በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የዘላለሙን ንጉሥ ይሖዋን አምልኩ

የዘላለሙን ንጉሥ ይሖዋን አምልኩ

“ለዘላለሙ ንጉሥ ክብርና ግርማ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሁን።”—1 ጢሞ. 1:17

1, 2. (ሀ) ‘የዘላለሙ ንጉሥ’ ማን ነው? ይህ ማዕረግ ይገባዋል የሚባለውስ ለምንድን ነው? (የመጀመሪያውን ሥዕል ተመልከት።) (ለ) ከንግሥናው ጋር በተያያዘ ወደ ይሖዋ እንድንቀርብ የሚያደርገን ምንድን ነው?

የስዋዚላንድ ገዢ የነበሩት ዳግማዊ ንጉሥ ሶቡዘ ለ61 ዓመታት ያህል ገዝተዋል። በንግሥና የቆዩበት ዘመን ርዝማኔ በዚህ የሥልጣኔ ዘመን ታይቶ የማይታወቅ ነው። ንጉሥ ሶቡዘ የገዙበት ዘመን ርዝማኔ አስገራሚ ነው፤ ይሁንና ገደብ ለሌላቸው ዘመናት የሚገዛ አንድ ንጉሥ አለ። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ፣ እሱ ‘የዘላለም ንጉሥ’ እንደሆነ ይናገራል። (1 ጢሞ. 1:17) አንድ መዝሙራዊ ይህን ሉዓላዊ ገዢ በስም በመጥቀስ “ይሖዋ ከዘላለም እስከ ዘላለም ንጉሥ ነው” ሲል ገልጿል።—መዝ. 10:16 NW

2 የአምላክ የንግሥና ዘመን ርዝማኔ አገዛዙን ከየትኛውም የሰው አገዛዝ የተለየ ያደርገዋል። ይሁን እንጂ ወደ ይሖዋ እንድንቀርብ የሚያደርገን የሚገዛበት መንገድ ነው። በጥንቷ እስራኤል ለ40 ዓመታት የገዛ አንድ ንጉሥ እንዲህ በማለት ለአምላክ ውዳሴ አቅርቧል፦ “እግዚአብሔር መሓሪና ይቅር ባይ፣ ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩም የበዛ ነው። እግዚአብሔር ዙፋኑን በሰማይ አጽንቶአል፤ መንግሥቱም ሁሉን ትገዛለች።” (መዝ. 103:8, 19) ይሖዋ ንጉሣችን ከመሆኑም በተጨማሪ አባታችን ነው፤ አዎ፣ በሰማይ የሚኖር አፍቃሪ አባታችን ነው። ይህ ጉዳይ ሁለት ጥያቄዎችን ያስነሳል፦ ይሖዋ አባት መሆኑን ያሳየው በምን መንገድ ነው? በኤደን ዓመፅ ከተነሳም በኋላ ይሖዋ ንጉሥ መሆኑንና ሁሉም ነገር በቁጥጥሩ ሥር እንደሆነ ያሳየው እንዴት ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጠው መልስ ይበልጥ ወደ ይሖዋ እንድንቀርብና በሙሉ ልባችን እንድናመልከው ያነሳሳናል።

 የዘላለሙ ንጉሥ አጽናፈ ዓለማዊ ቤተሰብ መሠረተ

3. የይሖዋ አጽናፈ ዓለማዊ ቤተሰብ የመጀመሪያው አባል ማን ነው? የአምላክ “ልጆች” የሆኑት ሌሎች ፍጥረታት እነማን ናቸው?

3 ይሖዋ አንድያ ልጁን ወደ ሕልውና ባመጣው ጊዜ ምንኛ ተደስቶ ይሆን! አምላክ የበኩር ልጁን ዝቅ አድርጎ አልተመለከተውም። ከዚህ ይልቅ ልጁ እንደመሆኑ መጠን ይወደው ነበር፤ ደግሞም ሌሎች ፍጹማን ተገዢዎችን በመፍጠሩ አስደሳች ሥራ እንዲሳተፍ ጋብዞታል። (ቆላ. 1:15-17) ከእነዚህም መካከል በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መላእክት ይገኙበታል። “ፈቃዱን የምትፈጽሙ አገልጋዮቹ” ተብለው የተጠሩት መላእክት አምላክን በደስታ ያገለግላሉ፤ እሱ ደግሞ ‘ልጆቼ’ ብሎ በመጥራት አክብሯቸዋል። እነዚህ የይሖዋ አጽናፈ ዓለማዊ ቤተሰብ ክፍል ናቸው።—መዝ. 103:20-22፤ ኢዮብ 38:7 የግርጌ ማስታወሻ

4. የአምላክ አጽናፈ ዓለማዊ ቤተሰብ የሰው ልጆችን ያካተተው እንዴት ነው?

4 ይሖዋ አምላክ ግዑዝ የሆኑትን ሰማያትንና ምድርን ከፈጠረ በኋላ አጽናፈ ዓለማዊው ቤተሰብ እየሰፋ እንዲሄድ አድርጓል። ይሖዋ ምድርን ራሷን በራሷ የምታድስ ውብ መኖሪያ አድርጎ ካዘጋጃት በኋላ የመጀመሪያውን ሰው አዳምን በራሱ አምሳል በመፍጠር በምድር ላይ ያከናወነውን ሥራ አስደናቂ በሆነ መንገድ አጠናቀቀ። (ዘፍ. 1:26-28) ይሖዋ ፈጣሪ ከመሆኑ አንጻር አዳም እንዲታዘዘው መጠበቁ ተገቢ ነው። ይሖዋ፣ አባት እንደመሆኑ መጠን መመሪያውን በሙሉ በፍቅርና በደግነት አስተላልፏል። እነዚህ መመሪያዎች በምንም መንገድ ሰውን ነፃነት የሚያሳጡ አይደሉም።—ዘፍጥረት 2:15-17ን አንብብ።

5. አምላክ ምድርን በሰብዓዊ ልጆቹ ለመሙላት ምን ዝግጅት አድርጓል?

5 ከብዙዎቹ ሰብዓዊ ነገሥታት በተለየ ይሖዋ ተገዢዎቹን እምነት የሚጣልባቸው የቤተሰቡ አባላት አድርጎ በመመልከት ለእነሱ ኃላፊነት መስጠት ያስደስተዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ሌሎች ሕያዋን ፍጥረታትን እንዲቆጣጠር ለአዳም ሥልጣን የሰጠው ከመሆኑም ሌላ ለእንስሳቱ ስም የማውጣት አስደሳች ብሎም ማሰብ የሚጠይቅ ሥራ ሰጥቶታል። (ዘፍ. 1:26፤ 2:19, 20) አምላክ ፍጹም የሆኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ፈጥሮ ምድርን እንዲሞሉ አላደረገም። ከዚህ ይልቅ ለአዳም ፍጹም የሆነች ማሟያ ይኸውም ሔዋንን መፍጠር መርጧል። (ዘፍ. 2:21, 22) ከዚያም እነዚህ ባልና ሚስት ልጆች በመውለድ ምድርን እንዲሞሉ ዝግጅት አደረገ። ምንም እንከን በሌለበት ሁኔታ ሰዎች ቀስ በቀስ የገነትን ድንበር በማስፋት መላዋን ምድር ገነት የማድረግ አጋጣሚ ነበራቸው። የአጽናፈ ዓለማዊው ቤተሰብ ክፍል በመሆን በሰማይ ከሚኖሩት መላእክት ጋር በኅብረት ይሖዋን ለዘላለም ማምለክ ይችሉ ነበር። እንዴት ያለ ግሩም ተስፋ ነው! በዚህ መንገድ ይሖዋ ታላቅ አባታዊ ፍቅሩን ገልጿል።

የአምላክን ንግሥና የናቁ ዓመፀኛ ልጆች

6. (ሀ) በአምላክ ቤተሰብ ውስጥ ዓመፅ የተቀሰቀሰው እንዴት ነው? (ለ) ዓመፅ መቀስቀሱ ይሖዋ ነገሮችን መቆጣጠር ተስኖታል የማያስብለው ለምንድን ነው?

6 አዳምና ሔዋን ይሖዋን እንደ ሉዓላዊ ገዢያቸው ተቀብለው ለመኖር ፈቃደኛ አለመሆናቸው የሚያሳዝን ነገር ነው። ከዚህ ይልቅ ዓመፀኛ የሆነን የአምላክ መንፈሳዊ ልጅ ይኸውም ሰይጣንን ለመከተል መረጡ። (ዘፍ. 3:1-6) ለአምላክ አንገዛም ማለታቸው በእነሱም ሆነ በዘሮቻቸው ላይ ሥቃይ፣ መከራና ሞት አስከትሏል። (ዘፍ. 3:16-19፤ ሮም 5:12) በዚያ ወቅት አምላክ በምድር ላይ በታዛዥነት የሚገዙ ሰዎች አልነበሩትም። እንዲህ ሲባል ግን ነገሮች ከአምላክ ቁጥጥር ውጭ ሆነዋል ማለት ነው? ደግሞስ በምድርና በነዋሪዎቿ ላይ ያለውን ሉዓላዊ ሥልጣን እርግፍ አድርጎ ትቶታል ማለት ነው? በፍጹም! ይልቁንም ባልና ሚስቱን ከኤደን የአትክልት ሥፍራ በማባረር ሥልጣኑን አሳይቷል፤ ተመልሰው መግባት እንዳይችሉም መግቢያውን የሚጠብቁ ኪሩቦችን መድቧል። (ዘፍ. 3:23, 24) በዚሁ ጊዜ አምላክ ለእሱ ያደሩ መንፈሳዊና ሰብዓዊ ልጆችን ያቀፈ አጽናፈ ዓለማዊ ቤተሰብ ለመመሥረት ያለው ዓላማ እንደሚፈጸም በማረጋገጥ አባታዊ ፍቅሩን ገልጿል። በተጨማሪም ሰይጣንን የሚያጠፋና የአዳም ኃጢአት ያስከተለውን መዘዝ የሚሽር “ዘር” እንደሚያስነሳ ቃል ገባ።ዘፍጥረት 3:15ን አንብብ።

7, 8. (ሀ) በኖኅ ዘመን ሁኔታዎች ምን ያህል ተበላሽተው ነበር? (ለ) ይሖዋ ምድርን ለማጽዳትና የሰብዓዊውን ቤተሰብ ሕልውና ለመጠበቅ ምን ዝግጅቶች አደረገ?

 7 ከዚያ በኋላ በነበሩት መቶ ዘመናት አንዳንድ ሰዎች ለይሖዋ ታማኝ ለመሆን መርጠዋል። ከእነሱ መካከል አቤልና ሄኖክ ይገኙበታል። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ሰዎች ይሖዋን እንደ አባታቸውና ንጉሣቸው አድርገው ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። በኖኅ ዘመን ምድር ‘በዓመፅ ተሞልታ’ ነበር። (ዘፍ. 6:11) ይህ ማለት ታዲያ ይሖዋ የምድርን ጉዳዮች መቆጣጠር አቁሟል ማለት ነው? በዚህ ረገድ ታሪክ ምን ይላል?

8 የኖኅን ታሪክ እንመልከት። ይሖዋ፣ ኖኅና ቤተሰቡ ከጥፋት መትረፍ ይችሉ ዘንድ ግዙፍ መርከብ እንዲሠራ ለኖኅ ዝርዝር መግለጫ የያዘ ንድፍም ሆነ የግንባታ መመሪያ ሰጥቶታል። ከዚህ በተጨማሪ አምላክ ኖኅን “የጽድቅ ሰባኪ” አድርጎ በመሾም ለመላው ሰብዓዊ ቤተሰብ ታላቅ ፍቅር እንዳለው አሳይቷል። (2 ጴጥ. 2:5) የኖኅ ስብከት ሰዎች ንስሐ እንዲገቡ የቀረበን ጥሪና ጥፋት እየመጣ መሆኑን የሚገልጽ ማስጠንቀቂያን እንደሚጨምር ምንም ጥያቄ የለውም፤ ይሁንና መልእክቱ ሰሚ ጆሮ አላገኘም። ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ኖኅና ቤተሰቡ ዓመፀኛ በሆነና የሥነ ምግባር አቋሙ ባዘቀጠ ዓለም ውስጥ ኖረዋል። አሳቢ አባት የሆነው ይሖዋ እነዚህን ስምንት ታማኝ ነፍሳት ጠብቋቸዋል እንዲሁም ባርኳቸዋል። ይሖዋ ዓለም አቀፍ የጥፋት ውኃ በማምጣት ዓመፀኛ በሆኑት ሰዎችና በክፉዎቹ መላእክት ላይ ያለውን ሥልጣን አሳይቷል። አዎ፣ ሁሉም ነገር በይሖዋ ቁጥጥር ሥር ነበር።—ዘፍ. 7:17-24

ይሖዋ መቼም ቢሆን ንጉሣዊ ሥልጣኑን ሲጠቀም ቆይቷል (አንቀጽ 6, 8, 10, 12 እና 17ን ተመልከት)

ከጥፋት ውኃ በኋላም ይሖዋ ገዢነቱን አሳይቷል

9. ይሖዋ ከጥፋት ውኃ በኋላ ለሰው ዘር የትኛውን አጋጣሚ ሰጠ?

9 ኖኅና ቤተሰቡ የጸዳችውን ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ ሲረግጡ ብሎም ንጹሑን አየር ሲተነፍሱ ይሖዋ ላደረገላቸው እንክብካቤና ጥበቃ ልባቸው በአመስጋኝነት ስሜት ተሞልቶ እንደሚሆን የተረጋገጠ ነው። ኖኅ ምንም ጊዜ ሳያባክን ለይሖዋ አምልኮ ለማቅረብ መሠዊያ ሠርቶ መሥዋዕት አቀረበ። አምላክ ኖኅንና ቤተሰቡን የባረካቸው ከመሆኑም ሌላ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏት” የሚል መመሪያ ሰጣቸው። (ዘፍ. 8:20 እስከ 9:1) የሰው ዘር አንድ ሆኖ የማምለክና ምድርን የመሙላት አጋጣሚ በድጋሚ ተከፈተለት።

10. (ሀ) ከጥፋት ውኃ በኋላ በይሖዋ ላይ ዓመፅ የተቀሰቀሰው የትና እንዴት ነበር? (ለ) ይሖዋ ፈቃዱ እንዲፈጸም ለማድረግ ምን እርምጃ ወሰደ?

10 ይሁን እንጂ የጥፋት ውኃው አለፍጽምናን ጠራርጎ አላስወገደም፤ የሰው ልጆችም ሰይጣንና ዓመፀኞቹ መላእክት የሚያሳድሩትን በዓይን የማይታይ ተጽዕኖ ተቋቁመው መኖር ነበረባቸው። ብዙም ሳይቆይ መልካም በሆነው የይሖዋ አገዛዝ ላይ በድጋሚ ዓመፅ ተቀሰቀሰ። ለምሳሌ ያህል፣ በኖኅ የትውልድ መሥመር አራተኛ የሆነው ናምሩድ በይሖዋ አገዛዝ ላይ የተነሳውን ዓመፅ የከፋ ደረጃ ላይ አደረሰው። ናምሩድ “ይሖዋን የሚቃወም ኃያል አዳኝ” (NW) እንደነበር ተገልጿል። እንደ ባቢሎን ያሉ ታላላቅ ከተሞችን የገነባ ከመሆኑም ሌላ “በሰናዖር ምድር” ራሱን አነገሠ። (ዘፍ. 10:8-12) የዘላለሙ ንጉሥ ይህን ዓመፀኛ ገዢ ምን ያደርገው ይሆን? ይሖዋ ‘ምድር እንድትሞላ’ ያለውን ዓላማ ለማጨናገፍ ናምሩድ የሚያደርገውን ጥረት በተመለከተስ ምን እርምጃ ይወስድ ይሆን? አምላክ የሕዝቡን ቋንቋ በማደበላለቅ የናምሩድን ተከታዮች “በምድር ሁሉ በተናቸው።” ሰዎቹ የሐሰት አምልኳቸውንና የሰብዓዊ አገዛዝ መርሖዎቻቸውን ይዘው ተበተኑ።—ዘፍ. 11:1-9

11. ይሖዋ ለወዳጁ ለአብርሃም ታማኝነት ያሳየው እንዴት ነው?

11 ከጥፋት ውኃው በኋላ ብዙዎች የሐሰት አማልክትን ያመልኩ የነበረ ቢሆንም አንዳንድ ታማኝ ሰዎች ይሖዋን ማምለካቸውን ቀጥለዋል። ከእነዚህ አንዱ አብርሃም ነው፤ ይህ ሰው በተሰጠው መመሪያ መሠረት ምቹ የሆነችውን የዑር ከተማ ለቆ በመውጣት ለበርካታ ዓመታት በድንኳን ኖሯል። (ዘፍ. 11:31፤ ዕብ. 11:8, 9) አብርሃም ዘላን ሆኖ በኖረበት ወቅት አብዛኛውን ጊዜ በሰብዓዊ ነገሥታት ተከብቦ ይኖር የነበረ ሲሆን አብዛኞቹ የሚኖሩት በግንብ በታጠሩ ከተሞች ውስጥ ነበር። ይሁንና ይሖዋ አብርሃምንና ቤተሰቡን ጠብቋቸዋል።  መዝሙራዊው የይሖዋን አባታዊ ጥበቃ በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦ “[አምላክ] ማንም ግፍ እንዲፈጽምባቸው አልፈቀደም፤ ስለ እነርሱም ነገሥታትን . . . ገሠጸ።” (መዝ. 105:13, 14) ይሖዋ ለወዳጁ ለአብርሃም ከነበረው ታማኝነት የተነሳ ‘ነገሥታት ከአንተ ይወጣሉ’ በማለት ቃል ገብቶለታል።—ዘፍ. 17:6፤ ያዕ. 2:23

12. ይሖዋ በግብፅ ላይ የበላይነቱን ያሳየው እንዴት ነው? ይህስ ለመረጣቸው ሕዝቦቹ ምን አስገኝቷል?

12 አምላክ ለአብርሃም ልጅ ለይስሐቅና ለልጅ ልጁ ለያዕቆብ እነሱን እንደሚባርክ የገባውን ቃል በድጋሚ ነግሯቸዋል፤ ይህ በረከት ከእነሱ ዘር ነገሥታት እንደሚነሱ የሚገልጸውን ተስፋ ያካትታል። (ዘፍ. 26:3-5፤ 35:11) ይሁን እንጂ በእስራኤል ብሔር ላይ ነገሥታት የሚሆኑት ከመወለዳቸው በፊት የያዕቆብ ዝርያዎች በግብፅ በባርነት ተገዝተዋል። ይህ ታዲያ ይሖዋ የሰጠውን ተስፋ አይፈጽምም ማለት ነው? ወይም ደግሞ በምድር ላይ ያለውን ሉዓላዊ ገዢነቱን እርግፍ አድርጎ ትቶታል ማለት ነው? በጭራሽ! ይሖዋ በወሰነው ጊዜ መለኮታዊ ኃይሉን ያሳየ ከመሆኑም ሌላ ግትር በሆነው በፈርዖን ላይ የበላይነቱን አሳይቷል። በባርነት ይማቅቁ የነበሩት እስራኤላውያን በይሖዋ ታምነዋል፤ እሱም ቀይ ባሕርን በማሻገር አስደናቂ በሆነ መንገድ አድኗቸዋል። በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ይሖዋ ያን ጊዜም ቢሆን የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዢ ነበር፤ አሳቢ አባት እንደመሆኑም መጠን ሕዝቡን ለመጠበቅ በታላቅ ኃይሉ ተጠቅሟል።ዘፀአት 14:13, 14ን አንብብ።

ይሖዋ የእስራኤል ንጉሥ ሆነ

13, 14. (ሀ) እስራኤላውያን የይሖዋን ንግሥና በተመለከተ ምን ብለው ዘምረዋል? (ለ) አምላክ ንግሥናን በተመለከተ ለዳዊት ምን ቃል ገብቶለት ነበር?

13 እስራኤላውያን ከግብፅ በተአምር ነፃ እንደወጡ የድል መዝሙር በመዘመር ይሖዋን አወደሱ። ዘፀአት ምዕራፍ 15 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው የድል መዝሙር ቁጥር 18 ላይ ይሖዋ “ከዘላለም እስከ ዘላለም ይነግሣል” የሚል ሐሳብ ይዟል። በእርግጥም ይሖዋ የአዲሱ ብሔር ንጉሥ ሆኗል። (ዘዳ. 33:5) ይሁን እንጂ ሕዝቡ በዓይን በማይታየው ገዢያቸው፣ በይሖዋ አልረኩም። ከግብፅ ከወጡ ከ400 ዓመታት ገደማ በኋላ አረማውያን ጎረቤቶቻቸው የነበራቸውን ዓይነት ሰብዓዊ ንጉሥ እንዲያነግሥላቸው አምላክን ጠየቁ። (1 ሳሙ. 8:5) በዚያን ጊዜም ቢሆን ይሖዋ ንጉሥ ነበር፤ የእስራኤል ሁለተኛ ንጉሥ በነበረው በዳዊት የግዛት ዘመን የዚህ እውነተኝነት ታይቷል።

14 ዳዊት ቅዱስ የሆነውን የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው። በዚህ አስደሳች ወቅት ሌዋውያኑ አንድ ትኩረት የሚስብ የውዳሴ መዝሙር  ዘምረው ነበር፤ በ1 ዜና መዋዕል 16:31 ላይ ‘በአሕዛብ መካከል “ይሖዋ ነገሠ!” ብላችሁ አስታውቁ’ ብለው እንደዘመሩ ተጠቅሷል። ይሁንና አንድ ሰው ‘ይሖዋ የዘላለም ንጉሥ ነው፤ ታዲያ በዚያ ወቅት ነገሠ ሊባል የሚችለው እንዴት ነው?’ ብሎ ይጠይቅ ይሆናል። ይሖዋ ነገሠ ሊባል የሚችለው ገዢነቱን ሲያሳይ ወይም በሆነ ጊዜ ላይ እሱን የሚወክል ወይም አንድን ሁኔታ የሚያከናውን ወኪል ሲሾም ነው። ይህ የይሖዋ ንግሥና መገለጫ ትልቅ ትርጉም አለው። ዳዊት ከመሞቱ በፊት ይሖዋ “በእግርህ እንዲተካ ከአብራክህ የተከፈለ ዘር አስነሣልሃለሁ፤ መንግሥቱንም አጸናለሁ” በማለት ንግሥናው ለዘላለም እንደሚቀጥል ቃል ገብቶለት ነበር። (2 ሳሙ. 7:12, 13) የኋላ ኋላ፣ ይህ የዳዊት “ዘር” ከ1,000 ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ ተገለጠ። ዘሩ ማን ሆኖ ተገኘ? የነገሠውስ መቼ ነው?

ይሖዋ አዲስ ንጉሥ ሾመ

15, 16. ኢየሱስ ለንግሥና የተቀባው መቼ ነበር? ምድር ላይ በነበረበት ጊዜስ ለመንግሥቱ ምን ቅድመ ዝግጅቶች አድርጓል?

15 በ29 ዓ.ም. አጥማቂው ዮሐንስ ‘መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች’ እያለ ይሰብክ ጀመር። (ማቴ. 3:2) ዮሐንስ ኢየሱስን ካጠመቀው በኋላ ይሖዋ ኢየሱስን በተስፋ ሲጠበቅ የነበረው መሲሕና የወደፊቱ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ አድርጎ ቀባው። ይሖዋ “በእሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” በማለት ለኢየሱስ ያለውን አባታዊ ፍቅር ገልጿል።—ማቴ. 3:17

16 ኢየሱስ አገልግሎቱን ባከናወነበት ጊዜ ሁሉ አባቱን አክብሯል። (ዮሐ. 17:4) ይህን ያደረገው ስለ አምላክ መንግሥት በመስበክ ነው። (ሉቃስ 4:43) ደግሞም ይህ መንግሥት እንዲመጣ ይጸልዩ ዘንድ ተከታዮቹን አስተምሯል። (ማቴ. 6:10) ኢየሱስ ለንግሥና ታጭቶ የነበረ እንደመሆኑ መጠን ተቃዋሚዎቹን “የአምላክ መንግሥት በመካከላችሁ ነው” ሊላቸው ችሏል። (ሉቃስ 17:21) ከጊዜ በኋላም ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ከተከታዮቹ ጋር ‘የመንግሥት ቃል ኪዳን’ ገባ። በዚህ መንገድ ከታማኝ ደቀ መዛሙርቱ መካከል አንዳንዶቹ በአምላክ መንግሥት አብረውት እንደሚነግሡ ተስፋ ሰጥቷል።ሉቃስ 22:28-30ን አንብብ።

17. ኢየሱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በተወሰነ መጠን መግዛት የጀመረው በምን መንገድ ነው? ሆኖም ምን ነገር ለማግኘት መጠበቅ አስፈልጎታል?

17 ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ መግዛት የሚጀምረው መቼ ነው? ንጉሣዊ ሥልጣኑን ወዲያውኑ አልያዘም። እንዲያውም በቀጣዩ ቀን ከሰዓት በኋላ ተገደለ፤ ተከታዮቹም ተበታተኑ። (ዮሐ. 16:32) ይሁን እንጂ እንደ ቀድሞው ሁሉ ይሖዋ በዚህ ጊዜም ሁሉንም ነገር ይቆጣጠር ነበር። በሦስተኛው ቀን ልጁን ከሞት አስነሳው፤ በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ በዓል ዕለት ደግሞ ኢየሱስ ቅቡዓን ወንድሞቹን ባቀፈው የክርስቲያን ጉባኤ ላይ መግዛት ጀመረ። (ቆላ. 1:13) ያም ሆኖ በተስፋ ሲጠበቅ የነበረው “ዘር” ማለትም ኢየሱስ ምድርን ለመግዛት የሚያስችል ሙሉ ንጉሣዊ ሥልጣን እስኪረከብ ድረስ መጠበቅ ነበረበት። ይሖዋ ልጁን “ጠላቶችህን ለእግርህ መርገጫ፣ እስከማደርግልህ ድረስ፣ በቀኜ ተቀመጥ” ብሎታል።—መዝ. 110:1

የዘላለሙን ንጉሥ አምልኩ

18, 19. ምን ለማድረግ ተነሳስተናል? በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንማራለን?

18 የይሖዋ አገዛዝ በሰማይም ሆነ በምድር ለበርካታ መቶ ዘመናት ግድድር ገጥሞታል። ይሖዋ ሉዓላዊ ገዢነቱን መቼም ቢሆን እርግፍ አድርጎ ትቶ አያውቅም፤ ሁሉንም ነገር ይቆጣጠራል። አፍቃሪ አባት እንደመሆኑ መጠን እንደ ኖኅ፣ አብርሃምና ዳዊት ላሉ ታማኝ ተገዢዎቹ ጥበቃና እንክብካቤ አድርጓል። ይህን ማወቃችን ለንጉሣችን እንድንገዛና ወደ እሱ ይበልጥ እንድንቀርብ አያነሳሳንም?

19 ይሁንና እንዲህ ብለን እንጠይቅ ይሆናል፦ ይሖዋ በእኛ ዘመን የነገሠው እንዴት ነው? የይሖዋ መንግሥት ታማኝ ዜጎች መሆናችንን ማስመሥከርና በአጽናፈ ዓለማዊው ቤተሰቡ ውስጥ ፍጹም ልጆች መሆን የምንችለው እንዴት ነው? የአምላክ መንግሥት እንዲመጣ መጸለያችን ምን ትርጉም አለው? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመለከታለን።