የይሖዋን ልብ ደስ የሚያሰኝ ልግስና
የይሖዋን ልብ ደስ የሚያሰኝ ልግስና
ታሪኩ እንኳ ደስ የሚል አይደለም። ንግሥት ጎቶልያ ተንኮል በመሸረብና ሕይወት በማጥፋት በይሁዳ ዙፋን ወረሰች። የወራሽነት መብት ያላቸውን ንጉሣዊ ቤተሰቦች በሙሉ ጠራርጋ እንዳጠፋች ስለተሰማት ራሷን ንግሥት አድርጋ ሾመች። ይሖዋንና ሕጎቹን በጥልቅ ትወድድ የነበረችው ሌላዋ ሴት ልዕልት ዮሳቤት ግን የንጉሣውያን ቤተሰብ ልጅ የሆነውን ሕፃኑን ኢዮአስን በድፍረት ወስዳ ደበቀችው። ዮሳቤትና ባለቤቷ ሊቀ ካህኑ ዮዳሄ ወራሹን ለስድስት ዓመት ያህል በቤተ መቅደሱ እልፍኝ ውስጥ ሸሸጉት።—2 ነገሥት 11:1-3
ኢዮአስ ሰባት ዓመት ሲሞላው ሊቀ ካህኑ ዮዳሄ በሸፍጥ ስልጣን የቀማችውን ንግሥት ከዙፋን ለማውረድ የነደፈውን እቅድ በተግባር ማዋል ጀመረ። የመንግሥቱ ትክክለኛ ወራሽ የሆነውን ሕፃን ከሸሸገበት በማውጣት ዘውድ ጫነለት። የንጉሡ ጠባቂዎች ክፉዋን ንግሥት ጎቶልያን ከቤተ መቅደሱ ውስጥ ጎትተው ካወጧት በኋላ ገደሏት። ይህ ለሕዝቡ እፎይታና ደስታን አስገኘ። የዮሳቤትና የዮዳሄ ድርጊት በይሁዳ ምድር እውነተኛው አምልኮ ተመልሶ እንዲቋቋም አስተዋጽኦ አበርክቷል። ከሁሉም በላይ ግን የመሲሑ መገኛ የሆነው የዳዊት የንግሥና መሥመር እንዳይቋረጥ ታላቅ ሚና ተጫውተዋል።—2 ነገሥት 11:4-21
አዲስ የተተካው ንጉሥም የይሖዋን ልብ ደስ የሚያሰኝ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ይጠበቅበት ነበር። የይሖዋ ቤት እድሳት ያስፈልገው ነበር። ጎቶልያ በእብሪተኝነት የይሁዳ ብቸኛ ንግሥት ለመሆን መነሳቷ ቤተ መቅደሱ ቸል እንዲባል ብቻ ሳይሆን ለዝርፊያም እንዲጋለጥ ምክንያት ሆኖ ነበር። ስለሆነም ኢዮአስ ቤተ መቅደሱን ለማደስና ወደ ቀድሞ ይዞታው ለመመለስ ቆርጦ ተነሳ። ነገ ዛሬ ሳይል የይሖዋን ቤት ለማደስ የሚያስፈልገው የገንዘብ መዋጮ እንዲሰባሰብ የሚያዝ አዋጅ አስነገረ። እርሱም “ከሕዝብ ቈጠራ የተገኘውንና በስእለት የገባውን እንዲሁም በራስ ፈቃድ ለቤተ መቅደሱ የተሰጠውን የተቀደሰ ገንዘብ በሙሉ ሰብስቡ። እያንዳንዱም ካህን ገንዘቡን ከገንዘብ ያዡ እጅ ይቀበል፤ እንደ አስፈላጊነቱም በቤተ መቅደሱ ውስጥ የፈረሰውን ለማደስ ይዋል” አላቸው።—2 ነገሥት 12:4, 5
ሕዝቡ በፈቃደኝነት መዋጮ አደረገ። ይሁንና ካህናቱ ቤተ መቅደሱን እንዲያድሱ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በሙሉ ልባቸው አልተወጡም። በመሆኑም ንጉሡ ራሱ ጉዳዩን በበላይነት ለመከታተል የወሰነ ከመሆኑም በላይ ማንኛውም መዋጮ በአንድ የተለየ ሣጥን ውስጥ እንዲጠራቀም አዘዘ። ሁኔታውን እንዲቆጣጠርም ዮዳሄን ሾመው፤ ይህን አስመልክቶ ዘገባው እንደሚከተለው ይላል፦ “ከዚያም ካህኑ ዮዳሄ አንድ ሣጥን ወስዶ በመክደኛው ላይ ቀዳዳ አበጀለት፤ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በሚያ[ስ]ገባው በስተቀኝ በኩል በመሠዊያው አጠገብ አኖረው። በራፉን የሚጠብቁት ካህናትም ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚመጣውን ገንዘብ በሙሉ በሣጥኑ ውስጥ ያስገቡ ነበር። በሣጥኑም ውስጥ ብዙ ገንዘብ መኖሩን በሚያዩበት ጊዜ ሁሉ፣ የንጉሡ ጸሐፊና ሊቀ ካህናቱ መጥተው ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የገባውን 2 ነገሥት 12:9-12
ገንዘብ ቈጥረው በየከረጢቱ በማስገባት ቋጥረው ያኖሩት ነበር። የገንዘቡ ልክም ተመዝኖ ከታወቀ በኋላ፣ የቤተ መቅደሱን ሥራ በኀላፊነት እንዲያሠሩ ለተመደቡት ሰዎች ገንዘቡን ያስረክቧቸዋል፤ ይህም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለሚሠሩ አናጢዎችና ግንበኞች፣ ለድንጋይ ጠራቢዎችና ለድንጋይ ቅርጽ አውጭዎች የሚከፈል እንዲሁም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ለሚታደስበት ዕንጨትና ጥርብ ድንጋይ መግዣ የሚውል ነበር።”—ሕዝቡ ከልብ የመነጨ ምላሽ ሰጥቶ ነበር። የይሖዋ አምልኮ አክብሮት በተሞላበት መንገድ መከናወኑን እንዲቀጥል ቤተ መቅደሱ ታድሷል። የተዋጣው ገንዘብ በሙሉ በአግባቡ ጥቅም ላይ ውሎ ነበር። ንጉሥ ኢዮአስም ይህን በሚገባ ተከታትሏል።
በዘመናችንም የይሖዋ ድርጅት፣ የይሖዋን አምልኮ ለማራመድ የሚደረገው የገንዘብ መዋጮ ሙሉ ለሙሉ ለታለመለት ዓላማ መዋሉን በጥንቃቄ ይከታተላል። እንዲሁም ጥንት እስራኤላውያን እንዳደረጉት ሁሉ እውነተኛ ክርስቲያኖችም አስፈላጊውን ምላሽ በሙሉ ልባቸው በመስጠት ላይ ይገኛሉ። ባለፈው የአገልግሎት ዓመት የመንግሥቱን ፍላጎት ለማሳካት የገንዘብ መዋጮ ካደረጉት መካከል አንተም ትኖርበት ይሆናል። ያደረግኸው መዋጮ ጥቅም ላይ ከዋለባቸው መንገዶች ውስጥ አንዳንዶቹን እስቲ እንመልከት።
ሕትመት
በዓለም ዙሪያ ለጥናትና ለስርጭት የተዘጋጁ የሕትመት ውጤቶች፦
• መጻሕፍት፦ 47,490,247
• ቡክሌቶች፦ 6,834,740
• ብሮሹሮች፦ 167,854,462
• የቀን መቁጠሪያዎች፦ 5,405,955
• መጽሔቶች፦ 1,179,266,348
• ትራክቶች፦ 440,995,740
• የቪዲዮ ካሴቶች፦ 3,168,611
የሕትመት ሥራው በአፍሪካ፣ በሰሜን፣ በመካከለኛው እና በደቡብ አሜሪካ፣ በእስያ፣ በአውሮፓ እንዲሁም በፓስፊክ ውቅያኖስ አገሮችና ደሴቶች ውስጥ የሚከናወን ሲሆን በአጠቃላይ በ19 አገሮች ይካሄዳል።
“ካትሊን ሜይ እባላለሁ፤ የስምንት ዓመት ልጅ ነኝ። ለሕትመት ሥራው ድጋፍ ይሆን ዘንድ ያለችኝን 28 የአሜሪካ ዶላር ልኬላችኋለሁ። ትንሿ እህታችሁ ካትሊን።”
“ቤተሰባችን ስለ አዳዲሶቹ ማተሚያዎች ለመወያየት ተሰብስቦ ነበር። የ11 እና የ9 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ልጆቻችን ካጠራቀሙት ገንዘብ ላይ በመላክ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ ወስነዋል። ያደረጉትን መዋጮ ከእኛ ጋር ጨምረን ስንልክላችሁ ደስ ይለናል።”
ግንባታ
የይሖዋ ምሥክሮችን እንቅስቃሴ ለመደገፍ ከተካሄዱት የግንባታ ፕሮጀክቶች መካከል አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው፦
• የገንዘብ አቅማቸው ውስን በሆኑ አገሮች የተገነቡ የመንግሥት አዳራሾች፦ 2,180
• ትላልቅ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፦ 15
• ቅርንጫፍ ቢሮዎች፦ 10
• ዓለም አቀፍ የሙሉ ጊዜ ፈቃደኛ ሠራተኞች፦ 2,342
“በዚህ ሳምንት በአዲሱ የመንግሥት አዳራሻችን ለመጀመሪያ ጊዜ ተሰበሰብን። አባታችንን ይሖዋ አምላክን የምናወድስበት ተስማሚ ስፍራ ስላገኘን እጅግ ተደስተናል። ተጨማሪ የመንግሥት አዳራሾችን በመገንባት ለሚያስፈልጉን ነገሮች ትኩረት ስለሰጣችሁ ይሖዋንም ሆነ እናንተን እናመሰግናለን። የመንግሥት አዳራሻችን ለአካባቢያችን ልዩ ድምቀት ሰጥቷል።”—ቺሊ
“የይሖዋ ድርጅት ላደረገልን እርዳታ የወንድሞችና የእህቶች ምስጋና የላቀ ነው። ከግንባታ አገልጋዮች ጋር ያሳለፍነውን ግሩም ጊዜ እስካሁን ድረስ እያነሳን እንጨዋወታለን።”—ሞልዶቫ
“እኔና ባለቤቴ የተጋባንበትን 35ኛ ዓመት በቅርቡ አክብረን ነበር። ለዚህ በዓል አንዳችን ለሌላው ምን ስጦታ እንደምንሰጥ ለመወሰን እየጣርን ሳለ ለይሖዋና ለድርጅቱ አንድ ነገር ማድረግ እንዳለብን ተሰማን፤ ምክንያቱም የእነርሱ ድጋፍ ባይጨመርበት ኖሮ ትዳራችን አይሰምርም ነበር። ከዚህ ደብዳቤ ጋር የላክንላችሁን ገንዘብ አቅማቸው ውስን በሆኑ አገሮች የሚሠሩ የመንግሥት አዳራሾችን ለመደገፍ ቢውል ደስ ይለናል።”
“በቅርብ ጊዜ ውርስ አገኘሁ። ይሁንና የምፈልገው ጥቂት ነው፤ የሚያስፈልገኝ ደግሞ ከዚያ ያነሰ ነው። የላክሁላችሁን ገንዘብ የመንግሥት አዳራሽ በጣም በሚያስፈልጋቸው አገሮች የምታደርጉትን ግንባታ ለመደገፍ ይዋልልኝ።”
በአደጋ የተጎዱትን መርዳት
በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ብዙውን ጊዜ የተፈጥሮም ሆኑ ሰው ሠራሽ አደጋዎች ድንገት ይከሰታሉ። በመሆኑም በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች በአደጋ በተጎዱ አካባቢዎች የሚኖሩ ወንድሞቻቸውን ለመርዳት ሲሉ ተጨማሪ መዋጮ ያደርጋሉ። ለማስታወስ ያህል በአደጋ ለተጎዱ አካባቢዎች ተብሎ የሚደረገው መዋጮ የሚታቀፈው በዓለም አቀፉ ሥራ ውስጥ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች እርዳታ ካደረጉባቸው ቦታዎች የሚከተሉት ይገኙበታል፦
• አፍሪካ
• እስያ
• የካሪቢያን አገሮች
• የፓስፊክ ደሴቶች
“አካባቢያችን በአውሎ ነፋስ በተጠቃ ጊዜ እኛን እንደገና ለማቋቋም አስፈላጊውን ነገር ሁሉ ስላደረጋችሁልን እኔም ሆንኩ ባለቤቴ እጅግ ልናመሰግናችሁ እንወዳለን። ቤታችንን አዲስ ጣሪያ ማልበስ ችለናል። አፋጣኝ ምላሽ ስለሰጣችሁን ከልብ እናደንቃችኋለን።”
“ስሜ ኮነር ሲሆን የ11 ዓመት ልጅ ነኝ። የሱናሚ አደጋ ያደረሰውን ጉዳት ስመለከት እኔም የበኩሌን ለመርዳት ወሰንኩ። ይህ ወንድሞቼንና እህቶቼን እንደሚረዳቸው ተስፋ አለኝ።”
የልዩ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች
በርካታ ክርስቲያኖች ወንጌላዊ በመሆን ወይም በቤቴል ቤቶች ውስጥ ሙሉ ጊዜያቸውን ያገለግላሉ። አንዳንድ ፈቃደኛ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች የሚረዱት በፈቃደኝነት በሚደረገው መዋጮ ነው። ከእነዚህ ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፦
• ሚስዮናውያን፦ 2,635
• ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች፦ 5,325
• ቤቴላውያን፦ 20,092
“ቤቴል ውስጥ ለማገልገል ዕድሜዬ ስለማይፈቅድ [የአምስት ዓመት ልጅ ነው] ይህን መዋጮ ከጥልቅ ፍቅር ጋር ልልክላችሁ እወዳለሁ። ሳድግ ቤቴል ገብቼ ጠንክሬ እሠራለሁ።”
የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ማስፋፋት
ኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮቹ ‘ሕዝቦችን ሁሉ ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ’ ተልእኮ ሰጥቷቸዋል። (ማቴዎስ 28:19) በዚህ ትእዛዝ መሠረት፣ የይሖዋ ምሥክሮች በ235 አገሮች በሚከናወነው የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት የመስበክና የማስተማር ሥራ ተጠምደዋል። በ413 ቋንቋዎችም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በማተም ያሰራጫሉ።
እውነት ነው፣ አንድ ክርስቲያን ብዙዎች ስለ አምላክና ስለ ዓላማዎቹ እንዲያውቁ ለመርዳት የሚለግሰው ከሁሉ የላቀ ስጦታ ጊዜውን ነው። የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎችን ለመርዳት ሲሉ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን ይሰዋሉ። በተጨማሪም ገንዘባቸውን በልግስና ይሰጣሉ፤ የሚያበረክቱት ይህን መሰሉ አስተዋጽኦ የይሖዋ ስምና ዓላማ በምድር ዙሪያ እንዲታወቅ በተለያዩ መንገዶች ጥቅም ላይ ይውላል። ይሖዋ ሌሎች ስለ እርሱ ብዙ እንዲያውቁ ለመርዳት የሚደረገውን ጥረት መባረኩን ይቀጥል ዘንድ እንመኛለን። (ምሳሌ 19:17) እንዲህ ዓይነቱ የፈቃደኝነት መንፈስ የይሖዋን ልብ ያስደስታል!—ዕብራውያን 13:15, 16
[ከገጽ 28-30 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
አንዳንዶች መዋጮ የሚያደርጉባቸው መንገዶች
ለዓለም አቀፉ ሥራ የሚደረጉ መዋጮዎች
ብዙዎች “ለዓለም አቀፉ ሥራ የሚደረግ መዋጮ—ማቴዎስ 24:14” ተብሎ የተለጠፈባቸው ሣጥኖች ውስጥ የሚጨምሩት የተወሰነ ገንዘብ ያስቀምጣሉ ወይም ይመድባሉ።
ጉባኤዎች የተዋጣውን ገንዘብ በአገራቸው ሥራውን ለሚቆጣጠረው የይሖዋ ምሥክሮች ቢሮ በየወሩ ይልካሉ። ከዚህ በተጨማሪ በፈቃደኝነት የሚደረጉ የገንዘብ መዋጮዎችን በቀጥታ Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania, Attention Treasurer’s Office, 25 Columbia Heights, Brooklyn, New York 11201-2483 በሚለው አድራሻ ወይም በአገራችሁ ለሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ መላክ ይቻላል። ቼኮች ከላይ ባለው አድራሻ ሲላኩ “ለይሖዋ ምሥክሮች” የሚከፈሉ መሆናቸው መገለጽ አለበት። ከውድ ማዕድናት የተሠሩ ጌጣጌጦችን ወይም ሌሎች ውድ ዕቃዎችንም መስጠት ይቻላል። የተላከው ዕቃ ሙሉ በሙሉ ስጦታ መሆኑን የሚገልጽ አጭር ደብዳቤ ተያይዞ መላክ ይኖርበታል።
ተመላሽ ሊሆን የሚችል ገንዘብ የሚሰጥበት ዝግጅት
አንድ ሰው ገንዘቡን የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ዓለም አቀፉን ሥራ ለማካሄድ በአደራ መልክ ሊሰጥና ሲያስፈልገው ማኅበሩን በመጠየቅ መልሶ ማግኘት ይችላል። ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ከላይ በተገለጸው አድራሻ መጠየቅ ይቻላል።
በእቅድ የሚደረግ ስጦታ
ገንዘብ በስጦታ ከመለገስና ተመላሽ ሊሆን የሚችል ገንዘብ ከመስጠት በተጨማሪ በመላው ዓለም የሚካሄደውን የመንግሥቱን ሥራ መደገፍ የሚቻልባቸው ሌሎች መንገዶችም አሉ። ይህም የሚከተሉትን ያጠቃልላል፦
ኢንሹራንስ፦ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የሕይወት ኢንሹራንስ ፖሊሲ ወይም የጡረታ ክፍያ ተጠቃሚ እንዲሆን ስም ሊዛወርለት ይችላል።
የባንክ ሒሳብ፦ የአገሩ ባንክ ደንብ በሚፈቅደው መሠረት የባንክ ሒሳቦች፣ ገንዘብ መቀመጡን የሚገልጽ የምሥክር ወረቀት ወይም የግል ጡረታ ሒሳቦች በአደራ ወይም በሞት ጊዜ የሚከፈል መሆኑ ተገልጾ ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ሊሰጥ ይችላል።
አክሲዮኖችና ቦንዶች፦ አክሲዮኖችንና ቦንዶችን በስጦታ መልክ ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር መስጠት ይቻላል።
ቋሚ ንብረት፦ ሊሸጥ ሊለወጥ የሚችል ቋሚ ንብረት በስጦታ መስጠት ወይም መኖሪያ ቤት በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ ባለ ንብረቱ በሕይወት እስካለ ድረስ ተጠቅሞበት ከዚያ በኋላ ማውረስ ይቻላል። አንድ ሰው ማንኛውንም የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤትነት ከማዛወሩ በፊት በአገሩ ከሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ጋር መነጋገር ይኖርበታል።
የስጦታ አበል፦ የስጦታ አበል አንድ ሰው ገንዘቡን ወይም የባለቤትነት መብትን የሚያረጋግጡ ሰነዶችን የይሖዋ ምሥክሮችን ወክሎ ለሚሠራው ማኅበር ለማዛወር የሚያደርገውን ዝግጅት ያመለክታል። በምላሹም ለጋሹ ወይም እርሱ የወከለው ግለሰብ በሕይወት እስካለ ጊዜ ድረስ የተወሰነ መጠን ያለው ገንዘብ በየዓመቱ በአበል መልክ ይከፈለዋል። ለጋሹ የስጦታ አበሉን ለማስተላለፍ ከተስማማበት ጊዜ አንስቶ የገቢ ግብር ቅናሽ ያገኛል።
ኑዛዜዎችና አደራዎች፦ ንብረት ወይም ገንዘብ በሕግ ፊት ተቀባይነት ባለው ኑዛዜ አማካኝነት ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በውርስ ሊሰጥ ወይም ማኅበሩ በአደራ የተሰጠው ንብረት ተጠቃሚ ተደርጎ ስሙ ሊዘዋወር ይችላል። አንድ ሃይማኖታዊ ድርጅት እንዲጠቀምበት በአደራ የተሰጠ ንብረት በቀረጥ ረገድ የሚያስገኛቸው አንዳንድ ጥቅሞች አሉ።
“በእቅድ የሚደረግ ስጦታ” የሚለው ሐረግ እንደሚያመለክተው እነዚህን የመሳሰሉ መዋጮዎች በሰጪው በኩል እቅድ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ያሳያሉ። የይሖዋ ምሥክሮችን ዓለም አቀፍ ሥራ በእቅድ በሚደረግ ስጦታ ለመደገፍ ለሚፈልጉ ግለሰቦች ጉዳዩን ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ ዓለም አቀፉን የመንግሥት ሥራ ለመደገፍ በእቅድ የሚደረግ ስጦታ የሚል ብሮሹር በእንግሊዝኛና በስፓንኛ ተዘጋጅቷል። ይህ ብሮሹር የተዘጋጀው ሰዎች ስጦታ ለመስጠት ወይም በሚሞቱበት ጊዜ በኑዛዜ ውርስ ለመተው የሚችሉባቸውን የተለያዩ መንገዶች አስመልክቶ መረጃ ለመስጠት ነው። ብዙዎች ይህን ብሮሹር ካነበቡ በኋላ ከራሳቸው የሕግ ወይም የቀረጥ አማካሪዎች ጋር በመማከር በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያከናውኑትን ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴና ሰብዓዊ እርዳታ ለመደገፍ ከመቻላቸውም በላይ እንዲህ በማድረጋቸው ከቀረጥ ጋር በተያያዘ የተሻለ ጥቅም ለማግኘት ችለዋል። ይህን ብሮሹር ለማግኘት በእቅድ የሚደረግ ስጦታን ጉዳይ የሚከታተለውን ቢሮ በቀጥታ መጠየቅ ይቻላል።
ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ከታች ያለውን አድራሻ ወይም ስልክ ቁጥር ተጠቅመህ በእቅድ የሚደረገውን ስጦታ ጉዳይ የሚከታተለውን ቢሮ መጠየቅ ትችላለህ። አሊያም በአገርህ ለሥራው አመራር ወደሚሰጠው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ሄደህ ማነጋገር ትችላለህ።
Charitable Planning Office
Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
100 Watchtower Drive,
Patterson, New York 12563-9204
ስልክ፦ (845) 306-0707
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Faithful video: Stalin: U.S. Army photo