በበጉ ሠርግ ደስ ይበላችሁ!
“የበጉ ሠርግ ስለደረሰ . . . እንደሰት፣ ሐሴትም እናድርግ።”—ራእይ 19:7
1, 2. (ሀ) በሰማይ ለደስታ ምክንያት የሚሆነው የማን ሠርግ ነው? (ለ) የትኞቹ ጥያቄዎች ይነሳሉ?
ለየትኛውም ሠርግ የሚደረግ ዝግጅት ጊዜ እንደሚጠይቅ የታወቀ ነው። አሁን ግን በዓይነቱ ልዩ በሆነ ሠርግ ያውም በአንድ ንጉሥ ሠርግ ላይ ትኩረት እናደርጋለን። ለዚህ ሠርግ ለ2,000 ዓመት ገደማ ዝግጅት ሲደረግ እንደቆየ ስታውቅ ትገረም ይሆናል! ሙሽራው ከሙሽሪት ጋር የሚጣመርበት ጊዜ በፍጥነት እየቀረበ ነው። በቅርቡ የንጉሡ ቤተ መንግሥት አስደሳች በሆነ የሙዚቃ ድምፅ ይሞላል፤ የሰማይ ሠራዊትም እንዲህ ብለው ይዘምራሉ፦ “ያህን አወድሱ፤ ምክንያቱም ሁሉን ቻይ የሆነው አምላካችን ይሖዋ ንጉሥ ሆኖ መግዛት ጀምሯል። የበጉ ሠርግ ስለደረሰና ሙሽራዋ ራሷን ስላዘጋጀች እንደሰት፣ ሐሴትም እናድርግ፤ ለእሱም ክብር እንስጠው።”—ራእይ 19:6, 7
2 በሰማይ ለደስታ ምክንያት የሚሆነው ‘የበጉ’ ሠርግ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ሠርግ ነው። (ዮሐ. 1:29) ሙሽራው ለሠርጉ የለበሰው ምን ዓይነት ልብስ ነው? ሙሽራይቱ ማን ናት? ለሠርጉ ምን ዝግጅት ስታደርግ ቆይታለች? ሠርጉ የሚከናወነው መቼ ነው? ይህ ሠርግ በሰማይ ደስታ እንዲሰፍን ያደርጋል፤ ይሁንና በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው ሰዎች የዚህ ደስታ ተካፋይ ይሆናሉ? መዝሙር 45ን በትኩረት ስንመረምር ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ እናገኛለን።
‘የልብሱ መዐዛ ያውዳል’
3, 4. (ሀ) የሙሽራውን የሠርግ ልብስ በተመለከተ ምን ተብሏል? ይበልጥ እንዲደሰት የሚያደርገውስ ነገር ምንድን ነው? (ለ) የሙሽራው ደስታ ተካፋይ የሆኑት “የነገሥታት ሴቶች ልጆች” እና “ንግሥቲቱ” ማንን ያመለክታሉ?
3 መዝሙር 45:8, 9ን አንብብ። ሙሽራው ኢየሱስ ክርስቶስ ግርማ ሞገስ የሚያጎናጽፈውን ንጉሣዊ የሠርግ ልብሱን ለብሷል። ልብሱ እንደ ከርቤና ብርጉድ ካሉ “ምርጥ ቅመሞች” ጋር የሚመሳሰል ደስ የሚል መዓዛ አለው፤ እነዚህ ቅመሞች በእስራኤል የተቀደሰ ቅብዓ ዘይት ለማዘጋጀት የሚያገለግሉ ነበሩ።—ዘፀ. 30:23-25
4 ሠርጉ እየተቃረበ ሲመጣ በሰማይ፣ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ የሚያስተጋባው የሙዚቃ ድምፅ ሙሽራው የበለጠ ደስታ እንዲሰማው ያደርጋል። “ንግሥቲቱ” ማለትም የአምላክ ድርጅት ሰማያዊ ክፍል የደስታው ተካፋይ ትሆናለች፤ የድርጅቱ ሰማያዊ ክፍል “የነገሥታት ሴቶች ልጆች” የተባሉትን ቅዱሳን መላእክት ያቀፈች ናት። የሰማይ ሠራዊት “የበጉ ሠርግ ስለደረሰ . . . እንደሰት፣ ሐሴትም እናድርግ” ብለው ሲዘምሩ መስማት እንዴት የሚያስደስት ነው!
ሙሽራዋ ለሠርጉ ተዘጋጅታለች
5. ‘የበጉ ሚስት’ ማን ነች?
5 መዝሙር 45:10, 11ን አንብብ። ሙሽራው ማን እንደሆነ አውቀናል፤ ሙሽራይቱስ ማን ነች? ኢየሱስ ክርስቶስ በሚመራው ጉባኤ አባላት የተገነባች ሙሽራ ነች። (ኤፌሶን 5:23, 24ን አንብብ።) እነዚህ ክርስቲያኖች የክርስቶስ መሲሐዊ መንግሥት አባላት ይሆናሉ። (ሉቃስ 12:32) በመንፈስ የተቀቡት እነዚህ 144,000 ክርስቲያኖች “ምንጊዜም በጉ በሄደበት ሁሉ [ይከተሉታል]።” (ራእይ 14:1-4) ‘የበጉ ሚስት’ ይሆናሉ፤ እንዲሁም በሰማይ ወደሚገኘው መኖሪያው አብረውት ይኖራሉ።—ራእይ 21:9፤ ዮሐ. 14:2, 3
6. ቅቡዓኑ “የንጉሥ ልጅ” ተብለው የተጠሩት ለምንድን ነው? ‘ሕዝባቸውን እንዲረሱ’ የተመከሩትስ ለምንድን ነው?
6 ዕጩዋ ሙሽራ “ልጄ ሆይ” ተብላ ከመጠራቷም ሌላ “የንጉሥ ልጅ” ተብላለች። (መዝ. 45:13) ይህ “ንጉሥ” ማን ነው? ቅቡዓን ክርስቲያኖች የይሖዋ “ልጆች” የመሆን መብት አግኝተዋል። (ሮም 8:15-17) ቅቡዓኑ በሰማይ ሙሽራ ስለሚሆኑ ‘ሕዝባቸውንና [የሥጋዊ] አባታቸውን ቤት’ እንዲረሱ ተመክረዋል። አእምሯቸው “በምድር ባሉት ነገሮች ላይ ሳይሆን ምንጊዜም በላይ ባሉት ነገሮች ላይ እንዲያተኩር” ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።—ቆላ. 3:1-4
7. (ሀ) ክርስቶስ ዕጩ ሙሽራዋን ሲያዘጋጃት የቆየው እንዴት ነው? (ለ) ሙሽራዋ ለዕጩ ሙሽራው ምን አመለካከት አላት?
7 ባለፉት መቶ ዘመናት ክርስቶስ ዕጩ ሙሽራዋን በሰማይ ለሚካሄደው ሠርግ ሲያዘጋጃት ቆይቷል። ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቶስ “ጉባኤውን እንደወደደና ለእሱ ራሱን አሳልፎ እንደሰጠ” ገልጿል፤ አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “እሱ ይህን ያደረገው ጉባኤውን በቃሉ አማካኝነት በውኃ አጥቦ በማንጻት ይቀድሰው ዘንድ ነው፤ ይህም ጉባኤውን ጉድፍ ወይም የቆዳ መጨማደድ ወይም እንዲህ ያሉ ነገሮች ምንም የማይገኙበት ቅዱስና እንከን የለሽ አድርጎ ውበቱን እንደጠበቀ ለራሱ ለማቅረብ ነው።” (ኤፌ. 5:25-27) ጳውሎስ በጥንቷ ቆሮንቶስ የነበሩትን ቅቡዓን ክርስቲያኖች እንዲህ ብሏቸዋል፦ “በአምላካዊ ቅናት እቀናላችኋለሁ፤ ምክንያቱም እኔ ራሴ እንደ አንዲት ንጽሕት ድንግል ለክርስቶስ አቀርባችሁ ዘንድ ለአንድ ባል አጭቻችኋለሁ።” (2 ቆሮ. 11:2) ሙሽራው፣ ንጉሡ ኢየሱስ ክርስቶስ የዕጩ ሙሽራይቱን መንፈሳዊ “ውበት” ያደንቃል። ሙሽራዋ ደግሞ እሱን ‘ጌታዋ’ አድርጋ በመቀበል ሙሽራውን ‘ታከብራለች’ ወይም እጅ ትነሳለች።
ሙሽራዋ ‘ወደ ንጉሡ ትወሰዳለች’
8. ሙሽራዋ ‘ከላይ እስከ ታች እንደተሸለመች’ ተደርጋ መገለጿ ተስማሚ የሆነው ለምንድን ነው?
8 መዝሙር 45:13, 14ሀን አንብብ። ሙሽራዋ ለንጉሣዊው ሠርግ “ከላይ እስከ ታች ተሸልማ” ተዘጋጅታለች። ራእይ 21:2 ላይ ሙሽራዋ በአንዲት ከተማ ይኸውም በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ተመስላ የተገለጸች ሲሆን ‘ለባሏ አጊጣለች።’ ይህች ሰማያዊት ከተማ “የአምላክን ክብር” የተላበሰች ከመሆኑም ሌላ ብርሃኗ “እጅግ እንደከበረ ድንጋይ፣ እንደ ኢያስጲድ ድንጋይ ሆኖ እንደ ክሪስታል ጥርት ብሎ [ያንጸባርቃል]።” (ራእይ 21:10, 11) አዲሲቱ ኢየሩሳሌም የተላበሰችው ዕፁብ ድንቅ የሆነ ውበት በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ማራኪ በሆነ መንገድ ተገልጿል። (ራእይ 21:18-21) መዝሙራዊው፣ ሙሽራዋ ‘ከላይ እስከ ታች እንደተሸለመች’ አድርጎ መግለጹ ምንም አያስገርምም! ደግሞም የንጉሡ ሠርግ የሚከናወነው በሰማይ ነው።
9. ሙሽራዋ የምትወሰደው ወደ የትኛው “ንጉሥ” ነው? አለባበሷስ ምን ይመስላል?
9 ሙሽራዋ የተወሰደችው ወደ ሙሽራው ይኸውም ወደ መሲሐዊው ንጉሥ ነው። “በቃሉ አማካኝነት በውኃ አጥቦ በማንጻት” ሲያዘጋጃት ቆይቷል። ሙሽራዋ “ቅዱስና እንከን የለሽ” ነች። (ኤፌ. 5:26, 27) በተጨማሪም ሙሽራዋ ለሠርጉ የሚስማማ አለባበስ ሊኖራት ይገባል። ደግሞም እጅግ ተውባለች! ‘ልብሷ ወርቀ ዘቦ’ ሲሆን ‘በጥልፍ ሥራ ባጌጠ ልብስ ወደ ንጉሡ ትወሰዳለች።’ ለበጉ ሠርግ “የሚያንጸባርቅና ንጹሕ የሆነ ጥሩ በፍታ እንድትጎናጸፍ ተሰጥቷታል፤ ምክንያቱም ይህ ጥሩ በፍታ የቅዱሳንን የጽድቅ ተግባር ያመለክታል።”—ራእይ 19:8
‘የበጉ ሠርግ ደርሷል’
10. የበጉ ሠርግ የሚከናወነው መቼ ነው?
10 ራእይ 19:7ን አንብብ። የበጉ ሠርግ የሚከናወነው መቼ ነው? ‘ሙሽራዋ ለሠርጉ ራሷን ያዘጋጀች’ ቢሆንም ከዚያ በመቀጠል የተጠቀሰው ሐሳብ ስለ ሠርጉ አይገልጽም። ከዚህ ይልቅ ስለ ታላቁ መከራ የመጨረሻ ምዕራፍ በግልጽ ይናገራል። (ራእይ 19:11-21) ይህ ማለት ታዲያ ሙሽራው ንጉሥ፣ ድሉን ከማጠናቀቁ በፊት ሠርጉ ይከናወናል ማለት ነው? አይደለም። በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሱት ራእዮች በጊዜ ቅደም ተከተል የተቀመጡ አይደሉም። በ45ኛው መዝሙር ላይ ስለ ንጉሡ ሠርግ የሚናገረው ሐሳብ የተጠቀሰው ንጉሡ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰይፉን ታጥቆ ጠላቶቹን ‘ድል ለማድረግ እንደሚገሰግስ’ ከተገለጸ በኋላ ነው።—መዝ. 45:3, 4
11. ክርስቶስ ድሉን ለማጠናቀቅ በቅደም ተከተል የሚወስዳቸው እርምጃዎች ምንድን ናቸው?
11 ስለዚህ የሚከናወኑት ነገሮች ቅደም ተከተል እንደሚከተለው ይሆናል ብለን መደምደም እንችላለን፦ በመጀመሪያ ክርስቶስ “በታላቂቱ ጋለሞታ” ይኸውም የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት በሆነችው በታላቂቱ ባቢሎን ላይ የፍርድ እርምጃ ይወስዳል። (ራእይ 17:1, 5, 16, 17፤ 19:1, 2) ከዚያም በምድር ላይ የሚገኘውን የቀረውን የሰይጣን ክፉ ሥርዓት ‘ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ ታላቅ የጦርነት ቀን’ ይኸውም በአርማጌዶን በማጥፋት የአምላክን ፍርድ ያስፈጽማል። (ራእይ 16:14-16፤ 19:19-21) በመጨረሻም ተዋጊው ንጉሥ ሰይጣንንና አጋንንቱን ወደ ጥልቁ ወርውሮ፣ የሞቱ ያህል ከእንቅስቃሴ ውጭ እንዲሆኑ በማድረግ ድሉን ያጠናቅቃል።—ራእይ 20:1-3
12, 13. (ሀ) የበጉ ሠርግ የሚከናወነው መቼ ነው? (ለ) በሰማይ በበጉ ሠርግ የሚደሰቱት እነማን ናቸው?
12 ክርስቶስ በሚገኝበት ወቅት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ምድራዊ ሕይወታቸውን እንዳጠናቀቁ ትንሣኤ አግኝተው በሰማይ ይኖራሉ። ታላቂቱ ባቢሎን ከጠፋች ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ኢየሱስ የቀሩትን የሙሽራዋ ክፍል አባላት በሙሉ እሱ ወዳለበት ይሰበስባቸዋል። (1 ተሰ. 4:16, 17) በመሆኑም የአርማጌዶን ጦርነት ከመፈንዳቱ በፊት ‘የሙሽራዋ’ አባላት በሙሉ ወደ ሰማይ ይሄዳሉ። ከጦርነቱ በኋላ የበጉ ሠርግ ይከናወናል። ይህ ሠርግ ምንኛ አስደሳች ይሆናል! ራእይ 19:9 “ወደ በጉ ሠርግ የራት ግብዣ የተጠሩ ደስተኞች ናቸው” ይላል። በእርግጥም የሙሽራዋ ክፍል አባላት የሆኑት 144,000ዎቹ ሐሴት ያደርጋሉ። ሙሽራው ንጉሥ፣ ተባባሪ ገዢዎቹ በጠቅላላ ከእሱ ጋር ሆነው በምሳሌያዊ ሁኔታ ‘በመንግሥቱ ከማዕዱ መብላታቸውና መጠጣታቸው’ እጅግ ያስደስተዋል። (ሉቃስ 22:18, 28-30) ይሁንና በበጉ ሠርግ ሐሴት የሚያደርጉት ሙሽራውና ሙሽራይቱ ብቻ አይደሉም።
13 ቀደም ሲል እንደተመለከትነው የሰማይ ሠራዊት በአንድነት “የበጉ ሠርግ ስለደረሰና ሙሽራዋ ራሷን ስላዘጋጀች እንደሰት፣ ሐሴትም እናድርግ፤ ለእሱም [ለይሖዋ] ክብር እንስጠው” በማለት ይዘምራሉ። (ራእይ 19:6, 7) በምድር ላይ ስላሉት የይሖዋ አገልጋዮች ምን ማለት ይቻላል? እነሱስ የዚህ ደስታ ተካፋዮች ይሆናሉ?
‘በደስታ ወደ ውስጥ ይመሯቸዋል’
14. በመዝሙር 45 ላይ የተጠቀሱት የሙሽራዋ ‘ደናግል ጓደኞች’ እነማን ናቸው?
14 መዝሙር 45:12, 14ለ, 15ን አንብብ። ነቢዩ ዘካርያስ በፍጻሜው ዘመን ከብሔራት የተውጣጡ ሰዎች ከመንፈሳዊ እስራኤል ቀሪዎች ጋር በደስታ እንደሚተባበሩ ተንብዮአል። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በእነዚያም ቀናት ከየወገኑና ከየቋንቋው ዐሥር ሰዎች የአንድን አይሁዳዊ ልብስ ዘርፍ አጥብቀው በመያዝ፣ ‘እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንዳለ ሰምተናልና አብረን እንሂድ’ ይሉታል።” (ዘካ. 8:23) በምሳሌያዊ ሁኔታ የተገለጹት እነዚህ “ዐሥር ሰዎች” መዝሙር 45:12 ላይ “የጢሮስ ሴት ልጅ” እና “ሀብታሞች” ተብለው ተገልጸዋል። የቅቡዓን ቀሪዎችን ሞገስና መንፈሳዊ እርዳታ ለማግኘት ስጦታ ይዘው ወደ እነሱ ይመጣሉ። ከ1935 ወዲህ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች፣ ቅቡዓን ቀሪዎች ‘ወደ ጽድቅ እንዲመልሷቸው’ ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል። (ዳን. 12:3) የቅቡዓን ክርስቲያኖች ታማኝ አጋሮች የሆኑት እነዚህ ሰዎች ሕይወታቸውን በማንጻት በመንፈሳዊ ደናግል ሆነዋል። እነዚህ የሙሽራዋ ‘ደናግል ጓደኞች’ ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ ከመሆኑም ሌላ የሙሽራው ንጉሥ ታማኝ ተገዢዎች መሆናቸውን አስመሥክረዋል።
15. የሙሽራዋ ‘ደናግል ጓደኞች’ በምድር ላይ ካሉት ቀሪ አባላት ጋር ተባብረው የሚሠሩት እንዴት ነው?
15 የሙሽራዋ ክፍል ቀሪ አባላት፣ “ደናግል ጓደኞቿ” ‘የመንግሥቱን ምሥራች’ በመላው ምድር ላይ በመስበክ ረገድ በቅንዓት ላበረከቱት አስተዋጽኦ አመስጋኞች ናቸው። (ማቴ. 24:14) “ና!” እያሉ ያሉት “መንፈሱና ሙሽራይቱ” ብቻ አይደሉም፤ ከዚህ ይልቅ ጥሪውን የሰሙትም “ና!” እያሉ ነው። (ራእይ 22:17) አዎ፣ “ሌሎች በጎች” በመንፈስ የተቀቡት የሙሽራዋ ክፍል አባላት የሚያሰሙትን “ና!” የሚለውን ግብዣ ተቀብለው የመጡ ከመሆኑም ሌላ ከሙሽራዋ ጋር ሆነው ለምድር ነዋሪዎች “ና!” የሚል ጥሪ እያቀረቡ ነው።—ዮሐ. 10:16
16. ይሖዋ ለሌሎች በጎች ምን መብት ሰጥቷቸዋል?
16 ቅቡዓን ቀሪዎች ለጓደኞቻቸው ከፍተኛ ፍቅር አላቸው፤ በተጨማሪም የሙሽራው አባት የሆነው ይሖዋ በምድር ላይ ለሚኖሩት ሌሎች በጎች በሰማይ የሚካሄደው የበጉ ሠርግ ደስታ ተካፋዮች እንዲሆኑ መብት እንደሰጣቸው ማወቃቸው ያስደስታቸዋል። እነዚህ “ደናግል ጓደኞቿ” “በደስታና በሐሤት ወደ ውስጥ” እንደሚወሰዱ ትንቢት ተነግሮ ነበር። አዎ፣ በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው ሌሎች በጎች በሰማይ የበጉ ሠርግ ሲፈጸም በሚኖረው አጽናፈ ዓለማዊ ደስታ ተካፋዮች ይሆናሉ። የራእይ መጽሐፍ ‘የእጅግ ብዙ ሕዝብ’ አባላት “በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆመው ነበር” ብሎ መግለጹ ተገቢ ነው። በመንፈሳዊ ቤተ መቅደሱ ምድራዊ አደባባይ ለይሖዋ ቅዱስ አገልግሎት ያቀርባሉ።—ራእይ 7:9, 15
“ወንዶች ልጆችህ በአባቶችህ እግር ይተካሉ”
17, 18. የበጉ ሠርግ ምን ውጤት ያስገኛል? ክርስቶስ በሺህ ዓመት ግዛቱ ወቅት አባት የሚሆነው ለእነማን ነው?
17 መዝሙር 45:16ን አንብብ። በሰማይ ያለችው የክርስቶስ ሙሽራ ‘ደናግል ጓደኞች’ ሠርጉ በአዲሱ ዓለም የሚያስገኘውን ውጤት በሚያዩበት ጊዜ ይበልጥ ይደሰታሉ። ሙሽራው ንጉሥ ትኩረቱን ወደ ምድር በማድረግ ምድራዊ ‘አባቶቹን’ ከሞት ያስነሳል፤ በዚህ ጊዜ ምድራዊ ‘ወንዶች ልጆቹ’ ይሆናሉ። (ዮሐ. 5:25-29፤ ዕብ. 11:35) ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹን ‘በምድር ሁሉ ላይ ገዢዎች’ አድርጎ ይሾማቸዋል። ክርስቶስ በዛሬው ጊዜ ካሉት ታማኝ ሽማግሌዎችም መካከል አንዳንዶቹን በአዲሱ ዓለም ውስጥ አመራር እንዲሰጡ እንደሚሾማቸው ምንም ጥርጥር የለውም።—ኢሳ. 32:1
18 ክርስቶስ በሺህ ዓመት ግዛቱ ወቅት ለሌሎችም አባት ይሆናል። እንዲያውም በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የሚያገኙ ሰዎች ሁሉ ይህን ሕይወት የሚያገኙት በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት በማመናቸው ነው። (ዮሐ. 3:16) በዚህ መንገድ ኢየሱስ “የዘላለም አባት” ይሆንላቸዋል።—ኢሳ. 9:6, 7
‘ስሙን ለማሳወቅ’ እንነሳሳለን
19, 20. በመዝሙር 45 ላይ የተጠቀሱት አስደሳች ክንውኖች በዛሬው ጊዜ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖችን በሙሉ የሚነኩት እንዴት ነው?
19 መዝሙር 45:1, 17ን በNW አንብብ። * በእርግጥም በመዝሙር 45 ላይ የተጠቀሱት ክንውኖች ሁሉንም ክርስቲያኖች የሚመለከቱ ናቸው። በምድር ላይ ያሉት ቅቡዓን ቀሪዎች በሰማይ ከወንድሞቻቸውና ከሙሽራው ጋር የሚገናኙበት ጊዜ እየተቃረበ በመሆኑ እጅግ ተደስተዋል። ሌሎች በጎች ደግሞ ክብራማ ለሆነው ንጉሣቸው ከምንጊዜውም ይበልጥ ለመገዛት የተነሳሱ ሲሆን በምድር ላይ ካሉት የሙሽራዋ ቀሪ አባላት ጋር ተባብሮ የመሥራት መብት በማግኘታቸው አመስጋኝ ናቸው። ክርስቶስና የመንግሥቱ ተባባሪ ገዢዎች ሠርጋቸው ከተጠናቀቀ በኋላ በምድር ላይ በሚኖሩት ሰዎች ላይ ይህ ነው የማይባል በረከት ያፈሳሉ።—ራእይ 7:17፤ 21:1-4
20 ከመሲሐዊው ንጉሥ ጋር በተያያዘ የተነገረው “መልካም የሆነ ነገር” የሚፈጸምበትን ጊዜ በጉጉት ስንጠባበቅ ‘ስሙን ለማሳወቅ’ አንነሳሳም? ‘ንጉሡን ከዘላለም እስከ ዘላለም ከሚያወድሱት’ ሰዎች መካከል ለመሆን ያብቃን!
^ አን.19 መዝሙር 45:1, 17 (NW)፦ “መልካም የሆነ ነገር ልቤን አነሳስቶታል። ‘መዝሙሬ ስለ አንድ ንጉሥ ነው’ እላለሁ። አንደበቴ የተዋጣለት ገልባጭ እንደሚጠቀምበት ብዕር ይሁን። ለሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ስምህን አሳውቃለሁ። በመሆኑም ሕዝቦች ከዘላለም እስከ ዘላለም ያወድሱሃል።”