መላእክት—“የሕዝብ አገልጋዮች የሆኑ መናፍስት”
መላእክት—“የሕዝብ አገልጋዮች የሆኑ መናፍስት”
“ሁሉም መዳን የሚወርሱትን እንዲያገለግሉ የሚላኩ የሕዝብ አገልጋዮች የሆኑ መናፍስት አይደሉም?”—ዕብ. 1:14
1. ማቴዎስ 18:10ና ዕብራውያን 1:14 ምን የሚያጽናና ሐሳብ ይዘዋል?
ኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮቹን ሊያሰናክል የሚችልን ማንኛውንም ሰው አስመልክቶ ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ “በሰማይ ያሉት መልአኮቻቸው ዘወትር በሰማይ ያለውን የአባቴን ፊት ስለሚያዩ ከእነዚህ ከታናናሾቹ መካከል አንዱንም እንዳትንቁ ተጠንቀቁ” ብሏል። (ማቴ. 18:10) ሐዋርያው ጳውሎስ ጻድቅ ስለሆኑ መላእክት ሲናገር “ሁሉም መዳን የሚወርሱትን እንዲያገለግሉ የሚላኩ የሕዝብ አገልጋዮች የሆኑ መናፍስት አይደሉም?” በማለት ጽፏል። (ዕብ. 1:14) እነዚህ ጥቅሶች አምላክ የሰው ልጆችን ለመርዳት ሰማያዊ ፍጥረታትን እንደሚጠቀም የሚያረጋግጡ በመሆናቸው ግሩም ማጽናኛ ይሆኑናል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መላእክት ምን ይላል? መላእክት የሚረዱን እንዴት ነው? ከእነሱስ ምን ልንማር እንችላለን?
2, 3. በሰማይ ያሉ መንፈሳዊ ፍጥረታት ከሚያከናውኗቸው ተግባራት አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
2 በሰማይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ታማኝ መላእክት አሉ። ሁሉም ‘ትእዛዙን የሚፈጽሙ ኀያላን’ መላእክት ናቸው። (መዝ. 103:20፤ ራእይ 5:11ን አንብብ።) እነዚህ የአምላክ መንፈሳዊ ልጆች አምላካዊ ባሕርያትን የሚያንጸባርቁ ሲሆን የራሳቸው የሆነ አመለካከትና የመምረጥ ነፃነትም አላቸው። መላእክት በላቀ መንገድ የተደራጁ ከመሆኑም ሌላ በአምላክ ዝግጅት ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን አላቸው፤ የመላእክት አለቃ ደግሞ ሚካኤል ነው። (ሚካኤል ኢየሱስ በሰማይ የሚጠራበት ስም ነው።) (ዳን. 10:13፤ ይሁዳ 9) “የፍጥረት ሁሉ በኩር” የሆነው ይህ የመላእክት አለቃ፣ “ቃል” ወይም የአምላክ ቃል አቀባይ ሲሆን ይሖዋ ሌሎች ነገሮችን ሁሉ ለመፍጠር ተጠቅሞበታል።—ቆላ. 1:15-17፤ ዮሐ. 1:1-3
3 በመላእክት አለቃ ሥር ሱራፌል የሚባሉ መላእክት አሉ። እነዚህ መንፈሳዊ ፍጥረታት የይሖዋን ቅድስና የሚያውጁ ከመሆኑም ሌላ የአምላክ ሕዝቦች መንፈሳዊ ንጽሕናቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ ይረዷቸዋል። በተጨማሪም ሉዓላዊነቱን የሚደግፉ ኪሩቦች አሉ። (ዘፍ. 3:24፤ ኢሳ. 6:1-3, 6, 7) ሌሎች መላእክት ወይም መልእክተኞች ደግሞ የአምላክን ፈቃድ በማስፈጸም ረገድ የተለያዩ ተግባራትን ያከናውናሉ።—ዕብ. 12:22, 23
4. መላእክት ምድር ስትመሠረት ምን ተሰምቷቸው ነበር? አዳምና ሔዋን የመምረጥ ነፃነታቸውን በአግባቡ ቢጠቀሙ ኖሮ የሰው ልጆች ምን ጥቅም ያገኙ ነበር?
4 ሁሉም መላእክት ‘ምድር ስትመሠረት’ ሐሴት ያደረጉ ከመሆኑም ሌላ በዓይነቷ ልዩ የሆነችው ይህች ውብ ፕላኔት ለሰው ልጆች ምቹ መኖሪያ እንድትሆን ተደርጋ ኢዮብ 38:4, 7) ይሖዋ ሰውን ‘ከመላእክት በጥቂት ያሳነሰው’ ቢሆንም በእሱ ‘መልክ’ የፈጠረው በመሆኑ ሰዎች የፈጣሪን ድንቅ ባሕርያት ማንጸባረቅ ይችላሉ። (ዕብ. 2:7፤ ዘፍ. 1:26) አዳምና ሔዋን የተሰጣቸውን የመምረጥ ነፃነት በአግባቡ ቢጠቀሙበት ኖሮ እነሱም ሆኑ ልጆቻቸው የማሰብ ችሎታ ያላቸውን ፍጥረታት ያቀፈው የይሖዋ ጽንፈ ዓለማዊ ቤተሰብ አባል ሆነው በገነት ውስጥ ለዘላለም መኖር ይችሉ ነበር።
በተዘጋጀችበት ጊዜ የተሰጣቸውን ሥራ በደስታ አከናውነዋል። (5, 6. በሰማይ ላይ ዓመጽ የተነሳው እንዴት ነው? አምላክስ ምን እርምጃ ወሰደ?
5 ቅዱሳን መላእክት፣ በአምላክ ቤተሰብ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ዓመጽ በተነሳበት ወቅት በጣም ደንግጠው እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ከመካከላቸው አንዱ ይሖዋን እያወደሰ መኖር ስላላስደሰተው እሱ ራሱ መመለክ ፈለገ። የይሖዋ አገዛዝ ትክክለኛ ስለመሆኑ ጥያቄ በማስነሳትና የአምላክን ሉዓላዊነት የሚቀናቀን አገዛዝ ለማቋቋም በመሞከር ራሱን ሰይጣን (ማለትም “ተቃዋሚ”) አደረገ። ሰይጣን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍሮ የሚገኘውን የመጀመሪያውን ውሸት በመናገር አዳምና ሔዋን አፍቃሪ በሆነው ፈጣሪያቸው ላይ እንዲያምጹና ከእሱ ጋር እንዲተባበሩ መሠሪ የሆነ ዘዴ ተጠቅሞ አግባባቸው።—ዘፍ. 3:4, 5፤ ዮሐ. 8:44
6 ይሖዋ የመጀመሪያውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት በመናገር ወዲያውኑ በሰይጣን ላይ የሚከተለውን የፍርድ ብያኔ አስተላለፈ፦ “በአንተና በሴቲቱ፣ በዘርህና በዘሯ መካከል፣ ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፤ አንተም ተረከዙን ትቀጠቅጣለህ።” (ዘፍ. 3:15) በሰይጣንና በአምላክ ‘ሴት’ መካከል ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ ጠላትነት ይኖራል። አዎን፣ ይሖዋ ታማኝ መንፈሳዊ ፍጥረታትን ያቀፈችውን ሰማያዊ ድርጅት ከእሱ ጋር በጋብቻ እንደተሳሰረች ተወዳጅ ሚስት አድርጎ ይመለከታታል። ይህ ትንቢት ደረጃ በደረጃ የሚገለጡ ዝርዝር ጉዳዮችን የያዘ “ቅዱስ ሚስጥር” ሆኖ የቆየ ቢሆንም ለተስፋችን አስተማማኝ መሠረት ጥሏል። የአምላክ ዓላማ፣ በድርጅቱ ሰማያዊ ክፍል ውስጥ ካሉት መንፈሳዊ ፍጥረታት አንዱ ዓመጸኞችን በሙሉ እንዲያጠፋ ማድረግ እንዲሁም በእሱ አማካኝነት “በሰማያት ያሉትን ነገሮችና በምድር ያሉትን ነገሮች” አንድ ላይ መጠቅለል ነው።—ኤፌ. 1:8-10
7. በኖኅ ዘመን አንዳንድ መላእክት ምን አደረጉ? ይህስ ምን ውጤት አስከተለባቸው?
7 በኖኅ ዘመን አንዳንድ መላእክት በራስ ወዳድነት ላይ የተመሠረተ ደስታ ለማሳደድ ሲሉ “ትክክለኛ መኖሪያቸውን” በመተው ሥጋዊ አካል ለብሰው ወደ ምድር መጡ። (ይሁዳ 6፤ ዘፍ. 6:1-4) ይሖዋ ዓመጸኞቹን መላእክት ወደ ድቅድቅ ጨለማ ጥሏቸዋል፤ እነዚህ መላእክት ከሰይጣን ጋር በማበር “ክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች” እንዲሁም የአምላክ አገልጋዮችን የሚጻረሩ ጠላቶች ሆነዋል።—ኤፌ. 6:11-13፤ 2 ጴጥ. 2:4
መላእክት የሚረዱን እንዴት ነው?
8, 9. ይሖዋ የሰው ልጆችን ለመርዳት በመላእክት የተጠቀመው እንዴት ነው?
8 የመላእክትን እርዳታ ካገኙ ሰዎች መካከል አብርሃም፣ ያዕቆብ፣ ሙሴ፣ ኢያሱ፣ ኢሳይያስ፣ ዳንኤል፣ ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ፣ ዮሐንስና ጳውሎስ ይገኙበታል። ጻድቅ የሆኑ መላእክት የአምላክን ፍርድ ያስፈጸሙ ከመሆኑም ሌላ የሙሴን ሕግ ጨምሮ ትንቢቶችንና መመሪያዎችን አስተላልፈዋል። (2 ነገ. 19:35፤ ዳን. 10:5, 11, 14፤ ሥራ 7:53፤ ራእይ 1:1) በአሁኑ ጊዜ ሙሉው የአምላክ ቃል ስላለን መላእክት መለኮታዊ መልእክቶችን ለእኛ ማስተላለፍ ላያስፈልጋቸው ይችላል። (2 ጢሞ. 3:16, 17) ይሁን እንጂ መላእክት ለሰው ልጆች በማይታይ ሁኔታ በትጋት የአምላክን ፈቃድ በማከናወንና አገልጋዮቹን በመርዳት ላይ ይገኛሉ።
9 መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔርን በሚፈሩት ዙሪያ የእግዚአብሔር መልአክ ይሰፍራል፤ ያድናቸዋልም” የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል። (መዝ. 34:7፤ 91:11) ንጹሕ አቋምን ከመጠበቅ ጋር በተያያዘ ጥያቄ በመነሳቱ ይሖዋ፣ ሰይጣን የተለያዩ ፈተናዎችን በእኛ ላይ እንዲያደርስ ፈቅዷል። (ሉቃስ 21:16-19) ይሁንና አምላክ ለእሱ ታማኝ መሆናችንን ለማሳየት እስከምን ድረስ መፈተን እንዳለብን ያውቃል። (1 ቆሮንቶስ 10:13ን አንብብ።) መላእክት ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ ጣልቃ በመግባት እርምጃ ለመውሰድ ምንጊዜም ዝግጁዎች ናቸው። ሲድራቅን፣ ሚሳቅን፣ አብደናጎን፣ ዳንኤልንና ጴጥሮስን ከሞት ታድገዋቸዋል፤ እስጢፋኖስንና ያዕቆብን ግን በጠላቶቻቸው እጅ ከመገደል አላዳኗቸውም። (ዳን. 3:17, 18, 28፤ 6:22፤ ሥራ 7:59, 60፤ 12:1-3, 7, 11) ይህ የሆነው ሁኔታዎቹም ሆኑ ከግለሰቦቹ ጋር ተያይዘው የተነሱት ጉዳዮች ስለሚለያዩ ነው። በተመሳሳይም በናዚ ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ከነበሩት ወንድሞቻችን መካከል አንዳንዶቹ ተገድለዋል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ይሖዋ አብዛኞቹ ወንድሞች በሕይወት እንዲተርፉ ረድቷቸዋል።
10. መላእክት ከሚያደርጉልን ድጋፍ በተጨማሪ ምን እርዳታ ማግኘት እንችላለን?
1 ዮሐ. 5:14) እርግጥ ነው፣ ይሖዋ እኛን ለመርዳት መልአክ ሊልክልን ይችላል፤ ይሁንና ከሌላ አቅጣጫም እርዳታ ልናገኝ እንችላለን። የእምነት አጋሮቻችን እኛን ለመርዳትና ለማጽናናት ሊነሳሱ ይችላሉ። አምላክ፣ ‘በሰይጣን መልአክ’ የተመታን ያህል የሚያሠቃየንን ‘ሥጋችንን የሚወጋውን እሾህ’ መቋቋም እንድንችል ጥበብና ውስጣዊ ጥንካሬ ሊሰጠን ይችላል።—2 ቆሮ. 12:7-10፤ 1 ተሰ. 5:14
10 ቅዱሳን መጻሕፍት በምድር ላይ ያለ እያንዳንዱ ሰው የራሱ የሆነ ጠባቂ መልአክ አለው ብለው አያስተምሩም። “የምንጠይቀው ነገር ምንም ይሁን ምን ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ እስከለመንን ድረስ” አምላክ እንደሚሰማን በመተማመን መጸለይ እንችላለን። (የኢየሱስን ምሳሌ ተከተሉ
11. አምላክ ኢየሱስን ለመርዳት በመላእክት የተጠቀመው እንዴት ነው? ኢየሱስ እስከ መጨረሻው ለአምላክ ታማኝ በመሆኑ ምን አሳይቷል?
11 ይሖዋ ከኢየሱስ ጋር በተያያዘ በመላእክት የተጠቀመው እንዴት እንደሆነ እንመልከት። መላእክት የኢየሱስን መወለድም ሆነ ከሞት መነሳት ያስታወቁ ከመሆኑም ሌላ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት አገልግለውታል። በጠላቶቹ እጅ እንዳይወድቅና በአሰቃቂ ሁኔታ እንዳይገደል ሊከላከሉለት ይችሉ ነበር። ሆኖም ይህን ከማድረግ ይልቅ አንድ መልአክ መጥቶ አበረታቶታል። (ማቴ. 28:5, 6፤ ሉቃስ 2:8-11፤ 22:43) ኢየሱስ ከይሖዋ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ መሥዋዕታዊ ሞት በመሞት፣ ፍጹም የሆነ ሰው ከባድ ፈተና ቢደርስበትም ንጹሕ አቋሙን ጠብቆ ከአምላክ ጎን መቆም እንደሚችል አሳይቷል። በመሆኑም ይሖዋ ኢየሱስን ከሞት አስነስቶ የማይሞት ሰማያዊ ሕይወት በማጎናጸፍ ‘ሥልጣንን ሁሉ’ የሰጠው ከመሆኑም ሌላ መላእክት እንዲገዙለት አድርጓል። (ማቴ. 28:18፤ ሥራ 2:32፤ 1 ጴጥ. 3:22) በዚህ መንገድ ኢየሱስ የአምላክ ‘ሴት’ ዋነኛ ‘ዘር’ ሆኗል።—ዘፍ. 3:15፤ ገላ. 3:16
12. ኢየሱስ የነበረውን ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ የምንችለው እንዴት ነው?
12 ኢየሱስ መላእክት ያድኑኛል በሚል ኃላፊነት በጎደለው መንገድ ሕይወቱን አደጋ ላይ በመጣል ይሖዋን መፈታተን እንደማይገባው ተገንዝቦ ነበር። (ማቴዎስ 4:5-7ን አንብብ።) ስለዚህ እኛም ስደትን በልበ ሙሉነት የምንጋፈጥ ቢሆንም እንኳ “ጤናማ አስተሳሰብ” ይዘን በመኖር ይኸውም ሳያስፈልግ ሕይወታችንን ለአደጋ ከማጋለጥ በመቆጠብ የኢየሱስን ምሳሌ እንከተል።—ቲቶ 2:12
ታማኝ ከሆኑት መላእክት ምን ልንማር እንችላለን?
13. በ2 ጴጥሮስ 2:9-11 ላይ የተጠቀሱት ጻድቃን መላእክት ከተዉት ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?
13 ሐዋርያው ጴጥሮስ የይሖዋን ቅቡዓን አገልጋዮች ‘የሚሳደቡ’ ሰዎችን በወቀሰበት ጊዜ ጻድቃን የሆኑ መላእክት የተዉትን ግሩም ምሳሌ ጠቅሷል። መላእክት ታላቅ ኃይል ያላቸው ቢሆንም “ለይሖዋ ካላቸው አክብሮት የተነሳ” በሌሎች ላይ ከመፍረድ በመቆጠብ ትሑት መሆናቸውን አሳይተዋል። (2 ጴጥሮስ 2:9-11ን አንብብ።) እኛም በሌሎች ላይ አላግባብ ከመፍረድ እንቆጠብ፤ በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት ላላቸው ወንድሞች አክብሮት እናሳይ፤ እንዲሁም የራሳችንን እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ነገሮችን የሁሉም ፈራጅ ለሆነው ለይሖዋ እንተው።—ሮም 12:18, 19፤ ዕብ. 13:17
14. መላእክት አገልግሎታቸውን በትሕትና በማከናወን ረገድ ምን ምሳሌ ትተውልናል?
14 የይሖዋ መላእክት አገልግሎታቸውን በትሕትና በማከናወን ረገድ ግሩም ምሳሌ ትተውልናል። አንዳንድ ዘፍ. 32:29፤ መሳ. 13:17, 18) በሰማይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ መንፈሳዊ ፍጥረታት ቢኖሩም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው የሚካኤልና የገብርኤል ስም ብቻ ነው። ይህም ለመላእክት ተገቢ ያልሆነ ክብር ከመስጠት እንድንቆጠብ ሊረዳን ይችላል። (ሉቃስ 1:26፤ ራእይ 12:7) ሐዋርያው ዮሐንስ በአንድ መልአክ ፊት ተደፍቶ አምልኮ ለማቅረብ በሞከረ ጊዜ ‘ተጠንቀቅ! ፈጽሞ ይህን እንዳታደርግ! እኔኮ ከአንተም ሆነ ከወንድሞችህ ጋር አብሬ የማገለግል ባሪያ ነኝ’ የሚል ማሳሰቢያ ተሰጥቶት ነበር። (ራእይ 22:8, 9) ጸሎቶቻችንን ጨምሮ አምልኮ ማቅረብ ያለብን ለአምላክ ብቻ ነው።—ማቴዎስ 4:8-10ን አንብብ።
መላእክት ስማቸውን ለሰዎች ለመናገር ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። (15. መላእክት ትዕግሥት በማሳየት ረገድ ምሳሌ የሚሆኑን እንዴት ነው?
15 መላእክት ትዕግሥት በማሳየት ረገድም ምሳሌ ይሆኑናል። የአምላክን ቅዱስ ሚስጥር የማወቅ ከፍተኛ ጉጉት ቢኖራቸውም ከዚህ ጋር በተያያዘ አንዳንድ የማያውቋቸው ነገሮች አሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “መላእክትም እነዚሁኑ ነገሮች በቅርበት ለማየት ይጓጓሉ” በማለት ይገልጻል። (1 ጴጥ. 1:12) ታዲያ ይህን ሚስጥር ለማወቅ ምን ያደርጉ ይሆን? “በርካታ ገጽታዎች ያሉት የአምላክ ጥበብ በጉባኤው አማካኝነት” ግልጽ የሚሆንበትን አምላክ የወሰነውን ጊዜ በትዕግሥት ይጠባበቃሉ።—ኤፌ. 3:10, 11
16. እኛ የምናሳየው ባሕርይ በመላእክት ላይ በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችለው እንዴት ነው?
16 ፈተና እየደረሰባቸው ያሉ ክርስቲያኖች ‘በመላእክት ፊት እንደ ትርዒት ይታያሉ።’ (1 ቆሮ. 4:9) መላእክት በታማኝነት የምናከናውናቸውን ነገሮች ሲመለከቱ በጣም የሚደሰቱ ከመሆኑም በላይ አንድ ኃጢአተኛ ንስሐ በሚገባበት ጊዜም ሐሴት ያደርጋሉ። (ሉቃስ 15:10) ክርስቲያን ሴቶች የሚያሳዩትን አምላካዊ ባሕርይ መላእክት በትኩረት ይከታተላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “በመላእክት ምክንያት ሴት በሥልጣን ሥር መሆኗን የሚያሳይ ምልክት በራሷ ላይ ታድርግ” ይላል። (1 ቆሮ. 11:3, 10) አዎን፣ ክርስቲያን ሴቶችም ሆኑ በምድር ላይ ያሉ ሌሎች የአምላክ አገልጋዮች ቲኦክራሲያዊ ሥርዓትንና የራስነትን ሥልጣን ሲያከብሩ መላእክት ይደሰታሉ። እንዲህ ያለው ታዛዥነት በሰማይ ለሚገኙት ለእነዚህ የአምላክ ልጆች ጥሩ ማሳሰቢያ ሆኖ ያገለግላቸዋል።
መላእክት የስብከቱን ሥራ ይደግፋሉ
17, 18. መላእክት የስብከቱ ሥራችንን እየደገፉ እንዳሉ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
17 መላእክት ‘በጌታ ቀን’ ከሚፈጸሙ አንዳንድ ታላላቅ ክንውኖች ጋር በተያያዘ የበኩላቸውን ድርሻ ያበረክታሉ። ከእነዚህ ክንውኖች መካከል በ1914 የአምላክ መንግሥት መወለዱ እንዲሁም “ሚካኤልና መላእክቱ” ሰይጣንና ራእይ 1:10፤ 11:15፤ 12:5-9) ሐዋርያው ዮሐንስ አንድ ‘መልአክ በምድር ላይ ለሚኖሩ ሁሉ ልክ እንደ አስደሳች ዜና የሚያበስረው የዘላለም ምሥራች ይዞ በሰማይ መካከል ሲበር’ አይቶ ነበር። መልአኩ እንዲህ ሲል አውጇል፦ “አምላክን ፍሩ፣ ክብርም ስጡት፤ ምክንያቱም እሱ ፍርድ የሚሰጥበት ሰዓት ደርሷል፤ በመሆኑም ሰማይን፣ ምድርን፣ ባሕርንና የውኃ ምንጮችን የሠራውን አምልኩ።” (ራእይ 14:6, 7) ስለዚህ የይሖዋ አገልጋዮች፣ ዲያብሎስ ኃይለኛ ተቃውሞ የሚሰነዝርባቸው ቢሆንም እንኳ በሰማይ የተቋቋመውን የአምላክ መንግሥት ምሥራች በሚሰብኩበት ጊዜ መላእክት እንደሚረዷቸው እርግጠኞች መሆን ይችላሉ።—ራእይ 12:13, 17
አጋንንቱን ከሰማይ መወርወራቸው ይገኙበታል። (18 አንድ መልአክ ፊልጶስን በማናገር ወደ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ እንዲሄድ እንደመራው ሁሉ ዛሬም መላእክት እኛን በማናገር ቅን ልብ ወዳላቸው ሰዎች ይመሩናል ብለን አንጠብቅም። (ሥራ 8:26-29) ይሁንና በዘመናችን የተገኙ ብዙ ተሞክሮዎች፣ መላእክት ከበስተጀርባ ሆነው የመንግሥቱን ስብከት ሥራችንን እየደገፉ እንዳሉና “የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ” ወዳላቸው ሰዎች እንደሚመሩን ያረጋግጣሉ። * (ሥራ 13:48) ‘አብን በመንፈስና በእውነት ማምለክ’ የሚፈልጉ ሰዎችን ለማግኘት በሚደረገው ጥረት የበኩላችንን ድርሻ ለማበርከት በአገልግሎት አዘውትረን መካፈላችን በጣም አስፈላጊ ነው!—ዮሐ. 4:23, 24
19, 20. መላእክት “በዚህ ሥርዓት መደምደሚያ” ላይ ከሚፈጸሙት ነገሮች ጋር በተያያዘ ምን ድርሻ ይኖራቸዋል?
19 ኢየሱስ ያለንበትን ዘመን አስመልክቶ ሲናገር “በዚህ ሥርዓት መደምደሚያ” መላእክት “ክፉዎችን ከጻድቃን ይለያሉ” በማለት ገልጿል። (ማቴ. 13:37-43, 49) መላእክት ቅቡዓኑን በመሰብሰቡና በማተሙ የመጨረሻ ሥራ ይካፈላሉ። (ማቴዎስ 24:31ን አንብብ፤ ራእይ 7:1-3) ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ‘በጎቹን ከፍየሎቹ በሚለይበት’ ጊዜ መላእክት አብረውት ይሠራሉ።—ማቴ. 25:31-33, 46
20 ‘ጌታ ኢየሱስ ከኃያላን መላእክቱ ጋር ከሰማይ በሚገለጥበት ጊዜ አምላክን የማያውቁና ስለ ጌታችን ኢየሱስ ለሚገልጸው ምሥራች የማይታዘዙ’ ሁሉ ይጠፋሉ። (2 ተሰ. 1:6-10) ዮሐንስ ይህንኑ ክንውን በራእይ በተመለከተ ጊዜ ኢየሱስና በሰማይ የሚገኘው የመላእክት ሠራዊት የጽድቅ ውጊያ ለማካሄድ በነጫጭ ፈረሶች ላይ ተቀምጠው ሲገሰግሱ እንዳየ ገልጿል።—ራእይ 19:11-14
21. ‘የጥልቁን ቁልፍና ታላቅ ሰንሰለት በእጁ የያዘው’ መልአክ በሰይጣንና በአጋንንቱ ላይ ምን እርምጃ ይወስዳል?
21 በተጨማሪም ዮሐንስ “የጥልቁን ቁልፍና ታላቅ ሰንሰለት በእጁ የያዘ አንድ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ” ተመልክቶ ነበር። ዲያብሎስን አስሮ ወደ ጥልቁ የሚጥለው ይህ መልአክ የመላእክት አለቃ ከሆነው ከሚካኤል ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም፤ አጋንንትም ከዲያብሎስ ጋር ወደ ጥልቁ እንደሚጣሉ ምንም ጥርጥር የለውም። በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ማብቂያ ላይ ፍጹም የሆኑ የሰው ልጆች ለመጨረሻ ጊዜ በሚፈተኑበት ወቅት ሰይጣንና አጋንንቱ ለአጭር ጊዜ ይፈታሉ። ከዚያ በኋላ ሰይጣንና ሌሎች ዓመጸኞች በሙሉ ይጠፋሉ። (ራእይ 20:1-3, 7-10፤ 1 ዮሐ. 3:8) በአምላክ ላይ የሚያምጹ ሁሉ ይወገዳሉ።
22. መላእክት በቅርቡ ከሚከናወኑት ነገሮች ጋር በተያያዘ ምን ድርሻ ይኖራቸዋል? እኛስ መላእክት የሚጫወቱትን ሚና በተመለከተ ምን ሊሰማን ይገባል?
22 ከሰይጣን ክፉ ሥርዓት ተገላግለን ታላቅ መዳን የምናገኝበት ጊዜ ቀርቧል። የይሖዋ ሉዓላዊነት እንዲረጋገጥ እንዲሁም ይሖዋ ለምድርና ለሰው ልጆች ያለው ዓላማ ሙሉ በሙሉ ዳር እንዲደርስ የሚያደርጉት እነዚህ ታላላቅ ክንውኖች በሚፈጸሙበት ጊዜ መላእክት ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ። በእርግጥም ጻድቃን የሆኑት መላእክት “መዳን የሚወርሱትን እንዲያገለግሉ የሚላኩ የሕዝብ አገልጋዮች የሆኑ መናፍስት” ናቸው። እንግዲያው ይሖዋ አምላክ ፈቃዱን እንድናደርግና የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ በመላእክት አማካኝነት እኛን ለመርዳት ላደረገው ዝግጅት አመስጋኞች እንሁን!
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.18 የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 549-551 ተመልከት።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• በሰማይ ያሉ መንፈሳዊ ፍጥረታት የተደራጁት እንዴት ነው?
• በኖኅ ዘመን አንዳንድ መላእክት ምን አድርገው ነበር?
• አምላክ እኛን ለመርዳት በመላእክት የሚጠቀመው እንዴት ነው?
• ጻድቅ የሆኑ መላእክት በእኛ ዘመን ምን ሚና ይጫወታሉ?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መላእክት የአምላክን ፈቃድ መፈጸም ያስደስታቸዋል
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዳንኤል ሁኔታ እንደታየው መላእክት ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ ጣልቃ ገብተው እርምጃ ለመውሰድ ምንጊዜም ዝግጁዎች ናቸው
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመንግሥቱ ስብከት ሥራ የመላእክት ድጋፍ ስላለው በድፍረት ማገልገላችሁን ቀጥሉ!
[የሥዕል ምንጭ]
ሉል፦ NASA photo