በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ ከልብ ለቀረበ ጸሎት የሰጠው መልስ

ይሖዋ ከልብ ለቀረበ ጸሎት የሰጠው መልስ

ይሖዋ ከልብ ለቀረበ ጸሎት የሰጠው መልስ

“ይህም ሰዎች ሁሉ ስምህ ይሖዋ የሆነው አንተ፣ በምድር ሁሉ ላይ አንተ ብቻ ልዑል እንደሆንክ ያውቁ ዘንድ ነው።”—መዝ. 83:18 NW

1, 2. ብዙ ሰዎች ስለ አምላክ ስም ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያውቁ ምን ተሰምቷቸዋል? የትኞቹ ጥያቄዎችስ ይነሳሉ?

ከተወሰኑ ዓመታት በፊት አንዲት ሴት በአካባቢዋ በተከሰተ አሳዛኝ አደጋ የተነሳ በጣም ተረብሻ ነበር። የሮም ካቶሊክ ሃይማኖት ተከታይ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ የተወለደችው ይህች ሴት እርዳታ ለማግኘት በአካባቢዋ ወደሚኖር አንድ ቄስ ሄደች፤ ሆኖም ቄሱ ሊያናግራት እንኳ ፈቃደኛ አልነበረም። በዚህም የተነሳ እንዲህ ስትል ወደ አምላክ ጸለየች፦ “ማን እንደሆንክ አላውቅም . . . መኖርህን ግን አውቃለሁ። እባክህ እንዳውቅህ እርዳኝ!” ብዙም ሳይቆይ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤቷ የመጡ ሲሆን ስትፈልገው የነበረውን ማጽናኛና እውቀት ማግኘት እንድትችል ረዷት። የይሖዋ ምሥክሮቹ በርካታ ነገሮችን ያስተማሯት ከመሆኑም ሌላ የአምላክ የግል ስም ይሖዋ እንደሆነ ገለጹላት። ይህች ሴት የአምላክን ስም ስታውቅ ልቧ በጥልቅ ተነካ። “ከልጅነቴ ጀምሮ ለማወቅ እጓጓ የነበረው ይህንን አምላክ ነው!” ስትል ተናገረች።

2 ብዙ ሰዎች የአምላክን ስም ሲያውቁ ተመሳሳይ ስሜት ተሰምቷቸዋል። በአብዛኛው የአምላክን ስም ለመጀመሪያ ጊዜ የተመለከቱት መዝሙር 83:18⁠ን ሲያነቡ ነው። ይህ ጥቅስ በአዲሱ ዓለም ትርጉም እንዲህ ይላል፦ “ይህም ሰዎች ሁሉ ስምህ ይሖዋ የሆነው አንተ፣ በምድር ሁሉ ላይ አንተ ብቻ ልዑል እንደሆንክ ያውቁ ዘንድ ነው።” መዝሙር 83 ለምን እንደተጻፈ አስበህ ታውቃለህ? ሁሉም ሰው፣ ይሖዋ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ መሆኑን አምኖ እንዲቀበል የሚያስገድዱት የትኞቹ ክንውኖች ናቸው? በዛሬው ጊዜ የምንኖር ክርስቲያኖች ከዚህ መዝሙር ምን ትምህርት እናገኛለን? በዚህ ርዕስ ውስጥ እነዚህን ጥያቄዎች እንመረምራለን። *

በይሖዋ ሕዝቦች ላይ የተጠነሰሰ ሤራ

3, 4. መዝሙር 83⁠ን ያቀናበረው ማን ነው? በመዝሙሩ ላይ የአምላክ ሕዝቦች ምን አስጊ ሁኔታ እንደተደቀነባቸው ተገልጿል?

3 በመዝሙር 83 አናት ላይ የሚገኘው ሐሳብ እንደሚገልጸው ይህ መዝሙር “የአሳፍ መዝሙር” ነው። ይህን መዝሙር ያቀናበረው በንጉሥ ዳዊት ዘመነ መንግሥት ታዋቂ ዘማሪ ከነበረው ከሌዋዊው ከአሳፍ የዘር ሐረግ የመጣ ሰው ሳይሆን አይቀርም። ይህ የአምላክ አገልጋይ፣ ይሖዋ ሉዓላዊነቱን ለማረጋገጥና ስሙ እንዲታወቅ ለማድረግ እርምጃ እንዲወስድ በመዝሙሩ ላይ ልመና አቅርቧል። ይህ መዝሙር የተቀናበረው ሰሎሞን ከሞተ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ መሆን አለበት። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም በዳዊትም ሆነ በሰሎሞን የግዛት ዘመን የጢሮስ ንጉሥ የእስራኤል ወዳጅ ነበር። መዝሙር 83 በተቀናበረበት ወቅት ግን የጢሮስ ነዋሪዎች እስራኤልን ለማጥቃት ከመነሳታቸውም በላይ ከእስራኤል ጠላቶች ጋር ግንባር ፈጥረው ነበር።

4 መዝሙራዊው የአምላክን ሕዝቦች ለማጥፋት ያሤሩ የነበሩ አሥር ብሔራትን ጠቅሷል። በእስራኤላውያን ዙሪያ ስለሚገኙትና ጠላቶቻቸው ስለሆኑት ስለ እነዚህ ብሔራት መዝሙራዊው እንዲህ ብሏል፦ “የኤዶምና የእስማኤላውያን ድንኳኖች፣ የሞዓብና የአጋራውያን ድንኳኖች፣ ጌባል፣ አሞንና አማሌቅ፣ ፍልስጥኤምም ከጢሮስ ሕዝብ ጋር ሆነው ዶለቱ፤ አሦርም ከእነርሱ ጋር ተባበረ።” (መዝ. 83:6-8) ይህ መዝሙር የሚናገረው ስለ የትኛው ጊዜ ነው? አንዳንዶች መዝሙሩ የሚገልጸው በኢዮሣፍጥ ዘመን አሞን፣ ሞዓብና የሴይር ተራራ ሰዎች በኅብረት ሆነው እስራኤልን ሊወጉ ስለመጡበት ጊዜ እንደሆነ ይናገራሉ። (2 ዜና 20:1-26) ሌሎች ደግሞ መዝሙሩ እስራኤላውያን በታሪክ ዘመናት ሁሉ በአጎራባች አገሮች የተጠሉ እንደነበሩ የሚያሳይ እንደሆነ ያምናሉ።

5. በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች ከመዝሙር 83 ምን ጥቅም ያገኛሉ?

5 በዚህ መዝሙር ላይ የተገለጸው ሐሳብ የተፈጸመው በየትኛውም ወቅት ቢሆን ይሖዋ አምላክ፣ የጸሎት ይዘት ያለው ይህ መዝሙር እንዲጻፍ ያደረገው የእስራኤል ብሔር አደጋ ላይ ወድቆ በነበረበት ጊዜ እንደሆነ ግልጽ ነው። በዛሬው ጊዜ የሚገኙት የአምላክ አገልጋዮችም ሊያጠፏቸው ቆርጠው በተነሱ ጠላቶቻቸው ሁልጊዜ ጥቃት ስለሚሰነዘርባቸው ይህ መዝሙር ለእነሱም የሚያበረታታ ሐሳብ ይዟል። ከዚህም በተጨማሪ በቅርቡ የማጎጉ ጎግ፣ አምላክን በመንፈስና በእውነት የሚያመልኩ የይሖዋ አገልጋዮችን በሙሉ ለማጥፋት ሠራዊቱን አሰባስቦ የመጨረሻ ጥቃት በሚሰነዝርበት ወቅት ይህ መዝሙር እንደሚያጠናክረን ምንም ጥርጥር የለውም።—ሕዝቅኤል 38:2, 8, 9, 16ን አንብብ።

መዝሙራዊውን በዋነኝነት ያሳሰበው ነገር

6, 7. (ሀ) መዝሙራዊው በመዝሙር 83 የመጀመሪያ ቁጥሮች ላይ ስለየትኛው ጉዳይ ጸልዮአል? (ለ) መዝሙራዊውን በዋነኝነት ያሳሰበው ምን ነበር?

6 መዝሙራዊው የልቡን አውጥቶ ለይሖዋ እንዴት እንደገለጸ ተመልከት፦ “አምላክ ሆይ፤ ዝም አትበል፤ አምላክ ሆይ፤ ጸጥ አትበል፤ ጭጭ አትበል። ጠላቶችህ እንዴት እንደ ተነሣሡ፣ ባላንጣዎችህም እንዴት ራሳቸውን ቀና ቀና እንዳደረጉ ተመልከት። በሕዝብህ ላይ በተንኰል አሤሩ፤ . . . በአንድ ሐሳብ ተስማምተው ተማከሩ፤ በአንተም ላይ ተማማሉ።”—መዝ. 83:1-3, 5

7 መዝሙራዊውን በዋነኝነት ያሳሰበው ምን ነበር? ይህ መዝሙራዊ የራሱም ሆነ የቤተሰቡ ደኅንነት በጣም አሳስቦት እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ሆኖም ጸሎቱ በዋነኝነት ያተኮረው በይሖዋ ስም ላይ በሚመጣው ነቀፌታ እንዲሁም የእሱን ስም የተሸከመው ብሔር በተሰነዘረበት ዛቻ ላይ ነበር። እኛም በዚህ አሮጌ ዓለም የመጨረሻ ቀን ውስጥ የሚያጋጥሙንን ችግሮች በጽናት በምንቋቋምበት ጊዜ እንዲህ ዓይነት ሚዛናዊ አመለካከት ለመያዝ ጥረት እናድርግ።—ማቴዎስ 6:9, 10ን አንብብ።

8. በእስራኤላውያን ላይ ያሤሩ የነበሩት ብሔራት ዓላማቸው ምን ነበር?

8 መዝሙራዊው፣ “የእስራኤል ስም ከእንግዲህ እንዳይታወስ፣ ኑና ሕዝብ እንዳይሆኑ እንደምስሳቸው” በማለት ጠላቶቻቸው እንደተናገሩ ገልጿል። (መዝ. 83:4) እነዚያ ብሔራት፣ አምላክ ለመረጣቸው ሕዝቦች እንዴት ያለ ጥላቻ ነበራቸው! ይሁንና በእስራኤል ላይ እንዲያሤሩ ያነሳሳቸው ምክንያት ይህ ብቻ አልነበረም። የእስራኤላውያንን ምድር ለመውረስ የተመኙ ከመሆኑም በላይ “የእግዚአብሔርን የግጦሽ ቦታ፣ [“ማደሪያ፣” NW] ወስደን የግላችን እናድርግ” በማለት ፎክረው ነበር። (መዝ. 83:12) በዘመናችንስ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ሁኔታ ተከስቷል? አዎን!

“ቅዱስ ማደሪያህ”

9, 10. (ሀ) በጥንት ዘመን የአምላክ ቅዱስ ማደሪያ ምን ነበር? (ለ) በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ቅቡዓን ቀሪዎችና “ሌሎች በጎች” ምን በረከቶች አግኝተዋል?

9 በጥንት ዘመን፣ ተስፋይቱ ምድር የአምላክ ቅዱስ ማደሪያ እንደሆነች ተደርጋ ትጠቀስ ነበር። እስራኤላውያን ከግብፅ ነፃ ከወጡ በኋላ የዘመሩትን የድል መዝሙር አስታውስ፤ ሕዝቡ እንዲህ ብለው ነበር፦ “በማይለወጠው ፍቅርህ፣ የተቤዥኻቸውን ሕዝብህን ትመራለህ፤ እነርሱን በብርታትህ፣ ወደ ቅዱስ ማደሪያህ ትመራቸዋለህ።” (ዘፀ. 15:13) ከጊዜ በኋላ ይህ “ማደሪያ” የክህነት አገልግሎት የሚካሄድበትን ቤተ መቅደስ እንዲሁም በዳዊት የዘር ሐረግ የመጡ ነገሥታት በይሖዋ ዙፋን ላይ የሚቀመጡባትን ኢየሩሳሌም የተባለችውን ዋና ከተማ የሚያካትት ሆኗል። (1 ዜና 29:23) ኢየሱስ፣ ኢየሩሳሌምን “የታላቁ ንጉሥ ከተማ” ብሎ የጠራት ያለ ምክንያት አልነበረም።—ማቴ. 5:35

10 በዘመናችንስ ይህ ማደሪያ ምን ያመለክታል? በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ አዲስ ብሔር ማለትም ‘የአምላክ እስራኤል’ ተወለደ። (ገላ. 6:16) የኢየሱስ ክርስቶስ ቅቡዓን ወንድሞችን ያቀፈው ይህ ብሔር ሥጋዊ እስራኤላውያን ማከናወን ያልቻሉትን ነገር ማለትም ለአምላክ ስም ምሥክር የመሆንን ኃላፊነት ተወጥቷል። (ኢሳ. 43:10፤ 1 ጴጥ. 2:9) ይሖዋ ለጥንቶቹ እስራኤላውያን “አምላካቸው እሆናለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ” በማለት ቃል ገብቶ ነበር፤ ለመንፈሳዊ እስራኤልም ተመሳሳይ ቃል ገብቷል። (2 ቆሮ. 6:16፤ ዘሌ. 26:12) በ1919 ይሖዋ ‘ለአምላክ እስራኤል’ ቀሪ አባላት ከእሱ ጋር ልዩ ዝምድና እንዲመሠርቱ አጋጣሚ ሰጥቷቸዋል፤ በዚያ ወቅት “አገር” እንዲወርሱ ማለትም መንፈሳዊ ገነትን ማጣጣም ወደሚችሉበት የመንፈሳዊ እንቅስቃሴ ግዛት እንዲገቡ አድርጓቸዋል። (ኢሳ. 66:8) ከ1930ዎቹ ወዲህ ባሉት ዓመታት ደግሞ በሚሊዮን የሚቆጠሩ “ሌሎች በጎች” ከጎናቸው ተሰልፈዋል። (ዮሐ. 10:16) በዛሬው ጊዜ የሚገኙት ክርስቲያኖች ያላቸው ደስታና መንፈሳዊ ብልጽግና የይሖዋን አገዛዝ ትክክለኛነት የሚያረጋግጥ አሳማኝ ማስረጃ ነው። (መዝሙር 91:1, 2ን አንብብ።) ይህ ሰይጣንን ምንኛ ያበሳጨው ይሆን!

11. ምንጊዜም ቢሆን የአምላክ ጠላቶች ዋነኛ ዓላማ ምንድን ነው?

11 በዚህ የመጨረሻ ዘመን ሰይጣን የእሱን ዓላማ የሚያራምዱ ሰዎች ቅቡዓን ቀሪዎችንና አጋሮቻቸው የሆኑትን ሌሎች በጎች እንዲቃወሟቸው አነሳስቷቸዋል። በምዕራብ አውሮፓ በናዚዎች፣ በምሥራቅ አውሮፓ ደግሞ በሶቭየት ኅብረት የኮሚኒስት አገዛዝ ሥር ቅቡዓን ቀሪዎችና ሌሎች በጎች ስደት ደርሶባቸዋል። በሌሎች በርካታ አገሮች ውስጥም ተመሳሳይ ስደት ያጋጠማቸው ሲሆን ወደፊት ደግሞ የማጎጉ ጎግ የመጨረሻ ጥቃት በሚሰነዝርበት ጊዜ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ያጋጥማቸዋል። ቀደም ባሉት ጊዜያት እንደሆነው ሁሉ ሰይጣን ይህንን ጥቃት በሚሰነዝርበት ወቅትም ተቃዋሚዎች የይሖዋን ሕዝቦች ሀብትና ንብረት ይቀራመቱ ይሆናል። ሆኖም ሰይጣን ምንጊዜም ቢሆን ዋነኛ ዓላማው እኛን በቡድን ደረጃ በማጥፋት አምላክ የሰጠን ስም ጨርሶ እንዳይታወስ ማድረግ ነው። ይሖዋ በሉዓላዊነቱ ላይ የሚነሳውን እንዲህ ያለውን ተቃውሞ እንዴት ይመለከተዋል? መዝሙራዊው ምን እንዳለ መለስ ብለን እንመልከት።

ይሖዋ ድል እንደሚያደርግ የሚያረጋግጥ ታሪክ

12-14. መዝሙራዊው፣ እስራኤላውያን በመጊዶ ከተማ አቅራቢያ የተቀዳጇቸው የትኞቹን ሁለት ድሎች ጠቅሷል?

12 መዝሙራዊው የእስራኤል ጠላት የሆኑ ብሔራት ያወጧቸውን እቅዶች ይሖዋ እንደሚያከሽፋቸው የነበረውን ጠንካራ እምነት ልብ በል። ይህ የአምላክ አገልጋይ፣ እስራኤላውያን በጥንቷ የመጊዶ ከተማ አቅራቢያ በጠላቶቻቸው ላይ የተቀዳጇቸውን ሁለት ወሳኝ ድሎች በመዝሙሩ ውስጥ ጠቅሷል። መጊዶ፣ በዚህ ስም በሚጠራ ሜዳ ላይ የምትገኝ ከተማ ነበረች። የመጊዶን ሜዳ አቋርጦ የሚያልፈው የቂሶን ወንዝ ዝናብ በማይኖርበት ወቅት የሚደርቅ ሲሆን ኃይለኛ ዝናብ ሲጥል ግን ወንዙ ሞልቶ ሜዳውን ያጥለቀልቀዋል። ይህ ወንዝ ‘የመጊዶ ውሆች’ ተብሎ የተጠራውም በዚህ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም።—መሳ. 4:13፤ 5:19

13 ከመጊዶ ሜዳ ባሻገር 15 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ የሞሬ ኰረብታ ይገኛል። በመስፍኑ ጌዴዎን ዘመን የምድያማውያን፣ የአማሌቃውያንና የምሥራቅ ሕዝቦች ጥምር ጦር ከእስራኤላውያን ጋር ለመዋጋት የተሰበሰበው በሞሬ ኰረብታ ላይ ነበር። (መሳ. 7:1, 12) የጌዴዎን ሠራዊት 300 ሰዎችን ብቻ የያዘ ቢሆንም በይሖዋ እርዳታ ከእነሱ በጣም የሚበልጠውን የጠላት ሠራዊት ድል ማድረግ ችሏል። እንዴት? ከጌዴዎን ጋር የነበሩት ሰዎች የአምላክን መመሪያ በመከተል በውስጡ ችቦ ያለበት ማሰሮ ይዘው የጠላትን የጦር ሠፈር በሌሊት ከበቡ። ጌዴዎን ምልክት ሲሰጣቸው አብረውት የነበሩት ሰዎች ማሰሮዎቻቸውን ሰበሯቸው፤ በዚህ ጊዜ የያዟቸው ችቦዎች የታዩ ሲሆን ሰዎቹም ቀንደ መለከቶቻቸውን በመንፋት ‘የይሖዋና የጌዴዎን ሰይፍ’ በማለት ጮኹ። ጠላቶቻቸው ግራ ስለተጋቡ እርስ በርሳቸው ተገዳደሉ፤ በሕይወት የተረፉት ደግሞ ዮርዳኖስን ተሻግረው ሸሹ። በዚህ መሃል ሌሎች እስራኤላውያንም ጠላቶቻቸውን ማሳደዱን ተያያዙት። በዚህ ውጊያ በአጠቃላይ 120,000 የጠላት ወታደሮች አለቁ።—መሳ. 7:19-25፤ 8:10

14 ከመጊዶ ሜዳ ባሻገር ከሚገኘው ከሞሬ ኰረብታ ማዶ ስድስት ኪሎ ሜትር ርቀት ገደማ ላይ ደግሞ የታቦር ተራራ ይገኛል። መስፍኑ ባርቅ 10,000 እስራኤላውያን ተዋጊዎችን በመሰብሰብ ከኢያቢስ ሠራዊት ጋር ውጊያ የገጠመው በዚህ ቦታ ነበር፤ ኢያቢስ በከነዓን የምትገኘው የሐጾር ንጉሥ ሲሆን የሠራዊቱ አዛዥ ደግሞ ሲሣራ ነበር። ይህ የከነዓናውያን ሠራዊት ረጅም ስለት የተገጠመላቸው 900 የጦር ሠረገሎች ነበሩት። የሲሣራ ሠራዊት፣ የረባ የጦር ትጥቅ ያልነበረው የእስራኤል ጦር በታቦር ተራራ ላይ እንደተሰበሰበ ሲያውቅ ወደ ሜዳው ወረደ። ከዚያም ይሖዋ “ሲሣራን ሰረገሎቹንም ሁሉ ሠራዊቱንም ሁሉ ከባርቅ ፊት . . . አስደነገጣቸው።” [የ1954 ትርጉም] ይህ የሆነው ድንገት በጣለው ዝናብ የተነሳ የቂሶን ወንዝ ሞልቶ አካባቢውን ስላጥለቀለቀው ሠረገሎቹ በጭቃ በመያዛቸው ሳይሆን አይቀርም። በዚህ ወቅት እስራኤላውያን ሠራዊቱን በሙሉ ፈጇቸው።—መሳ. 4:13-16፤ 5:19-21

15. (ሀ) መዝሙራዊው፣ ይሖዋ ምን እንዲያደርግ ጸልዮአል? (ለ) የአምላክ የመጨረሻ ጦርነት የሚጠራበት ስም ምን ያስታውሰናል?

15 መዝሙራዊው በዘመኑ እስራኤልን ለማጥፋት ይዝቱ በነበሩት ብሔራት ላይ ይሖዋ ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስድ ልመና አቅርቧል። እንዲህ ሲል ጸልዮአል፦ “በምድያም ላይ እንዳደረግኸው አድርግባቸው፤ በቂሶንም ወንዝ በሲሣራና በኢያቢስ ላይ ያደረስኸው ይድረስባቸው። እነርሱም በዐይንዶር ጠፉ፤ እንደ ምድርም ጕድፍ ሆኑ።” (መዝ. 83:9, 10) አምላክ በሰይጣን ዓለም ላይ የሚያካሂደው የመጨረሻ ጦርነት አርማጌዶን (“የመጊዶ ተራራ” ማለት ነው) መባሉ ትኩረት የሚስብ ነው። ይህ ስም በመጊዶ አቅራቢያ የተካሄዱትን ወሳኝ ውጊያዎች ያስታውሰናል። ይሖዋ በጥንት ጊዜ በተካሄዱት በእነዚያ ጦርነቶች የተቀዳጀው ድል በአርማጌዶንም እንደሚያሸንፍ እርግጠኞች እንድንሆን ያስችለናል።—ራእይ 16:13-16

የይሖዋ ሉዓላዊነት እንዲረጋገጥ እንጸልይ

16. በዛሬው ጊዜ የተቃዋሚዎች ‘ፊት በዕፍረት የተሞላው’ እንዴት ነው?

16 በዚህ ‘የመጨረሻ ዘመን’ ይሖዋ ሕዝቦቹን ለማጥፋት የተደረጉ ጥረቶች በሙሉ እንዲከሽፉ አድርጓል። (2 ጢሞ. 3:1) በዚህም የተነሳ ተቃዋሚዎች አፍረዋል። መዝሙራዊው በመዝሙር 83:16 ላይ “እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ሆይ፤ ስምህን ይሹ ዘንድ፣ ፊታቸውን በዕፍረት ሙላው” ሲል ይህ እንደሚሆን አስቀድሞ መናገሩ ነበር። ተቃዋሚዎች በተለያዩ አገሮች ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮችን ዝም ለማሰኘት ያደረጉት ጥረት ከንቱ ሆኗል። በእነዚህ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ የእውነተኛው አምላክ አገልጋዮች ከአቋማቸው ፍንክች አለማለታቸውና በጽናት መቀጠላቸው ቅን ልብ ላላቸው ሰዎች ምሥክርነት ከመስጠቱም በላይ ብዙዎች የይሖዋን ‘ስም እንዲሹ’ አድርጓቸዋል። በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ከፍተኛ ስደት ይደርስ በነበረባቸው ብዙ አገሮች ውስጥ በአሁኑ ጊዜ በአሥር ሺዎች እንዲያውም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ይሖዋን በደስታ እያወደሱት ነው። ይህ ለይሖዋ እንዴት ያለ ታላቅ ድል ነው! ጠላቶቹንስ ምንኛ የሚያሳፍር ነው!—ኤርምያስ 1:19ን አንብብ።

17. ለተቃዋሚዎች የተከፈተው የትኛው አጋጣሚ በቅርቡ ያበቃል? የትኛውን ጸሎት እናስታውሳለን?

17 እርግጥ ነው፣ አሁንም ተቃዋሚዎች የይሖዋ ምሥክሮችን ማሳደዳቸው እንዳላቆሙ እናውቃለን። እኛም ለተቃዋሚዎቻችንም ጭምር ምሥራቹን መስበካችንን አናቋርጥም። (ማቴ. 24:14, 21) ሆኖም እነዚህ ተቃዋሚዎች ንስሐ ገብተው መዳን እንዲያገኙ የተከፈተላቸው አጋጣሚ በቅርቡ ያበቃል። ከሰው ልጆች መዳን ይበልጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር የይሖዋ ስም መቀደስ ነው። (ሕዝቅኤል 38:23[NW] አንብብ።) * አስቀድሞ በተነገረው መሠረት ብሔራት በሙሉ የአምላክን ሕዝቦች ለማጥፋት ሲሰባሰቡ መዝሙራዊው “ለዘላለም ይፈሩ፤ ይታወኩም፤ በውርደትም ይጥፉ” በማለት ያቀረበውን ጸሎት እናስታውሳለን።—መዝ. 83:17

18, 19. (ሀ) የይሖዋን ሉዓላዊነት በመቃወም የሚቀጥሉ ሁሉ ምን ይጠብቃቸዋል? (ለ) ይሖዋ ሉዓላዊነቱን ለመጨረሻ ጊዜ የሚያረጋግጥበት ወቅት መቅረቡ ለአንተ ምን ትርጉም አለው?

18 የይሖዋን ሉዓላዊነት ለመቃወም ቆርጠው የተነሱ ሁሉ ኃፍረት ተከናንበው ይጠፋሉ። የአምላክ ቃል፣ ‘ለወንጌል ባለመታዘዛቸው’ የተነሳ በአርማጌዶን እርምጃ የሚወሰድባቸው ሰዎች ‘ለዘላለም እንደሚጠፉ’ ይናገራል። (2 ተሰ. 1:7-9) እነዚህ ሰዎች መጥፋታቸው እንዲሁም ይሖዋን በእውነት የሚያመልኩ ሰዎች ከጥፋቱ መዳናቸው ብቸኛው እውነተኛ አምላክ ይሖዋ መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ይሆናል። ይህ ታላቅ ድል በአዲሱ ዓለም ውስጥ ለዘላለም ሲታወስ ይኖራል። “ጻድቃንና ኀጥአን ከሙታን [ሲነሡ]” ስለ ይሖዋ ታላቅ ሥራ ይማራሉ። (ሥራ 24:15) እነዚህ ሰዎች፣ ለይሖዋ ሉዓላዊነት መገዛት የጥበብ አካሄድ መሆኑን የሚያሳይ አሳማኝ ማስረጃ በአዲሱ ዓለም ውስጥ ይመለከታሉ። ገሮችም ይሖዋ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ መሆኑን አምነው ለመቀበል ጊዜ አይፈጅባቸውም።

19 አፍቃሪ የሆነው የሰማዩ አባታችን፣ ታማኝ ለሆኑ አምላኪዎቹ እንዴት ያለ አስደናቂ ተስፋ አዘጋጅቶላቸዋል! መዝሙራዊው እንዲህ ሲል ጸልዮ ነበር፦ “[ጠላቶችህ] በውርደት ይጥፉ። ይህም ሰዎች ሁሉ ስምህ ይሖዋ የሆነው አንተ፣ በምድር ሁሉ ላይ አንተ ብቻ ልዑል እንደሆንክ ያውቁ ዘንድ ነው።” አንተስ መዝሙራዊው ላቀረበው ለዚህ ጸሎት ይሖዋ በቅርቡ የመጨረሻ መልስ እንዲሰጥ ለመጸለይ አትገፋፋም?—መዝ. 83:17, 18 NW

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.2 ይህንን ርዕስ ማጥናት ከመጀመርህ በፊት የመዝሙር 83⁠ን ይዘት ለማወቅ እንድትችል መዝሙሩን ብታነበው ጠቃሚ ይሆናል።

^ አን.17 ሕዝቅኤል 38:23 (NW) “ራሴን ገናና አደርጋለሁ እንዲሁም ራሴን አስቀድሳለሁ፤ በብዙ ብሔራትም ፊት ራሴን አሳውቃለሁ፤ እኔም ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ።”

ልታብራራ ትችላለህ?

መዝሙር 83 በተጻፈበት ወቅት እስራኤላውያን ምን ዓይነት ሁኔታ አጋጥሟቸው ነበር?

የመዝሙር 83 ጸሐፊ በዋነኝነት ያሳሰበው ነገር ምን ነበር?

• በዛሬው ጊዜ የሰይጣን የጥቃት ዒላማ የሆኑት እነማን ናቸው?

• ይሖዋ በመዝሙር 83:18 ላይ ለቀረበው ጸሎት የመጨረሻ ምላሽ የሚሰጠው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ካርታ/ሥዕል]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

በጥንቷ መጊዶ አቅራቢያ የተካሄዱት ውጊያዎች ወደፊት ከሚጠብቀን ሁኔታ ጋር ምን ተዛማጅነት አላቸው?

የቂሶን ወንዝ

አሪሶት

የቀርሜሎስ ተራራ

የኢይዝራኤል ሸለቆ

መጊዶ

ታዕናክ

የጊልቦዓ ተራራ

የሐሮድ ምንጭ

ሞሬ

ዐይንዶር

የታቦር ተራራ

የገሊላ ባሕር

የዮርዳኖስ ወንዝ

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ መዝሙራዊ ለይሖዋ ልባዊ ጸሎት እንዲያቀርብ ያነሳሳው ምንድን ነው?