የምትመርጡት መዝናኛ ጠቃሚ ነው?
የምትመርጡት መዝናኛ ጠቃሚ ነው?
“በጌታ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ነገር ምን እንደሆነ ምንጊዜም መርምራችሁ አረጋግጡ።”—ኤፌ. 5:10
1, 2. (ሀ) የአምላክ ቃል ይሖዋ በሕይወታችን ደስተኛ እንድንሆን እንደሚፈልግ የሚጠቁመው እንዴት ነው? (ለ) መዝናኛን ከይሖዋ እንደተገኘ “ችሮታ” አድርገን መመልከታችን ምን እንድናደርግ ያነሳሳናል?
ይሖዋ፣ በሕይወት እንድንኖር ብቻ ሳይሆን በሕይወታችን ደስተኞች እንድንሆን እንደሚፈልግ የሚጠቁሙ በርካታ ሐሳቦችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናገኛለን። ለምሳሌ ያህል፣ መዝሙር 104:14, 15 ይሖዋ “ከምድር ምግብን [እንደሚያወጣ]” እንዲሁም “የሰውን ልብ ደስ የሚያሰኝ ወይን፣ ፊቱን የሚያወዛ ዘይት፣ ልቡን የሚያበረታ እህል” እንደሚያዘጋጅ ይናገራል። አዎን፣ ይሖዋ እንደ እህል፣ ዘይትና ወይን ያሉ ለሕይወታችን አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን እንድናገኝ ሲል ዕፅዋትን ያበቅላል። ወይን ደግሞ “የሰውን ልብ ደስ [ያሰኛል]።” ወይን በሕይወት ለመኖር የግድ አስፈላጊ ባይሆንም ለደስታችን አስተዋጽኦ ያደርጋል። (መክ. 9:7፤ 10:19) በእርግጥም ይሖዋ ሐሴት እንድናደርግና ልባችን ‘በደስታ እንዲሞላ’ ይፈልጋል።—ሥራ 14:16, 17
2 በመሆኑም አልፎ አልፎ “የሰማይን ወፎች” እና ‘የሜዳ አበቦችን’ ልብ ብለን ብንመለከት ወይም መንፈሳችንን በሚያድሱና ሕይወታችንን አስደሳች በሚያደርጉ ሌሎች እንቅስቃሴዎች ብንካፈል ስህተት እንደሠራን ሊሰማን አይገባም። (ማቴ. 6:26, 28፤ መዝ. 8:3, 4) በሕይወት መደሰት የይሖዋ “ችሮታ ነው።” (መክ. 3:12, 13) እንግዲያው መዝናኛን አምላክ ከሰጠን ችሮታዎች መካከል እንደ አንዱ አድርገን መመልከታችን በመዝናናት የምናሳልፈውን ጊዜ እሱን በሚያስደስት መንገድ እንድናውለው ያነሳሳናል።
የምርጫ ልዩነትና ገደብ ማበጀት
3. ሰዎች በመዝናኛ ምርጫ ረገድ ልዩነት ሊኖራቸው እንደሚችል መጠበቁ ምክንያታዊ የሆነው ለምንድን ነው?
3 መዝናኛን በተመለከተ ሚዛናዊ አመለካከት ያላቸው ሰዎች በልዩ ልዩ ነገሮች ራሳቸውን ዘና ማድረግ እንደሚችሉ ቢያውቁም በዚህ ረገድ ገደብ ማበጀት እንዳለባቸውም ይገነዘባሉ። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ይህን ጥያቄ ለመመለስ እስቲ መዝናኛን ከምግብ ጋር እያነጻጸርን እንመልከት። ተወዳጅ የሆኑ ምግቦች እንደ አካባቢው ይለያያሉ። በአንድ አካባቢ ሰዎች በጣም የሚወዱት ምግብ በሌላ አካባቢ ደግሞ እምብዛም የማይወደድ ሊሆን ይችላል። በተመሳሳይም በአንድ አካባቢ ላሉ ክርስቲያኖች የሚያስደስታቸው መዝናኛ በሌላ ቦታ ለሚገኙ ክርስቲያኖች ያን ያህል ላይማርካቸው ይችላል። በአንድ አካባቢ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች እንኳ ለአንዱ አዝናኝ የሆነው ነገር (ለምሳሌ ቁጭ ብሎ ጥሩ መጽሐፍ ማንበብ) ለሌላው አሰልቺ ሊሆንበት ይችላል፤ በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ሰው መንፈስን እንደሚያድስ አድርጎ የሚያስበው ነገር (ለምሳሌ በብስክሌት መንሸራሸር) ለሌላው አድካሚ ሊሆንበት ይችላል። ያም ቢሆን እንደ ምግብና መዝናኛ ባሉት ጉዳዮች ረገድ ሰዎች የተለያየ ምርጫ ሊኖራቸው እንደሚችል መገንዘብ ይኖርብናል።—ሮም 14:2-4
4. በመዝናኛ ምርጫ ረገድ ገደብ ማበጀት የሚኖርብን ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።
4 ይሁን እንጂ በመዝናኛ ምርጫ ረገድ ልዩነት ሊኖር ይችላል ሲባል ያሻንን ለማድረግ ነፃነት አለን ማለት እንዳልሆነ መገንዘብ ይኖርብናል። ነጥቡን ይበልጥ ለመረዳት እስቲ አሁንም ምግብን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። የተለያዩ ምግቦችን መመገብ የምንወድ ብንሆንም ሆን ብለን የተበላሸ ምግብ አንበላም። ጤናማ አእምሮ ያለው ማንኛውም ሰው እንዲህ አያደርግም፤ ይህ ለጤንነትም ቢሆን አደገኛ ነው። በተመሳሳይም በልዩ ልዩ ዓይነት ጤናማ መዝናኛዎች መካፈል የምንወድ ቢሆንም ለአደጋ በሚያጋልጡ፣ የዓመፅ ድርጊት በሚንጸባረቅባቸው ወይም በሥነ ምግባር ባዘቀጡ መዝናኛዎች ጊዜያችንን ማሳለፍ አንፈልግም። እንደነዚህ ባሉ መዝናኛዎች መካፈላችን የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች እንድንጥስ የሚያደርገን ከመሆኑም ሌላ አካላዊና መንፈሳዊ ጤንነታችንን ለአደጋ ያጋልጣል። በመሆኑም በመዝናኛ ምርጫ ረገድ ገደብ ማበጀት ኤፌ. 5:10) ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
አለብን፤ ይህን ለማድረግ ደግሞ የምንመርጣቸው መዝናኛዎች ጠቃሚ ናቸው ወይስ አይደሉም? የሚለውን አስቀድመን ማመዛዘን ይኖርብናል። (5. የምንመርጠው መዝናኛ ከአምላክ መሥፈርቶች ጋር የሚስማማ መሆኑን እንዴት ማወቅ እንችላለን?
5 አንድ መዝናኛ እኛን የሚጠቅመንና ይሖዋን የሚያስደስት እንዲሆን በአምላክ ቃል ላይ ከሰፈሩት ግልጽ መሥፈርቶች ጋር የሚስማማ መሆን ይኖርበታል። (መዝ. 86:11) የምትወደው የመዝናኛ ዓይነት ጠቃሚና አምላክን የሚያስደስት መሆኑን ለማወቅ አንዳንድ ነጥቦችን መመርመር ትችላለህ። ልትመረምራቸው የሚገቡት ነጥቦች ምን፣ መቼ እና እነማን በሚሉት ሦስት ጥያቄዎች ጠቅለል ተደርገው ሊገለጹ ይችላሉ። እስቲ እነዚህን ጥያቄዎች አንድ በአንድ እየተመለከትን እንሂድ።
መዝናኛው ምን ነገሮችን ያካትታል?
6. ከየትኞቹ የመዝናኛ ዓይነቶች ልንርቅ ይገባል? ለምንስ?
6 በአንድ ዓይነት መዝናኛ ከመካፈልህ በፊት መጀመሪያ ልትጠይቀው የሚገባው ጥያቄ ‘ምን?’ የሚለው ነው፤ በሌላ አባባል ‘የሚማርከኝ መዝናኛ ምን ዓይነት ነው?’ ብለህ ራስህን መጠየቅ አለብህ ማለት ነው። ይህን ጥያቄ ለመመለስ ስታስብ መዝናኛዎች በሁለት እንደሚከፈሉ ልብ ልትል ይገባል። የመጀመሪያዎቹ የመዝናኛ ዓይነቶች ፈጽሞ ልንካፈልባቸው የማይገቡ ሲሆኑ ሁለተኛዎቹ ደግሞ ለግል ምርጫችን የተተዉ ናቸው። የመጀመሪያዎቹ የመዝናኛ ዓይነቶች ምን ነገሮችን ያካትታሉ? በዚህ ክፉ ሥርዓት ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ መዝናኛዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በግልጽ የሚጥሱ ወይም ከአምላክ ሕግ ጋር የሚጋጩ ናቸው። (1 ዮሐ. 5:19) እውነተኛ ክርስቲያኖች በእነዚህ መዝናኛዎች ፈጽሞ አይካፈሉም። ከእነዚህም መካከል በሌሎች ሥቃይ መደሰትን፣ አጋንንታዊ ሥራዎችን፣ ግብረ ሰዶምን፣ የብልግና ምስሎችን ወይም ዓመፅን የሚያሳዩ አሊያም ሌሎች የጭካኔ ድርጊቶችንና የሥነ ምግባር ብልግናን የሚያበረታቱ መዝናኛዎች ይገኙበታል። (1 ቆሮ. 6:9, 10፤ ራእይ 21:8ን አንብብ።) በየትኛውም ቦታ ብንሆን ከእነዚህ መዝናኛዎች በመራቅ ‘ክፉ የሆነውን ነገር እንደምንጸየፍ’ ለይሖዋ እናሳያለን።—ሮም 12:9፤ 1 ዮሐ. 1:5, 6
7, 8. አንድ መዝናኛ ጥሩ መሆን አለመሆኑን እንዴት መገምገም ትችላለህ? በምሳሌ አስረዳ።
7 ሁለተኛዎቹ የመዝናኛ ዓይነቶች ደግሞ የአምላክ ቃል በቀጥታ የማያወግዛቸውን ድርጊቶች ያካተቱ ናቸው። እንደነዚህ ባሉ መዝናኛዎች ለመካፈል ከመወሰናችን በፊት የምንመርጠው መዝናኛ ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከገለጻቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች አንጻር ጤናማ መሆኑን በጥንቃቄ መመርመር ይኖርብናል። (ምሳሌ 4:10, 11) ከዚያም ሕሊናችንን የማይቆረቁረን ውሳኔ ማድረግ ያስፈልገናል። (ገላ. 6:5፤ 1 ጢሞ. 1:19) ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? እስቲ አንድ ምሳሌ እንውሰድ፦ አንድ የማናውቀው ምግብ ከመመገባችን በፊት ምግቡ ከምን እንደተሠራ ማወቅ እንፈልጋለን። በተመሳሳይም፣ በአንድ ዓይነት መዝናኛ ከመካፈላችን በፊት መዝናኛው ምን ነገሮችን እንደሚያካትት መመርመር ይኖርብናል።—ኤፌ. 5:17
8 ለምሳሌ ስፖርት ትወድ ይሆናል፤ ይህም የሚያስገርም አይደለም። ስፖርት አስደሳችና አዝናኝ ሊሆን ይችላል። ይሁንና አንዳንድ የስፖርት ዓይነቶች ኃይለኛ የውድድር መንፈስ የሚንጸባረቅባቸው፣ ሕይወትን ለአደጋ የሚያጋልጡ፣ ለጉዳት የሚዳርጉ፣ መረን የለቀቁ ድርጊቶች የሚፈጸሙባቸው፣ ብሔራዊ ስሜት የሚንጸባረቅባቸው ወይም እንደነዚህ ያሉ ሌሎች ነገሮችን የሚያካትቱ በመሆናቸው የተነሳ የሚማርኩህ ቢሆንስ? እነዚህ ስፖርቶች ምን ነገሮችን እንደሚያካትቱ ስትመረምር አመለካከትህ ከይሖዋ አመለካከት እንዲሁም ከምንሰብከው የሰላምና የፍቅር መልእክት ጋር እንደሚጋጭ መገንዘብህ አይቀርም። (ኢሳ. 61:1፤ ገላ. 5:19-21) በሌላ በኩል ደግሞ አንድ መዝናኛ በይሖዋ ዓይን ጤናማ የሆኑ ነገሮችን የሚያካትት ከሆነ እንዲህ ያለው መዝናኛ ጠቃሚና መንፈስን የሚያድስ ሊሆንልህ ይችላል።—ገላ. 5:22, 23፤ ፊልጵስዩስ 4:8ን አንብብ።
የምዝናናው መቼ ነው?
9. ‘የምዝናናው መቼ ነው?’ ለሚለው ጥያቄ የምንሰጠው መልስ ምን ያሳያል?
9 ራስህን ልትጠይቅ የሚገባው ሁለተኛው ጥያቄ ‘መቼ?’ የሚለው ሲሆን ይህም ‘የምዝናናው መቼ ነው? ለመዝናኛስ ምን ያህል ጊዜ አውላለሁ?’ ብለህ መጠየቅ አለብህ ማለት ነው። ምን? ለሚለው ጥያቄ የምንሰጠው
መልስ ዝንባሌያችንን ይኸውም ተቀባይነት እንዳላቸው ወይም እንደሌላቸው አድርገን የምናያቸው ነገሮች የትኞቹ እንደሆኑ ይጠቁማል። መቼ? ለሚለው ጥያቄ የምንሰጠው መልስ ግን ቅድሚያ የምንሰጣቸው ነገሮች ይኸውም በሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ቦታ ያላቸው ነገሮች ምን እንደሆኑ ያሳያል። ታዲያ ለመዝናኛ ተገቢውን ቦታ እየሰጠን እንደሆነ እንዴት ማወቅ እንችላለን?10, 11. በማቴዎስ 6:33 ላይ የሚገኘው ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ ለመዝናኛ ምን ያህል ጊዜ ልናውል እንደሚገባ ለመወሰን የሚረዳን እንዴት ነው?
10 ኢየሱስ ክርስቶስ ለተከታዮቹ እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህ፣ በሙሉ አእምሮህና በሙሉ ኃይልህ ውደድ።” (ማር. 12:30) በመሆኑም ለይሖዋ ያለን ፍቅር በሕይወታችን ውስጥ ቅድሚያውን መያዝ ይኖርበታል። ኢየሱስ የሰጠውን የሚከተለውን ምክር ተግባራዊ በማድረግ ለይሖዋ ቅድሚያውን እንደምንሰጥ እናሳያለን፦ “ከሁሉ አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥትና ጽድቅ መፈለጋችሁን ቀጥሉ፤ እነዚህም ነገሮች ሁሉ ይሰጧችኋል።” (ማቴ. 6:33) ይህ ሐሳብ ለመዝናኛ ምን ያህል ጊዜና ቦታ ልንሰጥ እንደሚገባ ለመወሰን የሚረዳን እንዴት ነው?
11 ኢየሱስ ‘ከሁሉ አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥት መፈለጋችሁን ቀጥሉ’ እንጂ ‘የአምላክን መንግሥት ብቻ መፈለጋችሁን ቀጥሉ’ እንዳላለ ልብ በል። ኢየሱስ ከመንግሥቱ በተጨማሪ በሕይወታችን ውስጥ ሌሎች ብዙ ነገሮችን እንደምንፈልግ ያውቅ ነበር። መጠለያ፣ ምግብ፣ ልብስ፣ መሠረታዊ ትምህርት፣ ሥራ፣ መዝናኛና 1 ቆሮ. 7:29-31) ይህን መሠረታዊ እውነት ልብ ማለታችን ሁለተኛ ቦታ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን (መዝናኛንም ይጨምራል) የምናከናውንበት መንገድ ቅድሚያ ልንሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን (ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን) ለመፈጸም በሚያስችለን መልኩ እንዲሆን ሊያነሳሳን ይገባል። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ በተወሰነ መጠን መዝናናታችን ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።
ሌሎች ነገሮች ያስፈልጉናል። ይሁንና ከምንፈልጋቸው ነገሮች ሁሉ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባው ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ብቻ ናቸው። (12. በሉቃስ 14:28 ላይ የሚገኘው መሠረታዊ ሥርዓት በመዝናኛ ረገድ ሊሠራ የሚችለው እንዴት ነው?
12 እንግዲያው ለመዝናኛ ከምናውለው ጊዜ ጋር በተያያዘ አስቀድመን ወጪያችንን ማስላት ይኖርብናል። (ሉቃስ 14:28) አንድ ዓይነት መዝናኛ በጊዜ ረገድ ምን ያህል ወጪ እንደሚያስከፍለን ማወቅ ያስፈልገናል። ከዚያም በዚህ መዝናኛ በመካፈል ምን ያህል ጊዜ ማሳለፍ እንደሚገባን መወሰን ይኖርብናል። አንድ መዝናኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችንን፣ የቤተሰብ አምልኳችንን እንዲሁም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘትንና በስብከቱ ሥራ መካፈልን የመሳሰሉ አስፈላጊ እንቅስቃሴዎችን ችላ እንድንል የሚያደርገን ከሆነ የምንከፍለው መሥዋዕትነት ከምናገኘው ጥቅም ጋር አይመጣጠንም። (ማር. 8:36) አልፎ አልፎ የምንካፈልበት መዝናኛ ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ማስቀደማችንን እንድንቀጥል ኃይላችንን የሚያድስልን ከሆነ ግን በመዝናናት ያሳለፍነው ጊዜ የሚክስ ነው ማለት ነው።
የምዝናናው ከእነማን ጋር ነው?
13. የምንዝናናው ከእነማን ጋር እንደሆነ በጥንቃቄ መወሰን ያለብን ለምንድን ነው?
13 ራሳችንን ልንጠይቀው የሚገባው ሦስተኛው ጥያቄ ‘እነማን?’ ማለትም ‘አብረውኝ የሚዝናኑት እነማን ናቸው?’ የሚለው ነው። ከመዝናኛ ጋር በተያያዘ ይህን ጉዳይ በሚገባ ማጤናችን አስፈላጊ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም አብረውን የሚዝናኑት ሰዎች ጥሩ ባሕርይ ያላቸው መሆናቸው የመዝናኛ ምርጫችን ጥሩ እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ብዙውን ጊዜ ከጥሩ ወዳጆችህ ጋር አንድ ላይ መመገብ አስደሳች እንደሚሆንልህ ሁሉ ከጥሩ ወዳጆችህ ጋር መዝናናትም ይበልጥ አስደሳች ጊዜ ለማሳለፍ ያስችልሃል። በመሆኑም ብዙዎቻችን በተለይም ወጣቶች በኅብረት መዝናናት የሚያስደስተን ለምን እንደሆነ መገመት አያስቸግርም። ይሁን እንጂ ጠቃሚ በሆነ መዝናኛ መካፈል የምንፈልግ ከሆነ ወዳጆቻችን አድርገን የምንመርጣቸውን ወይም የማንመርጣቸው ሰዎች አስቀድመን መወሰን ይኖርብናል።—2 ዜና 19:2፤ ምሳሌ 13:20ን አንብብ፤ ያዕ. 4:4
14, 15. (ሀ) ኢየሱስ ጥሩ ወዳጅ በመምረጥ ረገድ ምን ምሳሌ ትቶልናል? (ለ) ከወዳጅነት ጋር በተያያዘ ራሳችንን የትኞቹን ጥያቄዎች ልንጠይቅ ይገባል?
14 ወዳጆቻችንን በምንመርጥበት ጊዜ የኢየሱስን ምሳሌ መከተላችን ምሳሌ 8:31) በምድር ላይ በነበረበት ጊዜም ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ፍቅራዊ አሳቢነት አሳይቷል። (ማቴ. 15:29-37) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ወዳጃዊ ስሜት በማሳየትና የቅርብ ወዳጅ በመሆን መካከል ልዩነት እንዳለ አሳይቷል። ሁሉንም ሰው ወዳጃዊ በሆነ መንገድ ይይዝ የነበረ ቢሆንም የቅርብ ወዳጆቹ አድርጎ የመረጠው የተወሰኑ ብቃቶችን የሚያሟሉ ሰዎችን ብቻ ነበር። ኢየሱስ 11 ታማኝ ሐዋርያቱን “እያዘዝኳችሁ ያለውን ነገር የምትፈጽሙ ከሆነ ወዳጆቼ ናችሁ” ብሏቸዋል። (ዮሐ. 15:14፤ ዮሐንስ 13:27, 30ንም ተመልከት።) ኢየሱስ እንደ ወዳጆቹ አድርጎ የተቀበለው እሱን የተከተሉትንና ይሖዋን የሚያገለግሉትን ሰዎች ብቻ ነበር።
በጣም ጠቃሚ ነው። ኢየሱስ ከፍጥረት ጊዜ ጀምሮ ለሰው ልጆች ፍቅር ነበረው። (15 በመሆኑም አንድን ግለሰብ እንደ ልብ ወዳጅህ አድርገህ ልትቆጥረው ይገባ እንደሆነና እንዳልሆነ በምትወስንበት ጊዜ ኢየሱስ የተናገረውን ሐሳብ በአእምሮህ መያዝህ የጥበብ እርምጃ ነው። ራስህን እንደሚከተለው እያልክ ጠይቅ፦ ‘ይህ ግለሰብ የይሖዋንና የኢየሱስን መመሪያዎች እንደሚታዘዝ በአነጋገሩም ሆነ በድርጊቱ ያሳያል? ልክ እንደ እኔ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ሥነ ምግባራዊ መሥፈርቶችና እሴቶች አሉት? ከእሱ ጋር ጊዜዬን ማሳለፌ በሕይወቴ ውስጥ መንግሥቱን እንዳስቀድምና ይሖዋን በታማኝነት እንዳገለግል ያነሳሳኛል?’ ለእነዚህ ጥያቄዎች የምትሰጠው መልስ ‘አዎ’ የሚል ከሆነ አብረኸው ልትዝናና የምትችል ጥሩ ወዳጅ አግኝተሃል ማለት ነው።—መዝሙር 119:63ን አንብብ፤ 2 ቆሮ. 6:14፤ 2 ጢሞ. 2:22
የምንመርጠው መዝናኛ መመዘኛውን ያልፋል?
16. ከመዝናኛ ምርጫችን ጋር በተያያዘ ምን ነገሮችን ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብናል?
16 በዚህ ርዕስ ውስጥ ከመዝናኛ ጋር በተያያዘ ሦስት ነገሮችን ይኸውም ጥራትን፣ ብዛትንና ወዳጅነትን በአጭሩ ተመልክተናል። የምንመርጠው መዝናኛ ጠቃሚ እንዲሆንልን በእነዚህ ሦስት አቅጣጫዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች ጋር የሚስማማ መሆን አለበት። በመሆኑም በአንድ ዓይነት መዝናኛ ከመካፈላችን በፊት መመዘኛውን ያልፍ እንደሆነ መገምገም ይኖርብናል። ከጥራት ጋር በተያያዘ የሚከተሉትን ነጥቦች ማወቅ እንፈልጋለን፦ ‘መዝናኛው ምን ነገሮችን ያካትታል? ጤናማ ነው ወይስ የረከሰ?’ (ምሳሌ 4:20-27) ከብዛት ጋር በተያያዘ የሚከተሉትን ነጥቦች መመርመር እንፈልጋለን፦ ‘በዚህ መዝናኛ ምን ያህል ጊዜ አሳልፋለሁ? ይህን ያህል ጊዜ ማሳለፌስ ተገቢ ነው?’ (1 ጢሞ. 4:8) ስለ ወዳጅነት ስናስብ ደግሞ የሚከተሉትን ነገሮች ከግምት ማስገባት ይኖርብናል፦ ‘የምዝናናው ከእነማን ጋር ነው? እነዚህ ሰዎች ጥሩ ወዳጆች ናቸው?’—መክ. 9:18፤ 1 ቆሮ. 15:33
17, 18. (ሀ) የምንመርጣቸው መዝናኛዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መሥፈርቶች የሚያሟሉ መሆናቸውን መመዘን የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ከመዝናኛ ምርጫህ ጋር በተያያዘ ምን ለማድረግ ወስነሃል?
17 አንድ መዝናኛ ከእነዚህ ሦስት አቅጣጫዎች በአንዱ እንኳ የመጽሐፍ ቅዱስን መሥፈርቶች የማያሟላ ከሆነ መመዘኛውን አላለፈም ማለት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የምንመርጣቸው መዝናኛዎች በእነዚህ በሦስቱም አቅጣጫዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መሥፈርቶች የሚያሟሉ ከሆነ የመዝናኛ ምርጫችን ለይሖዋ ክብር የሚያመጣ ከመሆኑም ሌላ ለእኛም ጥቅም ያስገኝልናል።—መዝ. 119:33-35
18 እንግዲያው ከመዝናኛ ጋር በተያያዘ ትክክል የሆነውን ነገር፣ በትክክለኛው ጊዜ እና ከትክክለኛ ሰዎች ጋር ለማድረግ እንጣር። ሁላችንም “ስትበሉም ሆነ ስትጠጡ ወይም ማንኛውንም ነገር ስታደርጉ ሁሉንም ነገር ለአምላክ ክብር አድርጉ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ከልብ እንጣር።—1 ቆሮ. 10:31
ልታብራራ ትችላለህ?
ከመዝናኛ ጋር በተያያዘ በሚከተሉት ጥቅሶች ላይ ያሉትን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
✔ምን
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
✔መቼ
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
✔እነማን
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወዳጆችንም ሆነ መዝናኛዎችን በምንመርጥበት ጊዜ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?