‘የእርስ በርስ ፍቅራችሁ እየጨመረ ነው’
‘የእርስ በርስ ፍቅራችሁ እየጨመረ ነው’
በ2004 ጃፓን በርካታ የተፈጥሮ አደጋዎች ደርሰውባታል። ከእነዚህም መካከል ኀይለኛ ዓውሎ ነፋስ፣ የጎርፍ መጥለቅለቅና የመሬት መንቀጥቀጥ ይገኙበታል። አደጋው የይሖዋ ምሥክሮችን ጨምሮ በብዙዎች ላይ ከባድ ጉዳት አድርሷል። (መክብብ 9:11) ይህም ቢሆን ግን፣ እነዚህ አደጋዎች የይሖዋ ምሥክሮቹ አንዳቸው ለሌላው የወንድማማች ፍቅር የሚያሳዩበት አጋጣሚ ከፍተውላቸዋል።—1 ጴጥሮስ 1:22
ለአብነት ያህል፣ በሐምሌ ወር በተከሰተው ኃይለኛ ዝናብ ሳቢያ በመካከለኛው ጃፓን የሚገኘው ወንዝ ሞልቶ አካባቢውን በማጥለቅለቁ ከ20 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች ቤቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል። በአንድ የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ደግሞ ውኃው ከወለሉ በላይ 1 ሜትር ያህል ከፍታ ላይ ደርሶ ነበር። በጎረቤት ጉባኤዎች የሚገኙ ምሥክሮች ወዲያውኑ ለእርዳታ ተሰባሰቡ። በመቶዎች የሚቆጠሩ ፈቃደኛ ሠራተኞች በጭቃ የቆሸሹትን ቤቶች አጸዱ። የመንግሥት አዳራሹ በሁለት ሳምንት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ጸድቶና ታድሶ አለቀ።
ጥቅምት 23 ቀን ደግሞ በሬክተር መለኪያ መጠኑ 6.8 የደረሰ የመሬት መንቀጥቀጥ በዚሁ አካባቢ ተከሰተ። ወደ 40 የሚጠጉ ሰዎች ለሕልፈተ ሕይወት የተዳረጉ ሲሆን ከ100,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለዋል። ውኃ፣ ጋዝና ኤሌክትሪክ ተቋርጦ ነበር። የመሬት መንቀጥቀጡ የተከሰተው ዕድሳት ከተደረገለት የመንግሥት አዳራሽ 50 ኪሎ ሜትር ያህል ብቻ ርቆ ቢሆንም እንኳ አዳራሹ ምንም ጉዳት አልደረሰበትም። ስለሆነም የመንግሥት አዳራሹ ወዲያውኑ ጊዜያዊ መጠለያ ሆነ። ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ደህና መሆናቸውን በፍጥነት ለማጣራት የሞከሩ ሲሆን ማንም የተጎዳ ወይም የሞተ አለመኖሩን ሲያውቁ ተረጋጉ። በነጋታው ጠዋት፣ በሐምሌ ወር በደረሰው የጎርፍ መጥለቅለቅ ጉዳት የደረሰባቸው ስድስት የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ወቅት ምግብና ልብስ ለማከፋፈል በፈቃደኝነት ራሳቸውን አቀረቡ። የመሬት መንቀጥቀጡ ከተከሰተ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ የእርዳታ ቁሳቁሶች መከፋፈል ጀመሩ።
አንድ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “በጎርፍ መጥለቅለቅ ጉዳት ደርሶባቸው የነበሩት ወንድሞች በመሬት መንቀጥቀጡ ለተጎዱት እርዳታ ማድረጋቸው [ቀደም ሲል] ለተደረገላቸው ነገር አመስጋኝ መሆናቸውን ለማሳየት የሚያስችል አጋጣሚ እንደሆነ ተሰምቷቸዋል። ከማለዳ ጀምረው እስከ ሌሊት በትጋት የሠሩ ሲሆን ፊታቸውም በደስታ ያበራ ነበር!”
የጎርፍ መጥለቅለቅም ሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ በፍቅር የተሳሰረውን የይሖዋ ምሥክሮች ክርስቲያናዊ የወንድማማች ማኅበር አይበግረውም። በተቃራኒው፣ እንደዚህ ዓይነት አደጋዎች ሲያጋጥሙ ክርስቲያኖች ጳውሎስ ‘የእርስ በርስ ፍቅራችሁም እየጨመረ መጥቷል’ በማለት በተሰሎንቄ ለነበሩት የእምነት አጋሮቹ የተናገራቸውን ቃላት በተግባር ለመመልከት ችለዋል።—2 ተሰሎንቄ 1:3