ይሖዋ ደስ የሚሰኝበት አገልጋይ
ይሖዋ ደስ የሚሰኝበት አገልጋይ
“አገልጋዬ፣ በእርሱም ደስ የሚለኝ ምርጤ ይህ ነው።”—ኢሳ. 42:1
1. የይሖዋ ሕዝቦች በተለይ የመታሰቢያው በዓል ሲቃረብ ምን እንዲያደርጉ ይበረታታሉ? ለምንስ?
የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ የሚከበርበት ጊዜ ሲቃረብ የአምላክ ሕዝቦች “የእምነታችን ዋና ወኪልና ፍጹም አድራጊ የሆነውን ኢየሱስን በትኩረት [እንዲመለከቱ]” ሐዋርያው ጳውሎስ የሰጠውን ምክር ተግባራዊ እንዲያደርጉ ይበረታታሉ። ጳውሎስ አክሎም እንዲህ ብሏል:- “እንግዲህ እንዳትደክሙና በነፍሳችሁ እንዳትዝሉ የራሳቸውን ጥቅም የሚጻረር ነገር የሚያደርጉ ኃጢአተኞች የሚያሰሙትን እንዲህ ዓይነቱን ተቃውሞ በጽናት የተቋቋመውን እሱን በጥሞና አስቡ።” (ዕብ. 12:2, 3) ቅቡዓን ክርስቲያኖችም ሆኑ አጋሮቻቸው የሆኑት ሌሎች በጎች ክርስቶስ መሥዋዕት እስኪሆን ድረስ የተከተለውን የታማኝነት ጎዳና በትኩረት መመልከታቸው ይሖዋን በታማኝነት ማገልገላቸውን እንዲቀጥሉ እንዲሁም ‘በነፍሳቸው እንዳይዝሉ’ ይረዳቸዋል።—ከገላትያ 6:9 ጋር አወዳድር።
2. ከአምላክ ልጅ ጋር ተያያዥነት ካላቸው በኢሳይያስ መጽሐፍ ውስጥ ከሚገኙት ትንቢቶች ምን እንማራለን?
2 ይሖዋ፣ ከልጁ ጋር በቀጥታ ተያያዥነት ያላቸው በርካታ ትንቢቶችን በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት አስነግሯል። እነዚህ ትንቢቶች “የእምነታችን ዋና ወኪልና ፍጹም አድራጊ የሆነውን [ክርስቶስ] ኢየሱስን በትኩረት [ለመመልከት]” ይረዱናል። * እነዚህ ትንቢቶች ስለ ኢየሱስ ባሕርያትና ስለሚደርስበት መከራ ዝርዝር መረጃ የሚሰጡ ከመሆኑም ሌላ ንጉሣችንና ቤዛችን በመሆን ከፍ ከፍ እንደሚደረግ ይገልጻሉ። ከዚህም በተጨማሪ ትንቢቶቹ፣ በዚህ ዓመት ሐሙስ ሚያዝያ 1, 2001 (April 9, 2009) ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ስለምናከብረው የመታሰቢያው በዓል ያለንን ግንዛቤ ያሰፉልናል።
የአገልጋዩ ማንነት ታወቀ
3, 4. (ሀ) ‘አገልጋይ’ ወይም ‘ባሪያ’ የሚሉት በኢሳይያስ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙት ቃላት የሚያመለክቱት ማንን ነው? (ለ) በኢሳይያስ ምዕራፍ 42, 49, 50, 52, እና 53 ላይ የተጠቀሰውን አገልጋይ ወይም ባሪያ ማንነት ለማወቅ መጽሐፍ ቅዱስ የሚረዳን እንዴት ነው?
3 ‘አገልጋይ’ ወይም ‘ባሪያ’ የሚሉት ቃላት በኢሳይያስ መጽሐፍ ውስጥ በተደጋጋሚ ጊዜያት ተጠቅሰዋል። እነዚህ ቃላት አልፎ አልፎ ኢሳይያስን ለማመልከት ተሠርቶባቸዋል። (ኢሳ. 20:3፤ 44:26) አንዳንድ ጊዜ ደግሞ መላውን የእስራኤል ብሔር ወይም ያዕቆብን ለማመልከት አገልግለዋል። (ኢሳ. 41:8, 9፤ 44:1, 2, 21) ይሁን እንጂ በኢሳይያስ ምዕራፍ 42, 49, 50, 52 እና 53 ላይ አገልጋዩን በተመለከተ ስለተነገሩት ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ትንቢቶችስ ምን ማለት ይቻላል? በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ የተጠቀሰውን የይሖዋ አገልጋይ ማንነት የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት በግልጽ ይነግሩናል። በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሰው ኢትዮጵያዊ ባለሥልጣን፣ ወንጌላዊው ፊልጶስ በመንፈስ ተመርቶ ባነጋገረው ጊዜ ያነብ የነበረው ከእነዚህ ትንቢቶች አንዱን መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። ይህ ባለሥልጣን በአሁኑ ጊዜ በኢሳይያስ 53:7, 8 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ካነበበ በኋላ ፊልጶስን “እባክህ ንገረኝ፣ ነቢዩ ይህን የተናገረው ስለ ማን ነው? ስለ ራሱ ነው ወይስ ስለ ሌላ ሰው?” በማለት ጠየቀው። ፊልጶስም፣ ኢሳይያስ የተናገረው ስለ መሲሑ ስለ ኢየሱስ መሆኑን ገለጸለት።—ሥራ 8:26-35
4 ኢየሱስ ገና ሕፃን እያለ ስምዖን የተባለ አንድ ጻድቅ ሰው በኢሳይያስ 42:6 እና 49:6 ላይ አስቀድሞ በተነገረው መሠረት ‘ሕፃኑ ኢየሱስ’ “ሕዝቦችን የጋረደውን መሸፈኛ የሚገልጥ ብርሃን” እንደሚሆን በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ተናግሮ ነበር። (ሉቃስ 2:25-32) ከዚህም በላይ ኢየሱስ ለፍርድ በቀረበበት ምሽት ስለሚደርስበት ውርደት በኢሳይያስ 50:6-9 ላይ አስቀድሞ ተነግሮ ነበር። (ማቴ. 26:67፤ ሉቃስ 22:63) በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከተከበረው የጴንጤቆስጤ በዓል በኋላ ሐዋርያው ጴጥሮስ የይሖዋ ‘አገልጋይ’ ወይም ‘ባሪያ’ የተባለው ኢየሱስ መሆኑን በግልጽ ተናግሯል። (ኢሳ. 52:13፤ 53:11፤ የሐዋርያት ሥራ 3:13, 26ን አንብብ። ) ስለ መሲሑ ከተነገሩት ከእነዚህ ትንቢቶች ምን እንማራለን?
ይሖዋ አገልጋዩን አሠልጥኖታል
5. የአምላክ አገልጋይ ምን ሥልጠና አግኝቷል?
5 ኢሳይያስ የአምላክ አገልጋይን በተመለከተ ከተናገራቸው ትንቢቶች አንዱ፣ የይሖዋ የበኩር ልጅ ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ከአባቱ ጋር ስለነበረው የጠበቀ ግንኙነት ያለንን ግንዛቤ ያሰፋልናል። (ኢሳይያስ 50:4-9ን አንብብ። ) ይህ አገልጋይ ይሖዋ ዘወትር ያሠለጥነው እንደነበረ ሲናገር “በመማር ላይ እንዳለ ተማሪ ለመስማት ጆሮዬን ያነቃዋል” ብሏል። (ኢሳ. 50:4) የይሖዋ አገልጋይ በእነዚያ ዓመታት ሁሉ ታዛዥ ተማሪ በመሆን አባቱን ይሰማ እንዲሁም ከእሱ ይማር ነበር። የአጽናፈ ዓለም ፈጣሪ ከሆነው አምላክ ትምህርት መቅሰም እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!
6. የአምላክ አገልጋይ ለአባቱ ሙሉ በሙሉ እንደሚገዛ ያሳየው እንዴት ነበር?
6 ከላይ በተጠቀሰው ትንቢት ላይ የአምላክ አገልጋይ አባቱን “ሉዓላዊ ጌታ ይሖዋ” [NW ] ብሎ ጠርቶታል። ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው ይህ አገልጋይ፣ ይሖዋ የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ጌታ መሆኑን ተምሯል። አገልጋዩ ለአባቱ ሙሉ በሙሉ እንደሚገዛ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “ልዑል እግዚአብሔር ጆሮዬን ከፍቶታል፤ እኔም ዐመፀኛ አይደለሁም፤ ወደ ኋላም አላፈገፈግሁም።” (ኢሳ. 50:5) ይሖዋ ግዑዙን ጽንፈ ዓለምና የሰውን ዘር በፈጠረበት ጊዜ አገልጋዩ “ዋና ባለሙያ” በመሆን ከአባቱ ጎን ይሠራ ነበር። ይህ “ዋና ባለሙያ” ‘የአምላክ በሆነው መላው ዓለም ሐሤት እያደረገ በሰው ልጆች ደስ በመሰኘት በይሖዋ ፊት ሁልጊዜ ሐሤት ያደርግ ነበር።’—ምሳሌ 8:22-31
7. የአምላክ አገልጋይ ፈተና ሲያጋጥመው የአባቱ ድጋፍ እንደማይለየው እርግጠኛ እንደነበር የሚያሳየው ምንድን ነው?
7 የአምላክ አገልጋይ ያገኘው ሥልጠና እንዲሁም ለሰው ዘር ያለው ፍቅር ወደ ምድር በመጣበት ወቅት ያጋጠመውን ከባድ ተቃውሞ ለመቋቋም ዝግጁ እንዲሆን ረድቶታል። ኃይለኛ ስደት ቢያጋጥመውም የአባቱን ፈቃድ በማድረግ ይደሰት ነበር። (መዝ. 40:8፤ ማቴ. 26:42፤ ዮሐ. 6:38) ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ ፈተና ባጋጠመው ጊዜ ሁሉ አባቱ ደስ እንደሚሰኝበትና እንደሚደግፈው እርግጠኛ ነበር። በኢሳይያስ ትንቢት ላይ እንደተገለጸው ኢየሱስ እንደሚከተለው ብሎ መናገር ይችል ነበር:- “ንጹሕ መሆኔን የሚያረጋግጥልኝ በአጠገቤ አለ፤ ታዲያ ማን ሊከሰኝ ይችላል? . . . የሚረዳኝ እርሱ ጌታ እግዚአብሔር ነው።” (ኢሳ. 50:8, 9) በኢሳይያስ መጽሐፍ ላይ የሚገኝ ሌላ ትንቢት እንደሚያሳየው የይሖዋ ታማኝ አገልጋይ በምድር ላይ አገልግሎቱን ባከናወነበት ጊዜ ሁሉ የአባቱ እርዳታ አልተለየውም።
አገልጋዩ በምድር ላይ ያከናወነው አገልግሎት
8. በኢሳይያስ 42:1 ላይ ይሖዋ “ምርጤ” ያለው ኢየሱስን መሆኑን የሚያሳየው ምንድን ነው?
8 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኢየሱስ በ29 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ሲጠመቅ የተከናወነውን ሁኔታ ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “መንፈስ ቅዱስም . . . በእሱ ላይ ወረደ፤ ከዚያም ‘አንተ የምወድህ ልጄ ነህ፤ በአንተ ደስ ይለኛል’ የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ።” (ሉቃስ 3:21, 22) ከዚህ ለመመልከት እንደምንችለው ይሖዋ በኢሳይያስ ትንቢት ላይ “ምርጤ” ያለው ማንን እንደሆነ በግልጽ አሳይቷል። (ኢሳይያስ 42:1-7ን አንብብ። ) ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ይህንን ትንቢት አስገራሚ በሆነ መንገድ ፈጽሞታል። ማቴዎስ በወንጌል ዘገባው ላይ በኢሳይያስ 42:1-4 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ በመጥቀስ ይህ ትንቢት በኢየሱስ ላይ እንደተፈጸመ ገልጿል።—ማቴ. 12:15-21
9, 10. (ሀ) ኢየሱስ በአገልግሎቱ ወቅት በኢሳይያስ 42:3 ላይ የሚገኘውን ትንቢት የፈጸመው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ‘ፍትሕን ያመጣው እንዴት ነበር? ‘ፍትሕን በምድር ላይ የሚያመጣውስ’ መቼ ነው?
9 የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ተራውን የአይሁድ ማኅበረሰብ ይንቁት ነበር። (ዮሐ. 7:47-49) ሕዝቡ ተጨቁኖ ስለነበር ‘ከተቀጠቀጠ ሸምበቆ” ወይም ሊጠፋ ከተቃረበ “የጧፍ ክር” ጋር ሊመሳሰል ይችል ነበር። ኢየሱስ ግን ለድሆችና ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ርኅራኄ አሳይቷል። (ማቴ. 9:35, 36) “እናንተ የደከማችሁና ሸክም የከበዳችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ” በማለት ለእነዚህ ሰዎች ደግነት የተንጸባረቀበት ግብዣ አቅርቦላቸዋል። (ማቴ. 11:28) ከዚህም በላይ ኢየሱስ፣ ይሖዋ ትክክል ወይም ስህተት ስለሆነው ነገር ያወጣውን መሥፈርት ለሰዎች በማስተማር ‘ፍትሕን አምጥቷል።’ (ኢሳ. 42:3) እንዲሁም ሕዝቡ የአምላክን ሕግ ተግባራዊ በሚያደርጉበት ጊዜ ምክንያታዊ መሆንና ምሕረትን ማሳየት እንዳለባቸው ጠቁሟል። (ማቴ. 23:23) ኢየሱስ፣ ለሀብታሞችም ሆነ ለድሆች ያለ አድልዎ በመስበክም ፍትሕን አሳይቷል።—ማቴ. 11:5፤ ሉቃስ 18:18-23
10 ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ “ምርጤ” ያለው ሰው ‘ፍትሕን በምድር ላይ እንደሚያመጣ’ የኢሳይያስ ትንቢት ገልጿል። (ኢሳ. 42:4) ኢየሱስ በቅርቡ ይህንን ይፈጽማል፤ የመሲሐዊው መንግሥት ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን ሁሉንም የፖለቲካ መንግሥታት አጥፍቶ ጽድቅ የሰፈነበትን የራሱን አገዛዝ ያቋቁማል። በዚህ መንገድ ‘ጽድቅ የሰፈነበት’ አዲስ ዓለም ያመጣል።—2 ጴጥ. 3:13፤ ዳን. 2:44
“ብርሃን” እና “ቃል ኪዳን”
11. በመጀመሪያው መቶ ዘመን ኢየሱስ ‘ለአሕዛብ ብርሃን’ የሆነው በምን መንገድ ነበር? ይህ ብርሃን እስከ ዘመናችን ድረስ የቀጠለውስ እንዴት ነው?
11 በኢሳይያስ 42:6 ላይ በሚገኘው ትንቢት መሠረት ኢየሱስ በእርግጥም ‘ለአሕዛብ ብርሃን’ ሆኗል። በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት በመጀመሪያ ለአይሁዳውያን መንፈሳዊ ብርሃን አብርቶላቸዋል። (ማቴ. 15:24፤ ሥራ 3:26) ሆኖም ኢየሱስ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” ብሎ ነበር። (ዮሐ. 8:12) በመሆኑም መንፈሳዊ ብርሃን በማብራት ብቻ ሳይሆን ለመላው የሰው ዘር ፍጹም ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ በመስጠት ጭምር ለአይሁድም ሆነ ለአሕዛብ ብርሃን ሆኗል። (ማቴ. 20:28) ኢየሱስ ትንሣኤ ካገኘ በኋላ ደቀ መዛሙርቱን “እስከ ምድር ዳር ድረስ” ምሥክሮቹ እንዲሆኑ አዟቸዋል። (ሥራ 1:8) ጳውሎስና በርናባስ በአገልግሎታቸው ወቅት፣ “የአሕዛብ ብርሃን” የሚለውን አገላለጽ ከጠቀሱ በኋላ ይህ ሐሳብ አይሁዳዊ ባልሆኑ ሰዎች መካከል ያከናውኑት ከነበረው የስብከት ሥራ ጋር በተያያዘ ፍጻሜውን እንዳገኘ ገልጸዋል። (ሥራ 13:46-48፤ ከኢሳይያስ 49:6 ጋር አወዳድር።) በምድር ላይ ያሉት የኢየሱስ ቅቡዓን ወንድሞችና አጋሮቻቸው፣ መንፈሳዊውን ብርሃን እያበሩ እንዲሁም ሰዎች “የአሕዛብ ብርሃን” በሆነው በኢየሱስ ላይ እምነት እንዲኖራቸው እየረዱ በመሆኑ ይህ ሥራ እስካሁን ድረስ ቀጥሏል።
12. ይሖዋ፣ አገልጋዩን “ለሕዝቡ ቃል ኪዳን” ያደረገው እንዴት ነው?
12 በዚሁ ትንቢት ላይ ይሖዋ፣ የመረጠውን አገልጋዩን “እጠብቅሃለሁ፤ ለሕዝቡ ቃል ኪዳን. . . አደርግሃለሁ” ብሎታል። (ኢሳ. 42:6) ሰይጣን፣ ኢየሱስን ለማጥፋትና በምድር ላይ የሚያከናውነውን አገልግሎት እንዳይፈጽም ለማገድ በተደጋጋሚ ጊዜያት ጥረት ቢያደርግም ይሖዋ፣ ኢየሱስ አልፎ እንዲሰጥ የወሰነው ጊዜ እስኪደርስ ድረስ ጥበቃ አድርጎለታል። (ማቴ. 2:13፤ ዮሐ. 7:30) ከዚያም ይሖዋ፣ ኢየሱስን ከሞት በማስነሳት በምድር ላይ ለሚኖሩ ሰዎች “ቃል ኪዳን” አድርጎታል። ይህ የጸና ቃል ኪዳን፣ የአምላክ ታማኝ አገልጋይ በመንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ ያሉትን ሰዎች ነፃ በማውጣት ‘ለአሕዛብ ብርሃን’ ሆኖ እንደሚቀጥል ያረጋግጣል።—ኢሳይያስ 49:8, 9ን አንብብ። *
13. ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት “በጨለማ የተቀመጡትን” ነፃ ያወጣቸው እንዴት ነበር? አሁንም እንዲህ ማድረጉን የቀጠለውስ እንዴት ነው?
ኢሳ. 42:7) ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ሐሰተኛ የሆኑ ሃይማኖታዊ ወጎችን በማጋለጥና ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸውን ምሥራች በመስበክ የኢሳይያስን ትንቢት ፈጽሟል። (ማቴ. 15:3፤ ሉቃስ 8:1) እንዲህ በማድረጉም አንዳንድ አይሁዳውያንን ከሐሰት ሃይማኖት ቀንበር ያላቀቃቸው ሲሆን እነዚህ ሰዎች የእሱ ደቀ መዛሙርት ሆነዋል። (ዮሐ. 8:31, 32) ኢየሱስ አይሁዳውያን ያልሆኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችንም በተመሳሳይ መንገድ ከመንፈሳዊ ጨለማ አውጥቷቸዋል። ክርስቶስ፣ ተከታዮቹን “ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” በማለት ያዘዛቸው ሲሆን “እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ” አብሯቸው እንደሚሆን ቃል ገብቶላቸዋል። (ማቴ. 28:19, 20) ክርስቶስ ኢየሱስ ከሰማይ ሆኖ በዓለም ዙሪያ የሚከናወነውን የስብከት ሥራ በበላይነት እየመራ ነው።
13 ከዚህ ቃል ኪዳን ጋር በሚስማማ መንገድ ይሖዋ ምርጤ ያለው አገልጋይ “የዕውሮችን ዐይን [ይከፍታል]” እንዲሁም “ምርኮኞችን ከእስር ቤት፣ በጨለማ የተቀመጡትንም ከወህኒ [ያወጣል]።” (ይሖዋ ‘አገልጋዩን’ ከፍ ከፍ አደረገው
14, 15. ይሖዋ፣ አገልጋዩን ከፍ ከፍ ያደረገው ለምንና እንዴት ነው?
14 ይሖዋ፣ መሲሕ የሆነውን አገልጋዩን ወይም ባሪያውን በተመለከተ ባስነገረው ሌላ ትንቢት ላይ ደግሞ እንዲህ ብሏል:- “እነሆ፤ ባሪያዬ የሚያከናውነው በማስተዋል ነው፤ ገናና ይሆናል፤ ከፍ ከፍ ይላል፤ እጅግ ይከብራልም።” (ኢሳ. 52:13) ኢየሱስ ለይሖዋ ሉዓላዊነት በታማኝነት በመገዛቱና ከሁሉ የከፋ ፈተና ቢደርስበትም በታማኝነት በመጽናቱ አባቱ ከፍ ከፍ አድርጎታል።
15 ሐዋርያው ጴጥሮስ ኢየሱስን በተመለከተ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እሱም ወደ ሰማይ የሄደ ሲሆን አሁን በአምላክ ቀኝ ይገኛል፤ እንዲሁም መላእክት፣ ሥልጣናትና ኃይላት እንዲገዙለት ተደርጓል።” (1 ጴጥ. 3:22) ሐዋርያው ጳውሎስም በተመሳሳይ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ራሱን ዝቅ በማድረግ እስከ ሞት ድረስ ያውም በመከራ እንጨት ላይ እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ ሆኗል። በዚህም ምክንያት አምላክ የላቀ ቦታ በመስጠት ከፍ ከፍ አደረገው፤ እንዲሁም ከሌላ ከማንኛውም ስም በላይ የሆነ ስም በደግነት ሰጠው፤ ይህም በሰማይና በምድር እንዲሁም ከምድር በታች ያሉ ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ ነው፤ ምላስም ሁሉ አባት ለሆነው አምላክ ክብር፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደሆነ በይፋ እውቅና እንዲሰጥ ነው።”—ፊልጵ. 2:8-11
16. በ1914 ኢየሱስ ‘እጅግ የከበረው’ እንዴት ነው? ከዚያ ጊዜ ወዲህ ምን አከናውኗል?
መዝ. 2:6፤ ዳን. 7:13, 14) ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ክርስቶስ ‘በጠላቶቹ መካከል ሆኖ እየገዛ’ ነው። (መዝ. 110:2) በመጀመሪያ ሰይጣንና አጋንንቱን ወደ ምድር ጣላቸው። (ራእይ 12:7-12) ከዚያም ታላቁ ቂሮስ የሆነው ክርስቶስ በምድር ላይ የቀሩ ቅቡዓን ወንድሞቹን ‘ከታላቂቱ ባቢሎን’ ቀንበር አላቀቃቸው። (ራእይ 18:2፤ ኢሳ. 44:28) ኢየሱስ በመጀመሪያ “የቀሩትን” መንፈሳዊ ወንድሞቹን ከዚያም ‘ትንሹን መንጋ’ በታማኝነት የሚደግፉትን በሚሊዮን የሚቆጠሩ “ሌሎች በጎች” ለመሰብሰብ የሚያስችለውን ዓለም አቀፍ የስብከት ሥራ እየመራ ነው።—ራእይ 12:17፤ ዮሐ. 10:16፤ ሉቃስ 12:32
16 በ1914 ደግሞ ይሖዋ፣ ኢየሱስን ይበልጥ ከፍ ከፍ አድርጎታል። ይሖዋ የመሲሐዊው መንግሥት ንጉሥ አድርጎ በሾመው ወቅት ኢየሱስ ‘እጅግ ከብሯል።’ (17. ኢሳይያስ ስለ ‘አገልጋዩ’ የተናገራቸውን ትንቢቶች በመመርመራችን ምን ትምህርት አግኝተናል?
17 በኢሳይያስ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን እነዚህን ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ትንቢቶች መመርመራችን ንጉሣችንና ቤዛችን ለሆነው ለክርስቶስ ኢየሱስ ያለንን አድናቆት እንደጨመረው ጥርጥር የለውም። ክርስቶስ በምድር ላይ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት ለአባቱ መገዛቱ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ምን ዓይነት ሥልጠና አግኝቶ እንደነበር የሚጠቁም ነው። ኢየሱስ ራሱ ባከናወነው አገልግሎት እንዲሁም እስከ አሁን ድረስ በበላይነት በሚመራው የስብከቱ ሥራ አማካኝነት “የአሕዛብ ብርሃን” መሆኑን አሳይቷል። መሲሕ የሆነው አገልጋይ ለእኛ ሲል እንደሚሠቃይና ሕይወቱን እንደሚሰጥ የሚገልጸውን ሌላ ትንቢት በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመለከታለን፤ የመታሰቢያው በዓል ሲቃረብ እነዚህን ነጥቦች ‘በጥሞና ልናስብባቸው’ ይገባል።—ዕብ. 12:2, 3
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.2 እነዚህ ትንቢቶች በኢሳይያስ 42:1-7፤ 49:1-12፤ 50:4-9 እንዲሁም 52:13 እስከ 53:12 ላይ ይገኛሉ።
^ አን.12 በኢሳይያስ 49:1-12 ላይ የሚገኘውን ትንቢት በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የኢሳይያስ ትንቢት—ለመላው የሰው ዘር የፈነጠቀ ብርሃን ጥራዝ 2 ገጽ 136-145ን ተመልከት።
ለክለሳ ያህል
• በኢሳይያስ መጽሐፍ ውስጥ በሚገኙት ትንቢቶች ላይ የተገለጸው ‘አገልጋይ’ ማን ነው? በምን እናውቃለን?
• ይሖዋ ለአገልጋዩ ምን ሥልጠና ሰጥቶታል?
• ኢየሱስ ‘ለአሕዛብ ብርሃን’ የሆነው እንዴት ነው?
• የአምላክ አገልጋይ ከፍ ከፍ የተደረገው እንዴት ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፊልጶስ፣ ኢሳይያስ የጠቀሰው ‘አገልጋይ’ መሲሑን ኢየሱስን እንደሚያመለክት በግልጽ ተናግሯል
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ የመረጠው አገልጋይ ማለትም ኢየሱስ ለድሆችና ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ርኅራኄ አሳይቷል
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ፣ ኢየሱስን ከፍ ከፍ ያደረገው ከመሆኑም በላይ የመሲሐዊው መንግሥት ንጉሥ አድርጎ ሾሞታል