በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የወንድማማችነት ፍቅራችሁ እያደገ ይሂድ

የወንድማማችነት ፍቅራችሁ እያደገ ይሂድ

የወንድማማችነት ፍቅራችሁ እያደገ ይሂድ

“ክርስቶስ እንደወደዳችሁ . . . እናንተም በፍቅር መመላለሳችሁን ቀጥሉ።”—ኤፌ. 5:2

1. ኢየሱስ ተከታዮቹን በተለይ ለይቶ የሚያሳውቃቸው የትኛው ባሕርይ እንደሆነ ጠቅሷል?

የይሖዋ ምሥክሮች ተለይተው የሚታወቁት የአምላክን መንግሥት ምሥራች ከቤት ወደ ቤት በመስበክ ነው። ያም ሆኖ ክርስቶስ ኢየሱስ፣ እውነተኛ ደቀ መዛሙርቱ ተለይተው የሚታወቁበት ምልክት እንደሆነ የጠቀሰው ሌላ ነገር ነበር። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ አዲስ ትእዛዝ እየሰጠኋችሁ ነው፤ ልክ እኔ እንደ ወደድኳችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። በመካከላችሁ ፍቅር ካለ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።”—ዮሐ. 13:34, 35

2, 3. በመካከላችን ያለው የወንድማማችነት ፍቅር ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን በሚመጡ ሰዎች ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል?

2 በእውነተኛ ክርስቲያኖች የወንድማማች ማኅበር ውስጥ ያለው ፍቅር በሰው ዘር ኅብረተሰብ ውስጥ ተወዳዳሪ የለውም። ማግኔት ብረትን እንደሚስብ ሁሉ ፍቅርም የይሖዋ አገልጋዮች አንድነት እንዲኖራቸው የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ወደ እውነተኛው አምልኮ ይስባቸዋል። በካሜሩን የሚኖረውን ማርሴሊኖን እንደ ምሳሌ እንመልከት። ማርሴሊኖ በሥራ ላይ እያለ ባጋጠመው አደጋ ምክንያት የማየት ችሎታውን አጣ። ከአደጋው በኋላ፣ ዓይኑን ያጣው ጠንቋይ ስለነበረ እንደሆነ የሚገልጽ ወሬ ተናፈሰ። በዚህ ጊዜ ፓስተሩም ሆነ ሌሎች የቤተ ክርስቲያኑ አባላት እሱን ከማጽናናት ይልቅ ከጉባኤያቸው አባረሩት። ማርሴሊኖ፣ አንድ የይሖዋ ምሥክር ስብሰባ እንዲመጣ ሲጋብዘው መጀመሪያ ላይ ለመሄድ አቅማምቶ ነበር። ምክንያቱም እዚያም ሰዎች እንዳያገልሉት ፈርቶ ነበር።

3 ማርሴሊኖ ወደ መንግሥት አዳራሹ ሲሄድ ግን በዚያ ያጋጠመው ነገር አስገረመው። የጉባኤው አባላት ወዳጃዊ በሆነ መንገድ የተቀበሉት ሲሆን የሰማው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርትም አጽናናው። ከዚያ በኋላ በሁሉም የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመረ፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ እድገት አድርጎ በ2006 ተጠመቀ። በአሁኑ ጊዜ፣ የተማረውን እውነት ለቤተሰቡና ለጎረቤቶቹ የሚያካፍል ሲሆን ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት እንዲጀምሩ ረድቷል። ማርሴሊኖ፣ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያስጠናቸው ሰዎች እሱ በአምላክ ሕዝቦች መካከል ያገኘውን ፍቅር እነሱም እንዲያገኙ ይፈልጋል።

4. ጳውሎስ “በፍቅር መመላለሳችሁን ቀጥሉ” በማለት የሰጠውን ማሳሰቢያ ተግባራዊ ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?

4 የወንድማማችነት ፍቅራችን ማራኪ ቢሆንም ይህንን ፍቅር ጠብቀን ለማቆየት ሁላችንም የበኩላችንን ማድረግ ይኖርብናል። ሰዎች በምሽት ሰብሰብ ብለው እሳት ሲሞቁ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ፤ ሰዎቹ ወደ እሳቱ እንዲቀርቡ ያደረጋቸው የእሳቱ ነበልባል የሚሰጠው ሙቀት ነው። ሆኖም እሳቱን የሚሞቁት ሰዎች እንጨት ካልጨመሩበት እሳቱ ይጠፋል። በተመሳሳይም በጉባኤ ውስጥ ያለውን አስደናቂ ፍቅር ለማጠናከር እያንዳንዱ ክርስቲያን ጥረት ካላደረገ ይህ ፍቅር ይቀዘቅዛል። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት መልሱን ይሰጠናል:- “ክርስቶስ እንደወደዳችሁና ጥሩ መዓዛ እንዳለው ሽታ ራሱን ስለ እናንተ መባና መሥዋዕት አድርጎ ለአምላክ እንደሰጠ ሁሉ እናንተም በፍቅር መመላለሳችሁን ቀጥሉ።” (ኤፌ. 5:2) እዚህ ላይ ሊነሳ የሚገባው ጥያቄ ‘በፍቅር መመላለሴን መቀጠል የምችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?’ የሚለው ነው።

“እናንተም በአጸፋው ልባችሁን ወለል አድርጋችሁ ክፈቱ”

5, 6. ጳውሎስ በቆሮንቶስ የሚገኙ ክርስቲያኖችን ‘ልባቸውን ወለል አድርገው እንዲከፍቱ’ ያሳሰባቸው ለምንድን ነው?

5 ሐዋርያው ጳውሎስ በጥንቷ ቆሮንቶስ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፎ ነበር:- “የቆሮንቶስ ወንድሞች ሆይ፣ በግልጽ ተናግረናችኋል፤ ልባችንም ወለል ብሎ ተከፍቶላችኋል። እኛ ልባችንን አላጠበብንባችሁም፤ እናንተ ግን ጥልቅ ፍቅር በማሳየት ረገድ ልባችሁን አጥብባችሁብናል። ስለዚህ ልጆችን እንደማናግር ሆኜ አናግራችኋለሁ፤ እናንተም በአጸፋው ልባችሁን ወለል አድርጋችሁ ክፈቱ።” (2 ቆሮ. 6:11-13) ጳውሎስ በቆሮንቶስ የሚገኙ ክርስቲያኖችን ፍቅር በማሳየት ረገድ ልባቸውን ወለል አድርገው እንዲከፍቱ ያሳሰባቸው ለምን ነበር?

6 እስቲ በመጀመሪያ በጥንቷ ቆሮንቶስ የነበረው ጉባኤ እንዴት እንደተቋቋመ እንመልከት። ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ የሄደው በ50 ዓ.ም. መገባደጃ ላይ ነበር። ሐዋርያው በቆሮንቶስ ስብከት ሲጀምር ተቃውሞ ቢያጋጥመውም መስበኩን አላቋረጠም። በአጭር ጊዜ ውስጥ በዚህች ከተማ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች በምሥራቹ አመኑ። ጳውሎስ አዲሱን ጉባኤ ለማስተማሩና ለማጠናከሩ ሥራ ራሱን በመስጠት “ለአንድ ዓመት ተኩል” ያህል በዚያ ቆየ። በግልጽ ማየት እንደሚቻለው በቆሮንቶስ ለሚገኙት ክርስቲያኖች ጥልቅ ፍቅር ነበረው። (ሥራ 18:5, 6, 9-11) እነሱም በምላሹ ጳውሎስን እንዲወዱትና እንዲያከብሩት የሚያነሳሳቸው በቂ ምክንያት ነበራቸው። ይሁን እንጂ በጉባኤ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ክርስቲያኖች ከእሱ ጋር መቀራረብ አይፈልጉም ነበር። ምናልባትም አንዳንዶች የሰጣቸውን ቀጥተኛ ምክር አልወደዱት ይሆናል። (1 ቆሮ. 5:1-5፤ 6:1-10) ሌሎች ደግሞ “ምርጥ ሐዋርያት” የሚባሉት ወንድሞች የጳውሎስን ስም ለማጥፋት ያናፈሱትን ወሬ ሰምተው ይሆናል። (2 ቆሮ. 11:5, 6) ጳውሎስ ሁሉም ወንድሞቹና እህቶቹ ከልባቸው እንዲወዱት ይፈልግ ነበር። በመሆኑም እሱንም ሆነ ሌሎች የእምነት ባልንጀሮቻቸውን በመቅረብ ‘ልባቸውን ወለል አድርገው እንዲከፍቱ’ ለምኗቸዋል።

7. የወንድማማችነት ፍቅር በማሳየት ረገድ ‘ልባችንን ወለል አድርገን መክፈት’ የምንችለው እንዴት ነው?

7 እኛስ? የወንድማማችነት ፍቅር በማሳየት ረገድ ‘ልባችንን ወለል አድርገን መክፈት’ የምንችለው እንዴት ነው? በዕድሜ እኩያሞች የሆኑ ወይም ተመሳሳይ ዘር ያላቸው ሰዎች በቀላሉ ይቀራረቡ ይሆናል። እንዲሁም በመዝናኛ ረገድ ተመሳሳይ ምርጫ ያላቸው ሰዎች አብረው ብዙ ጊዜ ማሳለፋቸው የተለመደ ነው። ይሁን እንጂ ከአንዳንድ ክርስቲያኖች ጋር ተመሳሳይ ፍላጎት ያለን መሆኑ ከሌሎቹ ጋር እንዳንቀራረብ የሚያደርገን ከሆነ ‘ልባችንን ወለል አድርገን መክፈት’ ያስፈልገናል። እንደሚከተለው በማለት ራሳችንን መጠየቃችን ጥበብ ነው:- ‘የቅርብ ወዳጆቼ ካልሆኑ ወንድሞችና እህቶች ጋር የማገለግለው ወይም ከእነሱ ጋር በሌሎች ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች የምካፈለው ከስንት አንዴ ነው? በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ የማገኛቸው አዳዲስ ሰዎች ጓደኞቼ ለመሆን ብቁ መሆናቸውን በጊዜ ሂደት ማሳየት እንዳለባቸው በማሰብ ከእነሱ ጋር ያለኝ ግንኙነት የተገደበ እንዲሆን አደርጋለሁ? ልጅ አዋቂ ሳልል ሁሉንም የጉባኤ አባላት ሰላም እላለሁ?’

8, 9. በ⁠ሮም 15:7 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው የጳውሎስ ምክር የወንድማማችነት ፍቅራችን እያደገ እንዲሄድ በሚያደርግ መንገድ እርስ በርስ ሰላም እንድንባባል የሚረዳን እንዴት ነው?

8 እርስ በርስ ሰላምታ በመለዋወጥ ረገድ ጳውሎስ በሮም ለሚገኙት ክርስቲያኖች የጻፈው ደብዳቤ ለእምነት ባልንጀሮቻችን ተገቢ አመለካከት እንድናዳብር ሊረዳን ይችላል። (ሮም 15:7ን አንብብ።) እዚህ ላይ “ተቀበሉ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል አንድን ሰው “በደግነት ወይም የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ በሚንጸባረቅበት መንገድ መቀበል፣ ወደ አንድ ማኅበረሰብ እንዲቀላቀል ማድረግ እንዲሁም ወዳጅ ማድረግ” የሚል ትርጉም አለው። በጥንት ዘመን አንድ ሰው ወዳጆቹን በቤቱ በሚያስተናግድበት ጊዜ እነሱን በእንግድነት በመቀበሉ ምን ያህል እንደተደሰተ ይገልጽላቸው ነበር። ክርስቶስ በምሳሌያዊ ሁኔታ በዚህ መንገድ ተቀብሎናል፤ እኛም የእምነት ባልንጀሮቻችንን በመቀበል ረገድ የእሱን ምሳሌ እንድንከተል ተመክረናል።

9 በመንግሥት አዳራሽም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ወንድሞቻችንን ሰላም በምንልበት ጊዜ ለተወሰነ ጊዜ ያላገኘናቸውን ወይም በቅርቡ ያላነጋገርናቸውን ወንድሞች ትኩረት ልንሰጣቸው ይገባል። እነዚህን ወንድሞች ለጥቂት ደቂቃዎችም ቢሆን ለምን አታጫውታቸውም? በሚቀጥለው ስብሰባ ላይ ደግሞ በተመሳሳይ መንገድ ከሌሎች ወንድሞች ጋር መጨዋወት እንችላለን። ይህም በአጭር ጊዜ ውስጥ ከአብዛኞቹ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር አስደሳች ውይይት ለማድረግ ያስችለናል። በሌላ በኩል ደግሞ ስብሰባ ላይ በአንድ ቀን ሁሉንም ወንድሞች ማነጋገር ባንችል መጨነቅ አይኖርብንም። ማንም ሰው በእያንዳንዱ ስብሰባ ላይ ሰላም ስላላልነው ቅር ሊሰኝ አይገባም።

10. በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሁሉ ምን ግሩም አጋጣሚ አላቸው? በዚህ አጋጣሚ ሙሉ በሙሉ መጠቀም የምንችለውስ እንዴት ነው?

10 ሌሎችን ለመቀበል ልንወስደው የሚገባን የመጀመሪያ እርምጃ ሰላምታ መስጠት ነው። እንዲህ ማድረጋችን አስደሳች ውይይት ለማድረግና ዘላቂ የሆነ ወዳጅነት ለመመሥረት በር ይከፍታል። ለምሳሌ ያህል፣ በአውራጃ፣ በወረዳ ወይም በልዩ ስብሰባ ላይ ወንድሞች ከሌሎች ጋር ከተዋወቁና ከተጨዋወቱ እንደገና ለመገናኘት ይጓጓሉ። በመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ላይ የሚካፈሉ ፈቃደኛ ሠራተኞች እንዲሁም በአደጋ ምክንያት ለተጎዱት እርዳታ የሚሰጡ ወንድሞች ተሞክሯቸውን ሲለዋወጡ አንዳቸው የሌላውን ግሩም ባሕርያት ማወቅ ስለሚችሉ አብዛኛውን ጊዜ ጥሩ ወዳጆች ይሆናሉ። በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ዘላቂ ወዳጅነት ለመመሥረት የሚያስችሉ በርካታ አጋጣሚዎች አሉ። ‘ልባችንን ወለል አድርገን የምንከፍት’ ከሆነ ብዙ ጓደኞች እናፈራለን፤ ይህም በእውነተኛው አምልኮ አንድነት እንዲኖረን የረዳን ፍቅር እንዲጠናከር ያደርጋል።

በቀላሉ የምትቀረቡ ሁኑ

11. በ⁠ማርቆስ 10:13-16 ላይ ከሚገኘው ዘገባ እንደምንመለከተው ኢየሱስ ምን ምሳሌ ትቷል?

11 ሁሉም ክርስቲያኖች እንደ ኢየሱስ በቀላሉ የሚቀረቡ ለመሆን ጥረት ማድረግ ይችላሉ። አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ኢየሱስ ሲያመጡ ደቀ መዛሙርቱ ሊከለክሏቸው በሞከሩ ጊዜ ኢየሱስ ምን እንዳለ እንመልከት:- “ልጆቹ ወደ እኔ ይምጡ፤ አትከልክሏቸው፤ ምክንያቱም የአምላክ መንግሥት እንደነዚህ ላሉት ነው።” “ልጆቹንም አቀፋቸው፤ እጁንም ጭኖ ይባርካቸው ጀመር።” (ማር. 10:13-16) እነዚያ ትንንሽ ልጆች ታላቁ አስተማሪ በፍቅር ተነሳስቶ እንደዚህ ያለ ትኩረት ስለሰጣቸው ምን ያህል ተደስተው እንደሚሆን መገመት ይቻላል!

12. ከሌሎች ጋር እንዳናወራ እንቅፋት ሊፈጥሩ የሚችሉት የትኞቹ ልማዶች ናቸው?

12 እያንዳንዱ ክርስቲያን ‘በቀላሉ የምቀረብ ነኝ? ወይስ ብዙ ጊዜ ሥራ የበዛብኝ ስለምመስል ሌሎች እኔን መቅረብ ይከብዳቸዋል?’ በማለት ራሱን መጠየቅ ይኖርበታል? አንዳንድ ልማዶች በራሳቸው ስህተት ባይሆኑም አንዳንድ ጊዜ ከሌሎች ጋር እንዳናወራ እንቅፋት ሊፈጥሩ ይችላሉ። ለምሳሌ፣ ከሰዎች ጋር ስንሆን ብዙ ጊዜ በሞባይል የምናወራ ወይም በጆሮ ማዳመጫ ተጠቅመን የተቀዱ ነገሮችን የምንሰማ ከሆነ ከእነሱ ጋር ማውራት እንደማንፈልግ እንዲሰማቸው ልናደርግ እንችላለን። ብዙውን ጊዜ በእጅ በሚያዝ አነስ ያለ ኮምፒውተር ስንጠቀም ሌሎች የሚያዩን ከሆነ ከእነሱ ጋር መጫወት እንደማንፈልግ ሊያስቡ ይችላሉ። እርግጥ ነው፣ “ለዝምታ ጊዜ አለው።” ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ ከሌሎች ጋር ስንሆን ‘ለመናገርም ጊዜ እንዳለው’ ማስታወስ ይኖርብናል። (መክ. 3:7) አንዳንዶች “ብቻዬን መሆን እመርጣለሁ” ወይም “በጠዋት ማውራት አልወድም” ይሉ ይሆናል። ይሁንና ማውራት በማንፈልግበት ጊዜም እንኳ ከሌሎች ጋር ወዳጃዊ ጭውውት ማድረጋችን “የራሱን ፍላጎት አያስቀድምም” የተባለው ዓይነት ፍቅር እንዳለን ያሳያል።—1 ቆሮ. 13:5

13. ጳውሎስ ስለ ክርስቲያን ወንድሞቹና እህቶቹ ምን ዓይነት አመለካከት እንዲኖረው ጢሞቴዎስን አበረታቶታል?

13 ጳውሎስ፣ ወጣቱን ጢሞቴዎስን ሁሉንም የጉባኤ አባላት በአክብሮት እንዲይዝ አበረታቶታል። (1 ጢሞቴዎስ 5:1, 2ን አንብብ።) እኛም በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖችን እንደ እናትና አባታችን እንዲሁም ወጣቶችን እንደ ሥጋ እህቶቻችንና ወንድሞቻችን አድርገን ልንመለከታቸው ይገባል። እንዲህ ዓይነት አመለካከት ካለን ውድ ከሆኑት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መካከል ማናቸውም ከእኛ ጋር ሲሆኑ የእንግድነት ስሜት አይሰማቸውም።

14. ከሌሎች ጋር የሚያንጽ ጭውውት ማድረግ የሚያስገኛቸው አንዳንድ ጥቅሞች ምንድን ናቸው?

14 ከወንድሞቻችን ጋር የሚያንጽ ጭውውት ስናደርግ መንፈሳዊነታቸው እንዲጠናከር እንዲሁም ጥሩ ስሜት እንዲሰማቸው የበኩላችንን ማድረግ እንችላለን። በአንድ ቅርንጫፍ ቢሮ የሚሠራ አንድ ወንድም ቤቴል በገባበት ወቅት በዕድሜ የገፉ በርካታ ቤቴላውያን ጊዜ ወስደው አዘውትረው ያጫውቱት እንደነበር ያስታውሳል። እነዚህ ወንድሞች የሰጡት ማበረታቻ የቤተሰቡ አባል እንደሆነና እንደሚፈለግ እንዲሰማው አድርጎት ነበር። በአሁኑ ወቅት እሱም የእነዚያን ወንድሞች ምሳሌ በመከተል ከሌሎች ቤቴላውያን ጋር ለመጫወት ጥረት ያደርጋል።

ትሕትና ሰላም ለመፍጠር ይረዳናል

15. በእውነተኛ የይሖዋ አምላኪዎች መካከል አለመግባባት ሊፈጠር እንደሚችል የሚያሳየው ምንድን ነው?

15 በጥንቷ ፊልጵስዩስ ይኖሩ የነበሩት ኤዎድያንና ሲንጤኪ የተባሉት ክርስቲያኖች በመካከላቸው የተፈጠረውን አለመግባባት መፍታት ከብዷቸው የነበረ ይመስላል። (ፊልጵ. 4:2, 3) በጳውሎስና በበርናባስ መካከል የተፈጠረው ኃይለኛ ጭቅጭቅ የአደባባይ ሚስጥር የነበረ ሲሆን ለጊዜውም ቢሆን ወደተለያየ አቅጣጫ እንዲሄዱ አድርጓቸዋል። (ሥራ 15:37-39) ከእነዚህ ዘገባዎች መመልከት እንደሚቻለው አንዳንድ ጊዜ በእውነተኛ የይሖዋ አምላኪዎች መካከል አለመግባባት ይፈጠራል። ይሖዋ ከወንድሞቻችን ጋር የተፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመፍታትና ወዳጅነታችን እንደቀድሞው እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችለንን እርዳታ ይሰጠናል። ሆኖም ከእኛ የሚፈልገው ነገር አለ።

16, 17. (ሀ) በግለሰቦች መካከል የሚፈጠር አለመግባባትን በመፍታት ረገድ ትሕትና ምን ያህል አስፈላጊ ነው? (ለ)  ያዕቆብ ከዔሳው ጋር ሲገናኝ ስላደረገው ነገር የሚገልጸው ዘገባ የትሕትናን አስፈላጊነት የሚያጎላው እንዴት ነው?

16 ከአንድ ጓደኛህ ጋር በመኪና ለመጓዝ ተዘጋጅታችኋል እንበል። ጉዞውን ከመጀመራችሁ በፊት ቁልፉን በመጠቀም የመኪናውን ሞተር ማስነሳት ይኖርባችኋል። በግለሰቦች መካከል የሚፈጠር አለመግባባትን ለመፍታትም የመጀመሪያው እርምጃ በቁልፍ መጠቀም ነው። ቁልፉ ትሕትና ነው። (ያዕቆብ 4:10ን አንብብ።) ከዚህ በታች የቀረቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች እንደሚያሳዩት እርስ በርስ የተቃቃሩ ሰዎች በዚህ ቁልፍ መጠቀማቸው የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በተግባር ማዋል እንዲጀምሩ ሊያደርጋቸው ይችላል።

17 ዔሳው፣ መንትያ ወንድሙ ያዕቆብ ብኩርናውን ስለወሰደበት ቂም ይዞ ወንድሙን ሊገድለው ካሰበ ሃያ ዓመታት አልፈዋል። ከዚህ ሁሉ ጊዜ በኋላ እነዚህ መንትዮች እንደገና ሊገናኙ ሲሉ ‘ያዕቆብ በታላቅ ፍርሀትና ጭንቀት ተዋጠ።’ ዔሳው ጥቃት ሊሰነዝርበት እንደሚችል ተሰምቶት ነበር። ሆኖም ወንድማማቾቹ ሲገናኙ ያዕቆብ ዔሳው ያልጠበቀውን ነገር አደረገ። ወደ ወንድሙ እየቀረበ ሲሄድ “ወደ መሬት ለጥ ብሎ እጅ ነሣ።” ከዚያስ ምን ሆነ? “ዔሳው . . . ሊገናኘው ወደ እርሱ ሮጦ ሄዶ ዐቀፈው፤ በዐንገቱም ላይ ተጠምጥሞ ሳመው፤ ሁለቱም ተላቀሱ።” ያዕቆብ እንደፈራው በመካከላቸው ጠብ አልተነሳም። ያዕቆብ ትሕትና በማሳየት ዔሳው ሊኖረው የሚችለው ማንኛውም ጥላቻ እንዲወገድ አድርጓል።—ዘፍ. 27:41፤ 32:3-8፤ 33:3, 4

18, 19. (ሀ) በግለሰቦች መካከል አለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜ ቅድሚያውን ወስደን የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ተግባራዊ ማድረጋችን አስፈላጊ ነው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ)  ከአንድ ሰው ጋር ሰላም ለመፍጠር መጀመሪያ ያደረግነው ጥረት ባይሳካ ተስፋ መቁረጥ የማይኖርብን ለምንድን ነው?

18 መጽሐፍ ቅዱስ አለመግባባቶችን እንዴት መፍታት እንደሚቻል የሚገልጽ ግሩም ምክር ይዟል። (ማቴ. 5:23, 24፤ 18:15-17፤ ኤፌ. 4:26, 27) * ትሑቶች በመሆን ይህንን ምክር ተግባራዊ ካላደረግን ግን ሰላም መፍጠር አንችልም። ችግሩን ለመፍታት የሚያስችለው ቁልፍ እኛም ጋ እያለ ማለትም ትሕትና ማሳየት እየቻልን ሌላው ሰው ትሕትና እንዲያሳይ መጠበቅ መፍትሔ አያመጣም።

19 ሰላም ለመፍጠር መጀመሪያ ያደረግነው ጥረት በሆነ ምክንያት ባይሳካ ተስፋ መቁረጥ የለብንም። ሌላው ሰው ስሜቱ እስኪረጋጋ ጊዜ ይወስድበት ይሆናል። የዮሴፍ ወንድሞች ከድተውት ነበር። ወንድማማቾቹ እንደገና የተገናኙት ከረጅም ጊዜ በኋላ ሲሆን በወቅቱ ዮሴፍ የግብፅ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሆኖ ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን ወንድሞቹ አመለካከታቸው ተለውጦ ስለነበር ይቅርታ እንዲያደርግላቸው ለመኑት። ዮሴፍ ለወንድሞቹ ምሕረት ያደረገላቸው ሲሆን የያዕቆብ ልጆች የይሖዋን ስም የመሸከም መብት ያገኘ ታላቅ ብሔር ሆኑ። (ዘፍ. 50:15-21) እኛም ምንጊዜም ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረን በማድረግ ጉባኤው ደስተኛና አንድነት ያለው እንዲሆን አስተዋጽኦ ማበርከት እንችላለን።—ቆላስይስ 3:12-14ን አንብብ።

“በተግባርና በእውነት” እንዋደድ

20, 21. ኢየሱስ የሐዋርያቱን እግር ማጠቡ ምን ትምህርት ይሰጠናል?

20 ኢየሱስ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ለሐዋርያቱ “እኔ እንዳደረግኩላችሁ እናንተም እንደዚሁ እንድታደርጉ አርዓያ ሆኜላችኋለሁ” ብሏቸው ነበር። (ዮሐ. 13:15) ይህን የተናገረው የ12ቱን ሐዋርያት እግር አጥቦ ሲጨርስ ነበር። ኢየሱስ እግራቸውን ያጠበው የተለመደ ባሕል ስለሆነ ወይም ደግነት ለማሳየት ብሎ አይደለም። ዮሐንስ ኢየሱስ እግራቸውን እንዳጠባቸው ከመጻፉ በፊት ባሉት ቁጥሮች ላይ “በዓለም ያሉትን ቀድሞውኑ ይወዳቸው የነበሩትን ተከታዮቹን እስከ መጨረሻው ወደዳቸው” የሚል ሐሳብ አስፍሯል። (ዮሐ. 13:1) ኢየሱስ በተለምዶ አንድ አገልጋይ የሚያከናውነውን ተግባር እንዲፈጽም ያነሳሳው ለደቀ መዛሙርቱ የነበረው ፍቅር ነው። ከዚህ በኋላ እነሱም ትሑቶች በመሆን አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን ፍቅር የሚያሳይ ነገር ማድረግ ይኖርባቸዋል። አዎ፣ እውነተኛ የወንድማማችነት ፍቅር ለሁሉም ክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አሳቢነት እንድናሳይ ሊያነሳሳን ይገባል።

21 የአምላክ ልጅ እግራቸውን ካጠባቸው ሐዋርያት አንዱ የሆነው ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ ያደረገው ነገር ትርጉም ገብቶት ነበር። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እንግዲህ ለእውነት በመታዘዝ ነፍሳችሁን ስላነጻችሁ ግብዝነት የሌለበት የወንድማማች መዋደድ ሊኖራችሁና እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ከልብ ልትዋደዱ ይገባል።” (1 ጴጥ. 1:22) ጌታ እግራቸውን ካጠባቸው ሐዋርያት መካከል ሌላው ዮሐንስ ሲሆን እሱም እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ልጆቼ ሆይ፣ በተግባርና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት ብቻ አንዋደድ።” (1 ዮሐ. 3:18) እኛም የወንድማማችነት ፍቅራችንን በተግባር የምናሳይ እንሁን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.18 የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 144-150 ተመልከት።

ታስታውሳለህ?

• እርስ በርስ ባለን ፍቅር ረገድ ‘ልባችንን ወለል አድርገን መክፈት’ የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

• በቀላሉ የምንቀረብ እንድንሆን ምን ይረዳናል?

• ሰላም በመፍጠር ረገድ ትሕትና ምን ሚና ይጫወታል?

• ለእምነት ባልንጀሮቻችን አሳቢነት እንድናሳይ ሊያነሳሳን የሚገባው ምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የእምነት ባልንጀሮቻችንን ሞቅ ባለ ስሜት እንቀበል

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከሌሎች ጋር ለመቀራረብ የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን አታሳልፏቸው