የወላጆቻቸውን ልብ ደስ አሰኝተዋል
የወላጆቻቸውን ልብ ደስ አሰኝተዋል
“ልጄ ሆይ፤ ልብህ ጠቢብ ቢሆን፣ የእኔም ልብ ሐሤት ያደርጋል።” (ምሳሌ 23:15) በእርግጥም ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸው አምላካዊ ጥበብ ሲኖራቸው ይደሰታሉ። ቅዳሜ መስከረም 10, 2005 በተከናወነው 119ኛው ክፍል ጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ምረቃ ላይ፣ ከልዩ ልዩ አገሮች የተውጣጡ 6, 859 ሰዎች ተገኝተው ነበር። በወቅቱ በዚያ የተገኙ ተሰብሳቢዎች በሙሉ በተለይም የ56ቱ ተመራቂዎች ወላጆች ልብ በደስታ ተሞልቶ ነበር።
ፕሮግራሙ የተከፈተው በዩናይትድ ስቴትስ ቤቴል ለረጅም ጊዜ ሲያገለግል የቆየው ዴቪድ ዎከር ባቀረበው ልብ የሚነካ ጸሎት ነበር። ቀጥሎም የፕሮግራሙ ሊቀ መንበርና የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል የሆነው ዴቪድ ስፕሌን የምረቃውን ፕሮግራም የመክፈቻ ንግግር አቀረበ። በዚህ ንግግር ላይ ለተመራቂዎቹ ወላጆች “ከፍተኛ ምሥጋና ሊቸራችሁ ይገባል። በልጆቻችሁ ውስጥ የተከላችኋቸው ባሕርያት ሚስዮናዊ ሆነው እንዲያገለግሉ አነሳስተዋቸዋል” በማለት ተናግሮ ነበር። ምናልባት እነዚህ ወላጆች፣ ልጆቻቸው በቅርቡ ሩቅ ወደ ሆኑ አካባቢዎች መሄዳቸው ስለማይቀር ስጋት ያድርባቸው ይሆናል። ይሁንና ወንድም ስፕሌን እንደሚከተለው ሲል አጽናንቷቸዋል:- “ስለ ልጆቻችሁ ስጋት አይግባችሁ፤ ይሖዋ አምላክ እናንተ ልታደርጉላቸው ከምትችሉት በላይ ይንከባከባቸዋል። ልጆቻችሁ ስለሚያከናውኗቸው መልካም ተግባራት አስቡ። በሥቃይ ውስጥ ያሉ ሰዎች በሕይወታቸው ለመጀመሪያ ጊዜ እውነተኛ ማጽናኛ ሊያገኙ ነው።”
ሌሎችን በማስደሰት መቀጠል የሚቻለው እንዴት ነው?
ከዚያ በመቀጠል ሊቀ መንበሩ አራት ተናጋሪዎች አስተዋወቀ። የመጀመሪያው ተናጋሪ የዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮ አባል የሆነው ራልፍ ዎልስ ሲሆን ያቀረበው ንግግር “ዓይኖቻችሁ ምንጊዜም አይከደኑ” የሚል ጭብጥ ያለው ነበር። በንግግሩም ላይ በመንፈሳዊ እውር መሆን ቃል በቃል ዓይንን ከመታወር እጅግ የከፋ እንደሆነ ጠበቅ አድርጎ ገልጿል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን በሎዶቅያ ይገኝ የነበረው ጉባኤ በመንፈሳዊ ታውሮ ነበር። በዚያ ጉባኤ የሚገኙ በመንፈሳዊ የታወሩ ክርስቲያኖች እርዳታ አግኝተዋል፤ ሆኖም ይህን ዓይነቱን ዓይነ ስውርነት መንፈሳዊ ዓይኖቻችን ምንጊዜም እንዳይከደኑ በማድረግ አስቀድመን መከላከሉ ከሁሉ የተሻለ ነው። (ራእይ 3:14-18) ቀጥሎም ተናጋሪው “ዓይኖቻችሁ ምንጊዜም አይከደኑ እንዲሁም ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞችን ይሖዋ በሚያያቸው መንገድ ተመልከቷቸው” ብሏል። ተመራቂዎቹ በጉባኤ ውስጥ ችግሮች ቢከሰቱ ከልክ በላይ መጨነቅ የለባቸውም። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች እንደሚከሰቱ ይገነዘባል። በመሆኑም ሁኔታዎቹ በተገቢው ጊዜ እንዲስተካከሉ ያደርጋል።
ቀጥሎም የበላይ አካል አባል የሆነው ሳሙኤል ኸርድ “ዝግጁ ናችሁ?” ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ሰጥቷል። አንድ መንገደኛ ለጉዞ የሚያስፈልጉትን ልብሶች ይዞ እንደሚሄድ ሁሉ ተመራቂዎቹም ዘወትር የአዲሱን ሰው ባሕርያት መልበስ ይገባቸዋል። ተማሪዎቹ የኢየሱስን ዓይነት ርኅራኄ ማሳየት አለባቸው። ለምጻሙ ሰው “ብትፈቅድ እኮ ልታነጻኝ ትችላለህ” ባለው ጊዜ ኢየሱስ “እፈቅዳለሁ፣ ንጻ” ብሎታል። (ማርቆስ 1:40-42) ከዚያም ተናጋሪው በመቀጠል “ሰዎችን ለመርዳት ልባዊ ፍላጎት ካላችሁ እንዲህ ለማድረግ የሚያስችላችሁ መንገድ አታጡም” ሲል ተናገረ። ፊልጵስዩስ 2:3 ክርስቲያኖች ‘ሌሎች ከእነሱ እንደሚሻሉ’ አድርገው መመልከት እንደሚገባቸው ይገልጻል። ወንድም ኸርድ እንደሚከተለው ብሏል:- “ትሑት መሆን አዋቂ ከመሆን ይበልጥ አስፈላጊ ነው። በአገልግሎት ላይ የሚያጋጥሟችሁ ሰዎችም ሆኑ በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንድሞቻችሁና እህቶቻችሁ ካላችሁ እውቀት መጠቀም የሚችሉት ትሑቶች ከሆናችሁ ብቻ ነው።” ተመራቂዎቹ ክርስቲያናዊ ፍቅርን መልበሳቸውን እስከቀጠሉ ድረስ ከፊታቸው ግሩም ውጤት እንደሚጠብቃቸው እርግጠኛ ሆነው ወደተመደቡበት ቦታ መሄድ እንደሚችሉ በመግለጽ ንግግሩን ደምድሟል።—ቈላስይስ 3:14
ከጊልያድ ትምህርት ቤት አስተማሪዎች ውስጥ አንዱ የሆነው ማርክ ኑሜር “ምንጊዜም ይህ መንፈስ ይኖራችሁ ይሆን?” በሚል ጭብጥ ያቀረበው ንግግር የአድማጮችን ልብ ያንጠለጠለ ነበር። “ይህ መንፈስ” የተባለው ለይሖዋ ጥሩነት ያለን የአመስጋኝነት ስሜት ነው። መዝሙር 103:2 “ነፍሴ ሆይ እግዚአብሔርን ባርኪ፤ ውለታውንም ሁሉ አትርሺ” ይላል። እስራኤላውያን ሕይወታቸው እንዲቀጥል የረዳቸውን መና “የማይረባ ምግብ” በማለት የአመስጋኝነት መንፈስ ሳያሳዩ ቀርተዋል። (ዘኍልቍ 21:5) ጊዜው እያለፈ ሲሄድ መና ያለውን ዋጋማነት ያልቀነሰ ቢሆንም እንኳ እነርሱ ግን የነበራቸውን የአድናቆት ስሜት አጥተው ነበር። አስተማሪው በመቀጠል እንደሚከተለው ብሏል:- “ይሖዋ ያደረገላችሁን ዘንግታችሁ የሚስዮናዊነት አገልግሎታችሁን እንደ ተራ ነገር አድርጋችሁ የምትቆጥሩ ከሆነ ይህ አመለካከታችሁ ይሖዋ የሰጣችሁን ሥራ በምትመለከቱበት መንገድ ላይ ተጽዕኖ ያደርግባችኋል።” መዝሙር 103:4 ይሖዋ ‘ምሕረትን እንደሚያቀዳጃችሁ’ ይናገራል። ተመራቂዎቹ በሚመደቡበት አዲስ ጉባኤ ውስጥ የይሖዋን ምሕረት ማለትም ፍቅራዊ ደግነቱን ይቀምሳሉ።
ሌላው የጊልያድ አስተማሪ የሆነው ሎውረንስ ቦወን “በረከቶቹ ያገኟችሁ ይሆን?” የሚል ርዕስ ያለው ንግግር አቅርቧል። በንግግሩ ላይም የ119ኛው ክፍል የጊልያድ ተመራቂዎች ስኬታማ ሚስዮናውያን ለመሆን የሚያስችላቸውን ከፍተኛ ሥልጠና መውሰዳቸውን ጠቅሷል። ይሁንና አሁን ከይሖዋና እርሱ ከሰጣቸው ሥራ ጋር መጣበቅ ይኖርባቸዋል። ወንድም ቦወን 144, 000ዎቹ ‘በጉ ወደሚሄድበት ሁሉ እንደሚከተሉት’ የተገለጸበትን ራእይ 14:1-4ን ጠቅሶ ተናገረ። መላው የዚህ ቡድን አባላት ብዙ መከራዎች ቢደርሱባቸውም እንኳ ለይሖዋና ለልጁ ያላቸውን ታማኝነት ጠብቀው በመኖር ያሰቡት ግብ ላይ መድረስ ችለዋል። ተናጋሪው “እኛም ምንም ዓይነት ሁኔታ ያጋጥመን ከይሖዋና እርሱ ከሰጠን አገልግሎት ጋር በታማኝነት ተጣብቀን መኖር ይገባናል” ሲል ገልጿል። ተመራቂዎቹም እንዲህ የሚያደርጉ ከሆነ የይሖዋ በረከቶች ‘ያገኟቸዋል።’—ዘዳግም 28:2 1954 ትርጉም
በአገልግሎት ያገኙት ፍሬ
ተማሪዎቹ በኮርሱ ላይ ባሳለፏቸው ሳምንታት ውስጥ ሁልጊዜ ቅዳሜና እሁድ በመስክ አገልግሎት ሲካፈሉ ቆይተዋል። የጊልያድ ትምህርት ቤት ሬጅስትራር የሆነው ዋላስ ሊቨራንስ በፕሮግራሙ ላይ ሲያነጋግራቸው በግልጽ እንደታየው ተመራቂዎቹ በመስኩ ውጤታማ ነበሩ። ምሥራቹን ከአሥር ባላነሱ ቋንቋዎች ሲሰብኩ የነበረ ከመሆኑም ባሻገር በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን አስጀምረዋል። የጊልያድ ተማሪዎች የሆኑ ባልና ሚስት አንድን ቻይናዊ መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ይጀምራሉ። ሁለት ጊዜ ተመላልሰው ካወያዩት በኋላ ይሖዋን በማወቁ ምን እንደተሰማው ጠየቁት። በዚህ ጊዜ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ዮሐንስ 17:3 በማውጣት ጥቅሱን እነርሱ ራሳቸው እንዲያነቡት ጋበዛቸው። ይህ ሰው ወደ ሕይወት የሚመራውን መንገድ እንዳገኘ ተሰምቶታል።
ከዚህ በኋላ፣ የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል የሆነው አንቶኒ ሞሪስ ከኮት ዲቩዋር፣ ከዶሚኒካን ሪፑብሊክና ከኢኳዶር ከመጡ የቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባላት ጋር ቃለ ምልልስ አደረገ። እነዚህ ወንድሞች፣ ተማሪዎቹ የተመደቡባቸው አገሮች ቅርንጫፍ ቢሮዎች የተመራቂዎቹን መምጣት በጉጉት እንደሚጠባበቁና ከአገልግሎት ምድባቸው ጋር እንዲላመዱ ለመርዳት አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርጉላቸው ገልጸዋል።
ቀጥሎም የዩናይትድ ስቴትስ ቤቴል አባል የሆነው ሊዮናርድ ፒርሰን ከኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ ከፓፑዋ ኒው ጊኒ እና ከኡጋንዳ ከመጡ የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላት ጋር ቃለ ምልልስ አደረገ። እነዚህ ወንድሞች ሙሉ በሙሉ በመስክ አገልግሎት እንዲካፈሉ ተመራቂዎችን አበረታቷቸው። በኮንጎ ውስጥ 21 ዓመታት የቆዩ ሚስዮናውያን ባልና ሚስት 60 ሰዎች ራሳቸውን ወስነው እንዲጠመቁ ረድተዋል። እነዚህ ባልና ሚስት በአሁን ጊዜ 30 የሚሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ሲኖሯቸው ከእነዚህ ውስጥ 22ቱ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ይገኛሉ። እንዲህ ዓይነቱ መንፈሳዊ መከር የበዛበት የአሁኑ ወቅት ሚስዮናዊ ሆኖ ለማገልገል አመቺ ነው።
በጥድፊያ ስሜት መመሥከር
የመጨረሻውን ንግግር ያቀረበው የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ጌሪት ሎሽ ነው። የንግግሩ ጭብጥ “በጌታ ቀን ውስጥ ስለ አምላክና ስለ ኢየሱስ መመሥከር” የሚል ነበር። በራእይ መጽሐፍ ውስጥ “ምሥክር”፣ “ምሥክሮች” እንዲሁም “መመሥከር” የሚሉት ቃላት ለ19 ጊዜያት ያህል ተደጋግመው ተጠቅሰዋል። በመሆኑም ይሖዋ ሕዝቦቹ ሊያከናውኑት የሚገባውን ሥራ በግልጽ አመልክቷል። እንዲህ ዓይነቱን ምሥክርነት የምንሰጠው ራእይ 1:9, 10) ይህ ቀን የጀመረው በ1914 ሲሆን እስከ ዘመናችንም ድረስ ዘልቋል፤ ወደ ፊትም ይቀጥላል። በራእይ 14:6, 7 ላይ እንደተገለጸው ስለ አምላክ የመመሥከሩ ሥራ መላእክታዊ ድጋፍ አለው። ስለ ኢየሱስ የመመሥከሩን ሥራ የመምራት ኃላፊነት በአደራ የተሰጠው ለቅቡዓን ክርስቲያን ቀሪዎች እንደሆነ ራእይ 22:17 ያሳያል። ሆኖም ሁላችንም ይህን በመሰለው መብት የመካፈል አጋጣሚ አግኝተናል። በዚሁ ምዕራፍ በቁጥር 20 ላይ ኢየሱስ “ቶሎ እመጣለሁ” ማለቱ ተዘግቦል። ወንድም ሎሽ፣ “‘የሕይወትን ውሃ በነፃ ውሰዱ’ የሚለውን ጥሪ ለሰዎች አውጁ። ኢየሱስ በቶሎ ይመጣል። እኛስ ዝግጁ ነን?” ሲል እዚያ የተገኙትን ሁሉ አሳስቧል።
መቼ ነው? “በጌታ ቀን” ውስጥ ነው። (በመጨረሻም በጊልያድ ትምህርት ቤት ለ11 ዓመታት ሲያስተምር የቆየው ፍሬድ ራስክ የሁሉንም ተሰብሳቢዎች ልብ የነካ የምስጋና ጸሎት ለይሖዋ በማቅረብ ፕሮግራሙን ደመደመ። ይህ ጸሎት በጣም አስደሳች ለነበረው ለዚያ ዕለት ግሩም መደምደሚያ ነበር።
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ተማሪዎቹን የሚመለከት አኃዛዊ መረጃ
ተማሪዎቹ የተውጣጡባቸው አገሮች ብዛት:- 10
የተመደቡባቸው አገሮች ብዛት:- 25
የተማሪዎቹ ብዛት:- 56
አማካይ ዕድሜ:- 32.5
በእውነት ውስጥ የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ:- 16.4
በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ:- 12.1
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት 119ኛ ክፍል ተመራቂዎች
ከዚህ በታች ባለው ዝርዝር ለእያንዳንዱ ረድፍ ቁጥር የተሰጠው ከፊት ወደ ኋላ ሲሆን ስሞቹ የሰፈሩት ከግራ ወደ ቀኝ ነው።
(1) ሳንድራ ሄልገሰን፣ ሃነ ዳውጎር፣ አሩኒ ፒየርሉሲ፣ ኢዛቤል ጆሰፍ፣ ካርላ ራካኔሊ፤ (2) ትሪሸ በርጂ፣ ዴኔል በትለር፣ ጁላይ ፍሪድለን፣ ካርመል ኑንየስ፣ ሳንድሪን ፓቫዦ፣ ታማራ ዱመን፤ (3) ኦስካር ካማቾ፣ ሊነ ሊነድክቪስት፣ አን ብሩመር፣ ኢለ ቨሰልስ፣ ጄኒ በርተን፣ ኦሊቪያ ዉድሃውስ፣ አላን ዱመን፤ (4) አይክ ቴሬዮን፣ ሉሲ ኮነሊ፣ ካንድረ ፉርኒያ፣ አንጀሊካ ጊል፣ ካታሪና ዮንሶን፣ ሌ ሃሚልተን፤ (5) ዳርለ በርድ፣ ኢንግረድ ስክራይብነር፣ ቤተኒ ካማቾ፣ ሄዘር ላሺንስኪ፣ መሼል ሃለሃን፣ ኦልጋ ሊቡዳ፤ (6) አሊክስ ጆሰፍ፣ ማርቲን ሊነድክቪስት፣ ካርል ሄልገሰን፣ ዳኒ ኑንየስ፣ ሾን ስክራይብነር፣ ጆርደን ፉርኒያ፤ (7) ፍራንክ ፒየርሉሲ፣ ቴሪ ፓቫዦ፣ ክሊንተን ብሩመር፣ ፒተር ራካኔሊ፣ ቶም በትለር፣ ማርቲን ዉድሃውስ፣ የንስ ሊቡዳ፤ (8) ማይክ ላሺንስኪ፣ ስካት ፍሪድለን፣ ኢያን በርተን፣ ሚካ ቴሬዮን፣ ማይክል በርድ፣ ጄፍሪ በርጂ፤ (9) ቶርስተን ቨሰልስ፣ ዴኒስ ሃለሃን፣ ስቲቭ ኮነሊ፣ ዳኒየል ጊል፣ ፖል ዳውጎር፣ ሴት ሃሚልተን፣ ቶማስ ዮንሶን።