የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄደህ ማገልገል ትችላለህ?
የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄደህ ማገልገል ትችላለህ?
“በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የተደላደለ ሕይወት እንመራ የነበረ ቢሆንም በዚያ ያለው ኅብረተሰብ ለቁሳዊ ነገሮች የሚሰጠው ከፍተኛ ግምት በእኛም ሆነ በልጆቻችን ላይ ውሎ አድሮ መጥፎ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል የሚል ስጋት አደረብን። እኔና ባለቤቴ ቀደም ሲል ሚስዮናውያን ሆነን እናገለግል ስለነበር አሁንም እንደዚያ ዓይነቱን ቀላል ሆኖም ደስታ የሚያስገኝ ሕይወት ለመምራት ፈለግን።”
በ1991 ራልፍና ፓም ይህን ፍላጎታቸውን ከግብ ለማድረስ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄደው ለማገልገል እንደሚሹ የሚገልጽ ደብዳቤ ለበርካታ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ጻፉ። በሜክሲኮ የሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ፣ በአገሪቱ ውስጥ ለሚገኙት እንግሊዝኛ ተናጋሪ ሰዎች የሚሰብኩ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎችን የማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው በመግለጽ ምላሽ ሰጣቸው። በእርግጥም ቅርንጫፍ ቢሮው የገለጸው ‘አዝመራ ነጥቶ’ ነበር። (ዮሐ. 4:35) ብዙም ሳይቆይ ራልፍና ፓም የቀረበላቸውን ግብዣ ተቀብለው በጊዜው የ8 እና የ12 ዓመት ዕድሜ ከነበራቸው ሁለት ወንዶች ልጆቻቸው ጋር ወደ ሜክሲኮ ለመሄድ ዝግጅት ማድረግ ጀመሩ።
እጅግ በጣም ሰፊ ክልል
ራልፍ እንደሚከተለው ሲል ተናግሯል፦ “ዩናይትድ ስቴትስን ለቅቀን ከመሄዳችን በፊት አሳቢ የሆኑ አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች እንዲህ ብለውን ነበር፦ ‘ወደ ባዕድ አገር መሄዳችሁ በጣም አደገኛ ነው!’ ‘ብትታመሙስ?’ ‘እንግሊዝኛ ተናጋሪ ሰዎች ወዳሉበት ክልል ለምን ሄዳችሁ ታገለግላላችሁ? በዚያ የሚገኙት እንግሊዝኛ ተናጋሪዎች ለእውነት ፍላጎት አይኖራቸውም!’ ይሁን እንጂ ለመሄድ ቁርጥ ውሳኔ አድርገን ነበር። ደግሞም ይህን ውሳኔ ያደረግነው በግብታዊነት አልነበረም። ለዓመታት ስናቅደው የነበረ ጉዳይ ነው። ዕዳ ውስጥ ላለመግባትና ገንዘብ ለማጠራቀም እንጥር የነበረ ከመሆኑም ሌላ ሊያጋጥሙን ስለሚችሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች በቤተሰብ ሆነን ብዙ ጊዜ እንወያይ ነበር።”
ራልፍና ቤተሰቡ ሜክሲኮ እንደደረሱ ቅርንጫፍ ቢሮውን ጎበኙ። በዚያ የሚገኙት ወንድሞች የአገሪቱን ካርታ ካሳዩአቸው በኋላ “የአገልግሎት ክልላችሁ ይህ ነው!” አሏቸው። ከዚያም የራልፍ ቤተሰብ፣ በጣም ብዙ የውጪ ዜጎች በሚኖሩባት ሳን ሚጌል ደ አየንዳ በተባለችው ከተማ መኖር ጀመረ፤ ይህቺ ከተማ የምትገኘው ከሜክሲኮ ሲቲ በስተ ሰሜን ምሥራቅ 240 ኪሎ ሜትር ርቃ ነው። ከሦስት ዓመት በኋላ በዚህች ከተማ 19 አስፋፊዎችን ያቀፈ በእንግሊዝኛ የሚመራ ጉባኤ ተቋቋመ። ይህ ጉባኤ በሜክሲኮ የተቋቋመው የመጀመሪያው የእንግሊዝኛ ጉባኤ ነበር፤ ይሁንና ገና ብዙ ሥራ ከፊታቸው ይጠብቃቸው ነበር።
በሜክሲኮ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ የዩናይትድ ስቴትስ ዜጎች እንደሚኖሩ ይገመታል። በተጨማሪም እንግሊዝኛ ሁለተኛ ቋንቋቸው የሆነ ብዙ ሜክሲካውያን ባለሙያዎችና ተማሪዎች ይገኛሉ። ራልፍ እንዲህ ብሏል፦ “ተጨማሪ የመንግሥቱ ሰባኪዎች እንዲመጡልን እንጸልይ ነበር። የአገሪቱ ሁኔታ ለመስበክ አመቺ መሆኑን ‘ለመሰለል’ የሚመጡ ወንድሞችና እህቶች የሚያርፉበት አንድ ክፍል አዘጋጅተን ነበር።”—ዘኍ. 13:2
አገልግሎታቸውን ለማስፋት ሲሉ ኑሯቸውን ቀለል አደረጉ
ብዙም ሳይቆይ፣ አገልግሎታቸውን ለማስፋት የሚፈልጉ በርካታ ወንድሞችና እህቶች ወደ ሜክሲኮ መምጣት ጀመሩ። ከእነዚህ መካከል ቢል እና ካቲ የተባሉ ከዩናይትድ ስቴትስ የመጡ ባልና ሚስት ይገኙበታል። እነዚህ ባልና ሚስት ላለፉት 25 ዓመታት የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉባቸው ቦታዎች ሲያገለግሉ ቆይተው ነበር። መጀመሪያ ላይ ስፓንኛ ለመማር አቅደው የነበረ ቢሆንም በቻፓላ ሐይቅ አቅራቢያ በምትገኘው አኼኼክ የተባለች ከተማ መኖር ሲጀምሩ ሐሳባቸውን ቀየሩ፤ በዚህች ውብ ከተማ ውስጥ ከዩናይትድ ስቴትስ የመጡ በርካታ ጡረተኞች ይኖሩ ነበር። ቢል እንዲህ ብሏል፦ “በአኼኼክ፣ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት መማር የሚፈልጉ እንግሊዝኛ ተናጋሪ ሰዎችን ለማግኘት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ተግተን እንሠራ ነበር።” ቢል እና ካቲ ወደ ከተማዋ ከተዛወሩ ከሁለት ዓመት በኋላ አዲስ ጉባኤ ሲቋቋም መመልከት በመቻላቸው በጣም ተደስተዋል፤ ይህ ጉባኤ በሜክሲኮ ውስጥ የተቋቋመው ሁለተኛው የእንግሊዝኛ ጉባኤ ነበር።
በካናዳ ይኖሩ የነበሩት ኬን እና ጆአን በስብከቱ ሥራ ይበልጥ ለመካፈል ሲሉ ኑሯቸውን ቀለል ለማድረግ ፈለጉ። በመሆኑም እነሱም ብሪትኒ ከተባለችው ልጃቸው ጋር ወደ ሜክሲኮ መጡ። ኬን እንዲህ ብሏል፦ “ለቀናት ሙቅ ውኃ ወይም መብራት በማይኖርበት እንዲሁም ስልክ በሚቋረጥበት አካባቢ መኖርን ለመልመድ ጊዜ ይጠይቃል።” ይሁን እንጂ በስብከቱ ሥራ መካፈል ታላቅ ደስታ ያስገኛል። ብዙም ሳይቆይ ኬን የጉባኤ አገልጋይ ሆኖ የተሾመ ሲሆን ከሁለት ዓመት በኋላም የጉባኤ ሽማግሌ ሆነ። መጀመሪያ ላይ ብሪትኒ በጣም ጥቂት ወጣቶች ብቻ በሚገኙበት አነስተኛ አባላት ባሉት እንግሊዝኛ ጉባኤ መሰብሰብ ከባድ ሆኖባት ነበር። በመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ መካፈል ከጀመረች በኋላ ግን በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ በርካታ ወዳጆችን ማፍራት ችላለች።
በዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው የቴክሳስ ግዛት ይኖሩ የነበሩት ፓትሪክና ሮክሳን፣ እንግሊዝኛ ተናጋሪ የሆኑ ሰዎችን ለመርዳት የሚያስችላቸው ከመኖሪያቸው ብዙም ያልራቀ ክልል መኖሩን ሲያውቁ በጣም ተደስተው ነበር። ፓትሪክ እንዲህ ብሏል፦ “በስተ ሰሜን ምሥራቅ ሜክሲኮ የምትገኘውን ሞንቴሬይ የተባለች ከተማ ከጎበኘን በኋላ ይሖዋ በዚያ እንድናገለግል እንደሚፈልግ ሆኖ ተሰማን።” በአምስት ቀናት ውስጥ በቴክሳስ የሚገኘውን ቤታቸውን ሸጠው በምሳሌያዊ አነጋገር ‘ወደ መቄዶንያ ተሻግረው መርዳት’ ጀመሩ። (ሥራ 16:9) በሜክሲኮ ለመተዳደሪያ የሚሆን ገቢ ማግኘት ለእነዚህ ባልና ሚስት ቀላል አልነበረም፤ ይሁንና 17 የይሖዋ ምሥክሮች ይገኙበት የነበረው አነስተኛ ቡድን በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ 40 አስፋፊዎችን ያቀፈ ጉባኤ ሲሆን መመልከታቸው እጅግ አስደስቷቸዋል።
አገልግሎታቸውን ለማስፋት ሲሉ ኑሯቸውን ቀላል ካደረጉት መካከል ጄፍ እና ዴብ የሚባሉ ባልና ሚስት ይገኙበታል። እነዚህ ባልና ሚስት በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘውን የተንጣለለ ቤታቸውን ከሸጡ በኋላ በሜክሲኮ ምሥራቃዊ ጠረፍ በምትገኝ ካንኩን የተባለች ከተማ አንድ አነስተኛ አፓርታማ ውስጥ መኖር ጀመሩ። በዩናይትድ ስቴትስ ሳሉ ትልልቅ ስብሰባዎችን ያደርጉ የነበረው ከቤታቸው ብዙም በማይርቅና አየር ማቀዝቀዣ መሣሪያ ባለው ምቹ አዳራሽ ውስጥ ነበር። አሁን ግን ቅርብ ወደሚባለው በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚካሄድ ትልቅ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ስምንት ሰዓት መጓዝ የሚጠበቅባቸው ሲሆን የሚሰበሰቡትም ምንም ጥላ በሌለው ስታዲየም ውስጥ ነው። ያም ሆኖ በካንኩን ወደ 50 የሚጠጉ አስፋፊዎች ያሉት ጉባኤ ሲቋቋም መመልከታቸው ከፍተኛ እርካታ አስገኝቶላቸዋል።
አንዳንድ ሜክሲካውያን ወንድሞችና እህቶችም በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚካሄደውን የስብከት ሥራ መደገፍ ጀመሩ። ለምሳሌ ሩበን እና ቤተሰቡ፣ ሳን ሚጌል ደ አየንዳ በተባለው ከተማ የመጀመሪያው የእንግሊዝኛ ጉባኤ መቋቋሙንና
የዚህ ጉባኤ የአገልግሎት ክልል መላው ሜክሲኮ መሆኑን ሲሰሙ ጉባኤውን ለመርዳት ወሰኑ። ይህን ለማድረግ ደግሞ እንግሊዝኛ ቋንቋ መማር፣ ከአዲስ ባሕል ጋር መተዋወቅና በስብሰባዎች ላይ ለመገኘት በየሳምንቱ 800 ኪሎ ሜትር መጓዝ ይጠበቅባቸው ነበር። ሩበን እንዲህ ብሏል፦ “በሜክሲኮ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ለኖሩ የውጪ ዜጎች ለመጀመሪያ ጊዜ በገዛ ቋንቋቸው ምሥራቹን እንዲሰሙ የማድረግ አስደሳች አጋጣሚ አግኝተን ነበር። አንዳንዶቹ ዓይኖቻቸው በእንባ ተሞልቶ ደስታቸውን ይገልጹልን ነበር።” ሩበን እና ቤተሰቡ፣ በሳን ሚጌል ደ አየንዳ የሚገኘውን ጉባኤ ሲረዱ ከቆዩ በኋላ በመካከለኛው ሜክሲኮ በምትገኘው ጉዋናጁዋቶ የምትባል ከተማ አቅኚዎች አገልግለዋል፤ በዚያም ከ30 የሚበልጡ አስፋፊዎች ያሉበት በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚመራ ጉባኤ እንዲቋቋም አስተዋጽኦ አበርክተዋል። በዛሬው ጊዜ ጉዋናጁዋቶ አቅራቢያ በምትገኝ ኢራፕዋቶ በምትባል ከተማ ውስጥ ያለን በእግሊዝኛ ቋንቋ የሚመራ ቡድን እየረዱ ነው።በቀላሉ ለማይገኙ ሰዎች ምሥራቹን ማድረስ
በአገሪቱ ከሚገኙ የውጪ ዜጎች በተጨማሪ በርካታ ሜክሲካውያንም እንግሊዝኛ መናገር ይችላሉ። በሀብታሞች ሰፈር ለሚኖሩት ለእነዚህ ሰዎች የመንግሥቱን ምሥራች ማድረስ አብዛኛውን ጊዜ በጣም አስቸጋሪ ነው፤ ምክንያቱም በእነዚህ አካባቢዎች በር የሚከፍቱት የቤት ሠራተኞች ናቸው። የቤቱ ባለቤቶች በሩን ቢከፍቱ እንኳ የይሖዋ ምሥክሮች በአገሪቱ ብቻ የሚገኙ የመናፍቃን ቡድን አባላት ስለሚመስሏቸው ለመልእክቱ ጆሮ አይሰጡም። ይሁን እንጂ ከእነዚህ ሰዎች አንዳንዶቹ የውጪ ዜጎች የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ሲያናግሯቸው ጥሩ ምላሽ ይሰጣሉ።
በመካከለኛው ሜክሲኮ በምትገኘው ኩዌሬታሮ የተባለች ከተማ የምትኖረውን የግሎሪያ ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ግሎሪያ እንዲህ ብላለች፦ “ከዚህ ቀደም የስፓንኛ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ቢያነጋግሩኝም ጆሮ አልሰጠኋቸውም ነበር። ይሁን እንጂ በቤተሰቤና በወዳጆቼ ላይ ችግር ሲደርስ በጣም ስለተጨነቅኩ መውጫውን
እንዲያሳየኝ ወደ አምላክ ጸለይኩ። ብዙም ሳይቆይ፣ እንግሊዝኛ ተናጋሪ የሆነች አንዲት ሴት በራችንን አንኳኳች። ቤታችን ውስጥ እንግሊዝኛ መናገር የሚችል ሰው እንዳለ ጠየቀችኝ። የውጪ ዜጋ መሆኗ ስለ እሷ ለማወቅ ጉጉት ስላሳደረብኝ እንግሊዝኛ መናገር እንደምችል ነገርኳት። ይዛ የመጣችውን መልእክት እየነገረችኝ ሳለ ‘ይህቺ የውጪ ዜጋ እዚህ ሰፈር ምን ልትሠራ መጣች?’ ብዬ አሰብኩ። ይሁንና አምላክ እንዲረዳኝ ጸልዬ ነበር። በመሆኑም ይህች ሴት የምትነግረኝ ነገር የጸሎቴ ምላሽ ሊሆን እንደሚችል አሰብኩ።” ግሎሪያ መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት የተስማማች ሲሆን ቤተሰቧ ቢቃወማትም ፈጣን እድገት አድርጋ መጠመቅ ችላለች። በአሁኑ ጊዜ ግሎሪያ የዘወትር አቅኚ ሆና እያገለገለች ከመሆኑም ሌላ ባለቤቷና ወንድ ልጇ የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል።አገልግሎታቸውን ለማስፋት የሚጥሩ ሰዎች የሚያገኙት በረከት
የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄዶ ማገልገል ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩትም ብዙ በረከት ያስገኛል። በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ራልፍ እንደሚከተለው ብሏል፦ “የብሪታንያ፣ የቻይና፣ የጃማይካና የስዊዲን ዜጎችን ሌላው ቀርቶ ከጋና የመጡ በማኅብረሰቡ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ያለው ቤተሰብ አባላትን መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ችለን ነበር። ከእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች መካከል አንዳንዶቹ በአሁኑ ጊዜ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እየተካፈሉ ነው። ባለፉት በርካታ ዓመታት ቤተሰባችን በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚመሩ ሰባት አዳዲስ ጉባኤዎች ሲቋቋሙ መመልከት ችሏል። ሁለቱም ወንዶች ልጆቻችን ከእኛ ጋር አቅኚዎች ሆነው ማገልገል የጀመሩ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው ቤቴል ውስጥ በማገልገል ላይ ናቸው።”
በአሁኑ ጊዜ በሜክሲኮ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚመሩ 88 ጉባኤዎችና በርካታ ቡድኖች ይገኛሉ። እንዲህ ያለ ፈጣን እድገት ሊገኝ የቻለው እንዴት ነው? በሜክሲኮ የሚኖሩት አብዛኞቹ እንግሊዝኛ የሚናገሩ ሰዎች ከዚያን ጊዜ በፊት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ፈጽሞ ተገናኝተው አያውቁም ነበር። ሌሎቹ ደግሞ በራሳቸው አገር ቢኖሩ ኖሮ ሊደርስባቸው ይችል ከነበረው የቤተሰብ፣ የጎረቤትና የጓደኛ ተጽዕኖ ነፃ ስለሆኑ አዎንታዊ ምላሽ ሊሰጡ ችለዋል። አንዳንዶች ደግሞ ጡረታ መውጣታቸው መንፈሳዊ ነገሮችን ለመመርመር የሚያስችል ጊዜ እንዲያገኙ ስላስቻላቸው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠኑ የቀረበላቸውን ግብዣ ተቀብለዋል። ከዚህም በተጨማሪ በእንግሊዝኛ ቋንቋ በሚመሩ ጉባኤዎች ውስጥ ካሉ አስፋፊዎች መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት የዘወትር አቅኚ ሆነው ማገልገላቸው በጉባኤዎቹ ውስጥ የአገልግሎት ቅንዓት እንዲኖርና እድገት እንዲገኝ አስተዋጽኦ አድርጓል።
ብዙ በረከት ማጨድ ትችላለህ
በምድር ዙሪያ የሚገኙ ሌሎች ሰዎችም የመንግሥቱ ምሥራች በራሳቸው ቋንቋ ሲሰበክላቸው በጎ ምላሽ እንደሚሰጡ ምንም ጥርጥር የለውም። በመሆኑም ወጣት አዋቂ፣ ያገቡ ያላገቡ ሳይባል መንፈሳዊ አመለካከት ያላቸው በርካታ ወንድሞችና እህቶች የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉባቸው ቦታዎች ሄደው ለማገልገል ፈቃደኛ መሆናቸው እጅግ የሚያስደስት ነው። እውነት ነው፣ እነዚህ ወንድሞችና እህቶች የተለያዩ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል፤ ያም ሆኖ የሚያጋጥማቸው ችግር፣ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ሲቀበሉ ማየት ከሚያስገኝላቸው ደስታ ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። አንተስ፣ በአገርህም ሆነ በባዕድ አገር በሚገኝ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ለማገልገል የሚያስችሉህን አንዳንድ ማስተካከያዎች ማድረግ ትችል ይሆን? * (ሉቃስ 14:28-30፤ 1 ቆሮ. 16:9) ከሆነ፣ ብዙ በረከት እንደምታጭድ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.21 የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄዶ ማገልገልን በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 111 እና 112ን ተመልከት።
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ደስተኛ የሆኑ ጡረተኞች የሌሎችን ትኩረት ሳቡ
ቤርል ከብሪታንያ ወደ ካናዳ ከተዛወረች በኋላ በበርካታ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ውስጥ ዋና ኃላፊ ሆና ሠርታለች። ከዚህም በተጨማሪ የተካነች የፈረስ ጋላቢ የሆነችው ይህች ሴት በ1980 በተካሄደው ኦሎምፒክ ላይ ካናዳን ወክላ ተወዳድራለች። እሷና ባለቤቷ ጡረታ ከወጡ በኋላ በቻፓላ፣ ሜክሲኮ መኖር የጀመሩ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ የሚመገቡት በአካባቢው በሚገኙ ምግብ ቤቶች ውስጥ ነበር። ቤርል ደስተኛ የሆኑ እንግሊዝኛ ተናጋሪ ጡረተኞችን ስትመለከት ሄዳ የመተዋወቅና ወደ ሜክሲኮ የመጡት ለምን እንደሆነ የመጠየቅ ልማድ ነበራት። ከምታነጋግራቸው ሰዎች ውስጥ አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች መሆናቸውን ተገነዘበች። ቤርል እና ባለቤቷ ‘ደስተኛ ለመሆንና ትርጉም ያለው ሕይወት ለመምራት ቁልፉ አምላክን ማወቅ ከሆነ እኛም እንዲህ ማድረግ ይኖርብናል’ ብለው አሰቡ። ቤርል ለበርካታ ወራት በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ከተገኘች በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ተስማማች። ቤርል ለብዙ ዓመታት የዘወትር አቅኚ ሆና ማገልገል ችላለች።
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
“እነሱ ከእኛ ጋር መሆናቸው ትልቅ በረከት ነው”
የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ የሄዱ ወንድሞችና እህቶች በአካባቢው በሚገኙ ወንድሞች ዘንድ አድናቆት አትርፈዋል። በካሪቢያን የሚገኝ አንድ ቅርንጫፍ ቢሮ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በአገራችን የሚያገለግሉት በመቶዎች የሚቆጠሩ የውጭ አገር ወንድሞችና እህቶች ከዚህ ቢሄዱ ጉባኤዎች በጣም ይጎዳሉ። እነሱ ከእኛ ጋር መሆናቸው ትልቅ በረከት ነው።”
የአምላክ ቃል “ብዙ ሴቶችም [ምሥራቹን፣ NW] አሰራጩ” በማለት ይናገራል። (መዝሙር 68:11 የ1980 ትርጉም) በመሆኑም ወደ ውጪ አገር ሄደው ከሚያገለግሉት መካከል አብዛኞቹ ያላገቡ እህቶች መሆናቸው ምንም አያስደንቅም። የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛ የሆኑት እነዚህ እህቶች ትልቅ እርዳታ እያበረከቱ ነው። በምሥራቅ አውሮፓ የሚገኝ አንድ ቅርንጫፍ ቢሮ እንዲህ ብሏል፦ “በብዙዎቹ ጉባኤዎቻችን ውስጥ የእህቶች ቁጥር ከፍተኛ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ እስከ 70 በመቶ ይደርሳል። ከእነዚህ እህቶች መካከል አብዛኞቹ አዳዲሶች ናቸው። ሆኖም ከሌሎች አገሮች የመጡ ያላገቡ አቅኚ እህቶች እነሱን በማሠልጠን ረገድ ይህ ነው የማይባል አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ከውጪ አገር የመጡት እነዚህ እህቶች ግሩም ስጦታ ሆነውልናል!”
እነዚህ እህቶችስ በውጪ አገር በማገልገላቸው ምን ይሰማቸዋል? በ30ዎቹ አጋማሽ ላይ የምትገኝ አንጀሊካ የተባለች ያላገባች አቅኚ እህት በውጪ አገር ለብዙ ዓመት አገልግላለች። አንጀሊካ እንዲህ ብላለች፦ “በአንድ ወቅት ተመድቤበት በነበረው የአገልግሎት ክልል፣ ጭቃማ በሆነ መንገድ ላይ በየቀኑ እጓዝ የነበረ ከመሆኑም ሌላ የአካባቢው ሰዎች ያሉበትን አስቸጋሪ ሁኔታ መመልከት በጣም ያስጨንቀኝ ነበር። ሆኖም በአገልግሎት አማካኝነት ሰዎችን መርዳት እርካታ አስገኝቶልኛል። በተጨማሪም የአካባቢው ወንድሞችና እህቶች እነሱን ለመርዳት በመምጣቴ ምስጋናቸውን መግለጻቸው በእጅጉ ያበረታታኝ ነበር። አንዲት እህት በአቅኚነት ለማገልገል ስል ረጅም ርቀት ተጉዤ ወደ እነሱ አገር መምጣቴ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንድትካፈል እንዳነሳሳት ነግራኛለች።”
በአቅኚነት የምታገለግለው በ50ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ የምትገኘው ሱ እንዲህ ብላለች፦ “ችግሮች እንደሚያጋጥሙ ምንም ጥርጥር የለውም፤ ያም ሆኖ ችግሩ ከምናገኘው በረከት አንጻር ሲታይ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። አገልግሎት በጣም አስደሳች ነው! አብዛኛውን ጊዜ የማገለግለው ከወጣት እህቶች ጋር በመሆኑ ያጋጠሟቸውን ችግሮች ለመቋቋም የሚረዷቸውን ከመጽሐፍ ቅዱስና ከጽሑፎቻችን የተወሰዱ ሐሳቦች አካፍላቸዋለሁ። በነጠላነት ባገለገልኩባቸው በርካታ ዓመታት ውስጥ ያጋጠሙኝን ችግሮች በጽናት እንደተወጣሁ መመልከታቸው እነሱም በሕይወታቸው ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ለመቋቋም እንዳስቻላቸው ብዙ ጊዜ ይነግሩኛል። እነዚህን እህቶች መርዳት ከፍተኛ እርካታ አስገኝቶልኛል።”
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ሜክሲኮ
ጉዋናጁዋቶ
ኢራፕዋቶ
ቻፓላ
አኼኼክ
ቻፓላ ሐይቅ
ሞንቴሬ
ሳን ሚጌል ደ አየንዳ
ኩዌሬታሮ
ሜክሲኮ ሲቲ
ካንኩን
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንዳንዶች፣ በሜክሲኮ የሚገኙ የውጪ አገር ዜጎች ለመጀመሪያ ጊዜ ምሥራቹን እንዲሰሙ የማድረግ አስደሳች አጋጣሚ አግኝተዋል