ከታሪክ ማኅደራችን
ንጉሡ እጅግ ተደሰቱ!
ጊዜው ነሐሴ 1936 ነበር። ቦታው ደግሞ የስዋዚላንድ ሮያል ክራል ወይም የንጉሡ ግቢ ውስጥ ነው። ሮበርትና ጆርጅ ኒዝቤት የድምፅ ማጉያ መሣሪያ ከተገጠመለት መኪና ላይ በመጀመሪያ የድርጅቱን ሙዚቃዎች ከዚያም የወንድም ራዘርፎርድን ንግግሮች አሰምተው ማብቃታቸው ነበር። በዚህ ጊዜ ዳግማዊ ንጉሥ ሶቡዛ እጅግ ተደሰቱ። ጆርጅ ሁኔታውን በማስታወስ እንዲህ ብሏል፦ “ንጉሡ የማጫወቻ መሣሪያውን፣ ንግግሮቹንና የድምፅ ማጉያውን ለመግዛት እንደሚፈልጉ ሲነግሩን የምንገባበት ጠፋን!”
ሮበርት ዕቃዎቹ የሚሸጡ አለመሆናቸውን እያስተዛዘነ ለንጉሡ ነገራቸው። ዕቃዎቹ የማይሸጡት ለምንድን ነው? ምክንያቱም የሌላ ግለሰብ ንብረት ናቸው። ንጉሡ የዕቃው ባለቤት ማን እንደሆነ ማወቅ ፈለጉ።
ሮበርት “የሌላ ንጉሥ ንብረት ነው” በማለት ተናገረ። ሶቡዛም ይህ ንጉሥ ማን እንደሆነ ጠየቁ። “የአምላክ መንግሥት ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” በማለት ሮበርት መለሰላቸው።
በዚህ ጊዜ ሶቡዛ በታላቅ አክብሮት “እሱማ ታላቅ ንጉሥ ነው፤ የእሱ ንብረት የሆነ አንዳች ነገር መውሰድ አልፈልግም” አሉ።
ሮበርት እንዲህ ሲል ጽፏል፦ ‘የዋናው አለቃ ማለትም የንጉሥ ሶቡዛ አስተሳሰብ በጣም አስደነቀኝ። ልቅም ያለ እንግሊዝኛ ይናገሩ የነበረ ቢሆንም ጉራም ሆነ ኩራት አይታይባቸውም፤ በተጨማሪም ግልጽና በጣም የሚቀረቡ ሰው ናቸው። ጆርጅ ውጭ ሆኖ ሙዚቃ እያጫወተ ሳለ እኔና እሳቸው ቢሯቸው ውስጥ ተቀምጠን ለ45 ደቂቃ ያህል ተነጋገርን።
‘በዚያው ዕለት፣ ምሥራቹን ለመስበክ ወደ ስዋዚ ብሔራዊ ትምህርት ቤት ሄድን፤ በዚያ በነበረን ቆይታ ከዚህ በፊት አጋጥሞን የማያውቅ በጣም አስደሳች ሁኔታ አጋጠመን። ለትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ስንመሠክርለት ደስ ብሎት አዳመጠን። የሸክላ ማጫወቻ መሣሪያ ይዘን እንደመጣንና በትምህርት ቤቱ ውስጥ ያለ ሰው ሁሉ ንግግሮቹን ማዳመጥ እንደሚችል ስንነግረው በሐሳቡ ተስማማ፤ ከዚያም መቶ የሚያህሉ ተማሪዎችን ጠርቶ ሣር ላይ ተቀምጠው እንዲያዳምጡ አደረገ። በዚህ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ወንዶች ልጆች ግብርና፣ አትክልተኝነት፣ አናፂነት፣ ግንባታ፣ እንግሊዝኛና ሒሳብ እንደሚማሩ እንዲሁም ሴቶች ልጆች ደግሞ የነርስነት ሥልጠና፣ የቤት አያያዝ ክህሎትና ሌሎች ጠቃሚ ሙያዎች እንደሚቀስሙ ተነገረን።’ ትምህርት ቤቱን ያቋቋሙት የዋናው አለቃ ሴት አያት ናቸው። *
ከ1933 አንስቶ ንጉሥ ሶቡዛ ወደ ንጉሡ ግቢ የሚመጡ አቅኚዎችን በደስታ ተቀብለው መልእክታቸውን ያዳምጡ ነበር። እንዲያውም በአንድ ወቅት 100 የሚያህሉ የግል ጠባቂዎቻቸውን ሰብስበው የተቀዳውን የመንግሥቱን መልእክት እንዲያዳምጡ አድርገዋል። ንጉሡ የመጽሔት ኮንትራት የገቡ ከመሆኑም ሌላ ጽሑፎችን ይወስዱ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ንጉሡ ቲኦክራሲያዊ ጽሑፎችን የያዘ የራሳቸው ቤተ መጻሕፍት ኖራቸው! ከዚህም በላይ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት አገሪቱን በቅኝ ግዛት የያዘው የብሪታንያ መንግሥት በጽሑፎቻችን ላይ እገዳ ጥሎ የነበረ ቢሆንም ንጉሡ ጽሑፎቻቸው እንዳለ ተጠብቀው እንዲቆዩ አድርገዋል።
ዳግማዊ ንጉሥ ሶቡዛ፣ በሎባምባ በሚገኘው ንጉሣዊ መኖሪያቸው የይሖዋ ምሥክሮችን በደስታ መቀበላቸውን ቀጥለው ነበር፤ እንዲያውም ንጉሡ፣ ቀሳውስቱ መጥተው የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሮችን እንዲያዳምጡ ያደረጉባቸው ጊዜያት ነበሩ። በአንድ ወቅት የአገሪቱ ተወላጅ የሆነ ሄልቪ መሻዚ የተባለ የይሖዋ ምሥክር ማቴዎስ ምዕራፍ 23ን እያብራራ ሳለ በዚያ የነበሩ ቄሶች በቁጣ ብድግ ብለው ወንድምን አስገድደው ለማስቀመጥ ሞከሩ። ይሁንና ንጉሡ ጣልቃ ገብተው ወንድም መሻዚ ንግግሩን እንዲቀጥል አደረጉ። ከዚህም በላይ ንጉሡ እዚያ የተሰበሰቡት ሰዎች በንግግሩ ላይ የተጠቀሱትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በሙሉ እንዲጽፉ አዘዙ!
በሌላ ወቅት ደግሞ አራት ቄሶች አንድ አቅኚ የሰጠውን ንግግር ካዳመጡ በኋላ “ከአሁን በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች ነን እንጂ ቄሶች አይደለንም” ሲሉ ገለጹ። ከዚያም ዋናው አለቃ ጋ የሚገኙት ዓይነት መጻሕፍት ይዞ እንደሆነ አቅኚውን ጠየቁት።
ዋናው አለቃ ከ1930ዎቹ አንስቶ በ1982 እስከ ሞቱበት ዕለት ድረስ የይሖዋ ምሥክሮችን በአክብሮት ይመለከቱ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ምሥክሮቹ በአገሪቱ የሚካሄዱትን የአምልኮ ሥርዓቶች ባለመከተላቸው ስደት እንዳይደርስባቸው ተከላክለዋል። በመሆኑም በአገሪቱ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች፣ አመስጋኝ እንዲሆኑ የሚያነሳሳ አጥጋቢ ምክንያት ነበራቸው፤ ደግሞም ንጉሡ በሞቱበት ወቅት ከልባቸው አዝነዋል።
በ2013 መጀመሪያ ላይ በስዋዚላንድ ከ3,000 የሚበልጡ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ነበሩ። ከአንድ ሚሊዮን ብዙም የማይበልጥ የሕዝብ ብዛት ባላት በዚህች አገር በአስፋፊዎቹና በሕዝቡ መካከል ያለው ሬሾ 1 ለ384 ነው። በ90 ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ ከ260 በላይ የሚሆኑ አቅኚዎች አገልግሎታቸውን በትጋት የሚያከናውኑ ሲሆን በ2012 በተከበረው የመታሰቢያ በዓል ላይ 7,496 ሰዎች ተገኝተዋል። ይህ አኃዝ ከፍተኛ እድገት ሊገኝ እንደሚችል ይጠቁማል። በእርግጥም፣ በስዋዚላንድ ምሥራቹ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሰበከባቸው በ1930ዎቹ ዓመታት ለስብከቱ ሥራ ጥሩ መሠረት ተጥሏል።—በደቡብ አፍሪካ ከሚገኘው የታሪክ ማኅደራችን
^ አን.8 ዘ ጎልደን ኤጅ፣ ሰኔ 30, 1937 ገጽ 629