‘ይሖዋ ደስ የሚያሰኝ መሆኑን በትኩረት ተመልከቱ’
አስጨናቂ ሁኔታዎች የስሜት ቀውስ ሊያስከትሉብን ይችላሉ። አስተሳሰባችንን ሊቆጣጠሩ፣ ኃይላችንን ሊያሟጥጡ እንዲሁም ለሕይወት ያለንን አመለካከት ሊያዛቡ ይችላሉ። የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት ብዙ መከራዎች ተፈራርቀውበት ነበር። ታዲያ የደረሱበትን መከራዎች እንዴት ተወጣቸው? ዳዊት የዘመረው የሚከተለው ልብ የሚነካ መዝሙር መልሱን ይሰጠናል፦ “ድምፄን ከፍ አድርጌ ወደ እግዚአብሔር እጮኻለሁ፤ ድምፄን ከፍ አድርጌ ወደ እግዚአብሔር ልመና አቀርባለሁ። ብሶቴን በፊቱ አፈስሳለሁ፤ ችግሬንም በፊቱ እናገራለሁ። መንፈሴ በውስጤ ሲዝል፣ መንገዴን የምታውቅ አንተ ነህ።” አዎ፣ ዳዊት አምላክ እንዲረዳው በትሕትና ጸሎት አቅርቧል።—መዝ. 142:1-3
ዳዊት በአስቸጋሪ ወቅቶች ይሖዋ እንዲረዳው በትሕትና ጸልዮአል
ዳዊት በሌላ መዝሙር ላይ እንዲህ ሲል ዘምሯል፦ “ይሖዋን አንድ ነገር ለመንኩት፤ ምኞቴም ይኸው ነው፦ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በይሖዋ ቤት እኖር ዘንድ፣ ይሖዋ ደስ የሚያሰኝ መሆኑን በትኩረት እመለከት ዘንድ፣ ቤተ መቅደሱንም በአድናቆት አይ ዘንድ ነው።” (መዝ. 27:4 NW) ዳዊት ሌዋዊ አልነበረም፤ ያም ሆኖ የእውነተኛው አምልኮ ማዕከል ከሆነው ከቤተ መቅደሱ ውጭ ቆሞ ይታይህ። ዳዊት ልቡ እንዲህ ባለ የአመስጋኝነት ስሜት ከመሞላቱ የተነሳ ቀሪ የሕይወት ዘመኑን በዚያ ቦታ ለማሳለፍና “ይሖዋ ደስ የሚያሰኝ መሆኑን በትኩረት” ለመመልከት ተመኝቷል።
“ደስ የሚያሰኝ” የሚለው ሐረግ “ለአእምሮ አሊያም ለስሜት የሚስማማ ወይም የሚያስደስት” ሁኔታን ወይም ባሕርይን ያመለክታል። ዳዊት፣ አምላክ ያቋቋመውን የአምልኮ ዝግጅት ምንጊዜም በአድናቆት ይመለከት ነበር። እኛም ‘የዳዊት ዓይነት ስሜት አለኝ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን ተገቢ ነው።
የአምላክን ዝግጅት ‘በአድናቆት እዩ’
በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ወደ እሱ ለመቅረብ እንድንችል ያደረገልን ዝግጅት ወደ አንድ ሕንፃ መሄድን የሚጠይቅ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ታላቅ ከሆነው የአምላክ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ይኸውም ከእውነተኛው አምልኮ ቅዱስ ዝግጅት ጋር የተያያዘ ነው። * እኛም ይህን ዝግጅት ‘በአድናቆት የምንመለከት’ ከሆነ “ይሖዋ ደስ የሚያሰኝ መሆኑን በትኩረት” ማየት እንችላለን።
እስቲ አሁን ደግሞ በመገናኛው ድንኳን መግቢያ ፊት ይገኝ ስለነበረው የሚቃጠል መባ ስለሚቀርብበት የነሐስ መሠዊያ አስብ። (ዘፀ. 38:1, 2፤ 40:6) ይህ መሠዊያ አምላክ የኢየሱስን ሰብዓዊ ሕይወት እንደ መሥዋዕት አድርጎ ለመቀበል ፈቃደኛ መሆኑን የሚያመለክት ነው። (ዕብ. 10:5-10) ይህ ለእኛ ምን ትርጉም እንዳለው ቆም ብለህ እስቲ አስብ! ሐዋርያው ጳውሎስ “ጠላቶች ሆነን ሳለን በልጁ ሞት አማካኝነት ከአምላክ ጋር [ታረቅን]” በማለት ጽፏል። (ሮም 5:10) በፈሰሰው የኢየሱስ ደም ላይ እምነት የምናሳድር ከሆነ የአምላክ ወዳጅ መሆን እንችላለን፤ ይህም የእሱን ሞገስ የሚያስገኝልን ከመሆኑም ሌላ የመተማመን ስሜት እንዲያድርብን ያደርጋል። በዚህ መንገድ “ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት” መመሥረት እንችላለን።—መዝ. 25:14 NW
‘ኃጢአታችን ስለሚደመሰስ ከይሖዋ ዘንድ የመታደስ ዘመን ይመጣልናል።’ (ሥራ 3:19) ሁኔታችን የሞት ፍርዱን እየተጠባበቀ ባለበት ወቅት በቀድሞ ምግባሩ ተጸጽቶ ሥር ነቀል ለውጥ ካደረገ እስረኛ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። አንድ ደግ ዳኛ ይህን ሲመለከት በሰውየው ላይ የተላለፈው ውሳኔ ይኸውም የሞት ፍርድ እንዲሻር አደረገ። በዚህ ጊዜ እስረኛው ከፍተኛ እፎይታና ደስታ እንደሚሰማው ጥርጥር የለውም! ልክ እንደዚህ ዳኛ ይሖዋም ንስሐ ለገቡ ሰዎች ሞገስ የሚያሳያቸው ከመሆኑም ሌላ የተላለፈባቸው የሞት ፍርድ እንዲሻር ያደርጋል።
በእውነተኛው አምልኮ ደስ ይበላችሁ
ዳዊት በይሖዋ ቤት ይከናወኑ ከነበሩት የእውነተኛው አምልኮ ገጽታዎች መካከል አንዳንዶቹን ማለትም በርካታ እስራኤላውያን ወገኖቹ በዚያ ሲሰበሰቡ፣ ሕጉ ለተሰበሰበው ሕዝብ ሲነበብና ሲብራራ እንዲሁም ዕጣን ሲጨስ ብሎም ካህናቱና ሌዋውያኑ ቅዱስ አገልግሎት ሲያቀርቡ መመልከቱ አይቀርም። (ዘፀ. 30:34-38፤ ዘኍ. 3:5-8፤ ዘዳ. 31:9-12) በጥንቷ እስራኤል በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ ይከናወኑ የነበሩት እነዚህ ነገሮች በዘመናችን ካሉ መንፈሳዊ ዝግጅቶች ጋር ተዛማጅነት አላቸው።
እንደ ቀድሞው ዘመን ሁሉ ዛሬም “ወንድሞች ተስማምተው በአንድነት ሲኖሩ፣ እንዴት መልካም ነው! ምንኛስ ደስ ያሰኛል!” (መዝ. 133:1) የዓለም አቀፉ “የወንድማማች ማኅበር” ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል። (1 ጴጥ. 2:17) በስብሰባዎቻችን ላይ የአምላክ ቃል ይነበባል እንዲሁም ይብራራል። ይሖዋ በድርጅቱ በኩል ሰፊ የትምህርት መርሐ ግብር አዘጋጅቷል። በተጨማሪም ለግልና ለቤተሰብ ጥናት ልንጠቀምበት የምንችል መንፈሳዊ ምግብ በታተሙ ጽሑፎች አማካኝነት በብዛት ይቀርብልናል። የበላይ አካል አባል የሆነ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “በይሖዋ ቃል ላይ ማሰላሰሌ፣ ያዘለውን ትርጉም በጥልቅ ለመረዳት መጣሬ እንዲሁም ጥልቅ ማስተዋልና ግንዛቤ ለማግኘት ምርምር ማድረጌ ሕይወቴ በእርካታና ውድ በሆኑ መንፈሳዊ እንቁዎች የተሞላ እንዲሆን ረድቶኛል።” አዎ፣ ‘ዕውቀት ነፍሳችንን ደስ ያሰኛል።’—ምሳሌ 2:10
በዛሬው ጊዜ የአምላክ አገልጋዮች የሚያቀርቧቸው ተቀባይነት ያላቸው ጸሎቶች በየዕለቱ ወደ ይሖዋ ያርጋሉ። እንዲህ ያሉት ጸሎቶች ለይሖዋ ጥሩ መዓዛ እንዳለው ዕጣን ናቸው። (መዝ. 141:2) ይሖዋ አምላክ በትሕትና ወደ እሱ ስንጸልይ እጅግ ደስ እንደሚሰኝ ማወቃችን ምንኛ የሚያጽናና ነው!
ሙሴ “የጌታ የአምላካችን ሞገስ በላያችን ይሁን፤ የእጆቻችንን ሥራ ፍሬያማ አድርግልን” በማለት ጸልዮአል። (መዝ. 90:17) አገልግሎታችንን በቅንዓት ስናከናውን ይሖዋ ሥራችንን ይባርክልናል። (ምሳሌ 10:22) አንዳንድ ሰዎች እውነትን እንዲያውቁ ረድተን ሊሆን ይችላል። ምናልባትም የሰዎች ግድየለሽነት፣ የጤና እክል፣ የስሜት ቀውስ ወይም ስደት እያጋጠመንም በአገልግሎት ለብዙ ዓመት ጸንተን ይሆናል። (1 ተሰ. 2:2) ያም ሆኖ “ይሖዋ ደስ የሚያሰኝ መሆኑን” አላየንም? ደግሞስ በሰማይ ያለው አባታችን በምናደርገው ጥረት እጅግ እንደሚደሰት አላስተዋልንም?
ዳዊት እንዲህ ሲል ዘምሯል፦ “[ይሖዋ] የርስት ድርሻዬና ጽዋዬ ነው፤ ዕጣዬም በእጅህ ናት። መካለያ ገመድ ባማረ ስፍራ ተጥሎልኛል።” (መዝ. 16:5, 6) ዳዊት ለተሰጠው ‘ድርሻ’ ይኸውም ከይሖዋ ጋር ለመሠረተው ዝምድና እና እሱን የማገልገል መብት አመስጋኝ ነበር። እኛም እንደ ዳዊት ልዩ ልዩ መከራ ሊደርስብን ይችላል፤ ሆኖም በርካታ መንፈሳዊ በረከቶች አግኝተናል! እንግዲያው በእውነተኛው አምልኮ ደስ መሰኘታችንን እንቀጥል፤ እንዲሁም የይሖዋን መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ምንጊዜም ‘በአድናቆት እንይ።’
^ አን.6 የሐምሌ 1, 1996 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 14-24 ተመልከት።