የገና በዓል መንፈስ ዓመቱን ሙሉ ሊዘልቅ ይችላል?
የገና በዓል መንፈስ ዓመቱን ሙሉ ሊዘልቅ ይችላል?
‘ክብር ለአምላክ በአርያም፣ ሰላምም እርሱ ለሚወዳቸው ሰዎች በምድር ይሁን!’—ሉቃስ 2:14
የአምላክ መላእክት፣ ሌሊት መንጎቻቸውን ይጠብቁ ለነበሩ እረኞች የኢየሱስን መወለድ ለማብሰር የተናገሯቸውን እነዚህን ቃላት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ያውቋቸዋል። አብያተ ክርስቲያናት ኢየሱስ ተወልዶበታል የሚሉት ቀን ሲቃረብ በርካታ ስመ ክርስቲያኖች ባሕርያቸውን ለማሻሻል ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። በገና በዓል ሰሞን እንደ ደስታ፣ ሰላም፣ ደግነትና ለሌሎች መልካም መመኘት ላሉት መልአኩ ለጠቀሳቸው ባሕርያት የሚሰጠው ከፍተኛ ትኩረት የገና በዓል መንፈስ በመባል ይታወቃል።
እንዲህ ዓይነቶቹ ግሩም ባሕርያት የገናን በዓል ከሃይማኖት ጋር አያይዘው የማይመለከቱትን ሰዎች እንኳ ይማርካሉ። በበዓሉ ሰሞን የሚታየውን ወዳጃዊ መንፈስም ያደንቁታል። በገና በዓል ሰሞን ተማሪዎችም ሆኑ ሠራተኞች እረፍት የሚሰጣቸው ከሆነ ለመዝናናት እንዲሁም ከቤተሰቦቻቸውና ከጓደኞቻቸው ጋር ጊዜ ለማሳለፍ ወይም ደግሞ የሚያስደስታቸውን ነገር ለማድረግ አጋጣሚ ያገኛሉ። እርግጥ ነው፣ በገና በዓል ሰሞን በዋነኝነት ሊከበር የሚገባው ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ የሚሰማቸው በርካታ ቅን ሰዎች አሉ።
የገና በዓል ምንም ያህል ትልቅ ቦታ ቢሰጠውም ብዙዎች በዚህ በዓል ሰሞን የሚታዩት መልካም ባሕርያት ዘላቂ እንዳልሆኑ ይሰማቸዋል። ሰዎች ብዙም ሳይቆዩ የቀድሞ ባሕርያቸውን ማንጸባረቅ ይጀምራሉ። በካናዳ ሮያል ባንክ የተዘጋጀው “የገና በዓል መንፈስ” የተባለው ጽሑፍ እንዲህ ይላል:- “‘ክርስቲያን የሆኑ’ ብዙ ሰዎች ለጎረቤቶቻቸው ደግነት በማሳየትና ለሌሎች መልካም በመመኘት እንደ ስማቸው የሚኖሩት በዓመት ውስጥ ለጥቂት ሳምንታት ብቻ ነው። ከዘመን መለወጫ በዓል በኋላ ግን ለሌሎች ደኅንነት ደንታ ቢስ በመሆን የራሳቸውን ጥቅም ማሳደድ ይቀጥላሉ።” የገና በዓል መንፈስ “መሠረታዊ ችግር” ሰዎች “ዓመቱን ሙሉ” ይህን መንፈስ ይዘው አለመቀጠላቸው መሆኑን ይኸው ጽሑፍ አክሎ ተናግሯል።
ከላይ ባለው ሐሳብ ተስማማህም አልተስማማህም፣ ይህ አባባል አንድ አስፈላጊ ጥያቄ ያስነሳል። ሰዎች እርስ በርስ ባላቸው ግንኙነት ረገድ ዘላቂ በሆነ መልኩ የወዳጅነት መንፈስና ልግስና ማሳየት ይችሉ ይሆን? ኢየሱስ በተወለደበት ምሽት፣ የአምላክ መላእክት የተናገሩት መልእክት በእርግጥ ይፈጸማል ብሎ ተስፋ ማድረግ ይቻላል? ወይስ እውነተኛ ሰላም የማግኘት ተስፋ እንዲያው ሕልም ብቻ ነው?