የአንባቢያን ጥያቄዎች
የአንባቢያን ጥያቄዎች
አንድ ክርስቲያን መኪና በሚያሽከረክርበት ጊዜ አደጋ አድርሶ የሰው ሕይወት ቢጠፋ ጉባኤው ምን የማድረግ ኃላፊነት አለበት?
ጉባኤው አደጋውን ያደረሰው ሰው በደም ዕዳ ተጠያቂ መሆን አለመሆኑን የማጣራት ኃላፊነት አለበት። ይህ የሚደረግበት አንዱ ምክንያት ጉባኤው በቡድን ደረጃ በደም ዕዳ ተጠያቂ እንዳይሆን ሲባል ነው። (ዘዳግም 21:1-9፤ 22:8) ግለሰቡ ይህን የመሰለውን ከባድ አደጋ ያደረሰው ግድ የለሽ በመሆኑ ወይም ደግሞ መንግሥት የሰዎችን ደኅንነት ለመጠበቅ ያወጣውን ደንብ አሊያም የትራፊክን ሕግ ሆን ብሎ በመጣሱ ምክንያት ከሆነ በደም ዕዳ ይጠየቃል። (ማርቆስ 12:14) ሆኖም ሊታሰብባቸው የሚገቡ ሌሎች ነጥቦችም አሉ።
በእስራኤል ውስጥ ወደነበሩት የመማጸኛ ከተሞች የሸሸ አንድ ነፍሰ ገዳይ ለፍርድ መቅረብ ነበረበት። ይህ ሰው ነፍስ ያጠፋው ሆን ብሎ ካልሆነ ተበቃዮቹ እንዳይገድሉት በከተማው ውስጥ እንዲኖር ይፈቀድለት ነበር። (ዘኍልቍ 35:6-25) በተመሳሳይም አንድ ክርስቲያን ባደረሰው አደጋ ምክንያት ሕይወት በሚጠፋበት ጊዜ ሽማግሌዎች ይህ ክርስቲያን በደም ዕዳ ተጠያቂ መሆን አለመሆኑን ለመወሰን ጉዳዩን ማጣራት ይኖርባቸዋል። ጉዳዩ የሚመለከተው የመንግሥት አካልም ሆነ ፍርድ ቤት ስለ ሁኔታው ያላቸው አስተያየትና የሚያስተላልፉት ብይን ጉባኤው በሚወስደው እርምጃ ላይ ምንም ዓይነት ተጽዕኖ ሊኖረው አይገባም።
ለምሳሌ ያህል፣ ጉዳዩን የተመለከተው ፍርድ ቤት ድርጊቱን የፈጸመው ግለሰብ አንድ ዓይነት የትራፊክ ሕግ መጣሱን በመጥቀስ ጥፋተኛ መሆኑን የሚገልጽ ብይን ያስተላልፍ ይሆናል፤ ይሁንና ጉዳዩን የሚያጣሩት ሽማግሌዎች አደጋው የተከሰተው ከአሽከርካሪው አቅም በላይ በሆነ ምክንያት እንደሆነ በማመን ይህ ሰው ከደም ዕዳ ነጻ እንደሆነ ሊወስኑ ይችላሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ፍርድ ቤቱ በነጻ ያሰናበተውን አንድ ግለሰብ ሽማግሌዎቹ በደም ዕዳ ተጠያቂ እንደሆነ ይወስኑ ይሆናል።
ጉዳዩን የሚያጣሩት ሽማግሌዎች የሚያስተላልፉት ውሳኔ በቅዱስ ጽሑፉና በተጨባጭ ማስረጃዎች ላይ የተመሠረተ መሆን ይኖርበታል። ይህም የአሽከርካሪውን የእምነት ክህደት ቃል እንዲሁም የሁለት ወይም የሦስት ታማኝ የዓይን ምሥክሮችን የምሥክርነት ቃል ይጨምራል። (ዘዳግም 17:6፤ ማቴዎስ 18:15, 16) አደጋውን ያደረሰው ክርስቲያን በደም ዕዳ ተጠያቂ መሆኑ ከተረጋገጠ የፍርድ ኮሚቴ ይቋቋማል። የፍርድ ኮሚቴው በደም ዕዳ ተጠያቂ የሆነው ሰው ንስሐ እንደገባ ካወቀ አስፈላጊው ቅዱስ ጽሑፋዊ ተግሣጽ እንዲሰጠው ያደርጋል፤ ግለሰቡ በጉባኤ ውስጥ ያሉትን ኃላፊነቶች ለመሸከም ብቁ አይሆንም። ሽማግሌ ወይም አገልጋይ ሆኖ መቀጠል አይችልም። ከዚህም ባሻገር ሌሎች እገዳዎች ሊደረጉበት ይችላል። በተጨማሪም በግድ የለሽነት፣ በቸልተኝነትና በጥንቃቄ ጉድለት የተነሳ ላደረሰው አደጋና ላጠፋው ሕይወት በይሖዋ ፊት በኃላፊነት ይጠየቃል።—ገላትያ 6:5, 7
በምሳሌ ለማስረዳት ያህል:- በአደጋው ወቅት የአየሩ ሁኔታ ጥሩ ካልነበረ አሽከርካሪው ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ነበረበት። እንቅልፍ እንቅልፍ እያለው ከነበረም መኪናውን አቁሞ እንቅልፉ እስኪያልፍለት ትንሽ ማሸለብ አሊያም ሌላ ሰው እንዲያሽከረክር ማድረግ ነበረበት።
ይህ ሰው ከተወሰነው የፍጥነት ገደብ በላይ እየበረረ ከነበረስ? ከተወሰነው የፍጥነት መጠን በላይ የሚያሽከረክር ማንኛውም ክርስቲያን “የቄሣርን ለቄሣር” የሚለውን ትእዛዝ ይተላለፋል። ከዚህም በተጨማሪ እንዲህ ማድረጉ የከፋ ጉዳት ሊያስከትል ስለሚችል ለሕይወት አክብሮት ሳያሳይ ቀርቷል። (ማቴዎስ 22:21) ይህን በተመለከተ ሌላም ተጨማሪ ጉዳይ እንመልከት። የቄሳርን የትራፊክ ሕግ ችላ የሚል አሊያም ሆን ብሎ የማይታዘዝ አንድ ሽማግሌ ለመንጋው ምን ዓይነት ምሳሌ ይሆናል?—1 ጴጥሮስ 5:3
ክርስቲያኖች፣ ከተወሰነው የፍጥነት መጠን በላይ ካላሽከረከሩ በቀር በቀጠሯቸው ቦታ እንደማይደርሱ እያወቁ በቦታው እንዲገኙ በሌሎች ወንድሞቻቸው ላይ ግፊት ማድረግ አይገባቸውም። አብዛኛውን ጊዜ ቀደም ብሎ መነሳት ወይም ለጉዞ የሚሆን በቂ ጊዜ ለማግኘት በማሰብ ቀጠሮውን ማራዘም ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል። እንዲህ መደረጉ አንድ ክርስቲያን ከሚገባው የፍጥነት መጠን በላይ ለማሽከርከር እንዳይፈተን ከዚህ ይልቅ ‘በሥልጣን ያሉት ሹማምንት’ ያወጧቸውን የትራፊክ ሕጎች መታዘዝ እንዲችል ያደርጋል። (ሮሜ 13:1, 5) ይህም አሽከርካሪው ለከባድ አደጋ እንዳይጋለጥና በዚህም ሳቢያ በደም ዕዳ ተጠያቂ እንዳይሆን ይጠብቀዋል። በተጨማሪም ለሌሎች መልካም አርዓያ እንዲሆንና በጎ ኅሊናውን ጠብቆ እንዲኖር ይረዳዋል።—1 ጴጥሮስ 3:16