የአንባቢያን ጥያቄዎች
የአንባቢያን ጥያቄዎች
በምሳሌ 8:22-31 ላይ ስለ ጥበብ የተሰጠው መግለጫ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ከመወለዱ በፊት ያሳለፈውን ሕይወት እንደሚያመለክት እንዴት ማወቅ እንችላለን?
በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የምሳሌ መጽሐፍ ጥበብን አስመልክቶ የሰጠው መግለጫ እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔር ከቀድሞ ሥራዎቹ በፊት፣ የተግባሮቹ መጀመሪያ አድርጎ አመጣኝ። . . . ተራሮች ገና ሳይመሠረቱ፣ ከኰረብቶችም በፊት ተወለድሁ፤ . . . ሰማያትን በዘረጋ ጊዜ፣ . . . እኔ እዚያ ነበርሁ፤ . . . በዚያን ጊዜ ከጐኑ ዋና ባለሙያ ነበርሁ። ሁልጊዜ በፊቱ ሐሤት እያደረግሁ፣ ዕለት ተዕለት በደስታ እሞላ ነበር፤ . . . በሰው ልጆች ደስ እሰኝ ነበር።”
ይህ ጥቅስ ስለ መለኮታዊው ጥበብ ወይም እንዲያው በጥቅሉ ስለ ጥበብ እየተናገረ ሊሆን አይችልም። ለምን? ምክንያቱም እዚህ ላይ የተጠቀሰው ጥበብ የይሖዋ ተግባሮች መጀመሪያ ‘መደረጉ’ ማለትም የተፈጠረ መሆኑ ተገልጿል። ይሖዋ አምላክ መጀመሪያ የሌለው ከመሆኑም በላይ ሁልጊዜ ጥበበኛ ነው። (መዝሙር 90:1, 2) የይሖዋ ጥበብ መጀመሪያ የለውም፤ የተፈጠረ ወይም ‘የተወለደ’ ነገር አይደለም። በተጨማሪም ይህ ጥበብ ረቂቅ የሆነውን ባሕርይ አያመለክትም የምንለው እንደ ሰው እየተናገረና የተለያዩ ተግባራትን እየፈጸመ እንዳለ ተደርጎ በመገለጹ ነው።—ምሳሌ 8:1
ጥበብ፣ ፈጣሪ በሆነው በይሖዋ ዘንድ ከጥንት ጀምሮ “ዋና ባለሙያ” እንደነበር የምሳሌ መጽሐፍ ይናገራል። ይህ ደግሞ ኢየሱስን እንደሚያመለክት ምንም ጥርጥር የለውም። ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ ከረጅም ጊዜ በፊት ከይሖዋ ጋር ተቀራርቦ ይሠራ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር እንዲህ ይላል:- “እርሱ ከሁሉ በፊት ነው፤ ሁሉም ነገር በአንድ ላይ ተያይዞ የጸናው በእርሱ ነው።”—ቈላስይስ 1:17፤ ራእይ 3:14
የአምላክ ልጅ፣ ጥበብ የተንጸባረቀባቸውን የይሖዋን ዓላማዎችና ትእዛዛት ግልጽ በማድረጉ በጥበብ መመሰሉ ተገቢ ነው። ኢየሱስ ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት የአምላክ ቃል ወይም ቃል አቀባይ ነበር። (ዮሐንስ 1:1) በተጨማሪም ክርስቶስ “የእግዚአብሔር ኀይል፣ የእግዚአብሔርም ጥበብ” እንደሆነ ተገልጿል። (1 ቆሮንቶስ 1:24, 30) ለሰው ልጆች ካለው ፍቅር የተነሳ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ለመስጠት የተገፋፋውን የአምላክ ልጅ ግሩም አድርጎ የሚገልጽ አባባል ነው!—ዮሐንስ 3:16
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
‘ከተራሮች በፊት ተወለድሁ’