በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ምንጊዜም ሥራ የበዛልኝ ለመሆን ጥሬያለሁ
በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ምንጊዜም ሥራ የበዛልኝ ለመሆን ጥሬያለሁ
ቨርነን ዙብኮ እንደተናገረው
ያደግሁት ካናዳ ውስጥ በሳስካችዋን ግዛት በሚገኝ ስቴነን በሚባል መንደር አቅራቢያ ባለ አንድ የእርሻ ቦታ ነበር። ፍሬድና አዴለ የተባሉት ወላጆቼ እኔን፣ ታላቅ እህቴን አውሬሊያን፣ ታናሽ እህቴን አሌግራን እንዲሁም አልቪንና ዳርል የሚባሉትን ታናናሽ ወንድሞቼን በመንፈሳዊም ሆነ በሥጋዊ ለመንከባከብ ጠንክረው ይሠሩ ነበር። ወላጆቻችን እውነትን ስላስተማሩን አሁንም ድረስ እናመሰግናቸዋለን።
ቅቡዕ ክርስቲያን የነበረው አባቴ ደፋር ወንጌላዊ ነበር። አባቴ ቤተሰቡን ለማስተዳደር ተግቶ ይሠራ የነበረ ቢሆንም ሁሉም ሰው የይሖዋ ምሥክር መሆኑን እንዲያውቅ ለማድረግ ይጥር ነበር። ሁልጊዜ ስለ እውነት ይናገር ነበር። የነበረው ቅንዓትና ድፍረት ምንጊዜም አይረሳኝም። ብዙ ጊዜ “በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ምንጊዜም ሥራ የበዛልህ ሁን፤ እንዲህ ካደረግህ ከብዙ ችግሮች ትድናለህ” ይለኝ ነበር።
በስቴነንና በአቅራቢያው ባሉ ከተሞች ውስጥ አዘውትረን የመንገድ ላይ ምሥክርነት እንሰጥ ነበር። ለእኔ እንዲህ ማድረግ ሁልጊዜ ቀላል አልነበረም። በእያንዳንዱ ከተማ ውስጥ ጉልበተኞች ስለነበሩ በእኔ ዕድሜ በሚገኙ ልጆች ላይ ያፌዙብን ነበር። በአንድ ወቅት የስምንት ዓመት ልጅ ሳለሁ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! ይዤ አንድ ጥግ ጋ ቆሜ ነበር፤ በዚህ ጊዜ የተወሰኑ ወጣቶች መጥተው ከበቡኝ። ከዚያም ያደረግኩትን አዲስ ባርኔጣ ቀምተው በአቅራቢያዬ በነበረ አንድ ምሰሶ ላይ ሰቀሉት። ደግነቱ በዓይኑ ይከታተለኝ የነበረ በዕድሜ ከእኔ የሚበልጥ ወንድም ሁኔታውን ተመልክቶ ነበር። ከዚያም ቀረብ አለና “ቨርን፣ ችግር አለ እንዴ?” ብሎ ጠየቀኝ። ልጆቹ ወዲያውኑ ከአጠገቤ ጠፉ። ያጋጠመኝ ሁኔታ ትንሽ አበሳጭቶኝ የነበረ ቢሆንም በመንገድ ላይ ምሥክርነት በምንሰጥበት ወቅት እንደ ምሰሶ አንድ ቦታ ላይ ከመቆም ይልቅ ወዲያ ወዲህ ማለት እንዳለብን አስተምሮኛል። በልጅነቴ ያገኘሁት እንዲህ ዓይነቱ ሥልጠና ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ለማገልገል የሚያስፈልገውን ድፍረት አስገኝቶልኛል።
እኔና አልቪን ግንቦት 1951 ተጠመቅን። በዚያን ጊዜ የ13 ዓመት ልጅ ነበርኩ። የጥምቀት ንግግሩን ያቀረበው ወንድም ጃክ ኔተን ስለ ይሖዋ ሳንናገር አንድም ወር ቢሆን እንዳያልፍብን የሰጠን ማሳሰቢያ አሁንም ድረስ ትዝ ይለኛል። * የአቅኚነት አገልግሎት በቤተሰባችን ውስጥ ከሁሉ የተሻለ ሥራ እንደሆነ ተደርጎ ይታይ ነበር። ስለዚህ በ1958 ትምህርቴን ስጨርስ በአቅኚነት ለማገልገል በማነቶባ ግዛት ውስጥ ወደሚገኘው ዊንፔግ የተባለ ከተማ ተዛወርኩ። ምንም እንኳን አባቴ የቤተሰባችን ንብረት በሆነው ድርጅት ውስጥ እንጨት በመላግ ሥራ ላይ ተሰማርቼ እሱን ባግዘው ደስ ይለው የነበረ ቢሆንም እሱም ሆነ እናቴ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንድጀምር በጣም አበረታተውኛል፤ እንዲሁም ወደ ዊንፔግ መሄዴን ደግፈዋል።
አዲስ አካባቢና አዲስ ጓደኛ
በ1959 ቅርንጫፍ ቢሮው ወንጌላውያን ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ወደ ኩዊቤክ ሄደው ማገልገል ለሚፈልጉ ሁሉ ጥሪ አቀረበ። እኔም አቅኚ ሆኜ ለማገልገል ወደ 1 ቆሮ. 9:22, 23
ሞንትሪያል ሄድኩ። ይህ እንዴት ያለ ለውጥ ነበር! ፈረንሳይኛ መማርና አዲስ ዓይነት ባሕል መልመድ ስለነበረብኝ ይህ ወቅት በሕይወቴ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል። የወረዳ የበላይ ተመልካቻችን “‘እኛ እንሠራ የነበረው እንዲህ ነው’ ብለህ በፍጹም አትናገር” በማለት መክሮኝ እንደነበር ትዝ ይለኛል። በእርግጥም ይህ ጥሩ ምክር ነበር።—ወደ ኩዊቤክ ስዛወር አቅኚ የሆነ የአገልግሎት ጓደኛ አልነበረኝም። ይሁን እንጂ ቀደም ሲል በዊንፔግ ከተዋወቅኳት ሽርሊ ተርኮት ከምትባል አንዲት ወጣት እህት ጋር የካቲት 1961 በተጋባን ጊዜ የዕድሜ ልክ የአገልግሎት ጓደኛ አገኘሁ። እሷም ብትሆን ይሖዋን በሚወድ ቤተሰብ ውስጥ ያደገች ነበረች። በወቅቱ ሙሉ በሙሉ ያልተገነዘብኩት ቢሆንም እንኳ ሽርሊ አብረን በኖርንባቸው ዓመታት ሁሉ ተወዳዳሪ የሌለው የጥንካሬና የብርታት ምንጭ ሆናልኛለች።
በጋስፔ ባሕረ ገብ መሬት እየተዘዋወሩ መስበክ
ከተጋባን ከሁለት ዓመት በኋላ የልዩ አቅኚነት መብት አግኝተን በኩዊቤክ ግዛት ወደምትገኘው ሪሙስኪ ወደተባለች ከተማ ሄድን። በቀጣዩ የጸደይ ወራት ቅርንጫፍ ቢሮው በካናዳ ምሥራቃዊ የባሕር ዳርቻ በሚገኘው በመላው የጋስፔ ባሕረ ገብ መሬት እየተዘዋወርን እንድንሰብክ ሐሳብ አቀረበልን። የተሰጠን ተልእኮ የተቻለውን ያህል ብዙ የእውነት ዘር መዝራት ነበር። (መክ. 11:6) በመኪናችን ላይ ከ1,000 በላይ መጽሔቶችንና ወደ 400 የሚጠጉ መጽሐፎችን እንዲሁም ምግብና ልብስ ከጫንን በኋላ አንድ ወር የሚፈጀውን የስብከት ሥራ ለማከናወን ጉዞ ጀመርን። በጋስፔ በሚገኙት ትንንሽ መንደሮች ውስጥ ሁሉ በሚገባ ሰበክን። የአካባቢው የሬዲዮ ጣቢያ የይሖዋ ምሥክሮች እየመጡ እንደሆነ በመግለጽ ጽሑፎቻችንን እንዳይቀበሉ ሕዝቡን አስጠነቀቀ። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ነዋሪዎች ማስታወቂያውን ጽሑፎቻችንን እንዲወስዱ የሚያበረታታ እንደሆነ አድርገው በተሳሳተ መንገድ ስለተረዱት የሰጠናቸውን ጽሑፎች ምንም ሳያንገራግሩ ተቀበሉ።
በእነዚያ ዓመታት በኩዊቤክ ግዛት ውስጥ ባሉ አንዳንድ ቦታዎች የመስበክ ነፃነት እንዳለን እምብዛም ስለማይታወቅ ብዙውን ጊዜ ፖሊስ ሥራችንን ያስቆም ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል አብዛኞቹ ሰዎች ጽሑፎች በተቀበሉበት በአንድ ከተማ ውስጥ እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞን ነበር። በዚያ ከተማ ውስጥ ስናገለግል አንድ የፖሊስ መኮንን ከእሱ ጋር ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንድንሄድ ስለጠየቀን አብረነው ሄድን። የከተማው ጠበቃ መስበካችንን እንድናቆም የሚያዝ ወረቀት ማውጣቱን ደረስኩበት። የፖሊስ አዛዡ በዚያ ቀን ስላልነበረ ለጠበቃው በቶሮንቶ ካለው ቅርንጫፍ ቢሮ የተሰጠንን የመስበክ መብት እንዳለን በዝርዝር የሚያስረዳ ደብዳቤ ሰጠሁት። እሱም ደብዳቤውን ካነበበ በኋላ ፈጠን ብሎ “ይኸውላችሁ፣ እኔ ምንም ችግር አልፈልግም። መስበካችሁን እንዳስቆም የነገረኝ የደብሩ ቄስ ነው” አለን። የአካባቢው ሕዝብ ሥራችን ሕገወጥ አለመሆኑን እንዲገነዘብ ስለፈለግን ወዲያውኑ ፖሊሱ አስቁሞን ወደነበረበት ቦታ ሄደን አገልግሎታችንን ቀጠልን።
በማግስቱ የፖሊስ አዛዡን ለማነጋገር ስንሄድ እንዳንሰብክ ተከልክለን እንደነበረ ሲሰማ በጣም ተበሳጨ። የሕግ ጠበቃውን በስልክ ሲያነጋግረው እንዴት እንደተቆጣው ብትሰሙ በጣም ይገርማችኋል! የፖሊስ አዛዡ ከዚያ በኋላ ችግር ካጋጠመን በቀጥታ ለእሱ እንድንነግረውና እሱም ለጉዳዩ እልባት እንደሚሰጠው ነገረን። ምንም እንኳ ለአካባቢው እንግዳ ብንሆንም እንዲሁም ፈረንሳይኛ በደንብ መናገር ቢያዳግተንም ሕዝቡ ደግና እንግዳ ተቀባይ እንደሆነ ተገንዝበናል። ይሁን እንጂ ‘እውነትን የሚቀበል ሰው ይኖር ይሆን?’ የሚለው ጉዳይ አሳስቦን ነበር። የዚህን ጥያቄ መልስ ያገኘነው ከዓመታት በኋላ በመላው ጋስፔ የመንግሥት አዳራሾችን ለመገንባት ተመልሰን በሄድንበት ጊዜ ነው። በዚያን ጊዜ ከመሠከርንላቸው ሰዎች መካከል ብዙዎቹ አሁን ወንድሞቻችን እንደሆኑ የማየት አጋጣሚ አግኝተናል። በእርግጥም የሚያሳድገው ይሖዋ ነው።—1 ቆሮ. 3:6, 7
ከይሖዋ ያገኘናት ስጦታ
ሴት ልጃችን ሊሳ በ1970 ተወለደች። ከይሖዋ ያገኘናት ይህች ስጦታ በሕይወታችን ውስጥ ተጨማሪ ደስታ አስገኝታልናለች። ሽርሊና ሊሳ በበርካታ የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ አብረውኝ ሠርተዋል። ሊሳ ትምህርቷን ስትጨርስ “በእኔ ምክንያት ለተወሰነ ጊዜ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ስላቋረጣችሁ አቅኚ በመሆን ያንን ለማካካስ እጥራለሁ” አለችን። ሊሳ አቅኚ ከሆነች ከ20 ዓመት በላይ ሆኗታል፤ በአሁኑ ጊዜ ከባለቤቷ
ከሲልቪያን ጋር በአቅኚነት እያገለገሉ ነው። ሁለቱም በበርካታ ዓለም አቀፍ የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ የመሥራት መብት አግኝተዋል። በቤተሰብ ደረጃ ግባችን ቀለል ያለ ኑሮ በመምራት ራሳችንን ለይሖዋ አገልግሎት ማቅረብ ነው። ሊሳ አቅኚነት ስትጀምር የተናገረችውን ሐሳብ ፈጽሞ አልረሳውም። እንዲያውም ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንድመለስ ያበረታታችኝ ሲሆን ከ2001 ጀምሮ አቅኚ ሆኜ እያገለገልኩ ነው። አቅኚነት ማንኛውንም ነገር ሳደርግ ምንጊዜም በይሖዋ መታመን እንዳለብኝ አስተምሮኛል፤ እንዲሁም ቀላል ሆኖም አርኪ ሕይወት እንድመራ አስችሎኛል።በግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ መካፈል ፍቅርና ታማኝነት ይጠይቃል
ይሖዋ እሱን ለማገልገል ራሳችንን በማቅረብ የተሰጠንን ማንኛውንም የሥራ ምድብ እስከተቀበልን ድረስ አትረፍርፎ እንደሚባርከን አስተምሮኛል። በመላው ኩዊቤክ እንዲሁም በሌሎች ቦታዎች ከሚገኙ ወንድሞቼና እህቶቼ ጋር በአካባቢ የግንባታ ኮሚቴ ውስጥና በግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ መሥራትን እንደ ውድ መብት እቆጥረዋለሁ።
አንዳንዶቹ ፈቃደኛ ሠራተኞች በመድረክ ላይ ግሩም ንግግር መስጠት ባይችሉም በመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ ግን የተዋጣላቸው ባለሙያዎች ናቸው። እነዚህ ውድ ወንድሞች ሥራቸውን በሙሉ ልብ ስለሚያከናውኑ ሙሉ ችሎታቸውን ይጠቀሙበታል። በዚህም ምክንያት በሁሉም ፕሮጀክቶች የሚገነቡት ለይሖዋ አምልኮ የሚውሉ ሕንፃዎች ውብና ማራኪ ናቸው።
“አንድ ፈቃደኛ ሠራተኛ በመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ላይ ሲሠራ በጣም የሚያስፈልጉት ባሕርያት የትኞቹ ናቸው?” የሚል ጥያቄ ይቀርብልኛል። ከራሴ ተሞክሮ እንዳየሁት በመጀመሪያ አንድ ሰው ይሖዋንና ልጁን አልፎ ተርፎ ወንድሞችንና እህቶችን መውደድ አለበት። (1 ቆሮ. 16:14) በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ታማኝነት አስፈላጊ ነው። አንዳንድ ጊዜ እንደሚያጋጥመው ነገሮች እኛ ባሰብነው መንገድ ላይሄዱ ይችላሉ፤ ያም ቢሆን አንድ ታማኝ ሰው ቲኦክራሲያዊውን ዝግጅት መደገፉን ይቀጥላል። ታማኝ መሆኑ ወደፊት ለሚካሄዱ ፕሮጀክቶች ራሱን በፈቃደኝነት እንዲያቀርብ ያነሳሳዋል።
ይሖዋን የማመሰግንባቸው ምክንያቶች
አባቴ በ1985 በሞት ያንቀላፋ ቢሆንም በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ሥራ የበዛልኝ እንድሆን የሰጠኝ ምክር እስካሁን ድረስ ከአእምሮዬ አልጠፋም። በይሖዋ ድርጅት ሰማያዊ ክፍል ውርሻቸውን እንደተቀበሉት እንደ ሌሎቹ ቅቡዓን ሁሉ እሱም በሥራ እንደተጠመደ ጥርጥር የለውም። (ራእይ 14:13) እናቴ አሁን 97 ዓመቷ ነው። በጭንቅላቷ ውስጥ ደም በመፍሰሱ ምክንያት እንደቀድሞው መናገር አትችልም። ያም ሆኖ መጽሐፍ ቅዱሷን ታውቀዋለች። ደብዳቤ ስትጽፍልን ጥቅሶች የምትጋብዘን ከመሆኑም ሌላ ይሖዋን በታማኝነት ማገልገላችንን እንድንቀጥል ታበረታታናለች። እኔም ሆንኩ ወንድሞቼና እህቶቼ እንዲህ ያሉ አፍቃሪ ወላጆች በማግኘታችን በጣም አመስጋኞች ነን!
በተጨማሪም ታማኝ ጓደኛዬ ስለሆነችው ስለ ባለቤቴ ሽርሊንም ይሖዋን አመሰግነዋለሁ። እናቷ፣ “ቨርነ በእውነት ቤት ውስጥ ብዙ ሥራ ስለሚኖረው ሌሎች በእሱ እንዲጠቀሙ መፍቀድን መማር ያስፈልግሻል” በማለት የሰጧት ምክር ምንጊዜም ከአእምሮዋ አይጠፋም። ከ49 ዓመታት በፊት ስንጋባ ይህ ሥርዓት እያለ ካረጀን እስከ መጨረሻው ድረስ ይሖዋን አብረን ልናገለግል፣ ይህን ሥርዓት በሕይወት ካለፍን ደግሞ ወደ ወጣትነት ተመልሰን እሱን አብረን ለዘላለም ለማገልገል ቁርጥ ውሳኔ አድርገን ነበር። አዎን፣ ‘የጌታ ሥራ በዝቶልናል።’ (1 ቆሮ. 15:58) ይሖዋም በሚገባ የተንከባከበን ሲሆን መልካም ከሆነው ሁሉ አንዳች ነገር አጥተን አናውቅም።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.6 የጃክ ሀሊዴይ ኔተንን የሕይወት ታሪክ በመስከረም 1, 1990 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 10-14 ላይ ተመልከት።
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“በቤተሰብ ደረጃ ግባችን ቀለል ያለ ኑሮ በመምራት ራሳችንን ለይሖዋ አገልግሎት ማቅረብ ነው”