የምትመርጠው ሃይማኖት ለውጥ ያመጣል?
የምትመርጠው ሃይማኖት ለውጥ ያመጣል?
አብዛኞቻችን ገበያ ስንወጣ የምንፈልገውን ዕቃ መግዛት እንድንችል ብዙ ምርጫ ቢኖረን ደስ ይለናል። ገበያ ላይ የተለያዩ ፍራፍሬዎችና አትክልቶች ካሉ የምንወዳቸውንና ለቤተሰባችን ጠቃሚ የሆኑትን መምረጥ እንችላለን። በተመሳሳይም አንድ የልብስ ሱቅ የተለያየ ዓይነትና ቀለም ያላቸውን ልብሶች በተመጣጣኝ ዋጋ ካቀረበ ለእኛ የሚስማማንን እንመርጣለን። በሕይወታችን ውስጥ የምናደርጋቸው አንዳንዶቹ ምርጫዎች የግል ፍላጎታችንን ከማንጸባረቅ ያለፈ ፋይዳ የላቸውም። ሌሎች ምርጫዎቻችን ግን በደኅንነታችን ላይ ተጽዕኖ ያደርጋሉ፤ ለጤንነታችን የሚጠቅም ምግብ ወይም ጥሩ ጓደኞች መምረጥን እንደ ምሳሌ መውሰድ እንችላለን። ታዲያ የሃይማኖት ምርጫችንን በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? አምልኳችን የግል ምርጫችንን የሚያንጸባርቅ ብቻ ሊሆን ይገባል? ወይስ በደኅንነታችን ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ይኖራል?
በዛሬው ጊዜ ብዙ ሃይማኖቶች አሉ። በርካታ አገሮች የሃይማኖት ነጻነት የሚሰጡ በመሆኑ ሰዎች የወላጆቻቸውን ሃይማኖት መተው እንደሚችሉ ይሰማቸዋል። በዩናይትድ ስቴትስ የተካሄደ ጥናት እንዳመለከተው 80 በመቶ የሚሆኑት አሜሪካውያን “የተለያዩ ሃይማኖቶች መዳን ሊያስገኙ እንደሚችሉ ያምናሉ።” ይኸው ጥናት እንደሚያሳየው “አስተያየት ከሰጡት ሰዎች መካከል ከአምስቱ አንዱ ትልቅ ሰው ከሆነ በኋላ ሃይማኖቱን እንደለወጠ ተናግሯል።” በብራዚል የተካሄደ ጥናት እንዳመለከተው ከአጠቃላይ የአገሪቱ ዜጎች ውስጥ ወደ 25 በመቶ ገደማ የሚሆኑት ብራዚላውያን ሃይማኖታቸውን ለውጠዋል።
ቀደም ባሉት ዓመታት ሰዎች ሃይማኖቶች በሚለያዩበት መሠረተ ትምህርት ላይ በጋለ ስሜት ይከራከሩ ነበር። አሁን ግን ‘የትኛውንም ሃይማኖት ብትመርጥ ለውጥ አያመጣም’ የሚለው አመለካከት በጣም የተለመደ ሆኗል። ሆኖም ይህ አመለካከት እውነት ነው? የምትመርጠው ሃይማኖት በአንተ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ይኖራል?
አስተዋይ የሆኑ ሸማቾች የሚገዟቸው ዕቃዎች የት እንደተመረቱ እንደሚጠይቁ ሁሉ አንተም ‘እነዚህ ሁሉ ሃይማኖቶች እንዴትና ለምን ተጀመሩ?’ ብለህ መጠየቅህ የጥበብ እርምጃ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ መልሱን ይሰጠናል።
ሃይማኖቶች የሚጀመሩት እንዴት ነው?
ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ ከአንድ ሺህ ዓመት ገደማ በፊት የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ኢዮርብዓም አዲስ ሃይማኖት አቋቁሞ ነበር። ኢዮርብዓም ከእስራኤል የተገነጠለው የሰሜናዊው መንግሥት የመጀመሪያው ንጉሥ ነበር። ይህ ንጉሥ ዓላማውን በሚያሳካ መንገድ ሕዝቡን ለመምራት ስለፈለገ አስቸጋሪ ሥራ ገጥሞት ነበር። ዘገባው “ንጉሡ ከመከረበት በኋላ ሁለት የወርቅ ጥጆች አሠርቶ ሕዝቡን፣ ‘እስራኤል ሆይ፤ ወደ ኢየሩሳሌም እስካሁን የወጣኸው ይበቃል፤ . . . አማልክትህ እነዚህ ናቸው’ አለ” በማለት ይናገራል። (1 ነገሥት 12:28) በግልጽ ለመመልከት እንደሚቻለው ንጉሡ፣ ሕዝቡ ለአምልኮ ወደ ኢየሩሳሌም መሄዳቸውን ትተው ለእርሱ ታማኝ እንዲሆኑ ለማድረግ በሃይማኖት ተጠቅሟል። ኢዮርብዓም የመሠረተው ሃይማኖት ለበርካታ መቶ ዓመታት የዘለቀ ሲሆን ከጊዜ በኋላ አምላክ ከሃዲ የሆነውን የእስራኤል ብሔር በቀጣበት ወቅት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸውን እንዲያጡ ወይም በግዞት እንዲወሰዱ ምክንያት የሆነውም ይኸው ሃይማኖት ነበር። ኢዮርብዓም ሃይማኖት ያቋቋመው ፖለቲካዊ ጥቅም ለማግኘት ነበር። በዛሬው ጊዜ ያሉ አንዳንድ የመንግሥት ሃይማኖቶችም በተመሳሳይ የተመሠረቱት ፖለቲካዊ ኃይልን ለማጠናከር ሲባል ነው።
ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ሰዎች አዲስ ሃይማኖት ለማቋቋም የሚነሳሱበትን ሌላ ምክንያት እንዲህ በማለት ገልጿል:- “እኔ ከሄድሁ በኋላ፣ ነጣቂ ተኩላዎች መጥተው በመካከላችሁ ሰርገው እንደሚገቡና ለመንጋውም እንደማይራሩ ዐውቃለሁ። ከእናንተው መካከል እንኳ የራሳቸውን ደቀ መዛሙርት ለማፍራት እውነትን የሚያጣምሙ ይነሣሉ።” (የሐዋርያት ሥራ 20:29, 30) አብዛኛውን ጊዜ እብሪተኛ መሪዎች የሰዎችን ትኩረት ወደ ራሳቸው ለመሳብ ሲሉ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ ይጀምራሉ። ክርስቲያን ነን በማለት በሐሰት የሚናገሩ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት በተለያዩ ቡድኖች ተከፋፍለዋል።
ሃይማኖቶች ማስደሰት የሚፈልጉት ማንን ነው?
አንዳንዶች የብዙኃኑን ጥያቄ ለማስተናገድ ሲሉ አዲስ ሃይማኖት ያቋቁማሉ። ለአብነት ያህል፣ ኤኮኖሚስት የተባለው መጽሔት በዩናይትድ ስቴትስ ስለሚገኙ በርካታ አባላት እንዳሏቸው የሚነገርላቸው አብያተ ክርስቲያናት አንድ ዘገባ አውጥቶ ነበር። መጽሔቱ የእነዚህ አብያተ ክርስቲያናት አባላት እየተበራከቱ የሄዱት “ስኬታማ የሆኑ የንግድ ተቋሟት በሙሉ ተግባራዊ የሚያደርጉትን ‘ለደንበኛ ፍላጎት ቅድሚያ መስጠት’ የሚለውን ደንብ ስለሚከተሉ” እንደሆነ ገልጿል። ከእነዚህ አብያተ ክርስቲያናት አንዳንዶቹ “በቪዲዮ፣ በድራማና በዘመናዊ ሙዚቃ የታጀቡ የሚያዝናኑ መንፈሳዊ ስብከቶችን” ያቀርባሉ። በእነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የሚገኙ የተወሰኑ የሃይማኖት መሪዎች፣ አባላቶቻቸውን “ሀብታምና ጤነኛ እንዲሆኑ እንዲሁም ዘና ያለ ሕይወት እንዲመሩ” እንደሚያስተምሯቸው ይናገራሉ። እንደነዚህ ያሉት አብያተ ክርስቲያናት ወደ መዝናኛው ዓለም በመግባታቸው ወይም “ራስ አገዝ የሆኑ ንግዶችን” በማቋቋማቸው ቢነቀፉም ይኸው መጽሔት ቤተ ክርስቲያናቱ “የአባላቶቻቸውን ፍላጎት ከማሟላት ውጪ ያደረጉት ነገር የለም” በማለት ዘግቧል። በመጨረሻም “በሃይማኖትና በንግዱ ዓለም መካከል የተካሄደው ውሕደት በጣም ስኬታማ ሆኗል” በማለት ደምድሟል።
ሌሎች ሃይማኖቶች የንግዱን ዓለም ዝንባሌ የዚህን ያህል በግልጽ ባያንጸባርቁም እንኳ ‘የአባላቶቻቸውን ፍላጎት ለማሟላት’ የሚጥሩ አብያተ ክርስቲያናት ጳውሎስ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ እንድናስታውስ ያደርጉናል። ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ሰዎች ትክክለኛ የሆነውን ትምህርት የማይቀበሉበት ጊዜ ይመጣል፤ ከዚህ ይልቅ ለገዛ ምኞቶቻቸው የሚስማማውን፣ የሚያሳክክ ጆሮአቸው ሊሰማ የሚፈልገውን እንዲነግሯቸው በዙሪያቸው ብዙ አስተማሪዎችን ይሰበስባሉ። እውነትን ከመስማት ጆሮአቸውን ይመልሳሉ፤ ወደ ተረትም ዘወር ይላሉ።”—2 ጢሞቴዎስ 4:3, 4
በርካታ ሃይማኖቶች የተቋቋሙት ፖለቲካዊ ሥልጣንና ክብር እንዲሁም በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት እንጂ አምላክን ለማስደሰት ባለመሆኑ ሃይማኖቶች በሙስና፣ በጦርነት ወይም በሽብርተኝነት መካፈላቸው ብሎም በልጆች ላይ በደል መፈጸማቸው ምንም አያስገርምም። አብዛኛውን ጊዜ ሃይማኖት ማታለያ ነው። አንተስ እንዳትታለል ምን ማድረግ ትችላለህ?
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
በርካታ ሃይማኖቶች የተቋቋሙት ፖለቲካዊ ሥልጣንና ክብር እንዲሁም በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት እንጂ አምላክን ለማስደሰት አይደለም