የሕይወት ታሪክ
ወዳጅነታችን 60 ዓመታት ቢያስቆጥርም ገና መጀመሩ ነው
በ1951 በአንድ ሞቃት ምሽት ላይ በ20ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ የሚገኙ አራት ወጣቶች፣ ጎን ለጎን ሆነው ወደተሠሩ ስልክ መደወያ ቤቶች ገቡ። በኢተካ፣ ኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙት እነዚህ ወጣቶች የሚደውሉት ወደ ሚሺገን፣ አዮዋ እና ካሊፎርኒያ ነው። የሰሙትን ምሥራች ሩቅ ላሉት ቤተሰቦቻቸው ለማካፈል ጓጉተው ነበር!
ከዚያ ቀደም ብሎ በየካቲት ወር 122 አቅኚዎች በ17ኛው የጊልያድ ትምህርት ቤት ለመካፈል በሳውዝ ላንሲንግ፣ ኒው ዮርክ ተሰባስበው ነበር። የሚስዮናዊነት ሥልጠና ለማግኘት ከመጡት መካከል ሎውል ተርነር፣ ዊልያም (ቢል) ካስተን፣ ሪቻርድ ኬልሲ እና ሬመን ቴምፐልተን ይገኙበታል። ከሚሺገን የመጡት ሎውልና ቢል፣ ከአዮዋ የመጣው ሪቻርድ እንዲሁም ከካሊፎርኒያ የመጣው ሬመን ጓደኛሞች ለመሆን ጊዜ አልወሰደባቸውም።
ከአምስት ወራት በኋላ፣ ወንድም ናታን ኖር ለተማሪዎቹ ንግግር ለመስጠት ከዋናው መሥሪያ ቤት እንደሚመጣ ማስታወቂያ ሲነገር ሁሉም በጣም ጓጉ። አራቱ ወንድሞች ከተቻለ በአንድ አገር ቢመደቡ ደስ እንደሚላቸው ገልጸው ነበር። ታዲያ ወንድም ኖር፣ ሚስዮናዊ ሆነው የሚላኩት ወዴት እንደሆነ ይነግራቸው ይሆን? አዎን፣ ምድባቸውን የሚያውቁበት ሰዓት ተቃርቧል!
ወንድም ኖር ለተማሪዎቹ ምድባቸውን መናገር ሲጀምር ሁሉም ጭንቅ ብሏቸው ነበር። ወደ መድረኩ መጀመሪያ የተጠሩት አራቱ ወጣቶች ናቸው፤ አራቱም ወደ መድረኩ የወጡት ልባቸው በኃይል እየመታ ቢሆንም አንድ ላይ እንደተመደቡ ሲያውቁ እፎይ አሉ! ይሁንና የተመደቡት የት ነው? ወደ ጀርመን እንደሚላኩ ሲነገራቸው ሌሎቹ ተማሪዎች በጣም የተገረሙ ከመሆኑም ሌላ ጭብጨባው ከዳር እስከ ዳር አስተጋባ።
በጀርመን የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ከ1933 ጀምሮ በሂትለር አገዛዝ ሥር ያሳዩት ታማኝነት በሁሉም ቦታ የሚገኙ ወንድሞቻቸውን አስደንቋል። ብዙዎቹ ተማሪዎች ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ በአውሮፓ ለሚገኙ ወንድሞቻቸው ልብሶችንና ኬር የተባለው ድርጅት (ከጦርነቱ ለተረፉ ሰዎች እርዳታ የሚያቀርብ ድርጅት ነው) የሚያቀርባቸውን የእርዳታ ቁሳቁሶች አዘጋጅተው በመላኩ ሥራ እንደተካፈሉ ያስታውሳሉ። በጀርመን የሚገኙት የአምላክ ሕዝቦች የላቀ እምነት፣ ጽናትና ድፍረት በማሳየት እንዲሁም በይሖዋ በመታመን ረገድ ግሩም ምሳሌ ትተዋል። ሎውል ‘አሁን እነዚህን ውድ ወንድሞችና እህቶች በቅርብ ለማወቅ የሚያስችል አጋጣሚ እናገኛለን’ ብሎ አስቦ እንደነበር ያስታውሳል። አራቱም በምድባቸው በጣም መደሰታቸውና በዚያኑ ምሽት ለወዳጅ ዘመዶቻቸው ስልክ መደወላቸው ምንም አያስገርምም!
ወደ ጀርመን አቀኑ
ሐምሌ 27 ቀን 1951 ሆምላንድ የተባለችው መርከብ አራቱን ጓደኛሞች አሳፍራ ከኒው ዮርክ፣ ኢስት ሪቨር በመነሳት ወደ ጀርመን ለመሄድ 11 ቀናት የሚፈጀውን ጉዞ ተያያዘችው። ከጊልያድ አስተማሪዎች አንዱ የነበረውና ከጊዜ በኋላ
የበላይ አካሉ አባል የሆነው ወንድም አልበርት ሽሮደር ለአራቱ ወጣቶች በጀርመንኛ የመግባቢያ ዓረፍተ ነገሮችን አስተምሯቸው ነበር። በመርከቧ ላይ በርካታ ጀርመናውያን ተሳፍረው ስለነበር አራቱ ወጣቶች ቋንቋውን የበለጠ መማር እንደሚችሉ ተሰምቷቸው ይሆናል። ይሁንና ጀርመንኛ የሚናገሩት ተሳፋሪዎች የተጠቀሙባቸው ቀበሌኛዎች የተለያዩ ሳይሆኑ አልቀሩም። ወጣቶቹ ምንኛ ግራ ተጋብተው ይሆን!እነዚህ ወንድሞች የባሕሩ ጉዞ ሲያንገላታቸው ከቆየ በኋላ ማክሰኞ ነሐሴ 7 ሃምቡርግ፣ ጀርመን ደረሱ። ከስድስት ዓመታት በፊት ያበቃው ጦርነት ትቶት ያለፈውን አሻራ በሄዱበት ሁሉ ይመለከቱ ስለነበር ሁኔታው አሳዘናቸው። ከዚያም በምሽቱ ባቡር ተሳፍረው በወቅቱ በቪስባደን ይገኝ ወደነበረው ቅርንጫፍ ቢሮ አቀኑ።
በጀርመን መጀመሪያ ያገኙት የይሖዋ ምሥክር ሃንስ የተባለ በጀርመንኛ የተለመደ ስም ያለው ወንድም ነበር። ሃንስ፣ ረቡዕ ጠዋት ባቡር ጣቢያ መጥቶ ከተቀበላቸው በኋላ ወደ ቤቴል ወሰዳቸው፤ በዚያም ከአንዲት ኮስተር ያለች በዕድሜ የገፋች እህት ጋር አገናኝቷቸው ሄደ። ይህች እህት እንግሊዝኛ ፈጽሞ አትችልም ነበር። ያም ቢሆን ጮክ ብላ ከተናገረች እንደሚረዷት ሳታስብ አልቀረችም። እህት ድምፅዋን የቱንም ያህል ከፍ ብታደርግ እሷም ሆነች አራቱ ወንድሞች ይበልጥ ግራ ከመጋባት ውጪ ሊግባቡ አልቻሉም። በመጨረሻም በቅርንጫፍ ቢሮው የሚከናወነውን ሥራ በበላይነት የሚከታተለው ወንድም ኤሪክ ፍሮስት መጣና ሞቅ ባለ ሁኔታ ተቀበላቸው። ወንድም ፍሮስት በእንግሊዝኛ ሰላም ሲላቸው አራቱ ወንድሞች ቀለል አላቸው።
በነሐሴ ወር መጨረሻ አካባቢ አራቱ ወንድሞች በጀርመንኛ በተካሄደ ትልቅ ስብሰባ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ተገኙ፤ “ንጹሕ አምልኮ” የተባለው ይህ ትልቅ ስብሰባ የተካሄደው በፍራንክፈርት አም ማይን ነበር። አራቱ ወጣቶች የተሰብሳቢዎቹ ከፍተኛ ቁጥር 47,432 እንደደረሰና 2,373 ሰዎች እንደተጠመቁ ሲመለከቱ ሚስዮናዊ ሆነው በስብከቱ ሥራ የመካፈል ፍላጎታቸው እንደ አዲስ ተቀጣጠለ። ይሁንና ከጥቂት ቀናት በኋላ ወንድም ኖር በቤቴል እንዲያገለግሉ መመደባቸውን ነገራቸው።
በተመደቡበት ቦታ ሲያገለግሉ ያገኙት ደስታ፣ ምንጊዜም የተሻለውን የሚያውቀው ይሖዋ እንደሆነ እንዲተማመኑ አድርጓቸዋል
ሬመን በሚስዮናዊነት የማገልገል ፍላጎት ስለነበረው ከዚያ በፊት በዩናይትድ ስቴትስ ቤቴል እንዲያገለግል የቀረበለትን ግብዣ አልተቀበለም ነበር። ሪቻርድም ሆነ ቢል በቤቴል የማገልገል ሐሳብ አልነበራቸውም። ሆኖም ከዚያ በኋላ በቤቴል ሲያገለግሉ ያገኙት ደስታ፣ ምንጊዜም የተሻለውን የሚያውቀው ይሖዋ እንደሆነ ሙሉ በሙሉ እንዲተማመኑ አድርጓቸዋል።
በእርግጥም የራሳችንን ምርጫ ብቻ ከማሰብ ይልቅ የይሖዋን መመሪያ ተከትለን እሱ በሚፈልገው ቦታ ማገልገል የጥበብ አካሄድ ነው። ይህን የተገነዘበ ሰው በየትኛውም ቦታ ወይም በማንኛውም የሥራ ምድብ ይሖዋን በደስታ ማገልገል ይችላል።ፌርቦተን!
ብዙዎቹ የጀርመን ቤቴል አባላት ከአሜሪካውያኑ ጋር በመነጋገር የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታቸውን ማሻሻል የሚችሉበት አጋጣሚ እንዳገኙ ስለተሰማቸው ተደስተው ነበር። ይሁንና አንድ ቀን በመመገቢያ አዳራሹ የተነገረው ማሳሰቢያ ይህን ተስፋቸውን አጨለመባቸው። ወንድም ፍሮስት እንደተለመደው ግለት በሚንጸባረቅበት መንገድ በጀርመንኛ አንድ ነገር መናገር ጀመረ፤ የሚናገረው ነገር ከበድ ያለ ይመስል ነበር። በመመገቢያ አዳራሹ ውስጥ ጸጥታ ሰፈነ፤ አብዛኞቹ የቤተሰቡ አባላት አንገታቸውን አቀረቀሩ። አዲሶቹ ቤቴላውያን የሚነገረው ነገር ባይገባቸውም ቀስ በቀስ ግን ጉዳዩ ከእነሱ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ተረዱ። በመሆኑም ወንድም ፍሮስት ከፍ ባለ ድምፅ “ፌርቦተን!” (“ክልክል ነው!”) በማለት እየደጋገመ ሲናገር ጨነቃቸው። እንዲህ በኃይል የተናገረው ምን አድርገው ይሆን?
የምግብ ሰዓቱ ሲያበቃ ሁሉም ወደየክፍሉ ገብቶ ተሸጎጠ። በኋላ ላይ አንድ ወንድም ለአራቱ ወጣቶች እንዲህ አላቸው፦ “እኛን መርዳት እንድትችሉ ጀርመንኛ መናገር አለባችሁ። ወንድም ፍሮስት፣ ጀርመንኛ እስክትችሉ ድረስ ከእናንተ ጋር በእንግሊዝኛ መነጋገር ፌርቦተን (ክልክል) እንደሆነ የተናገረው ለዚህ ነው።”
የቤተሰቡ አባላት የተሰጣቸውን መመሪያ ለመታዘዝ ፈጣኖች ነበሩ። ይህም አዲሶቹ ቤቴላውያን ጀርመንኛ እንዲማሩ የረዳቸው ከመሆኑም ሌላ አንድ አፍቃሪ ወንድም የሚሰጠውን ምክር መቀበል መጀመሪያ ላይ ከባድ ቢሆንም ብዙውን ጊዜ ጥቅም እንደሚያስገኝ አስገንዝቧቸዋል። የወንድም ፍሮስት ምክር፣ ለይሖዋ ድርጅት እንደሚያስብና ለወንድሞቹም ፍቅር እንዳለው የሚያሳይ ነበር። * በእርግጥም አራቱ ወጣቶች እያደር ይህን ወንድም እየወደዱት መሄዳቸው ምንም አያስገርምም!
ከወዳጆቻችን መማር
ፈሪሃ አምላክ ካላቸው ወዳጆቻችን ብዙ ጠቃሚ ትምህርቶችን እናገኛለን፤ ይህ ደግሞ ከይሖዋ ጋር ያለን ወዳጅነት ይበልጥ እንዲጠናከር ያደርጋል። አራቱ ሚስዮናውያን፣ ከብዛታቸው የተነሳ በስም ሊዘረዝሯቸው ከማይችሉ በርካታ ታማኝ ጀርመናውያን ወንድሞችና እህቶች ብዙ ትምህርት ቀስመዋል፤ በሌላ በኩል ደግሞ አንዳቸው ከሌላው ትምህርት አግኝተዋል። ሪቻርድ እንዲህ ብሏል፦ “ሎውል ጀርመንኛ በመጠኑ ይችል ስለነበር ብዙም አልተቸገረም፤ ሌሎቻችን ግን ቋንቋውን መማር ከብዶን ነበር። ሎውል በዕድሜም ይበልጠን ስለነበር ከቋንቋው ጋር በተያያዘም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች መመሪያ እንዲሰጠን እንጠብቅ ነበር።” ሬመን ደግሞ እንዲህ ይላል፦ “በጀርመን አንድ ዓመት ከቆየን በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ እረፍት ወጣን፤ በዚህ ጊዜ፣ ስዊዘርላንዳዊ የሆነ አንድ ወንድም በስዊስ
ተራሮች ላይ በሚገኘው ቤቱ የእረፍት ጊዜያችንን እንድናሳልፍ ስለፈቀደልን በጣም ተደስቼ ነበር። ሁለት ሳምንት ሙሉ ጀርመንኛ ስለ መለማመድ ሳንጨነቅ ዘና ብለን ማሳለፍ እንደምንችል አሰብኩ! ሆኖም ሎውል ምን እንዳሰበ አላወቅሁም ነበር። በየቀኑ ጠዋት ላይ የዕለቱን ጥቅስ በጀርመንኛ እያነበብን መወያየት አለብን ብሎ ድርቅ አለ! ነገሩ በጣም ቢያናድደኝም ሎውል በአቋሙ ጸና። ሆኖም እንዲህ በማድረጉ ጠቃሚ የሆነ ትምህርት አግኝተናል። አንዳንድ ጊዜ ባይዋጥላችሁም እንኳ ከልብ የሚያስቡላችሁ ሰዎች የሚሰጧችሁን መመሪያ ስሙ። እኛ እንዲህ ማድረጋችን ባለፉት ዓመታት ሁሉ የጠቀመን ከመሆኑም ሌላ የሚሰጠንን ቲኦክራሲያዊ መመሪያ መቀበል ቀላል እንዲሆንልን ረድቶናል።”ፊልጵስዩስ 2:3 “ሌሎች ከእናንተ እንደሚበልጡ አድርጋችሁ በትሕትና አስቡ” ይላል፤ አራቱ ጓደኛሞችም አንዳቸው የሌላውን ጠንካራ ጎን ያደንቁ ነበር። ጓደኛሞቹ፣ ቢል አንዳንድ ሁኔታዎችን ከእነሱ በተሻለ መንገድ ሊወጣ እንደሚችል ስለተገነዘቡ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥማቸው ለእሱ ይተዉለት ነበር። ሎውል እንዲህ ብሏል፦ “ጠንከር ያለ ወይም ለእኛ የሚከብደን ዓይነት እርምጃ መውሰድ የሚጠይቁ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን መፍትሔ የምንሻው ከቢል ነበር። ደስ የማይሉ ሁኔታዎች በሚፈጠሩበት ጊዜ ችግሩን ለማስተካከል ተገቢ የሆነው አካሄድ የትኛው እንደሆነ ሁላችንም ብንስማማም ይህን ለማድረግ ድፍረቱም ሆነ ችሎታው አይኖረንም፤ ቢል ግን ይህን ማድረግ ይችል ነበር።”
አስደሳች ትዳሮች
አንድ በአንድ አራቱም ጓደኛሞች ትዳር መሠረቱ። ለጓደኝነታቸው መሠረት የሆነው፣ ሁሉም ይሖዋንና የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን የሚወዱ መሆናቸው ነበር፤ ስለሆነም ለይሖዋ ቅድሚያ የሚሰጡ የትዳር ጓደኞች ይፈልጉ ነበር። ከመቀበል ይልቅ መስጠት ደስታ እንደሚያስገኝ እንዲሁም ከራሳቸው ፍላጎት ይበልጥ ቅድሚያ ሊሰጡ የሚገባው ከመንግሥቱ ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች እንደሆነ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ካሳለፉት ሕይወት ተምረዋል። በመሆኑም ሁሉም ያገቡት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ የነበሩ እህቶችን ነው። እንዲህ በማድረጋቸውም የአራቱም ትዳር ጠንካራና ደስታ የሰፈነበት ሊሆን ችሏል።
ወዳጅነትም ሆነ ትዳር ዘላቂ እንዲሆን ይሖዋ በመካከል ሊኖር ይገባል። (መክ. 4:12) ቢልና እና ሬመን ከጊዜ በኋላ የትዳር ጓደኞቻቸውን በሞት ቢያጡም ሁለቱም ታማኝና ደጋፊ የሆነች ሚስት ማግባት የሚያስገኘውን ደስታ ማጣጣም ችለዋል። ሎውልና ሪቻርድ አሁንም ድረስ የትዳር ጓደኞቻቸው ድጋፍ አልተለያቸውም፤ ቢል እንደገና ያገባ ሲሆን በዚህ ጊዜም ቢሆን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመቆየት የሚያስችለው ጥበብ የተንጸባረቀበት ምርጫ አድርጓል።
ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ እነዚህ አራት ጓደኛሞች በተለያዩ ቦታዎች የተመደቡ ሲሆን ከእነዚህም መካከል በዋነኝነት ጀርመን፣ ኦስትሪያ፣ ሉክሰምበርግ፣ ካናዳ እና ዩናይትድ ስቴትስ ይገኙበታል። በዚህም ምክንያት አራቱ ጓደኛሞች የሚፈልጉትን ያህል አብረው ማገልገል አልቻሉም። ይሁንና ርቀት ቢለያያቸውም ግንኙነታቸውን አላቋረጡም፤ አንዳቸው ለሌላው የደስታውም ሆነ የሐዘኑ ተካፋይ ነበሩ። (ሮም 12:15) እንዲህ ያሉ ወዳጆች በጣም ውድ በመሆናቸው ከፍ ተደርገው ሊታዩ ይገባል። ከይሖዋ የተገኙ ውድ ስጦታዎች ናቸው። (ምሳሌ 17:17) በዛሬው ጊዜ በዓለም ላይ እውነተኛ ወዳጆች ብርቅ ናቸው። እውነተኛ ክርስቲያኖች ግን እንዲህ ያሉ በርካታ ወዳጆችን ማፍራት ይችላሉ። የይሖዋ ምሥክሮች፣ በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ የእምነት ባልደረቦቻችን ከሁሉም በላይ ደግሞ ከይሖዋ አምላክና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ወዳጅነት መመሥረት ችለናል።
ሁላችንም እንደሚያጋጥመን ሁሉ እነዚህ አራት ጓደኛሞችም ያሳለፉት ሕይወት አልጋ በአልጋ አልነበረም፤ ካጋጠሟቸው አስቸጋሪ ሁኔታዎች መካከል የትዳር ጓደኛን በሞት ማጣት የሚያስከትለው ሐዘን፣ ከባድ በሽታን ተቋቁሞ መኖር የሚያስከትለው ውጥረት፣ በዕድሜ የገፉ ወላጆችን መንከባከብ የሚያስከትለው ጭንቀት፣ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ ሆኖ ልጅን ማሳደግ የሚያስከትለው ፈተና፣ አዲስ ቲኦክራሲያዊ የሥራ ምድብ መቀበል የሚፈጥረው ስጋት እንዲሁም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከዕድሜ መግፋት ጋር ተያይዘው የሚመጡት እየባሱ የሚሄዱ ችግሮች የሚጠቀሱ ናቸው። ያም ቢሆን ግን ይሖዋን የሚወዱ ሰዎች በየዕለቱ የሚያጋጥማቸውን እያንዳንዱን ችግር በተሳካ ሁኔታ መወጣት እንዲችሉ በቅርብም ሆነ በሩቅ ያሉ ወዳጆቻቸው እንደሚረዷቸው እነዚህ ጓደኛሞች ከራሳቸው ተሞክሮ መገንዘብ ችለዋል።
ለዘላለም የሚዘልቅ ወዳጅነት
ሎውል በ18፣ ሬመን በ12፣ ቢል በ11 እና ሪቻርድ በ10 ዓመታቸው ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰናቸው እንዲሁም ሁሉም ከ17 እስከ 21 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ እያሉ ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት መግባታቸው የሚደነቅ ነው። በመክብብ 12:1 ላይ የሚገኘውን “በወጣትነትህ ጊዜ፣ ፈጣሪህን አስብ” የሚለውን ማበረታቻ ተግባራዊ አድርገዋል።
አንተም ወጣት ክርስቲያን ከሆንክና ሁኔታህ የሚፈቅድ ከሆነ ይሖዋ ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንድትገባ ያቀረበልህን ግብዣ እንድትቀበል እናበረታታሃለን። እንዲህ ካደረግህ እንደ አራቱ ጓደኛሞች ይሖዋ ለአንተም በጸጋው አስደሳች የሆኑ የአገልግሎት መብቶችን ይሰጥሃል፤ ከእነዚህም መካከል በወረዳ፣ በአውራጃ ወይም በዞን ሥራ የመካፈል፣ የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል መሆንን ጨምሮ በቤቴል የማገልገል፣ በመንግሥት አገልግሎትና በአቅኚዎች ትምህርት ቤት የማስተማር እንዲሁም በትላልቅ ስብሰባዎችና በጉባኤ ንግግር የማቅረብ መብቶች ይገኙበታል። እነዚህ አራት ጓደኛሞች፣ ያከናወኑት ሥራ በአሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን እንደጠቀመ ሲያውቁ ምን ያህል ተደስተው ይሆን! ይህን ሁሉ ማከናወን የቻሉት ይሖዋ በሙሉ ነፍሳቸው እንዲያገለግሉት ያቀረበላቸውን ፍቅር የተንጸባረቀበት ግብዣ በወጣትነታቸው በመቀበላቸው ነው።—ቆላ. 3:23
አሁን ሎውል፣ ሪቻርድና ሬመን በሴልተርስ፣ ጀርመን በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ እንደገና አብረው እያገለገሉ ነው። በዩናይትድ ስቴትስ በልዩ አቅኚነት ያገለግል የነበረው ቢል በ2010 በሞት አንቀላፋ። ሦስቱ ወንድሞች የ60 ዓመት ወዳጃቸውን በሞት መነጠቃቸው ያሳዝናል! ይሁንና አምላካችን ይሖዋ፣ ወዳጆቹን ፈጽሞ አይረሳም። በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር፣ ሁሉም ክርስቲያኖች በሞት ምክንያት ለጊዜው ያጧቸውን ወዳጆቻቸውን መልሰው እንደሚያገኙ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።
“በጓደኝነት ባሳለፍናቸው 60 ዓመታት ውስጥ በመካከላችን የተፈጠረ አንድም ደስ የማይል ነገር ትዝ አይለኝም”
ቢል ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ እንዲህ በማለት ጽፎ ነበር፦ “በጓደኝነት ባሳለፍናቸው 60 ዓመታት ውስጥ በመካከላችን የተፈጠረ አንድም ደስ የማይል ነገር ትዝ አይለኝም። ወዳጅነታችን ምንጊዜም ለእኔ በጣም ውድ ነው።” ሦስቱ ወዳጆቹም በአዲሱ ዓለም ጓደኝነታቸውን እንደሚቀጥሉ በማሰብ “ወዳጅነታችን ገና መጀመሩ ነው” ብለዋል።
^ አን.17 የወንድም ፍሮስት የሕይወት ታሪክ በሚያዝያ 15, 1961 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ከገጽ 244-249 ላይ ወጥቷል።