ከአምላክ ጋር በመሄድ መልካሙን እጨዱ
ከአምላክ ጋር በመሄድ መልካሙን እጨዱ
“ነፋስን ይዘራሉ፤ ዐውሎ ነፋስንም ያጭዳሉ።”—ሆሴዕ 8:7
1. ከይሖዋ ጋር መሄድ የምንችለው እንዴት ነው?
አደገኛ በሆነ አካባቢ በምንጓዝበት ጊዜ ቦታውን ጠንቅቆ የሚያውቅ መሪ አብሮን መኖሩ አደጋ እንዳይደርስብን ጥበቃ ይሆነናል። መንገዱን ብቻችንን ከምንያያዘው ይልቅ እንዲህ ካለው መሪ ጋር መጓዙ የጥበብ እርምጃ ነው። በአንዳንድ መንገዶች ይህ ምሳሌ የምንገኝበትን ሁኔታ ጥሩ አድርጎ ይገልጸዋል። ይሖዋ፣ በዚህ ክፉ ዓለም ሰፊ ምድረ በዳ ውስጥ በምሳሌያዊ አነጋገር እኛን ለመምራት ፈቃደኛ መሆኑን ገልጾልናል። ጥበበኛ ከሆንን አካሄዳችንን በራሳችን ለማቅናት ከመሞከር ይልቅ ከእርሱ ጋር እንሄዳለን። ከአምላክ ጋር መሄድ የምንችለው እንዴት ነው? በቃሉ አማካኝነት የሚሰጠንን መመሪያ በመከተል ነው።
2. በዚህ ርዕስ ውስጥ የምንወያየው ስለምንድን ነው?
2 በመጀመሪያው የጥናት ርዕስ፣ በሆሴዕ ምዕራፍ 1 እስከ 5 ላይ የሚገኘውን ትንቢታዊ ድራማ ተመልክተናል። ከጥናቱ እንደተማርነው ድራማው ከአምላክ ጋር ለመሄድ የሚረዱ ተግባራዊ ትምህርቶች ይዟል። አሁን ደግሞ ከምዕራፍ 6 እስከ 9 ላይ ከሚገኘው ትንቢት አንዳንድ ጎላ ያሉ ነጥቦችን እንመርምር። በመጀመሪያ የእነዚህን አራት ምዕራፎች አጠቃላይ ይዘት ብንመለከት ጠቃሚ ይሆናል።
አጠቃላይ ይዘቱን በአጭሩ መቃኘት
3. በሆሴዕ ምዕራፍ 6 እስከ 9 ላይ የሚገኙትን ሐሳቦች በአጭሩ ግለጽ።
3 ይሖዋ፣ ሆሴዕን በዋነኝነት ለሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት ትንቢት እንዲናገር ልኮታል። ከአሥሩ ነገዶች መካከል ጉልህ ሥፍራ በሚይዘው በኤፍሬም ነገድ ስምም የሚጠራው ይህ ብሔር ከአምላክ ርቆ ነበር። በሆሴዕ ምዕራፍ 6 እስከ 9 ላይ ሕዝቡ የይሖዋን ቃል ኪዳን በመተላለፍና ክፋት በመፈጸም የክህደት መንገድ እንደተከተለ እንመለከታለን። (ሆሴዕ 6:7) እስራኤላውያን ወደ ይሖዋ ከመመለስ ይልቅ በዓለማዊ ሸሪኮቻቸው ተማምነዋል። መጥፎ ዘር መዝራታቸውን ስለቀጠሉ መጥፎ ፍሬ ያጭዳሉ። በሌላ አባባል የቅጣት ፍርድ የሚቀበሉበት ጊዜ ደርሷል። ሆኖም ሆሴዕ ደስ የሚያሰኙ ቃላትም ተናግሯል። ነቢዩ እስራኤላውያን ከልባቸው ንስሐ ከገቡ ወደ ይሖዋ ሊመለሱና ምሕረት ሊደረግላቸው እንደሚችል አረጋግጦላቸዋል።
4. ከሆሴዕ ትንቢት የሚገኙትን የትኞቹን ትምህርቶች እንመለከታለን?
4 በእነዚህ የሆሴዕ ትንቢት አራት ምዕራፎች ላይ ከአምላክ ጋር እንድንመላለስ የሚረዱ ተጨማሪ መመሪያዎች ማግኘት እንችላለን። ከእነዚህ ምዕራፎች የምናገኛቸውን ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ አራት ትምህርቶች እንመልከት:- (1) እውነተኛ ንስሐ የሚገለጸው በድርጊት እንጂ በቃል ብቻ አይደለም፤ (2) መሥዋዕት ብቻውን አምላክን ደስ አያሰኘውም፤ (3) ይሖዋ አምላኪዎቹ ከእርሱ በሚርቁበት ጊዜ ያዝናል እንዲሁም (4) መልካም ነገር ማጨድ ከፈለግን መልካም ነገር መዝራት ይኖርብናል።
እውነተኛ ንስሐ የሚገለጸው እንዴት ነው?
5. በሆሴዕ 6:1-3 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ፍሬ ነገር ተናገር።
5 በሆሴዕ ትንቢት ውስጥ ንስሐ ስለ መግባትና ስለ ምሕረት ብዙ ትምህርት እናገኛለን። ሆሴዕ 6:1-3 እንዲህ ይላል:- “ኑ፤ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ፤ እርሱ ሰባብሮናል፤ እርሱም ይጠግነናል፤ እርሱ አቍስሎናል፤ እርሱም ይፈውሰናል። ከሁለት ቀን በኋላ ያነቃናል፤ በእርሱም ፊት እንድንኖር፣ በሦስተኛው ቀን ያስነሣናል። እግዚአብሔርን እንወቀው፤ የበለጠ እናውቀውም ዘንድ እንትጋ፤ እንደ ንጋት ብርሃን፣ በእርግጥ ይገለጣል፤ ምድርን እንደሚያረሰርስ የበልግ ዝናብ፣ እንደ ክረምትም ዝናብ ወደ እኛ ይመጣል።”
6-8. የእስራኤላውያን ንስሐ ችግሩ ምን ነበር?
6 በዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኙትን ቃላት የተናገረው ማን ነው? አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን ከዳተኞቹ እስራኤላውያን የተናገሯቸው እንደሆኑና ታዛዥ ያልሆነው ሕዝብ ለይስሙላ ያህል ብቻ ንስሐ በመግባት በአምላክ ምሕረት አላግባብ እንደተጠቀመ የሚያሳይ ሐሳብ መሆኑን ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ ነቢዩ ሆሴዕ ሕዝቡ ወደ ይሖዋ እንዲመለስ በመማጸን የተናገረው መሆኑን ይገልጻሉ። በዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘውን ሐሳብ የተናገረው ማንም ይሁን ማን ወሳኙ ጥያቄ፣ አሥሩን ነገድ ባቀፈው መንግሥት ውስጥ የሚገኙት እስራኤላውያን በአጠቃላይ ከልባቸው ንስሐ ገብተው ወደ ይሖዋ ተመልሰዋል? የሚለው ነው። መልሱ አልተመለሱም ነው። ይሖዋ በሆሴዕ በኩል እንዲህ ብሏል:- “ኤፍሬም ሆይ፤ ምን ላድርግህ? ይሁዳ ሆይ፤ ምን ላድርግህ? ፍቅራችሁ [“ፍቅራዊ ደግነታችሁ፣” NW] እንደ ማለዳ ጉም፣ እንደሚጠፋም የጧት ጤዛ ነው።” (ሆሴዕ 6:4) በእርግጥም ይህ የአምላክ ሕዝቦች የነበሩበትን ያዘቀጠ መንፈሳዊ ሁኔታ የሚያጋልጥ አነጋገር ነው! ፍቅራዊ ደግነት ወይም ጽኑ ፍቅር የጠዋት ጀምበር ብቅ ስትል በኖ እንደሚጠፋ ጉም ከእስራኤል ጠፍቷል። ሕዝቡ የይምሰል ንስሐ ያሳዩ እንጂ ይሖዋ ምሕረት የሚገባቸው ሆነው አላገኛቸውም። ችግሩ ምን ነበር?
7 የእስራኤላውያን ንስሐ ከልብ የመነጨ አልነበረም። “ከልባቸው ወደ እኔ አይጮኹም፤ ነገር ግን በዐልጋቸው ላይ ሆነው ያለቅሳሉ” የሚለው በሆሴዕ 7:14 ላይ የሚገኘው ጥቅስ ይሖዋ በሕዝቡ ምን ያህል እንዳዘነ ያሳያል። ቁጥር 16 አክሎ “ወደ ከንቱ ነገር ተመለሱ” ወይም እንደ 1980 ትርጉም “ወደ ከንቱ አምልኮ ተመለሱ” ይላል። ሕዝቡ ከይሖዋ ጋር ለመታረቅ የሚያስፈልጋቸውን ለውጥ በማድረግ ከፍተኛ ደረጃ ወዳለው የይሖዋ አምልኮ ለመመለስ ፈቃደኛ አልነበሩም። በእርግጥም ከአምላክ ጋር ለመሄድ ልባዊ ፍላጎት አልነበራቸውም።
8 የእስራኤል ንስሐ ሌላም ችግር ነበረው። ሕዝቡ አሁንም ኃጢአት መሥራታቸውን አልተዉም ነበር፤ እንዲያውም ማታለልን፣ ግድያን፣ ስርቆትን፣ ጣዖት አምልኮንና ከሌሎች ብሔራት ጋር አጉል ወዳጅነት መመሥረትን ጨምሮ ብዙ ዓይነት ኃጢአቶች ይፈጽሙ ነበር። በውስጣቸው እንደ እሳት የሚነድ ክፉ ምኞት ስለነበራቸው በሆሴዕ 7:4 ላይ ‘በምድጃ’ ተመስለዋል። ታዲያ እንዲህ ባለው አስከፊ መንፈሳዊ ሁኔታ ውስጥ እያሉ ምሕረት ሊደረግላቸው ይገባል? በፍጹም! ሆሴዕ ዓመጸኞቹን ሰዎች በተመለከተ “እግዚአብሔር ክፋታቸውን ያስባል፤ ስለ ኀጢአታቸውም ይቀጣቸዋል” ሲል ተናግሯል። (ሆሴዕ 9:9) ሕዝቡ ምንም ዓይነት ምሕረት አያገኙም!
9. የሆሴዕ ትንቢት ስለ ንስሐና ስለ ምሕረት ምን ያስተምረናል?
9 ሆሴዕ ከተናገረው ነገር ስለ ንስሐና ስለ ምሕረት ምን እንማራለን? ከይሖዋ ምሕረት ለመጠቀም ከፈለግን ከልባችን ንስሐ መግባት እንደሚኖርብን ከእምነት የለሾቹ እስራኤላውያን የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ትምህርት እናገኛለን። እንዲህ ያለው ንስሐ የሚገለጸው እንዴት ነው? ይሖዋ በእንባ ወይም በባዶ ቃላት አይሞኝም። ልባዊ ንስሐ የሚገለጸው በተግባር ነው። አንድ ክፉ አድራጊ ምሕረት ማግኘት ከፈለገ የኃጢአተኝነት አካሄዱን እርግፍ አድርጎ መተውና አኗኗሩን ላቅ ያለው የይሖዋ አምልኮ ከሚጠይቀው ከፍተኛ የሥነ ምግባር መሥፈርት ጋር ማስማማት ይኖርበታል።
መሥዋዕት ብቻውን ይሖዋን አያስደስተውም
10, 11. ከእስራኤላውያን ታሪክ መመልከት እንደሚቻለው መሥዋዕት ብቻውን ይሖዋን የማያስደስተው ለምንድን ነው?
10 አሁን ደግሞ ከይሖዋ ጋር እንድንሄድ የሚረዳንን ሁለተኛ ነጥብ እንመልከት። ይህም መሥዋዕት ብቻውን ይሖዋን ደስ አያሰኘውም የሚለው ይሆናል። ሆሴዕ 6:6 ላይ ይሖዋ እንዲህ ብሏል:- “ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን [“ፍቅራዊ ደግነትን፣” NW]፣ ከሚቃጠልም መሥዋዕት ይልቅ እግዚአብሔርን ማወቅ እሻለሁና።” ይሖዋ የሚደሰተው ውስጣዊ ባሕርይ በሆነው ፍቅራዊ ደግነት ወይም ታማኝ ፍቅር እንዲሁም ስለ እርሱ በማወቅ እንደሆነ ልብ በል። ይሁን እንጂ ‘ጥቅሱ ይሖዋ “በመሥዋዕት” ወይም “በሚቃጠል መሥዋዕት” ደስ እንደማይለው የሚናገረው ለምንድን ነው? መሥዋዕት ማቅረብ የሙሴ ሕግ የሚያዝዘው ነገር አይደለም?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል።
11 አዎን፣ በሙሴ ሕግ ሥር መሥዋዕትና ቁርባን ማቅረብ ግዴታ ነበር። ይሁን እንጂ በሆሴዕ ዘመን የነበሩት እስራኤላውያን አንድ ከባድ ችግር ነበረባቸው። ለአምላክ ያደሩ መስለው ለመታየት ሲሉ ግዴታቸው እንደሆነ በማሰብ መሥዋዕትና ቁርባን የሚያቀርቡ አንዳንዶች እንደነበሩ ከሁኔታዎቹ መረዳት ይቻላል። በሌላ በኩል ደግሞ ኃጢአት መፈጸማቸውን አልተዉም። የኃጢአት ድርጊታቸው በልባቸው ምንም ዓይነት ታማኝ ፍቅር እንደሌለ አሳይቷል። በተጨማሪም አኗኗራቸው ስለ አምላክ ካላቸው እውቀት ጋር የሚስማማ ባለመሆኑ የአምላክን እውቀት ችላ ማለታቸውን አሳይተዋል። ሕዝቡ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ እስካልኖራቸውና የጽድቅ አኗኗር እስካልተከተሉ ድረስ የሚያቀርቡት መሥዋዕት ምን ዋጋ ይኖረዋል? መሥዋዕቶቻቸው በይሖዋ አምላክ ዘንድ አስጸያፊ ነበሩ።
12. ሆሴዕ 6:6 በዛሬው ጊዜ ለሚኖሩ ሰዎች ምን ማስጠንቀቂያ ይዟል?
12 የሆሴዕ ቃላት በዘመናችን ላሉ በርካታ የቤተ ክርስቲያን ተሳላሚዎች የማስጠንቀቂያ ትምህርት ይዘዋል። እነዚህ ሰዎች ለአምላክ መሥዋዕት የሚያቀርቡት ሃይማኖታዊ ሥራዎች በመሥራት ነው። ይሁን እንጂ አምልኮታቸው በዕለት ተዕለት አኗኗራቸው ላይ የሚያሳድረው አንዳችም በጎ ተጽዕኖ የለም። እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ልባቸው የአምላክን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙና ከኃጢአት ድርጊታቸው ተመልሰው ያገኙትን እውቀት ሥራ ላይ እንዲያውሉ ካልገፋፋቸው አምላክን ደስ ያሰኙታል ማለት ይቻላል? ማንም ሰው ቢሆን ሃይማኖታዊ ሥራዎች መሥራት በራሱ አምላክን ያስደስታል ብሎ ማሰብ የለበትም። ይሖዋ ቃሉን ሳይታዘዙ ውጪያዊ የሆኑ የአምልኮ ሥርዓቶችን በሚፈጽሙ ሰዎች ፈጽሞ ደስ አይሰኝም።—2 ጢሞቴዎስ 3:5
13. በዛሬው ጊዜ ምን ዓይነት መሥዋዕት እናቀርባለን? ሆኖም መሥዋዕታችን ተቀባይነት እንዲያገኝ ከፈለግን ምን ልናስታውሰው የሚገባ ነገር አለ?
13 እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን መሥዋዕት ብቻውን አምላክን እንደማያስደስት እንገነዘባለን። ለይሖዋ የእንስሳት መሥዋዕት እንደማናቀርብ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ “የምስጋናን መሥዋዕት ይኸውም ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ” እናቀርባለን። (ዕብራውያን 13:15) ለአምላክ በምናቀርበው እንዲህ ያለ መንፈሳዊ መሥዋዕት አማካኝነት የምንሠራውን ኃጢአት ማካካስ እንችላለን ብለን በማሰብ በሆሴዕ ዘመን እንደነበሩት ኃጢአተኛ እስራኤላውያን ዓይነት ድርጊት ላለመፈጸም መጠንቀቃችን በጣም አስፈላጊ ነው። በስውር ዝሙት ትፈጽም የነበረችን አንዲት ወጣት እንደ ምሳሌ እንመልከት። “ኃጢአቴን ይሸፍንልኝ ይሆናል ብዬ በማሰብ የመስክ አገልግሎት እንቅስቃሴዬን ከፍ አደረግኩ” በማለት ከጊዜ በኋላ ተናግራለች። ይህ ዓመጸኞቹ እስራኤላውያን ካደረጉት ነገር ጋር ይመሳሰላል። ለይሖዋ የምናቀርበው የምስጋና መሥዋዕት በእርሱ ዘንድ ተቀባይነት ሊያገኝ የሚችለው ከትክክለኛ የልብ ዝንባሌና ከአምላካዊ ባሕርይ የመነጨ ሲሆን ብቻ ነው።
ይሖዋ አምላኪዎቹ ከእርሱ ሲርቁ ያዝናል
14. የሆሴዕ ትንቢት ስለ አምላክ ስሜት ምን ይገልጽልናል?
14 በሆሴዕ ምዕራፍ 6 እስከ 9 ላይ የምናገኘው ሦስተኛ ትምህርት ይሖዋ አምላኪዎቹ ከእርሱ ሲርቁ ምን ይሰማዋል የሚለው ነው። ይሖዋ በአንድ በኩል ርኅሩኅ በሌላ በኩል ደግሞ ጥብቅ እርምጃ የሚወስድ አምላክ ነው። ከኃጢአታቸው ንስሐ ለሚገቡ ሰዎች የሚራራ ከመሆኑም በላይ እንዲህ በማድረጋቸው ደስ ይለዋል። በሌላ በኩል ግን ሕዝቡ ንስሐ ለመግባት ፈቃደኛ በማይሆንበት ጊዜ ኃይለኛና ወሳኝ እርምጃ ይወስዳል። አምላክ በጥልቅ ስለሚያስብልን ከእርሱ ጋር በታማኝነት ስንሄድ ደስ ይለዋል። መዝሙር 149:4 ይሖዋ “በሕዝቡ ደስ ይለዋል” ይላል። ይሁንና አገልጋዮቹ ታማኝ ሳይሆኑ ሲቀሩ አምላክ ምን ይሰማዋል?
15. በሆሴዕ 6:7 መሠረት አንዳንድ እስራኤላውያን ምን ያደርጉ ነበር?
15 ይሖዋ ታማኝ ስላልነበሩት እስራኤላውያን ሲናገር “እንደ አዳም ቃል ኪዳንን ተላለፉ፤ በዚያም ለእኔ ታማኝ አልነበሩም” ብሏል። (ሆሴዕ 6:7) “ታማኝ አልነበሩም” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “መክዳት፣ ማታለል” የሚል ትርጉምም አለው። በሚልክያስ 2:10-16 ላይ ይኸው የዕብራይስጥ ቃል ለትዳር ጓደኞቻቸው ታማኝ ያልነበሩት እስራኤላውያን የፈጸሙትን የክህደት ድርጊት ለመግለጽ ተሠርቶበታል። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ ይህ ቃል ሆሴዕ 6:7 ላይ ስለተሠራበት መንገድ ሲገልጽ “በጋብቻ የተጣመሩ ሰዎች በግለሰብ ደረጃ በትዳር ውስጥ የሚያንጸባርቁትን ባሕርይ ለመግለጽ የገባ ምሳሌያዊ አነጋገር ነው። . . . አፍቃሪ በሆነው ወገን ላይ የተፈጸመን በደል የሚያመለክት ሁኔታ ነው” ይላል።
16, 17. (ሀ) እስራኤላውያን በብሔር ደረጃ ከአምላክ ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን ምን አደረጉ? (ለ) እኛስ በምንወስዳቸው እርምጃዎች ረገድ ምን ማስታወስ ይኖርብናል?
16 ይሖዋ ከእስራኤል ብሔር ጋር ቃል ኪዳን በመግባቱ ምክንያት በምሳሌያዊ ሁኔታ ሚስቱ እንደሆነች ተናግሯል። ስለዚህ ሕዝቦቹ የገቡትን ቃል ኪዳን በማፍረሳቸው ምንዝር እንደፈጸሙ ይቆጠራል። አምላክ እንደ አንድ ታማኝ ባል የነበረ ቢሆንም ሕዝቦቹ ግን ከዱት!
17 እኛስ? አምላክ ከእርሱ ጋር መሄድ አለመሄዳችን ያሳስበዋል። “እግዚአብሔር ፍቅር” መሆኑንና የምንወስዳቸው እርምጃዎች ስሜቱን እንደሚነኩት ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው። (1 ዮሐንስ 4:16) የተሳሳተ አካሄድ ከተከተልን ይሖዋን ልናሳዝነው እንችላለን፤ ድርጊታችንም እንደማያስደስተው ግልጽ ነው። ይህንን በአእምሯችን መያዛችን በፈተና ላለመውደቅ ጠንካራ መከላከያ ይሆነናል።
መልካም የሆነውን ማጨድ የምንችለው እንዴት ነው?
18, 19. በሆሴዕ 8:7 ላይ ምን መሠረታዊ ሥርዓት እናገኛለን? ይህስ በእስራኤላውያን ላይ የተፈጸመው እንዴት ነው?
18 ከሆሴዕ ትንቢት የምናገኘውን አራተኛ ትምህርት ይኸውም መልካም የሆነውን እንዴት ማጨድ እንደምንችል እንመልከት። ሆሴዕ “ነፋስን ይዘራሉ፤ ዐውሎ ነፋስንም ያጭዳሉ” በማለት እስራኤላውያን የተከተሉት የክህደት ጎዳና የማያዋጣና ከንቱ መሆኑን ገልጿል። (ሆሴዕ 8:7) እዚህ ላይ ነቢዩ ፈጽሞ ልንዘነጋው የማይገባ መሠረታዊ ሥርዓት ጠቅሷል:- አሁን በምናደርገው እና ወደፊት በሚደርስብን ነገር መካከል ቀጥተኛ ዝምድና አለ። ይህ መሠረታዊ ሥርዓት በከዳተኞቹ እስራኤላውያን ላይ በትክክል የተፈጸመው እንዴት ነው?
19 እስራኤላውያኑ በኃጢአት ጎዳና በመጽናት መጥፎ ዘር ዘርተዋል። ታዲያ ምንም ቅጣት ሳይደርስባቸው በዚሁ አካሄዳቸው መቀጠል ይችላሉ? በፍጹም! ሆሴዕ 8:13 “[ይሖዋ] ክፋታቸውን ያስታውሳል፤ ኀጢአታቸውን ይቀጣል” ይላል። ሆሴዕ 9:17 ደግሞ “ባለመታዘዛቸው ምክንያት፣ አምላኬ ይጥላቸዋል፤ በአሕዛብም መካከል ተንከራታች ይሆናሉ” ይላል። ይሖዋ እስራኤላውያንን ለሠሩት ኃጢአት ተጠያቂ ያደርጋቸዋል። መጥፎ ዘር ስለዘሩ መጥፎ ምርት ያጭዳሉ። አሦራውያን በ740 ከክርስቶስ ልደት በፊት አሥሩን ነገዶች ያቀፈውን የእስራኤል መንግሥት ገልብጠው ነዋሪዎቹን በግዞት በወሰዱበት ጊዜ እስራኤላውያን የአምላክን የቅጣት ፍርድ ተቀብለዋል።
20. የእስራኤላውያን ታሪክ ምን ያስተምረናል?
20 በእነዚህ እስራኤላውያን ላይ የደረሰው ነገር አንድ ሊሻር የማይችል ሐቅ ያስገነዝበናል:- የዘራነውን ያንኑ እናጭዳለን። የአምላክ ቃል “አትታለሉ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ያንኑ ያጭዳል” በማለት ያስጠነቅቀናል። (ገላትያ 6:7) መጥፎ ዘር ከዘራን መጥፎ ፍሬ እናጭዳለን። ለምሳሌ ያህል፣ ሥነ ምግባር የጎደለው አኗኗር የሚከተሉ ሰዎች መራራ ውጤት ያጭዳሉ። ንስሐ የማይገባ ኃጢአተኛም አሳዛኝ ፍሬ ያጭዳል።
21. መልካም የሆነውን ማጨድ የምንችለው እንዴት ነው?
21 ታዲያ መልካሙን ማጨድ የምንችለው እንዴት ነው? ቀላል ምሳሌ በመጠቀም ለዚህ ጥያቄ መልስ መስጠት ይቻላል። አንድ ገበሬ ስንዴ ማምረት ከፈለገ በቆሎ ይዘራል? በፍጹም! ገበሬው ማጨድ የፈለገውን መዝራት ይኖርበታል። በተመሳሳይ እኛም መልካም ነገር ማጨድ ከፈለግን መልካም ነገር መዝራት ይገባናል። መልካም ነገር ማጨድ ማለትም በአሁኑ ጊዜ አርኪ ሕይወት፣ ወደፊት ደግሞ በአምላክ አዲስ ሥርዓት ውስጥ የዘላለም ሕይወት ማግኘት ትፈልጋላችሁ? ከሆነ ከአምላክ ጋር በመሄድና ከጽድቅ ሕግጋቱ ጋር ተስማምታችሁ በመኖር መልካም የሆነውን መዝራታችሁን መቀጠል ይኖርባችኋል።
22. ከሆሴዕ 6 እስከ 9 ባሉት ምዕራፎች ውስጥ ምን ትምህርት አግኝተናል?
22 ከሆሴዕ 6 እስከ 9 ባሉት ምዕራፎች ውስጥ ከአምላክ ጋር እንድንሄድ የሚረዱንን አራት ቁም ነገሮች አግኝተናል:- (1) እውነተኛ ንስሐ የሚገለጸው በተግባር ነው፤ (2) መሥዋዕት ብቻውን አምላክን አያስደስትም፤ (3) ይሖዋ አምላኪዎቹ ከእርሱ ሲርቁ ያዝናል እንዲሁም (4) መልካም ነገር ለማጨድ መልካም ነገር መዝራት ይኖርብናል። የዚህ መጽሐፍ የመጨረሻ አምስት ምዕራፎች ከአምላክ ጋር እንድንሄድ የሚረዱን እንዴት ነው?
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• እውነተኛ ንስሐ የሚገለጸው እንዴት ነው?
• በሰማይ የሚኖረው አባታችን በመሥዋዕቶች ብቻ የማይደሰተው ለምንድን ነው?
• አምላክ አገልጋዮቹ ሲርቁት ምን ይሰማዋል?
• መልካም የሆነውን ለማጨድ ምን መዝራት አለብን?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የእስራኤል ታማኝ ፍቅር እንደ ጠዋት ጉም ጠፍቷል
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እስራኤላውያን በውስጣቸው የሚነድድ ክፉ ምኞት ስለነበራቸው እንደ ምድጃ ሆነው ነበር
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ የሕዝቡን መሥዋዕት ያልተቀበለው ለምን ነበር?
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መልካሙን ለማጨድ መልካሙን መዝራት አለብን