የአምላክን ዓላማ ለመፈጸም የሚያገለግል አስተዳደር
የአምላክን ዓላማ ለመፈጸም የሚያገለግል አስተዳደር
‘አምላክ ሁሉን በፈቃዱ ምክር መሠረት ይሠራዋል።’—ኤፌሶን 1:11
1. ሁሉም የይሖዋ ምሥክሮች ሚያዝያ 12, 2006 በየጉባኤያቸው የሚሰበሰቡት ለምንድን ነው?
ረቡዕ ሚያዝያ 12, 2006 ምሽት ላይ 16 ሚሊዮን ያህል ሰዎች የጌታ እራትን ለማክበር ይሰበሰባሉ። በእያንዳንዱ የመሰብሰቢያ ቦታ የክርስቶስን ሥጋ የሚወክል ያልቦካ ቂጣና ደሙን የሚወክል ቀይ ወይን ጠጅ በጠረጴዛ ላይ ይቀርባል። የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ በዓል ምን ትርጉም እንዳለው የሚያወሳው ንግግር ወደ መደምደሚያው ሲቃረብ፣ በመጀመሪያ ቂጣው ከዚያም ወይኑ በበዓሉ ላይ ለተገኙት ሰዎች ይዞራሉ። በጥቂት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ አንድ ወይም ከዚያ በላይ ሰዎች ከቂጣው ይበላሉ እንዲሁም ከወይኑ ይጠጣሉ። በአብዛኞቹ ጉባኤዎች ውስጥ ግን ከተሰብሳቢዎቹ መካከል ይህን የሚያደርግ ሰው አይኖርም። በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው አብዛኞቹ ተሰብሳቢዎች ከቂጣና ከወይኑ ሳይካፈሉ በሰማይ የመኖር ተስፋ ያላቸው ጥቂት ክርስቲያኖች ብቻ የሚካፈሉት ለምንድን ነው?
2, 3. (ሀ) ይሖዋ በዓላማው መሠረት የፍጥረት ሥራዎችን ያከናወነው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ምድርንና የሰው ዘሮችን የፈጠረበት ዓላማ ምንድን ነው?
2 ይሖዋ የዓላማ አምላክ ነው። ዓላማውን ለመፈጸምም “ሁሉን በፈቃዱ ምክር መሠረት እንደሚሠራ” ተገልጿል። (ኤፌሶን 1:11) በዚህ መሠረት በመጀመሪያ አንድያ ልጁን ፈጠረ። (ዮሐንስ 1:1, 14፤ ራእይ 3:14 የ1954 ትርጉም ) ከዚያም በዚህ ልጁ አማካኝነት፣ መንፈሳዊ ልጆችን ያቀፈውን ቤተሰብ እንዲሁም ምድርንና የሰው ዘሮችን በውስጡ የያዘውን ግዑዙን አጽናፈ ዓለም ፈጠረ።—ኢዮብ 38:4, 7፤ መዝሙር 103:19-21፤ ዮሐንስ 1:2, 3፤ ቈላስይስ 1:15, 16
3 በርካታ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት እንደሚያስተምሩት ይሖዋ ምድርን የፈጠረው በሰማይ ከሚገኘው የመንፈሳዊ ልጆቹ ቤተሰብ ጋር የሚቀላቀሉ ሰዎችን ለመፈተን የምታገለግል ቦታ እንድትሆን አስቦ አይደለም። ምድርን የፈጠረው ግልጽ የሆነ ዓላማ በአእምሮው ይዞ ይኸውም “የሰው መኖሪያ” እንድትሆን አስቦ ነው። (ኢሳይያስ 45:18) አምላክ ምድርን የፈጠረው ለሰው ልጆች ሲሆን የሰው ልጆችም የተፈጠሩት በምድር ላይ ለመኖር ነው። (መዝሙር 115:16) ዓላማው መላዋ ፕላኔት ገነት እንድትሆንና ይህን ገነት በሚያለሙና በሚንከባከቡ ጻድቅ ሰዎች እንድትሞላ ነበር። የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ባልና ሚስት ከጊዜ በኋላ ወደ ሰማይ የመሄድ ተስፋ ፈጽሞ አልተሰጣቸውም።—ዘፍጥረት 1:26-28፤ 2:7, 8, 15
የይሖዋ ዓላማ እንቅፋት ገጠመው
4. በሰው ዘር ታሪክ መጀመሪያ ላይ፣ ይሖዋ ሉዓላዊነቱን የሚጠቀምበትን መንገድ በተመለከተ ጥያቄ የተነሳው እንዴት ነው?
4 ከአምላክ መንፈሳዊ ልጆች አንዱ በአምላክ ላይ በማመጽ የተሰጠውን የመምረጥ ነጻነት አላግባብ ተጠቅሞ የይሖዋን ዓላማ ለማደናቀፍ ቆርጦ ተነሳ። ይህ እርምጃው በፍቅር ተነሳስተው ለይሖዋ ሉዓላዊነት የሚገዙ ፍጥረታትን ሰላም አደፈረሰው። ሰይጣን የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ባልና ሚስት ከአምላክ ርቀው ራሳቸውን እንዲመሩ አደረጋቸው። (ዘፍጥረት 3:1-6) ዲያብሎስ ይሖዋ ኃይል እንዳለው ባይክድም አምላክ ሉዓላዊነቱን የሚጠቀምበት መንገድ እንዲሁም የመግዛት መብቱ አጠያያቂ እንዲሆን አደረገ። በመሆኑም በሰው ዘር ታሪክ መጀመሪያ ላይ የይሖዋን ሉዓላዊነት በተመለከተ በምድር ላይ ጥያቄ ተነሳ።
5. ሰይጣን ምን ተጨማሪ ጥያቄ አስነሳ? ጉዳዩ እነማንንም ይመለከታል?
5 ሰይጣን፣ የይሖዋን አጽናፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት አስመልክቶ ካስነሳው ጥያቄ ጋር በተያያዘ በኢዮብ ዘመን ደግሞ ሌላ ጉዳይ አነሳ። ዲያብሎስ የይሖዋ ፍጥረታት ለእርሱ የሚገዙበትና እርሱን የሚያገለግሉበት ምክንያት አጠያያቂ እንደሆነ ገለጸ። የአምላክ ፍጥረታት እርሱን የሚያገለግሉት በራስ ወዳድነት ተነሳስተው እንደሆነና ፈተና ቢያጋጥማቸው አምላክን እንደሚተዉት ተናገረ። (ኢዮብ 1:7-11፤ 2:4, 5) ይህ ነጥብ የተነሳው ከይሖዋ ሰብዓዊ ፍጥረታት ጋር በተያያዘ ቢሆንም ግድድሩ የአምላክን መንፈሳዊ ልጆች ሌላው ቀርቶ አንድያ ልጁን እንኳ ይመለከታል።
6. ይሖዋ ለዓላማውና ለስሙ ታማኝ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?
6 ይሖዋ ለዓላማውና ለስሙ ትርጉም ታማኝ በመሆን የነቢይነትና የአዳኝነት ሚና ተጫውቷል። a ሰይጣንን “በአንተና በሴቲቱ፣ በዘርህና በዘሯ መካከል፣ ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፤ አንተም ተረከዙን ትቀጠቅጣለህ” ብሎታል። (ዘፍጥረት 3:15) ይሖዋ “በሴቲቱ” ዘር ወይም ሰማይ ባለው የድርጅቱ ክፍል አማካኝነት ሰይጣን ላስነሳው ግድድር መልስ ከመስጠትም አልፎ የአዳም ዘሮች የመዳን ተስፋና ሕይወት እንዲያገኙ ዝግጅት አደረገ።—ሮሜ 5:21፤ ገላትያ 4:26, 31
‘የፈቃዱ ቅዱስ ምስጢር’
7. ይሖዋ በሐዋርያው ጳውሎስ አማካኝነት የትኛውን ዓላማውን ገልጿል?
7 ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ይሖዋ ዓላማውን ለመፈጸም ነገሮችን የሚያስተዳድርበትን መንገድ ለማመልከት ግሩም የሆነ መግለጫ ተጠቅሟል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በክርስቶስ ያቀደውንም የፈቃዱን ምስጢር [“ቅዱስ ምስጢር፣” NW ] እንደ በጎ ሐሳቡ እንድናውቅ አደረገ። በዘመን ፍጻሜ ይሆን ዘንድ ያለው ሐሳቡ [“አስተዳደር ለማቋቋም ይኸውም፣” NW ] በሰማይም በምድርም ያሉትን ነገሮች ሁሉ ራስ በሆነው በክርስቶስ ሥር ለመጠቅለል ነው።” (ኤፌሶን 1:9, 10) አስደናቂ የሆነው የይሖዋ ዓላማ፣ በፍቅር ተነሳስተው ለሉዓላዊነቱ የሚገዙ ፍጡራንን ያቀፈ አጽናፈ ዓለማዊ አንድነት ለመመሥረት ነው። (ራእይ 4:11) በዚህ መንገድ ስሙ ይቀደሳል፤ ሰይጣን ውሸታም መሆኑ ይረጋገጣል እንዲሁም የአምላክ ፈቃድ ‘በሰማይ እንደ ሆነ፣ እንዲሁ በምድር’ ይሆናል።—ማቴዎስ 6:10
8. “አስተዳደር” ተብሎ የተተረጎመው ቃል ትርጉሙ ምንድን ነው?
8 የይሖዋ ‘በጎ ሐሳብ’ ወይም ዓላማ በአንድ “አስተዳደር” አማካኝነት ይፈጸማል። ጳውሎስ እዚህ ላይ የተጠቀመበት ቃል በቀጥታ ሲተረጎም “የቤት አስተዳደር” ማለት ነው። ይህ ቃል እንደ መሲሐዊው መንግሥት ያለ አገዛዝን ሳይሆን ነገሮች የሚከናወኑበትን መንገድ ይጠቁማል። b ይሖዋ ዓላማውን ለመፈጸም ነገሮችን የሚያስተዳድርበት አስደናቂ መንገድ “ቅዱስ ምስጢር” ሲሆን ይህ ምስጢር በተለያዩ ዘመናት ውስጥ ቀስ በቀስ ተገልጧል።—ኤፌሶን 1:10፤ 3:9 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ
9. ይሖዋ የፈቃዱን ቅዱስ ምስጢር ቀስ በቀስ የገለጠው እንዴት ነው?
9 ይሖዋ በዔድን ገነት ውስጥ ተስፋ የተሰጠበትን ዘር በተመለከተ ያለው ዓላማ እንዴት እንደሚፈጸም በተለያዩ ጊዜያት በገባቸው ቃል ኪዳኖች አማካኝነት ቀስ በቀስ ገልጿል። ከአብርሃም ጋር በገባው ቃል ኪዳን ላይ ተስፋ የተደረገበት ዘር ወደ ምድር የሚመጣው በእርሱ የዘር ሐረግ በኩል እንደሆነና “የምድር ሕዝቦች ሁሉ” በዚህ ዘር አማካኝነት ራሳቸውን እንደሚባርኩ ተገለጸ። ይህ ቃል ኪዳን ሌሎች ሰዎች ከዘሩ ዋነኛ ክፍል ጋር እንደሚተባበሩም በተዘዋዋሪ መንገድ ጠቁሟል። (ዘፍጥረት 22:17, 18) ይሖዋ ከሥጋዊ እስራኤላውያን ጋር በገባው የሕግ ቃል ኪዳን አማካኝነት ደግሞ “የመንግሥት ካህናት” የማዘጋጀት ዓላማ እንዳለው ገለጸ። (ዘፀአት 19:5, 6) ከዳዊት ጋር የገባው ቃል ኪዳን ዘሩ ለዘላለም የአንድ መንግሥት ራስ እንደሚሆን የሚጠቁም ነበር። (2 ሳሙኤል 7:12, 13፤ መዝሙር 89:3, 4) የሕጉ ቃል ኪዳን አይሁዳውያንን ወደ መሲሑ ካደረሳቸው በኋላ ይሖዋ ዓላማው የሚፈጸምበትን መንገድ ይበልጥ ግልጽ አደረገ። (ገላትያ 3:19, 24) ከዘሩ ዋነኛ ክፍል ጋር የሚተባበሩት የሰው ዘሮች አስቀድሞ በትንቢት እንደተነገረው “የመንግሥት ካህናት” ይሆናሉ፤ እነርሱም አዲስ ማለትም መንፈሳዊ “እስራኤል” በመሆን ‘በአዲስ ቃል ኪዳን’ ውስጥ ይታቀፋሉ።—ኤርምያስ 31:31-34፤ ዕብራውያን 8:7-9 c
10, 11. (ሀ) ይሖዋ፣ አስቀድሞ የተነገረው ዘር ማንነት ግልጽ እንዲሆን ያደረገው እንዴት ነበር? (ለ) የአምላክ አንድያ ልጅ ወደ ምድር የመጣው ለምን ነበር?
10 ውሎ አድሮ፣ በዔድን ውስጥ ትንቢት የተነገረለት ዘር የአምላክን ዓላማ ለማስፈጸም ወደ ምድር የሚመጣበት ጊዜ ደረሰ። ይሖዋ፣ መልአኩን ገብርኤልን በመላክ ለማርያም ኢየሱስ ተብሎ የሚጠራ ልጅ እንደምትወልድ እንዲነግራት አደረገ። መልአኩ “እርሱም ታላቅ ይሆናል፤ የልዑል ልጅም ይባላል፤ ጌታ አምላክ የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብም ቤት ላይ ለዘላለም ይነግሣል፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም” አላት። (ሉቃስ 1:32, 33) በዚህ መንገድ ተስፋ የተሰጠበት ዘር ማንነት ግልጽ ሆነ።—ገላትያ 3:16፤ 4:4
11 የይሖዋ አንድያ ልጅ ወደ ምድር መጥቶ እስከ መጨረሻው ድረስ መፈተን ነበረበት። ሰይጣን ላነሳው ጥያቄ የማያዳግም መልስ የመስጠቱ ኃላፊነት በእርሱ ላይ ወደቀ። ለአባቱ ታማኝ ሆኖ ይጸና ይሆን? ይህ ቅዱስ ምስጢር ነበር። ከጊዜ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ ኢየሱስ የተጫወተውን ሚና ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “የእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት ምስጢር [“ቅዱስ ምስጢር፣” NW ] ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፤ እርሱ በሥጋ ተገለጠ፤ በመንፈስ ጸደቀ፤ በመላእክት ታየ፤ በአሕዛብ ዘንድ ተሰበከ፤ በዓለም ባሉት ታመነ፤ በክብር ዐረገ።” (1 ጢሞቴዎስ 3:16) አዎን፣ ኢየሱስ እስከ ሞት ድረስ ታማኝ በመሆን ያሳየው የማይበገር ጽናት ሰይጣን ላስነሳው ግድድር የማያዳግም መልስ ሰጥቷል። ሆኖም ገና ግልጽ ያልሆኑ የቅዱሱ ምስጢር ክፍሎች ነበሩ።
‘የእግዚአብሔር መንግሥት ቅዱስ ምስጢር’
12, 13. (ሀ) ‘የእግዚአብሔር መንግሥት ቅዱስ ምስጢር’ አንዱ ገጽታ ምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ወደ ሰማይ እንዲሄዱ ሲመርጥ ምን ማድረግ አስፈልጎታል?
12 ኢየሱስ ለስብከት ወደ ገሊላ በሄደበት ወቅት፣ ቅዱሱ ምስጢር እርሱ ንጉሥ ሆኖ ከሚያስተዳድረው መሲሐዊ መንግሥት አገዛዝ ጋር በቅርብ የተዛመደ መሆኑን ጠቁሟል። ለደቀ መዛሙርቱ “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማይን ምስጢር [“ቅዱስ ምስጢር፣” NW ] ማወቅ ተሰጥቶአችኋል” ብሏቸው ነበር። (ማቴዎስ 13:11) በማርቆስ 4:11 ላይ ደግሞ “ለእናንተ የእግዚአብሔር መንግሥት ምስጢር [“ቅዱስ ምስጢር፣” NW ] ተሰጥቶአችኋል” ብሏል። ይሖዋ ከልጁ ጋር የዘሩ ክፍል የሚሆኑና በሰማይ አብረውት የሚገዙ 144, 000 ሰዎችን ያቀፈ “ታናሽ መንጋ” መምረጡ የዚህ ምስጢር አንዱ ገጽታ ነው።—ሉቃስ 12:32 የ1954 ትርጉም ፤ ራእይ 14:1, 4
13 ሰዎች የተፈጠሩት በምድር ላይ እንዲኖሩ በመሆኑ የተወሰኑ ሰዎች ወደ ሰማይ እንዲሄዱ ለማድረግ ይሖዋ “አዲስ ፍጥረት” መሥራት ነበረበት። (2 ቆሮንቶስ 5:17) ወደ ሰማይ የመሄድ ልዩ ተስፋ ካላቸው ሰዎች አንዱ የሆነው ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባትና አምላክ ይባረክ፤ እርሱ ከታላቅ ምሕረቱ የተነሣ በኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት መነሣት ምክንያት ለሕያው ተስፋ በሚሆን አዲስ ልደት፣ እንዲሁም በሰማይ ለማይጠፋ፣ ለማይበላሽና ለማይለወጥ ርስት እንደገና ወለደን።”—1 ጴጥሮስ 1:3, 4
14. (ሀ) ‘የእግዚአብሔር መንግሥት ቅዱስ ምስጢር’ አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎችን የሚነካቸው እንዴት ነው? (ለ) ይህን “የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር” መረዳት የቻልነው እንዴት ነው?
14 ከመጪው የአምላክ መንግሥት ጋር የተያያዘው ሌላው የቅዱሱ ምስጢር ክፍል ደግሞ ከክርስቶስ ጋር በሰማይ እንዲገዙ ከተጠሩት ጥቂት ቁጥር ያላቸው ሰዎች መካከል አይሁዳውያን ያልሆኑ ግለሰቦችም እንዲካተቱ ያደረገው የአምላክ ዓላማ ነው። ጳውሎስ ከዚህ ጋር የተያያዘውን የይሖዋ “አስተዳደር” ገጽታ ወይም ዓላማውን የሚፈጽምበትን መንገድ ሲያብራራ እንዲህ ብሏል:- “ይህም ምስጢር አሁን ለቅዱሳኑ ሐዋርያትና ነቢያት የተገለጠውን ያህል ባለፉት ዘመናት ለነበሩ ሰዎች አልተገለጠም ነበር። ይህም ምስጢር አሕዛብ በወንጌል አማካይነት ከእስራኤል ጋር አብረው ወራሾች፣ አብረው የአንዱ አካል ብልቶች እንዲሁም በክርስቶስ ኢየሱስ በሆነው ተስፋ አብረው ተካፋይ መሆናቸው ነው።” (ኤፌሶን 3:5, 6) ይህ የቅዱሱ ምስጢር ክፍል “ለቅዱሳኑ ሐዋርያት” ተገልጦላቸው ነበር። ዛሬም በተመሳሳይ የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ ባናገኝ ኖሮ ይህን “የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር” መረዳት አንችልም ነበር።—1 ቆሮንቶስ 2:10፤ 4:1፤ ቈላስይስ 1:26, 27
15, 16. ይሖዋ የክርስቶስን ተባባሪ ገዢዎች ከሰው ልጆች መካከል የመረጣቸው ለምንድን ነው?
15 በሰማይ ባለችው የጽዮን ተራራ ላይ ‘ከበጉ’ ጋር ቆመው የታዩት “መቶ አርባ አራቱ ሺህ” ሰዎች ‘ከምድር የተዋጁ’ እንዲሁም “ለእግዚአብሔርና ለበጉ በኵራት እንዲሆኑ ከሰዎች መካከል የተዋጁ” እንደሆኑ ተገልጿል። (ራእይ 14:1-4) ይሖዋ በሰማይ ካሉት ልጆቹ መካከል የመጀመሪያውን በዔድን ውስጥ ተስፋ የተሰጠበት ዘር ዋነኛ ክፍል እንዲሆን መርጦታል፤ ሆኖም ከክርስቶስ ጋር አብረው የሚገዙትን ከሰው ዘሮች መካከል የመረጠው ለምንድን ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ ውስን ቁጥር ያላቸውን እነዚህን ሰዎች ይሖዋ “እንደ በጎ ፈቃዱ” እና ‘እንደ ሐሳቡ እንደጠራቸው’ ገልጿል።—ሮሜ 8:17, 28-30፤ ኤፌሶን 1:5, 11፤ 2 ጢሞቴዎስ 1:9
16 የይሖዋ ዓላማ፣ ታላቅና ቅዱስ የሆነውን ስሙን ማስቀደስ እንዲሁም አጽናፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነቱን ማረጋገጥ ነው። ተወዳዳሪ በሌለው ጥበቡ ባዘጋጀው “አስተዳደር” ወይም ነገሮችን በሚያስፈጽምበት መንገድ በመጠቀም የበኩር ልጁን ወደ ምድር ልኮታል፤ እርሱም እስከ ሞት ድረስ ተፈትኗል። ከዚህም በላይ ይሖዋ በልጁ የሚተዳደረው መሲሐዊ መንግሥት፣ እስከ ሞት ድረስ ለሉዓላዊነቱ ታማኞች መሆናቸውን ያሳዩ የሰው ልጆችንም እንዲጨምር አድርጓል።—ኤፌሶን 1:8-12፤ ራእይ 2:10, 11
17. ክርስቶስም ሆነ ተባባሪ ገዢዎቹ በአንድ ወቅት በምድር ላይ የኖሩ ሰዎች መሆናቸውን ማወቃችን የሚያስደስተን ለምንድን ነው?
17 ይሖዋ፣ ልጁ ወደ ምድር እንዲመጣ በማድረግና በመንግሥቱ ውስጥ ከልጁ ጋር ተባባሪ ወራሾች የሚሆኑ ሰዎችን ከሰው ዘሮች መካከል በመምረጥ ለአዳም ዝርያዎች ታላቅ ፍቅር እንዳለው አሳይቷል። ከአቤል ጀምሮ ታማኝነታቸውን የጠበቁ ሌሎች ሰዎች ከዚህ ምን ጥቅም ያገኛሉ? የይሖዋ የመጀመሪያ ዓላማ እንዲፈጸም የኃጢአትና የሞት ባሪያዎች ሆነው የተወለዱት የሰው ልጆች በመንፈሳዊም ሆነ በአካላዊ ሁኔታ መፈወስና ወደ ፍጽምና መድረስ ያስፈልጋቸዋል። (ሮሜ 5:12) በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ተስፋ የሚያደርጉ በሙሉ ንጉሣቸው በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ለደቀ መዛሙርቱ እንዳደረገው ሁሉ እነርሱንም እንደሚወዳቸውና ስሜታቸውን እንደሚረዳላቸው በማወቃቸው በጣም ይበረታታሉ! (ማቴዎስ 11:28, 29፤ ዕብራውያን 2:17, 18፤ 4:15፤ 7:25, 26) በሰማይ የክርስቶስ ተባባሪ የሆኑት ነገሥታትና ካህናትም ልክ እንደ እኛው ከግል ድክመቶቻቸው ጋር ይታገሉ የነበሩና የሕይወትን ችግሮች የቀመሱ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች መሆናቸውን መገንዘባቸው የሚያበረታታ ነው!—ሮሜ 7:21-25
የይሖዋ ዓላማ መፈጸሙ አይቀርም
18, 19. በኤፌሶን 1:8-11 ላይ የሚገኙት የጳውሎስ ቃላት ግልጽ የሆኑልን እንዴት ነው? በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
18 በኤፌሶን 1:8-11 ላይ የሚገኘውን ጳውሎስ በመንፈስ ለተቀቡት ክርስቲያኖች የጻፈውን መልእክት ትርጉም አሁን የበለጠ መረዳት ችለናል። ጳውሎስ፣ ለእነዚህ ክርስቲያኖች ይሖዋ “የፈቃዱን ምስጢር [“ቅዱስ ምስጢር፣” NW ]” እንዳሳወቃቸው፣ ከክርስቶስ ጋር ‘ርስትን እንደተቀበሉ፣ (የ1954 ትርጉም )’ እንዲሁም ‘ሁሉን በፈቃዱ ምክር መሠረት እንደሚሠራው እንደ እርሱ ዕቅድ [“ዓላማ፣” NW ] አስቀድመው እንደተወሰኑ’ ገልጿል። ይህም ይሖዋ ዓላማውን ለመፈጸም ከተጠቀመበት ድንቅ “አስተዳደር” ጋር የተያያዘ እንደሆነ ተገንዝበናል። ከዚህም በላይ ይህን ማወቃችን በጌታ እራት ላይ ከቂጣው የሚበሉትና ከወይኑ የሚጠጡት ጥቂት ክርስቲያኖች ብቻ የሆኑበትን ምክንያት መረዳት እንድንችል ያደርገናል።
19 በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ፣ ወደ ሰማይ የመሄድ ተስፋ ላላቸው ክርስቲያኖች የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ምን ትርጉም እንዳለው እንመለከታለን፤ ከዚህ በተጨማሪ በምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ የሚያደርጉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለመታሰቢያው በዓል ትርጉም ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጡት ለምን እንደሆነ እንመረምራለን።
[የግርጌ ማስታወሽዎች]
a መለኮታዊው ስም ቃል በቃል ሲተረጎም “ይሆናል” የሚል ትርጉም አለው። ይሖዋ ዓላማውን ለመፈጸም የሚያስፈልገውን ሁሉ መሆን ይችላል።—ዘፀአት 3:14 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻን እንዲሁም ወደ ይሖዋ ቅረብ ከተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 1 አንቀጽ 8 ን ተመልከት።
b ከጳውሎስ አነጋገር መረዳት እንደሚቻለው ‘አስተዳደሩ’ በእርሱ ዘመን እየሠራ ነበር፤ መሲሐዊው መንግሥት ግን እስከ 1914 ድረስ እንዳልተቋቋመ ቅዱሳን ጽሑፎች ያሳያሉ።
c የአምላክን ዓላማ ለማስፈጸም ስላገለገሉት ስለ እነዚህ ቃል ኪዳኖች ሰፋ ያለ ማብራሪያ ለማግኘት የየካቲት 1, 1989 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 10-15ን [w-AM 3-110 ገጽ 10-15ን] እንዲሁም የየካቲት 1, 1998 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 8-18 ን ተመልከት።
ለክለሳ ያህል
• ይሖዋ ምድርን የፈጠረውና የሰው ልጆችን በምድር ላይ ያስቀመጣቸው ለምንድን ነው?
• የይሖዋ አንድያ ልጅ በምድር ላይ መፈተን የነበረበት ለምንድን ነው?
• ይሖዋ የክርስቶስን ተባባሪ ገዥዎች ከሰው ልጆች መካከል የመረጠው ለምንድን ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]