ልብህ እንዳያታልልህ ተጠንቀቅ
“የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ ነው፤ ፈውስም የለውም” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ኤር. 17:9) አንድ ነገር ለማድረግ በጣም ስንፈልግ የልባችንን ምኞት ለማሳካት ሰበብ መደርደር ይቀናናል።
ቅዱሳን መጻሕፍት “ከልብ ክፉ ሐሳብ፣ ግድያ፣ ምንዝር፣ ዝሙት፣ ሌብነት፣ በሐሰት መመስከርና ስድብ ይወጣሉ” በማለት ያስጠነቅቁናል። (ማቴ. 15:19) ምሳሌያዊው ልባችን ሊያታልለንና ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚጋጭ ነገር ለመፈጸም ሰበብ እንድንፈጥር ሊያደርገን ይችላል። ልባችን እንዳታለለን የምንገነዘበው ጥበብ የጎደለው ድርጊት ከፈጸምን በኋላ ሊሆን ይችላል። ታዲያ የተሳሳተ ድርጊት ከመፈጸም መራቅ እንድንችል በልባችን ውስጥ ያለው ምን እንደሆነ በትክክል ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?
በልብህ ውስጥ ያለውን ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ አንብብ፤ እንዲሁም ባነበብከው ነገር ላይ አሰላስል።
ሐዋርያው ጳውሎስ “የአምላክ ቃል ሕያውና ኃይለኛ ነው፤ በሁለት በኩል ስለት ካለው ከየትኛውም ሰይፍ የበለጠ ስለታም ነው፤ ነፍስንና መንፈስን . . . እስኪለያይ ድረስ ሰንጥቆ ይገባል” በማለት ጽፏል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የአምላክ መልእክት ‘የልብን ሐሳብና ዓላማ መረዳት ይችላል።’ (ዕብ. 4:12) በእርግጥም ቅዱሳን መጻሕፍት ከሚናገሩት አንጻር ራሳችንን መመርመር ልባችንን ለማወቅ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል። እንግዲያው የአምላክን ቃል በየዕለቱ በማንበብና ባነበብነው ነገር ላይ በማሰላሰል የይሖዋ ዓይነት አስተሳሰብና አመለካከት ማዳበራችን በጣም አስፈላጊ ነው!
ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክሮችን መቀበላችንና የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ማዋላችን በውስጣችን ሆኖ ‘የሚመሠክርልንን’ ሕሊናችንን ለማሠልጠን ይረዳናል። (ሮም 9:1) ሕሊናችን የሚያሰማው ማስጠንቀቂያ የተሳሳተ አካሄድ ለመከተል ሰበብ ከማቅረብ እንድንቆጠብ ይረዳናል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ‘ማስጠንቀቂያ’ ሆነው ሊያገለግሉን የሚችሉ ምሳሌዎችን ይዟል። (1 ቆሮ. 10:11) ከእነዚህ ምሳሌዎች ትምህርት መውሰዳችን ወደተሳሳተ አቅጣጫ የሚመራ ጎዳና ከመከተል እንድንርቅ ሊረዳን ይችላል። ታዲያ እያንዳንዳችን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
አምላክ የልብህን ዝንባሌ ለማወቅ እንዲረዳህ ጸልይ።
ይሖዋ ‘ልብን ይመረምራል።’ (1 ዜና 29:17) እሱ “ከልባችን ይበልጥ ታላቅ ነው፤ ደግሞም ሁሉንም ነገር ያውቃል።” (1 ዮሐ. 3:20) አምላክ ሊታለል አይችልም። የሚያሳስበንን ነገር፣ ስሜታችንንና ምኞታችንን በጸሎት ለይሖዋ በግልጽ ከነገርነው የልባችንን ዝንባሌ ማወቅ እንድንችል ይረዳናል። ሌላው ቀርቶ አምላክን “ንጹሕ ልብ ፍጠርልኝ” ብለን ልንጠይቀው እንችላለን። (መዝ. 51:10) ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው የልባችንን ዝንባሌ በማወቅ ረገድ ጸሎት ትልቅ ሚና ይጫወታል።
በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በጥሞና አዳምጥ።
በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የሚቀርበውን ትምህርት በትኩረት መከታተላችን ውስጣዊ ማንነታችንን ይኸውም ልባችንን በሐቀኝነት እንድንመረምር ሊረዳን ይችላል። እርግጥ ነው፣ በስብሰባዎቻችን ላይ አዲስ እውቀት የምናገኘው ሁልጊዜ አይደለም፤ ያም ቢሆን በስብሰባ ላይ መገኘታችን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በተመለከተ የተሻለ ግንዛቤ ለማግኘት እንዲሁም ጠቃሚ ማሳሰቢያዎችን ለመማር ያስችለናል፤ ይህ ደግሞ የልባችንን ምኞት ለማወቅ ይረዳናል። ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሚሰጧቸው ሐሳቦችም ንጹሕ ልብ እንዲኖረን በማድረግ ረገድ የማይናቅ ድርሻ ያበረክታሉ። (ምሳሌ 27:17) አዘውትረን በስብሰባዎች ላይ በመገኘት ከክርስቲያን ባልንጀሮቻችን ጋር ከመቀራረብ ይልቅ ራሳችንን ከሌሎች የምናገልል ከሆነ ጉዳት ይደርስብናል። ይህ ዓይነቱ አካሄድ ‘የራሳችንን ፍላጎት ብቻ እንድንከተል’ ያደርገናል። (ምሳሌ 18:1) እንግዲያው ‘በሁሉም ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሬ እገኛለሁ? ከእነዚህ ስብሰባዎችስ ጥቅም ለማግኘት ጥረት አደርጋለሁ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን ብልኅነት ነው።—ዕብ. 10:24, 25
ልባችን ሊያታልለን የሚችለው እንዴት ነው?
ተንኮለኛው ልባችን ሊያታልለንና በተለያዩ የሕይወታችን ዘርፎች የተሳሳተ ውሳኔ እንድናደርግ ሊገፋፋን ይችላል። ቁሳዊ ነገሮችን ከማሳደድ፣ ከአልኮል መጠጥ፣ ከጓደኛ ምርጫ እንዲሁም ከመዝናኛ ጋር በተያያዘ ልባችን ሊያታልለን የሚችለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
ቁሳዊ ሀብት ማሳደድ፦
የሚያስፈልጉንን ነገሮች ለማሟላት መፈለጋችን ምንም ስህተት የለውም። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ለቁሳዊ ሀብት ከልክ ያለፈ ትኩረት መስጠትን በሚመለከት የተናገረውን የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ማስታወስ ይኖርብናል። ኢየሱስ ጎተራዎቹ ሙሉ ስለሆኑ አንድ ሀብታም ሰው የሚገልጽ ምሳሌ ተናግሮ ነበር። ሀብታሙ ሰው፣ ጎተራዎቹ ከመሙላታቸው የተነሳ ያገኘውን የተትረፈረፈ ምርት የሚያስቀምጥበት ቦታ አልነበረውም። በመሆኑም ሰውየው የነበሩትን ጎተራዎች ለማፍረስና ሌሎች ትላልቅ ጎተራዎች ለመሥራት አሰበ። በልቡም እንዲህ አለ፦ “በዚያም [በአዳዲሶቹ ጎተራዎች] እህሌን ሁሉና ያሉኝን ጥሩ ነገሮች ሁሉ አከማቻለሁ፤ ነፍሴንም ‘ነፍሴ ሆይ፣ ለብዙ ዘመን የሚበቃ የተከማቸ ሀብት አለሽ፤ እንግዲህ ዘና በይ፣ ብዪ፣ ጠጪ፣ ደስም ይበልሽ’ እላታለሁ።” ይሁን እንጂ ይህ ሀብታም ሰው የዘነጋው ትልቅ ሐቅ ነበር፤ በዚያ ምሽት ሕይወቱን ሊያጣ እና ያከማቸው ሁሉ ከንቱ ሊሆን እንደሚችል አላሰበም።—ሉቃስ 12:16-20
እኛም ዕድሜያችን እየገፋ ሲሄድ በእርጅና ዘመናችን መጦሪያ የሚሆነንን ሀብት ስለ ማከማቸት ከልክ በላይ እንጨነቅ ይሆናል፤ በዚህም የተነሳ ይህን ሰበብ በማድረግ ክርስቲያናዊ ኃላፊነቶቻችንን ችላ ማለት ወይም ከስብሰባ ቀርተንም ቢሆን ተጨማሪ ሰዓት መሥራት ልንጀምር እንችላለን። እንዲህ ዓይነት ዝንባሌ እንዳናዳብር መጠንቀቅ አይኖርብንም? በሌላ በኩል ደግሞ በወጣትነት ዕድሜ ላይ የምንገኝ ልንሆን እንችላለን፤ በሕይወታችን ልናከናውነው የምንችለው ከሁሉ የተሻለ ነገር በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መሰማራት እንደሆነ ብንገነዘብም አቅኚ ከመሆናችን በፊት በኑሮ ልንደላደል እንደሚገባ እናስባለን? በአምላክ ዘንድ ሀብታም ለመሆን ዛሬውኑ የምንችለውን ሁሉ ማድረግ አይገባንም? ደግሞስ ነገ በሕይወት መኖር አለመኖራችንን ማን ያውቃል?
የአልኮል መጠጥ፦
ምሳሌ 23:20 “ብዙ የወይን ጠጅ ከሚጠጡ . . . ጋር አትወዳጅ” በማለት ይናገራል። አንድ ሰው የአልኮል መጠጥ በጣም የሚወድ ከሆነ አዘወትሮ መጠጣት ምንም ችግር እንደሌለው ያስብ ይሆናል። የሚጠጣው ዘና ለማለት እንጂ ለመስከር እንዳልሆነ ይናገር ይሆናል። ይሁንና ዘና ለማለት የአልኮል መጠጥ የሚያስፈልገን ከሆነ ልባችንን በሐቀኝነት መመርመር ይኖርብናል።
የጓደኛ ምርጫ፦
በእርግጥ በትምህርት ቤት፣ በሥራ ቦታና በአገልግሎት በምንካፈልበት ጊዜ ከማያምኑ ሰዎች ጋር መገናኘታችን የማይቀር ነው። ይሁንና ከእነሱ ጋር ከሚገባው በላይ ጊዜ ማሳለፍ አልፎ ተርፎም የቅርብ ወዳጅነት መመሥረት ተገቢ አይሆንም። እነዚህ ሰዎች ብዙ ጥሩ ባሕርያት እንዳሏቸው በማሰብ ከእነሱ ጋር መወዳጀታችን ምንም ስህተት እንደሌለው ለማስመሰል እንሞክራለን? መጽሐፍ ቅዱስ “አትታለሉ። መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን አመል ያበላሻል” በማለት ያስጠነቅቃል። (1 ቆሮ. 15:33) ቆሻሻ ትንሽም እንኳ ቢሆን ንጹሕ ውኃ ውስጥ ከገባ ውኃውን እንደሚበክለው ሁሉ መንፈሳዊ ካልሆኑ ሰዎች ጋር ወዳጅነት መፍጠራችንም መንፈሳዊነታችንን ሊበክለውና በአመለካከታችን፣ በአለባበሳችን፣ በአነጋገራችን እንዲሁም በምግባራችን ዓለምን እንድንመስል ሊያደርገን ይችላል።
መዝናኛ፦
ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተለያዩ የመዝናኛ ዓይነቶችን በቀላሉ ለማግኘት ያስችለናል፤ ይሁንና ከእነዚህ መዝናኛዎች አብዛኞቹ አጠያያቂ ወይም ለክርስቲያን የማይገቡ ናቸው። ጳውሎስ “ማንኛውም ዓይነት ርኩሰት . . . በመካከላችሁ ከቶ አይነሳ” በማለት ጽፏል። (ኤፌ. 5:3) ርኩስ የሆነ ነገር ለመመልከት ወይም ለማዳመጥ ብንፈተንስ? ሁሉም ሰው ዘና ማለት እንደሚያስፈልገውና የመዝናኛ ምርጫ የግል ውሳኔ እንደሆነ ይሰማን ይሆናል። ይሁንና የጳውሎስን ምክር ልብ በማለት ርኩስ የሆነ ነገር ላለማየት ወይም ላለመስማት ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ይኖርብናል።
ለውጥ ማድረግ እንችላለን
በተንኮለኛው ልባችን ተታልለን ለራሳችን ሰበብ እያቀረብን የተሳሳቱ ድርጊቶችን መፈጸም ልማድ ሆኖብን ሊሆን ይችላል፤ ይሁንና ለውጥ ማድረግ እንችላለን። (ኤፌ. 4:22-24) እስቲ ሁለት ዘመናዊ ምሳሌዎችን እንመልከት።
ሚጌል * ስለ ቁሳዊ ሀብት የነበረውን አስተሳሰብ ማስተካከል አስፈልጎት ነበር። እንዲህ ይላል፦ “እኔና ሚስቴ እንዲሁም ልጃችን የምንኖረው ምርጥና በጣም ዘመናዊ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ሊያመልጡን እንደማይገባ እንዲሁ የተንደላቀቀ ሕይወት ሊኖረን እንደሚገባ በሚታሰብበት አገር ነው። በአንድ ወቅት፣ ዓለም የሚያቀርበውን ነገር ሁሉ ለማግኘት ጥረት ባደርግም በፍቅረ ንዋይ ወጥመድ እንደማልወድቅ ተሰምቶኝ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ግን ቁሳዊ ሀብትን ማሳደድ መውጫ የሌለው ሽክርክሪት ውስጥ እንደ መግባት መሆኑን ተገነዘብኩ። በዚህ ጊዜ አመለካከቴንና የልቤን ምኞት በተመለከተ ወደ ይሖዋ ጸለይኩ። በቤተሰብ አንድ ላይ ሆነን እሱን በሙሉ ልብ ማገልገል እንደምንፈልግ ገለጽኩለት። ከዚያም አኗኗራችንን ቀላል ለማድረግና የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄደን ለማገልገል ወሰንን። ብዙም ሳይቆይ አቅኚዎች ሆነን ማገልገል ጀመርን። የሚያረካና ደስተኛ ሕይወት ለመምራት የግድ ቁሳዊ ሀብት እንደማያስፈልግ ተገንዝበናል።”
የሊ ተሞክሮ ደግሞ ራስን በሐቀኝነት መመርመር ከመጥፎ ጓደኝነት ለመላቀቅ እንዴት እንደሚረዳ ያሳያል። ሊ እንዲህ ብሏል፦ “ሥራዬ፣ ዕቃ ከሚያቀርቡልን ሰዎች ጋር አዘውትሬ ጊዜ እንዳሳልፍ ያደርገኛል። ከእነዚህ ሰዎች ጋር ስሆን ብዙ መጠጥ እንደሚቀርብ ባውቅም በስብሰባዎቹ ላይ መገኘት ያስደስተኝ ነበር። ለመስከር ጥቂት እስኪቀረኝ ድረስ የጠጣሁባቸው ጊዜያት ብዙ ናቸው፤ በኋላ ላይ ግን እንዲህ ማድረጌ ይጸጽተኛል። በመሆኑም ልቤን በሐቀኝነት መመርመር ነበረብኝ። ከአምላክ ቃል ያገኘሁት ምክርና የጉባኤ ሽማግሌዎች ያካፈሉኝ ጠቃሚ ሐሳብ ወዳጅነት የመሠረትኩት ይሖዋን ከማይወዱ ሰዎች ጋር እንደሆነ እንድገነዘብ ረዳኝ። አሁን በተቻለ መጠን ሥራዬን በስልክ ለማከናወን የምጥር ሲሆን ዕቃ ከሚያቀርቡልኝ ሰዎች ጋር በአካል የምገናኝበትን አጋጣሚ ለመቀነስ እሞክራለሁ።”
በልባችን ውስጥ ያለውን ለማወቅ ራሳችንን በሐቀኝነት መመርመር ያስፈልገናል። ይህንንም ስናደርግ፣ ይሖዋ “ልብ የሰወረውን የሚረዳ” አምላክ መሆኑን በማስታወስ እሱ እንዲረዳን በጸሎት መጠየቅ ይኖርብናል። (መዝ. 44:21) በተጨማሪም አምላክ እንደ መስታወት ሆኖ የሚያገለግለንን ቃሉን ሰጥቶናል። (ያዕ. 1:22-25) ከዚህም ሌላ በክርስቲያናዊ ጽሑፎችና በስብሰባዎቻችን ላይ የምናገኛቸው ማሳሰቢያዎችና ምክሮች በጣም ጠቃሚ ናቸው! እንደዚህ ባሉት ዝግጅቶች ከተጠቀምን ልባችንን መጠበቅና በጽድቅ መንገድ መጓዛችንን መቀጠል እንችላለን።
^ စာပိုဒ်၊ 18 ስሞቹ ተቀይረዋል።