“ወዲያውኑ ነጻ መውጣት ይችሉ ነበር”
“ወዲያውኑ ነጻ መውጣት ይችሉ ነበር”
የቀድሞው የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት የቻርለስ ደ ጎል የወንድም ልጅ የሆነችው ዠንቭዬቭ ደ ጎል በሰሜን ጀርመን፣ ራቨንስብሩክ በሚገኘው የናዚ ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ የነበሩትን የይሖዋ ምሥክሮች በግለሰብ ደረጃ ታውቃቸው ነበር። ነሐሴ 1945 በጻፈችው ደብዳቤ ከላይ ያሉትን ቃላት አስፍራለች።
ጥር 27, 1945 ናዚዎች በኦሽዊትዝ፣ ፖላንድ የሚገኘውን የማጎሪያ ካምፕ የለቀቁበት ቀን ነው። ከ1996 ጀምሮ በሂትለር ሦስተኛ ራይክ አገዛዝ ጭቆና ለደረሰባቸው ሰዎች መታሰቢያ እንዲሆን ይህ ቀን በጀርመን አገር ይከበራል።
የባዴን ዉርተምበርግ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት የሆኑት ፔቴ ሻትራውብ ጥር 27, 2003 ባደረጉት የመታሰቢያ ንግግር ላይ እንዲህ በማለት ተናግረው ነበር:- “በሃይማኖታቸው ወይም በፖለቲካዊ አመለካከታቸው ምክንያት መከራ የደረሰባቸው እንዲሁም የሂትለርን አገዛዝ ፈቃድ ከመፈጸም ይልቅ ሞትን የመረጡ ሁሉ በቃላት ልንገልጸው ከምንችለው በላይ ከፍ ያለ አክብሮት ይገባቸዋል። በወቅቱ ከነበሩት ሃይማኖቶች ሁሉ የሂትለር አገዛዝ ያቀረበውን ጥያቄ ፈጽሞ ያልተቀበሉት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ነበሩ፤ እጃቸውን በማንሳት ለሂትለር ሰላምታ ለመስጠት ፈቃደኛ አልነበሩም። የውትድርናም ሆነ የጉልበት ሥራ ለመሥራት እንዲሁም ‘ለመሪውና ለመንግሥቱ’ በታማኝነት ድጋፍ እንደሚሰጡ ለመግለጽ ፈቃደኛ አልሆኑም። ልጆቻቸውም ቢሆኑ የሂትለር የወጣቶች ንቅናቄ አባል አልነበሩም።”
ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ተከታዮቹ ሲናገር “እኔ ከዓለም እንዳልሆንሁ ሁሉ፣ እነርሱም ከዓለም አይደሉም” ብሏል። (ዮሐንስ 17:16) ስለዚህ የይሖዋ ምሥክሮች ከላይ እንደተገለጸው ዓይነት አቋም የወሰዱት በሃይማኖታዊ እምነታቸው ምክንያት ነበር። ሻትራውብ በመቀጠል እንዲህ ይላሉ:- “ከሌሎች በተለየ መልኩ ከእስር ነጻ የመውጣትና ከሞት የመትረፍ አጋጣሚ የነበራቸው ከወይን ጠጅ ጨርቅ የተሠራ ባለ ሦስት ማዕዘን ቅርጽ አርማ የተለጠፈበት ልብስ እንዲለብሱ ይገደዱ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ናቸው። ነጻ ለመውጣት እምነታቸውን እንደካዱ በሚገልጽ ቅጽ ላይ መፈረም ብቻ በቂ ነበር።”
ለአብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች እምነታቸውን መካድ ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነበር። በዚህም ምክንያት በናዚ አገዛዝ ወቅት ወደ 1,200 ገደማ የሚሆኑ ሕይወታቸውን ሲያጡ ሁለት መቶ ሰባ የሚያህሉት ደግሞ በሕሊናቸው ምክንያት በጦርነት አንካፈልም በማለታቸው ተገድለዋል። “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል!” የሚሉትን ቃላት ከመናገር አልፈው ተግባራዊ አድርገዋቸዋል።—የሐዋርያት ሥራ 5:29
የሰሜኑ ራይን ዌስትፋሊያ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት የሆኑት ኡልሪክ ሽሚድት የይሖዋ ምሥክሮች ልዩ ሰዎች እንዳልነበሩ ተናግረዋል። ላንታግ ኢንተርን የተባለው ብሮሹር እኚህ ሰው ያቀረቡትን ንግግር በመጥቀስ የይሖዋ ምሥክሮች “ሕሊናቸውን በመከተል ለሃይማኖታዊ እምነታቸው ጸንተው የቆሙ፣ ደፋሮችና በክርስቲያናዊ እምነታቸው የተነሳ የናዚን ርዕዮተ ዓለም የተቃወሙ ተራ ሰዎች” እንደሆኑ ገልጿል። ይሖዋ አምላክ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ሥር እያሉም ከእርሱ ጎን ታማኝ ሆነው በሚቆሙ አገልጋዮቹ እንደሚደሰት እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ምሳሌ 27:11 “ልጄ ሆይ፤ ጠቢብ ሁን፤ ልቤን ደስ አሰኘው፤ ለሚንቁኝ ሁሉ መልስ መስጠት እችል ዘንድ” ይላል።
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Courtesy of United States Holocaust Memorial Museum