላክ መንግሥት ቀርቧል” የተሰኘውን ንግግር ለማዳመጥ በተሰበሰቡ 2,300 ሰዎች ጢም ብሎ ሞላ። አንድ ሺህ የሚያህሉ ሌሎች ሰዎች በቦታ ጥበት ምክንያት ንግግሩን ሳያዳምጡ ለመመለስ ተገደዱ። ከ600 በላይ የሆኑ ተሰብሳቢዎች ከንግግሩ በኋላ በተደረገው የጥያቄና መልስ ፕሮግራም ላይ ለመካፈል አዳራሹ ውስጥ ቀርተው ነበር። በቀጣዮቹ ወራት ደግሞ በኪዮቶና በምዕራባዊ ጃፓን በሚገኙ ሌሎች ከተሞችም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ የሕዝብ ንግግሮች ቀርበዋል።
ጥቅምት 1927 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ በቶኪዮ ንግግሮች እንዲቀርቡ ዝግጅት አደረጉ። እንደ ቀድሞው ሁሉ አሁንም የመጋበዣ ወረቀቶችን ለግለሰቦች ላኩ፤ ከእነዚህ መካከል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የፓርላማ አባላት እንዲሁም ሃይማኖታዊና ወታደራዊ መሪዎችን ጨምሮ ሌሎች ታላላቅ ሰዎች ይገኙበታል። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ማስታወቂያ ሰሌዳዎችን፣ የጋዜጣ ማስታወቂያዎችንና 710,000 የጥሪ ወረቀቶችን የተጠቀሙ ሲሆን በጃፓን ዋና ከተማ የተሰጡ ሦስት ንግግሮችን ለማዳመጥ በጠቅላላው 4,800 ተሰብሳቢዎች ተገኝተው ነበር።
ቀናተኛ ኮልፖርተሮች
ከቤት ወደ ቤት በመሄድ ለሰዎች በግለሰብ ደረጃ የመንግሥቱን መልእክት ለማድረስ ኮልፖርተሮች (አቅኚዎች) ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። ከመጀመሪያዎቹ ኮልፖርተሮች መካከል አንዷ የነበረችው ማትሱኤ ኢሺ እና ባለቤቷ ጂዞ በሰሜናዊ ጫፍ ከምትገኘው ከሰፖሮ ጀምሮ እስከ ሰንዳይ፣ ቶኪዮ፣ ዮኮሃማ፣ ናጎያ፣ ኦሳካ፣ ኪዮቶ፣ ኦካያማ እና ቶኩሺማ ድረስ በመሄድ የአገሪቱን ሦስት አራተኛ ክፍል ሸፍነዋል። እህት ኢሺ እና ሳኪኮ ታናካ የሚባሉ አንዲት አረጋዊት እህት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ለማነጋገር ሲሄዱ ባሕላዊ ልብስ የሆነውን ኪሞኖ ይለብሱ ነበር። ከባለሥልጣናቱ መካከል አንዱ ዘ ሃርፕ ኦቭ ጎድ እና ዴሊቨረንስ የተባሉት መጻሕፍት እስር ቤት በሚገኙ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ እንዲቀመጡ ለማድረግ ከእያንዳንዳቸው 300 ቅጂዎች ጠየቀ።
በአንድ ወቅት ካትሱኦ እና ሀጊኖ ሚኦራ የተባሉ ባልና ሚስት ከእህት ኢሺ መጻሕፍት የተቀበሉ ሲሆን እነሱም ወዲያውኑ እውነትን እንዳገኙ ተገነዘቡ። ከዚያም በ1931 ተጠምቀው ኮልፖርተሮች ሆኑ። ሀሩኢቺ እና ታኔ ያማዳ የተባሉ ባልና ሚስት ደግሞ ከበርካታ ዘመዶቻቸው ጋር ከ1930 በፊት የመንግሥቱን መልእክት ተቀብለው ነበር። እነዚህ ባልና ሚስት ኮልፖርተር የሆኑ ሲሆን ልጃቸው ዩኪኮ ደግሞ በቶኪዮ በሚገኘው ቤቴል ማገልገል ጀመረች።
ትላልቅና ትናንሽ “ኢዩዎች”
በዚያን ጊዜ የመኪኖች ዋጋ በጣም ውድ ነበር፤ መንገዶቹም ቢሆን ጥሩ አልነበሩም። ስለዚህ ካዙሚ ሚኖውራ እና ሌሎች ወጣት ኮልፖርተሮች የሚጠቀሙት ያለነዳጅ በሚንቀሳቀሱ ተጎታች ቤቶች ነበር። እነዚህ ተሽከርካሪዎች፣ ሠረገላውን በፍጥነት በመንዳት በሚታወቀውና በኋላም የእስራኤል ንጉሥ በሆነው በኢዩ ስም ይጠሩ ነበር። (2 ነገ. 10:15, 16) ሦስት ትላልቅ ኢዩዎች የነበሩ ሲሆን እነሱም 2.2 ሜትር ርዝመት፣ 1.9 ሜትር ስፋትና 1.9 ሜትር ከፍታ ነበራቸው፤ በእያንዳንዱ ኢዩ ውስጥ ስድስት አቅኚዎች ማደር ይችሉ ነበር። በተጨማሪም በጃፓን ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ የተሠሩ በብስክሌት የሚጎተቱ ሁለት ሰው የሚይዙ 11 ትናንሽ ኢዩዎች ነበሩ። እነሱን በመሥራት እርዳታ ያበረከተው ኪኢቺ ኢዋሳኪ “እያንዳንዱ ኢዩ ድንኳንና ለመብራት የሚሆን ኤሌክትሪክ የሚያመነጭ የመኪና ባትሪ ነበረው” በማለት ያስታውሳል። ኮልፖርተሮች ከሰሜናዊዋ ሆካይዶ እስከ ደቡባዊዋ ኪዩሹ ድረስ ኢዩዎቻቸውን ዳገት ላይ እየገፉና ቁልቁለት ላይ እየጎተቱ እንዲሁም ሸለቆዎችን እያቋረጡ በመላዋ ጃፓን የእውነትን ብርሃን አዳርሰዋል።
ኢኩማትሱ ኦታ የተባለ ኮልፖርተር እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ወደ አንድ ከተማ ስንገባ ኢዩአችንን በወንዝ ዳር ወይም ሜዳ ላይ እናቆም ነበር። መጀመሪያ ላይ በከተማዋ ውስጥ እንደ ከንቲባው ያሉ ታዋቂ ሰዎችን ካነጋገርን በኋላ ጽሑፎቻችንን ለማሰራጨት ወደ እያንዳንዱ ሰው ቤት እንሄድ ነበር። ክልሉን ከሸፈንን በኋላ ወደሚቀጥለው ከተማ እንሄዳለን።”
ቀደም ሲል እንደተገለጸው እነዚያ 36 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በኮቤ የመጀመሪያውን ትልቅ ስብሰባ አደረጉ፤ ያ ወቅት ‘ሥራው በትንሹ የተጀመረበት ቀን’ ነበር። (ዘካ. 4:10 NW) ከአምስት ዓመታት በኋላ ማለትም በ1932 በጃፓን የአገልግሎት እንቅስቃሴያቸውን ሪፖርት ያደረጉ 103 ኮልፖርተሮችና አስፋፊዎች 14,000 መጻሕፍት አበርክተዋል። በዛሬው ጊዜ በጃፓን ትላልቅ ከተሞች ውስጥ የአደባባይ ምሥክርነት በተደራጀ መንገድ እየተካሄደ ነው፤ ወደ 220,000 የሚጠጉ አስፋፊዎች በፀሐይ መውጫዋ ምድር ከጫፍ እስከ ጫፍ ብርሃናቸው እያበሩ ነው።—በጃፓን ካለው የታሪክ ማኅደራችን