ፍትሕ የተዛባበት ዓለም
ፍትሕ የተዛባበት ዓለም
ፍትሕ በተዛባበት ዓለም ውስጥ እንኖራለን ቢባል አትስማማም? እንደምትስማማ አያጠራጥርም። የፈለገው ዓይነት ተሰጥኦ ቢኖረን ወይም ሕይወታችንን የቱንም ያህል በእቅድ ብንመራ እነዚህ ነገሮች ሀብትና ስኬት ሌላው ቀርቶ ምግብ እንኳ ለማግኘት ዋስትና ሊሆኑን እንደማይችሉ የታወቀ ነው። አብዛኛውን ጊዜ ሁኔታው በጥንት ዘመን የኖረው ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “እንጀራ ለጥበበኞች፣ ወይም ባለጠግነት ለብልኆች፣ ወይም ሞገስ ለዐዋቂዎች አይሆንም” ብሎ እንደተናገረው ነው። እንዲህ የማይሆነው ለምንድን ነው? ሰሎሞን ‘ጊዜና አጋጣሚ ሁሉን ይገናኛቸዋል’ በማለት ምክንያቱን ይነግረናል።—መክብብ 9:11 NW
‘ሳይታሰብ የሚመጣ ክፉ ጊዜ’
አዎን፣ ‘ጊዜና አጋጣሚ’ የሚለው አነጋገር አብዛኛውን ጊዜ በአጉል ሰዓት አጉል ቦታ መገኘት ማለት ሲሆን በጥንቃቄ የነደፍነውን እቅድ ሊያበላሽብን እንዲሁም የጓጓንለትን ተስፋ ሊያጨልምብን ይችላል። ሰሎሞን እንደተናገረው “ዓሦች በክፉ መረብ እንደሚያዙ፣ ወይም ወፎች በወጥመድ እንደሚጠመዱ” እኛም ‘ሳናስበው በሚመጣብን ክፉ ጊዜ እንጠመዳለን።’ (መክብብ 9:12) ለምሳሌ ያህል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አርሰው ቤተሰቦቻቸውን ለመመገብ ያለመታከት ይሠራሉ። ሆኖም ዝናብ ጠፍቶ ሰብላቸው በድርቅ ሲመታ ‘ክፉ ጊዜ’ ድንገት ይመጣባቸዋል።
እንዲህ ባለ ወቅት አንዳንዶች እርዳታ ለመስጠት ይሞክራሉ፤ ይሁን እንጂ የዓለም ኅብረተሰብ ‘የክፉ ጊዜ’ ሰለባ ለሆኑ ሰዎች የሚሰጠው እርዳታ አብዛኛውን ጊዜ ሚዛናዊነት የሚጎድለው ይመስላል። ለምሳሌ ያህል፣ በቅርብ ዓመት በረሃብ ላይ በተደረገው ዘመቻ “ለመላው [የአፍሪካ] አህጉር የተሰጠው እርዳታ ለባሕረ ሰላጤው ጦርነት ከተመደበው ገንዘብ በአምስት ጊዜ ያንሳል” በማለት አንድ የታወቀ የእርዳታ ድርጅት አስታውቋል። እነዚህ አገሮች በአንድ አህጉር ውስጥ ረሃብ ያስከተለውን ሥቃይና መከራ ለማስታገስ ከሰጡት እርዳታ ይልቅ በአንዲት አገር ውስጥ ጦርነት ለማካሄድ የመደቡት ገንዘብ በአምስት እጥፍ የሚበልጥ መሆኑ በእርግጥ ፍትሐዊ ነው? በተጨማሪም ብዙዎች በበለጸጉበት በዚህ ወቅት ላይ በምድር ከሚኖሩት አራት ሰዎች መካከል አንዱ በፍጹም ድህነት ተቆራምዶ የሚኖር መሆኑ ወይም ደግሞ በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕፃናት ቢታከሙት በቀላሉ ሊድን በሚችል በሽታ መሞታቸው ፍትሐዊ ነው? ፍትሐዊ እንዳልሆነ አይካድም!
እርግጥ ነው፣ ‘ክፉ ጊዜ ሳይታሰብ’ የሚመጣው ‘በጊዜና አጋጣሚ’ ብቻ አይደለም። ከአቅማችን በላይ የሆኑ ብርቱ ኃይሎች ሕይወታችንን ሊቆጣጠሩና በሚደርስብን ነገር ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ። በ2004 የበልግ
ወራት ሩሲያ ውስጥ በሰሜን ኦሴሺያ ግዛት የተፈጸመው ነገር ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ ይሆነናል። በዚያ ወቅት በአሸባሪዎችና በደኅንነት ኃይሎች መካከል በተፈጠረው ከባድ ግጭት በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለው ነበር። ሕይወታቸውን ካጡት ውስጥ አብዛኛዎቹ ለመጀመሪያ ጊዜ ትምህርት ቤት የሄዱ ሕፃናት ነበሩ። በዚያ አሳዛኝ ክስተት ወቅት አንዳንዶች መሞታቸው ሌሎች ደግሞ መትረፋቸው እንዲያው የአጋጣሚ ጉዳይ ቢሆንም ለዚህ ‘ክፉ ጊዜ’ መከሰት ዋነኛው መንስኤ የሰዎች ግጭት ነው።ዓለም በዚህ ሁኔታ ይቀጥል ይሆን?
አንዳንድ ሰዎች በዓለም ላይ ስለሚታየው የፍትሕ መዛባት ሲያወሩ “ምን ይደረግ፣ ሕይወት እንዲህ ነው፤ በፊትም እንዲሁ ነበር፤ ወደፊትም እንዲሁ ይቀጥላል” ይላሉ። እንደ እነርሱ አባባል ከሆነ ጉልበት ያለው ሁልጊዜ ደካማውን እንደጨቆነና ሀብታሙም የድሃውን ጉልበት እንደበዘበዘ ይኖራል። ይህ ሁኔታ ‘ከጊዜና አጋጣሚ’ ጋር ተዳምሮ የሰው ዘር በምድር ላይ እስከኖረ ድረስ መሠቃየቱን ይቀጥላል ይላሉ።
በእርግጥ ዓለም በዚህ ሁኔታ ይቀጥል ይሆን? ችሎታቸውን በማስተዋል እና በጥበብ የሚጠቀሙ ሰዎች ለጥረታቸው ተገቢውን ወሮታ የሚያገኙበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? ማንኛውንም ነገር አድርጎ ቋሚና ዘላቂ ለውጥ ማምጣት የሚችል ይኖር ይሆን? ይህን በተመለከተ የሚቀጥለው ርዕሰ ጉዳይ የሚሰጠውን ሐሳብ ተመልከት።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
MAXIM MARMUR/AFP/Getty Images