“ቀጥል! ቀጥል!”
“ቀጥል! ቀጥል!”
ኒዝሎብናየ፣ ሩስያ በሚገኝ አንድ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ በሥነ ጽሑፍ ትምህርት ክፍለ ጊዜ ሚካኤል ቡልጋኮፍ በተባለው ሩሲያዊ ደራሲ ሥራዎች ላይ ውይይት ይደረግ ነበር። ከዚህ ደራሲ ሥራዎች መካከል ኢየሱስ ክርስቶስን የሚያቃልል ሰይጣንን ደግሞ እንደ ጀግና አድርጎ የሚገልጽ አንድ ጽሑፍ ይገኝበታል። ከውይይቱ በኋላ አስተማሪዋ ተማሪዎቹ በዚህ ሥራ ላይ ተንተርሰው ጽሑፍ እንዲያዘጋጁ ፈተና ሰጠቻቸው። ሆኖም አንድሬ የተባለው 16 ዓመት የሆነው የይሖዋ ምሥክር ተማሪ ወደ አስተማሪዋ ቀርቦ እንዲህ ዓይነቱን ጽሑፍ ለማጥናት ሕሊናው ስለማይፈቅድለት ፈተናውን መፈተን እንደማይፈልግ በትሕትና ነገራት። በምትኩ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ምን አመለካከት እንዳለው የሚገልጽ አንድ ጽሑፍ ማዘጋጀት እንደሚችል ነገራት። መምህርቷም አንድሬ ባቀረበው ሐሳብ ተስማማች።
አንድሬ ባዘጋጀው ጽሑፍ ላይ የሌሎች ሰዎችን አስተያየት የሚያከብር መሆኑን ከጠቀሰ በኋላ ስለ ኢየሱስ ለማወቅ ግን ከሁሉ የተሻለ መንገድ ሆኖ ያገኘው ከአራቱ የወንጌል ዘገባዎች መካከል አንዱን ማንበብ እንደሆነ ገልጿል። ይህን በማድረግ “የዓይን ምሥክሮች ከጻፉት ዘገባ ስለ ኢየሱስ ሕይወትም ሆነ ስለ ትምህርቶቹ ማወቅ ትችላላችሁ” ብሏል። አንድሬ በመቀጠል “ሌላው ጉዳይ ደግሞ ሰይጣን የተገለጸበት መንገድ ነው። አንዳንዶች ሰይጣንን ጀግና አድርጎ የሚገልጽ መጽሐፍ ማንበባቸው ሊያዝናናቸው ቢችልም እኔን ግን አያስደስተኝም” በማለት ጽፏል። እንዲያውም ሰይጣን በአምላክ ላይ በማመጽ በሰው ልጆች ላይ ክፋት፣ መከራና ስቃይ ያመጣ ብርቱ ኃይል ያለው ክፉ መንፈሳዊ ፍጡር እንደሆነ አብራራ። አንድሬ እንዲህ በማለት ጽሑፉን ደምድሟል:- “ይህን ጽሑፍ ባነብ እጠቀማለሁ ብዬ አላምንም። እርግጥ ነው፣ በቡልጋኮፍ ላይ ምንም ጥላቻ የለኝም። ይሁን እንጂ በግሌ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ታሪክ ለማወቅ መጽሐፍ ቅዱስን ባነብ እመርጣለሁ።”
የአንድሬ መምህርት በጽሑፉ በጣም ከመደሰቷ የተነሳ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የቃል ሪፖርት እንዲያቀርብ ጋበዘችው። አንድሬም ምንም ሳያቅማማ ግብዣውን ተቀበለ። በቀጣዩ የሥነ ጽሑፍ ክፍለ ጊዜ ላይ በክፍል ተማሪዎቹ ሁሉ ፊት ሪፖርቱን አነበበ። አንድሬ፣ ኢየሱስ በምድር ላይ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው እንደሆነ የሚያምንበትን ምክንያት አብራራ። ከዚያም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከሆነው ከማቴዎስ መጽሐፍ ስለ ኢየሱስ ሞት የሚዘግብ አንድ ምዕራፍ አነበበላቸው። አንድሬ ለሪፖርቱ የተመደበለት ሰዓት እያለቀ መምጣቱን ሲገነዘብ ንግግሩን ለማቆም ፈለገ፤ ይሁን አንጂ የክፍል ጓደኞቹ “ቀጥል! ቀጥል! ከዚያ በኋላስ ምን ተከሰተ?” በማለት ይጠይቁት ጀመር። በዚህም ምክንያት ስለ ኢየሱስ ትንሣኤ የሚናገረውን የማቴዎስ መጽሐፍ ዘገባ አነበበላቸው።
አንድሬ ሪፖርቱን አቅርቦ ከጨረሰ በኋላ የክፍል ጓደኞቹ ኢየሱስንም ሆነ ይሖዋን በተመለከተ ብዙ ጥያቄዎች ጠየቁት። “ይሖዋ ጥበብ እንዲሰጠኝ የጠየቅኩት ሲሆን እርሱም ለጸሎቴ ምላሽ ሰጥቶኛል። ጥያቄዎቻቸውን ሁሉ መመለስ ችያለሁ!” ብሏል። አንድሬ ከትምህርት ክፍለ ጊዜው በኋላ እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው a የተባለውን መጽሐፍ ለመምህርቷ ሲሰጣት በጉጉት ተቀበለችው። “ላቀረብኩት ሪፖርት ከፍተኛ ውጤት የሰጠችኝ ከመሆኑም በላይ የራሴ የሆነ አቋም ስላለኝና በዚህ አቋሜም የማላፍርበት በመሆኔ አደነቀችኝ። እንዲሁም እኔ በማምንባቸው አንዳንድ ነገሮች እንደምታምን ነገረችኝ” ብሏል።
አንድሬ፣ የይሖዋንም ይሁን የልጁን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር ዝቅ የሚያደርግ መጽሐፍ እንዳያነብ የከለከለውን በመጽሐፍ ቅዱስ የሰለጠነ ሕሊናውን ለመከተል በመወሰኑ በጣም ተደስቷል። እንደዚህ ያለውን ቁርጥ ውሳኔ ማድረጉ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ አመለካከቶች ተጽዕኖ እንዳያደርጉበት የጠበቀው ከመሆኑም ሌላ ወሳኝ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ለሌሎች ሰዎች ለማካፈል የሚያስችለውን ግሩም አጋጣሚ ከፍቶለታል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።