ከታሪክ ማኅደራችን
ወቅታዊ የሆነ “ፈጽሞ የማይረሳ” ፊልም
“ፈጽሞ የማይረሳ!” ብዙዎች “የፍጥረት ድራማ” የተሰኘውን ፊልም የገለጹት በዚህ መንገድ ነበር። ይህ ፊልም የወጣው አስፈላጊ በሆነ ወቅት ላይ ሲሆን በተመለከቱት ሰዎች አእምሮ ውስጥ የማይፋቅ ትዝታ ጥሎ አልፏል። በእርግጥም “የፍጥረት ድራማ” የሂትለር አገዛዝ በአውሮፓ በነበሩት የይሖዋ ሕዝቦች ላይ ኃይለኛ የስደት ማዕበል ከማስነሳቱ ትንሽ ቀደም ብሎ ስለ ይሖዋ ታላቅ ምሥክርነት ሰጥቷል። ይሁን እንጂ “የፍጥረት ድራማ” ምንድን ነው?
በብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው የይሖዋ ሕዝቦች ዋና መሥሪያ ቤት በ1914 “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” የተባለውን ፊልም አውጥቶ ነበር። “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” ስምንት ሰዓት የሚወስድ ሲሆን ባለ ቀለም ሥዕሎች ያሉትና በድምፅ የተቀነባበረ ተንቀሳቃሽ ፊልም ነው። በመላው ዓለም የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይህን ፊልም ተመልክተውታል። “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” አጠር ባለ መንገድ የቀረበበት “ዩሬካ ድራማ” የተባለ ስላይድ ፊልምም በ1914 ወጥቶ ነበር። ይሁን እንጂ በ1920ዎቹ ዓመታት ስላይዶቹ፣ ፊልሞቹና የማሳያ መሣሪያዎቹ ከአገልግሎት ብዛት በጣም አረጁ። በሌላ በኩል ግን “ፎቶ ድራማ” የተባለውን ፊልም እንደገና ለማየት ብዙዎች ጥያቄ እያቀረቡ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በጀርመን የሉድቪክስበርክ ከተማ ነዋሪዎች “‘የፍጥረት ድራማ’ በድጋሚ የሚታየው መቼ ነው?” በማለት ይጠይቁ ነበር። ታዲያ ምን ማድረግ ይቻል ይሆን?
ድራማው መታየቱን እንዲቀጥል ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ሲባል በ1920ዎቹ ውስጥ በማግድበርግ፣ ጀርመን ቤቴል የሚገኙ ወንድሞች ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለመሥራት የሚያስችሉ ፊልሞችን ከፓሪስ፣ ፈረንሳይ እንዲሁም ስላይዶችን በላይፕሲግ እና በድሬዝደን ከሚገኙ ኩባንያዎች ገዙ። ከዚያም እነዚህን ፊልሞችና ስላይዶች “ፎቶ ድራማ” ከተባለው ከድሮው ፊልም ላይ ከተወሰዱና አገልግሎት መስጠት ከሚችሉ ስላይዶች ጋር አንድ ላይ አቀናጇቸው።
የሙዚቃ ተሰጥኦ የነበረው ወንድም ኤሪክ ፍሮስት ደግሞ ፊልሞቹንና ስላይዶቹን የሚያጅብ ሙዚቃ አዘጋጀ። የፊልሙ ትረካ በከፊል የተወሰደው ፍጥረት ከተሰኘው መጽሐፋችን ላይ ነበር። ተሻሽሎ የወጣው “የፎቶ ድራማ” ፊልም “የፍጥረት ድራማ” የሚል አዲስ ስያሜ የተሰጠው ለዚህ ነው።
እንደ “ፎቶ ድራማ” ሁሉ አዲሱ ፊልምም የሚወስደው ጊዜ ስምንት ሰዓት ሲሆን ታሪኩ ተከፋፍሎ ለተከታታይ ቀናት ምሽት ላይ ይቀርብ ነበር። ይህ ፊልም ስለ ፍጥረት ቀናት ስሜት በሚማርክ መልኩ በዝርዝር የቀረቡ ዘገባዎችን የያዘ ከመሆኑም ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስንና የዓለምን ታሪክ በማስቃኘት የሐሰት ሃይማኖት በሰው ዘር ላይ ያደረሰውን ጉዳት ያሳያል። “የፍጥረት ድራማ” በሉክሰምበርግ፣ በስዊዘርላንድ፣ በኦስትሪያና በጀርመን እንዲሁም ጀርመንኛ ተናጋሪዎች ባሉባቸው ሌሎች ቦታዎች ታይቷል።
ኤሪክ ፍሮስት እንዲህ ብሏል፦ “በፊልሙ መካከል ባለው የእረፍት ጊዜ ባልደረቦቼን፣ በተለይም በኦርኬስትራው ውስጥ የሚሠሩትን ወደ ተመልካቾቹ ሄደው ግሩም የሆኑትን መጽሐፎቻችንንና ቡክሌቶቻችንን እንዲያበረክቱ አበረታታኋቸው። ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል ከምናበረክተው በላይ በዚህ መንገድ ብዙ ጽሑፎችን ማበርከት ችለናል።” በፖላንድና በአሁኗ ቼክ ሪፑብሊክ ፊልሙን ለማሳየት የተደረገውን ዝግጅት ያደራጀው ዮሐንስ ራውተ፣ ፊልሙን የተመለከቱ ብዙ ሰዎች ቤታቸው ሄደን እንድናነጋግራቸው አድራሻዎቻቸውን ለወንድሞች እንደሰጡ ያስታውሳል። እነዚህን አድራሻዎች ማግኘታችን ውጤታማ ተመላልሶ መጠይቆችን እንድናደርግ አስችሎናል።
በ1930ዎቹ ውስጥም “የፍጥረት ድራማ” ሲታይ በጣም ብዙ ሰዎች የተገኙ ሲሆን የይሖዋ ምሥክሮች የከተማው ሕዝብ የመነጋገሪያ ርዕስ ሆነው ነበር። እስከ 1933 ባሉት ዓመታት ውስጥ በጀርመን የነበረው ቅርንጫፍ ቢሯችን ፊልሙን ለማሳየት ባዘጋጃቸው ፕሮግራሞች ላይ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ተገኝቷል። ኬቴ ክራውስ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ በማስታወስ እንዲህ ብላለች፦ “አምስቱንም ቀናት ጫካ እያቋረጥን እንዲሁም ተራራ እየወጣንና እየወረድን ፊልሙ የሚታይበት ቦታ ለመድረስ ብቻ በእግራችን 10 ኪሎ ሜትር እንጓዝ ነበር።” ኤልዘ ቢልሃርትስ ደግሞ “ለእውነት ፍቅር እንዳዳብር መሠረት የሆነኝ ‘የፍጥረት ድራማ’ ነው” ብላለች።
አልፍሬድ አልሜንዲንገር፣ እናቱ ፊልሙን ካየች በኋላ ምን እንዳደረገች ሲገልጽ “እጅግ ከመደሰቷ የተነሳ መጽሐፍ ቅዱስ ገዝታ ‘መንጽሔ’ የሚለውን ቃል መፈለጓን ተያያዘችው” ብሏል። ይህን ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ልታገኘው ስላልቻለች ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄዷን ያቆመች ሲሆን ተጠምቃ የይሖዋ ምሥክር ሆነች። ኤሪክ ፍሮስት “ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች ‘በፍጥረት ድራማ’ አማካኝነት ወደ እውነት መጥተዋል” በማለት ያስታውሳል።—3 ዮሐ. 1-3
“የፍጥረት ድራማ” የተባለው ፊልም ለብዙዎች እየታየ በነበረበት ወቅት የናዚ ፓርቲ ማዕበል አውሮፓን እያጥለቀለቀው መጣ። ከ1933 አንስቶ በጀርመን የይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ ታገደ። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በ1945 እስኪያበቃ ድረስ በአውሮፓ የሚገኙ የይሖዋ አገልጋዮች ከፍተኛ ስደት ደርሶባቸዋል። ኤሪክ ፍሮስት ስምንት ዓመት ያህል በእስራት አሳልፏል። ይሁን እንጂ በሕይወት የተረፈ ሲሆን ከጊዜ በኋላ በቪስባደን፣ ጀርመን በሚገኘው ቤቴል አገልግሏል። “የፍጥረት ድራማ” የተባለው ፈጽሞ የማይረሳ ፊልም በጣም ብዙ ክርስቲያኖች በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የደረሰባቸውን የእምነት ፈተና ለመቋቋም ድፍረት እንዲያገኙ ስለረዳቸው በእርግጥም ወቅታዊ ነበር ማለት ይቻላል!—በጀርመን ካለው የታሪክ ማኅደራችን