በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክርስቲያኖች የይሖዋን ክብር ያንጸባርቃሉ

ክርስቲያኖች የይሖዋን ክብር ያንጸባርቃሉ

ክርስቲያኖች የይሖዋን ክብር ያንጸባርቃሉ

“የእናንተ ዐይኖች ስለሚያዩ፣ ጆሮዎቻችሁም ስለሚሰሙ . . . የተባረኩ ናቸው።”ማቴዎስ 13:16

1. እስራኤላውያን ሙሴ ከሲና ተራራ ሲወርድ ሲመለከቱ የወሰዱት እርምጃ ምን ጥያቄ ያስነሳል?

 በሲና ተራራ ግርጌ የተሰበሰቡት እስራኤላውያን ወደ ይሖዋ ለመቅረብ የሚያነሳሳ በቂ ምክንያት ነበራቸው። ይሖዋ ከግብፅ ባርነት በታላቅ እጅ ነፃ አውጥቷቸዋል። በምድረ በዳ ምግብና ውኃ በመስጠት የሚያስፈልጋቸውን አሟልቶላቸዋል። ቆየት ብሎም ሊወጓቸው በመጡት አማሌቃውያን ላይ ድል አጎናጽፏቸዋል። (ዘፀአት 14:26-31፤ 16:2 እስከ 17:13) ሕዝቡ በምድረ በዳ በሲና ተራራ ፊት ለፊት ሰፍረው እያለ ነጎድጓዱንና መብረቁን በጣም ከመፍራታቸው የተነሳ ይንቀጠቀጡ ነበር። በኋላም ሙሴ ከሲና ተራራ ሲወርድ ፊቱ የይሖዋን ክብር ሲያንጸባርቅ ተመለከቱ። ሆኖም እስራኤላውያን የይሖዋን ክብር ከማድነቅ ይልቅ ሸሹ። እንዲያውም “ወደ [ሙሴ] ለመቅረብም ፈርተው ነበር።” (ዘፀአት 19:10-19፤ 34:30) ሕዝቡ ያን ሁሉ መልካም ነገር ያደረገላቸውን የይሖዋን ክብር ነጸብራቅ ለማየት የፈሩት ለምን ነበር?

2. እስራኤላውያን ሙሴ የአምላክን ክብር ሲያንጸባርቅ ለመመልከት የፈሩት ለምን ሊሆን ይችላል?

2 እስራኤላውያን በዚህ ወቅት እንዲፈሩ ያደረጋቸው ከዚያ ጥቂት ቀደም ብሎ የተፈጸመው ሁኔታ ሳይሆን አይቀርም። የወርቅ ጥጃ በመሥራት ሆን ብለው የይሖዋን ትእዛዝ በመጣሳቸው ይሖዋ ቀጥቷቸው ነበር። (ዘፀአት 32:4, 35) ታዲያ ይሖዋ ከሰጣቸው ተግሣጽ ትምህርት በመውሰድ አድናቆት አሳይተው ይሆን? አብዛኞቹ ለተሰጣቸው ተግሣጽ አመስጋኞች አልነበሩም። ሙሴ በሕይወቱ ማብቂያ አካባቢ እስራኤላውያን ታዛዥ ያልነበሩባቸውን ሌሎች አጋጣሚዎች ጨምሮ የወርቁን ጥጃ የሠሩበትን ሁኔታ በማስታወስ ለሕዝቡ እንዲህ ብሏቸው ነበር:- “እናንተ ግን በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ላይ ዐመፃችሁ፤ እርሱን አልታመናችሁበትም፤ አልታዘዛችሁትምም። እኔ እናንተን ካወቅኋችሁ ጊዜ ጀምሮ፣ በእግዚአብሔር ላይ እንዳመፃችሁ ናችሁ።”—ዘዳግም 9:15-24

3. ሙሴ ፊቱን ይሸፍን የነበረው ምን ጊዜ ነው?

3 ሙሴ እስራኤላውያን ፊቱን ለማየት በመፍራታቸው ምን እንዳደረገ ተመልከት። ዘገባው እንዲህ ይላል:- “ሙሴ ለእነርሱ ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ በፊቱ ላይ መሸፈኛ አደረገ። [በመገናኛው ድንኳን ውስጥ] ከእርሱ ጋር ለመነጋገር ወደ እግዚአብሔር ሀልዎት በሚገባበት ጊዜ ሁሉ ግን፣ እስከሚወጣ ድረስ መሸፈኛውን ያነሣ ነበር፤ በወጣም ጊዜ የታዘዘውን ለእስራኤላውያን ነገራቸው። ፊቱ የሚያበራ መሆኑን አዩ፤ ከዚያም ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ለመነጋገር ተመልሶ እስኪሄድ ድረስ መሸፈኛውን መልሶ በፊቱ ላይ ያደርግ ነበር።” (ዘፀአት 34:33-35) ሙሴ አንዳንድ ጊዜ ፊቱን ይሸፍን የነበረው ለምንድን ነው? ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጠው መልስ እኛም ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና እንድንመረምር ይረዳናል።

የነበሯቸውን አጋጣሚዎች አልተጠቀሙባቸውም

4. ሐዋርያው ጳውሎስ ሙሴ መሸፈኛ ማድረጉ ምን ትርጉም እንዳለው ገልጿል?

4 ሐዋርያው ጳውሎስ ሙሴ መሸፈኛ ማድረጉ ከእስራኤላውያን አስተሳሰብና የልብ ዝንባሌ ጋር የተያያዘ መሆኑን ሲገልጽ “እስራኤላውያን ከፊቱ ክብር የተነሣ የሙሴን ፊት ትኵር ብለው ማየት [ተሳናቸው] . . . ልቡናቸው እንደ ደነዘዘ ነው” በማለት ጽፏል። (2 ቆሮንቶስ 3:7, 14) ይህ ምንኛ አሳዛኝ ነው! እስራኤላውያን የይሖዋ ምርጥ ሕዝቦች ስለነበሩ አምላክ ወደ እርሱ እንዲቀርቡ ይፈልግ ነበር። (ዘፀአት 19:4-6) ሆኖም የአምላክን ክብር ነጸብራቅ ትኩር ብለው መመልከት አልፈለጉም። ከወሰዱት እርምጃ መመልከት እንደሚቻለው ይሖዋን በልባቸውም ሆነ በሐሳባቸው በማፍቀር ለእርሱ ከማደር ይልቅ በተወሰነ መጠን ከእርሱ ርቀው ነበር።

5, 6. (ሀ) በሙሴ ጊዜና በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበሩት እስራኤላውያን መካከል ምን ተመሳሳይነት አለ? (ለ) ኢየሱስን ባዳመጡት ሰዎችና ሊሰሙት ፈቃደኛ ባልነበሩት አይሁዳውያን መካከል የነበረው ልዩነት ምንድን ነው?

5 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ሁኔታ ተፈጽሞ ነበር። ጳውሎስ ወደ ክርስትና በተለወጠበት ወቅት የሕጉ ቃል ኪዳን ታላቁ ሙሴ ኢየሱስ ክርስቶስ መካከለኛ በሆነለት በአዲሱ ቃል ኪዳን ተተክቶ ነበር። ኢየሱስ በንግግሩም ሆነ በድርጊቱ የይሖዋን ክብር ፍጹም በሆነ መልኩ አንጸባርቋል። ጳውሎስ ከሞት ስለተነሳው ኢየሱስ ሲጽፍ እርሱ “የእግዚአብሔር ክብር ነጸብራቅና የባሕርዩ ትክክለኛ ምሳሌ” እንደሆነ ገልጿል። (ዕብራውያን 1:3) አይሁዳውያን እንዴት ያለ ድንቅ አጋጣሚ ነበራቸው! የዘላለምን ሕይወት ቃል ከራሱ ከአምላክ ልጅ መስማት ይችሉ ነበር! የሚያሳዝነው ግን ኢየሱስ ከሰበከላቸው ሰዎች አብዛኞቹ አልሰሙትም። ይሖዋ በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት ያስነገረውን ትንቢት በመጥቀስ ኢየሱስ ስለ እነዚህ ሰዎች እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “የሕዝቡ ልብ ደንድኖአልና፤ ጆሮአቸውም አይሰማም፤ እንዳያዩም ዐይናቸውን ጨፍነዋል፤ ይህ ባይሆን ኖሮ፣ በዐይናቸው አይተው፣ በጆሮአቸው ሰምተው፣ በልባቸውም አስተውለው፣ ወደ እኔ በተመለሱና በፈወስኋቸው ነበር።”—ማቴዎስ 13:15፤ ኢሳይያስ 6:9, 10

6 በአይሁዳውያንና በኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መካከል ከፍተኛ ልዩነት ነበረ። ኢየሱስ ስለ ደቀ መዛሙርቱ ሲናገር “የእናንተ ዐይኖች ስለሚያዩ፣ ጆሮዎቻችሁም ስለሚሰሙ . . . የተባረኩ ናቸው” ብሏል። (ማቴዎስ 13:16) እውነተኛ ክርስቲያኖች ይሖዋን ለማወቅና እርሱን ለማገልገል ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈረውን የእርሱን ፈቃድ ማድረግ ያስደስታቸዋል። ስለዚህ በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች በአዲሱ ኪዳን አገልግሎታቸው የይሖዋን ክብር የሚያንጸባርቁ ሲሆን የሌሎች በጎች አባላትም እንዲሁ ያደርጋሉ።—2 ቆሮንቶስ 3:6, 18

ምሥራቹ የተከደነባቸው ለምንድን ነው?

7. ብዙዎች ምሥራቹን ለመስማት ፈቃደኛ አለመሆናቸው የማያስገርመው ለምንድን ነው?

7 ቀደም ሲል እንደተመለከትነው በኢየሱስም ሆነ በሙሴ ዘመን የነበሩት አብዛኞቹ እስራኤላውያን የተከፈተላቸውን ልዩ አጋጣሚ ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። በዘመናችንም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። አብዛኞቹ ሰዎች የምንሰብከውን የምሥራች አይቀበሉም። “ወንጌላችን የተከደነ ቢሆን እንኳ፣ የተከደነው ለሚጠፉት ነው። . . . የዚህ ዓለም አምላክ የማያምኑትን ሰዎች ልቡና አሳውሮአል” ከሚለው የጳውሎስ ደብዳቤ አንጻር ይህ መሆኑ አያስገርመንም። (2 ቆሮንቶስ 4:3, 4) ሰይጣን ምሥራቹን ለመደበቅ ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪ ብዙ ሰዎች ማየት ስለማይፈልጉ ዓይናቸውን ይሸፍኑታል።

8. ብዙዎች ባለማወቅ የታወሩት እንዴት ነው? እኛም ተመሳሳይ ነገር እንዳይገጥመን ራሳችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

8 ብዙዎች አምላክን ባለማወቃቸው ምሳሌያዊ ዓይናቸው ታውሯል። መጽሐፍ ቅዱስ አሕዛብ “ከልባቸው መደንደን የተነሣ ስለማያስተውሉ ልቦናቸው ጨልሞአል፤ ከእግዚአብሔርም ሕይወት ተለይተዋል” በማለት ይናገራል። (ኤፌሶን 4:18) ሕጉን በደንብ ያውቅ የነበረው ጳውሎስ ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት ምሥራቹን ባለማወቁ ታውሮ ስለነበር የአምላክን ጉባኤ ያሳድድ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 15:9) ሆኖም ይሖዋ እውነትን ገለጠለት። ጳውሎስ እንዲህ ብሏል:- “ክርስቶስ ኢየሱስ በእርሱ ለሚያምኑና የዘላለምን ሕይወት ለሚቀበሉ ወሰን የሌለው ትዕግሥቱን ከኀጢአተኞች ዋና በሆንሁት በእኔ እንደ ምሳሌ አድርጎ ያሳይ ዘንድ ምሕረትን አገኘሁ።” (1 ጢሞቴዎስ 1:16) ልክ እንደ ጳውሎስ ሁሉ በአንድ ወቅት የአምላክን እውነት ይቃወሙ የነበሩ ብዙዎች አሁን ይሖዋን እያገለገሉ ነው። ይህም ለሚቃወሙን ሰዎች እንኳ መመሥከራችንን እንድንቀጥል የሚገፋፋ ጥሩ ምክንያት ነው። እኛም የአምላክን ቃል አዘውትረን በማጥናትና የተማርነውን ለመረዳት በመጣር ባለማወቅ ይሖዋን የሚያሳዝን ነገር ከማድረግ ልንጠበቅ እንችላለን።

9, 10. (ሀ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት አይሁዶች ለመማር ፈቃደኞች እንዳልሆኑና ግትር አመለካከት እንዳላቸው ያሳዩት እንዴት ነው? (ለ) ዛሬስ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ሁኔታ አለ? አብራራ።

9 ብዙዎች ለመማር ፈቃደኛ ባለመሆናቸውና ግትር አመለካከት ስላላቸው መንፈሳዊ እይታቸው ተጋርዷል። ብዙ አይሁዳውያን ኢየሱስንም ሆነ ትምህርቶቹን መቀበል ያልፈለጉት የሙሴን ሕግ የሙጥኝ በማለታቸው ነበር። እርግጥ ነው፣ እንዲህ ዓይነት አመለካከት የነበራቸው ሁሉም አይሁዳውያን አይደሉም። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ከሞት ከተነሣ በኋላ “ከካህናትም ብዙዎቹ ለእምነት የታዘዙ ሆኑ” የሚል ዘገባ ሰፍሯል። (የሐዋርያት ሥራ 6:7) ያም ሆኖ ግን ጳውሎስ አብዛኞቹን አይሁዳውያን አስመልክቶ “እስከ ዛሬም ድረስ የሙሴ መጻሕፍት በተነበቡ ቊጥር መሸፈኛው ልቡናቸውን ይሸፍናል” በማለት ጽፏል። (2 ቆሮንቶስ 3:15) ጳውሎስ ከዚያ ቀደም ብሎ ኢየሱስ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎችን “በእነርሱ የዘላለም ሕይወትን የምታገኙ እየመሰላችሁ፣ መጻሕፍትን ትመረምራላችሁ፤ እነዚሁ መጻሕፍት ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው” በማለት እንደተናገራቸው ሳያውቅ አይቀርም። (ዮሐንስ 5:39) የሃይማኖት መሪዎቹ በትጋት የሚያጠኗቸው ቅዱሳን ጽሑፎች ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን እንዲገነዘቡ ሊረዷቸው ይገባ ነበር። ሆኖም አይሁዳውያን እነዚህን መጻሕፍት የተረዷቸው በራሳቸው አመለካከት ስለነበር የአምላክ ልጅ ተዓምራት ቢሠራም እንኳ አመለካከታቸውን እንዲለውጡ ሊያሳምናቸው አልቻለም።

10 ዛሬም በሕዝበ ክርስትና ውስጥ የሚገኙ ብዙ ሰዎች ተመሳሳይ አመለካከት አላቸው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት አይሁዳውያን ‘ለእግዚአብሔር ቀናተኛ ቢሆኑም ቅናታቸው ግን ከዕውቀት የተነሣ አይደለም።’ (ሮሜ 10:2) አንዳንዶች መጽሐፍ ቅዱስን ቢያጠኑም የሚናገረውን ማመን አይፈልጉም። ይሖዋ በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖችን ባቀፈው ታማኝና ልባም ባሪያ አማካኝነት ሕዝቡን እንደሚያስተምር መቀበል አይፈልጉም። (ማቴዎስ 24:45 የ1954 ትርጉም) እኛ ግን ይሖዋ ሕዝቡን እንደሚያስተምርና መለኮታዊውን እውነት የምንረዳው ደረጃ በደረጃ መሆኑን እንገነዘባለን። (ምሳሌ 4:18) ይሖዋ እንዲያስተምረን በመፍቀዳችን ስለ ፈቃዱና ስለ ዓላማው የማወቅ መብት አግኝተናል።

11. ሰዎች ማመን የሚፈልጉትን ብቻ ማመናቸው እውነት እንዲደበቅባቸው ያደረገው እንዴት ነው?

11 ሌሎች ደግሞ የሚያምኑት ማመን የሚፈልጉትን ብቻ በመሆኑ ታውረዋል። አንዳንዶች በአምላክ ሕዝቦችና ስለ ኢየሱስ መገኘት በሚያውጁት መልእክት ላይ እንደሚዘብቱ አስቀድሞ ተነግሮ ነበር። ሐዋርያው ጴጥሮስ አምላክ በኖኅ ዘመን በነበረው ዓለም ላይ የጥፋት ውኃ እንዳመጣ አንዳንዶች “ሆን ብለው ይክዳሉ” በማለት ጽፏል። (2 ጴጥሮስ 3:3-6) በተመሳሳይም ክርስቲያን ነን የሚሉ ብዙዎች ይሖዋ መሐሪ፣ ደግና ይቅር ባይ መሆኑን በቀላሉ ቢቀበሉም በደለኛውን ሳይቀጣ እንደማያልፍ ግን መቀበል አይፈልጉም። (ዘፀአት 34:6, 7) እውነተኛ ክርስቲያኖች የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት በትክክል ለመረዳት ጥንቃቄ ያደርጋሉ።

12. ሰዎች በወግ የታወሩት እንዴት ነው?

12 ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱ አብዛኞቹ ሰዎች በወግና በልማድ ታውረዋል። ኢየሱስ በዘመኑ ለነበሩት የሃይማኖት መሪዎች “ለወጋችሁ ብላችሁ የእግዚአብሔርን ቃል ትሽራላችሁ” ብሏቸው ነበር። (ማቴዎስ 15:6) አይሁዳውያን ከባቢሎን ግዞት ከተመለሱ በኋላ ለይሖዋ በመቅናት ንጹሑን አምልኮ እንደገና ቢያቋቁሙም የሃይማኖት መሪዎቹ ግን ኩሩና ተመጻዳቂ ሆኑ። ሃይማኖታዊ በዓሎቻቸውን የሚያከብሩት በዘልማድ ከመሆኑም በላይ ሕዝቡ ለአምላክ እውነተኛ አክብሮታዊ ፍርሃት እንደጎደላቸው ይታይ ነበር። (ሚልክያስ 1:6-8) ኢየሱስ ወደ ምድር በመጣበት ወቅት ጻፎችና ፈሪሳውያን በሙሴ ሕግ ላይ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ወጎች ጨምረው ነበር። እነዚህ ሰዎች ሕጉ የተመሠረተበትን የጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓት ማስተዋል አቅቷቸው ስለነበር ኢየሱስ ግብዞች እንደሆኑ በመናገር አጋልጧቸዋል። (ማቴዎስ 23:23, 24) እውነተኛ ክርስቲያኖች የሰው ልጆች ያወጧቸው ሃይማኖታዊ ወጎች ከንጹሕ አምልኮ እንዳያርቋቸው መጠንቀቅ አለባቸው።

‘የማይታየውን እንዳየው አድርጎ መቊጠር’

13. ሙሴ የአምላክን ክብር የተመለከተው በየትኞቹ ሁለት መንገዶች ነው?

13 ሙሴ በተራራው ላይ የይሖዋን ክብር ለማየት የጠየቀ ሲሆን ይሖዋ ካለፈ በኋላ ከጀርባው ክብሩን መመልከት ችሏል። ወደ መገናኛው ድንኳን ሲሄድም መሸፈኛ አያደርግም ነበር። ሙሴ ጠንካራ እምነት ያለውና የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ የሚፈልግ ሰው ነበር። ሙሴ በተወሰነ መጠን የይሖዋን ክብር በራእይ የመመልከት መብት ቢያገኝም ይህ ከመሆኑም በፊት ቢሆን አምላክን በእምነት ዓይን ተመልክቶት ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ሙሴ “የማይታየውንም እንዳየው አድርጎ በመቊጠር በሐሳቡ ጸና” ይላል። (ዕብራውያን 11:27፤ ዘፀአት 34:5-7) የአምላክን ክብር ያንጸባረቀውም ለተወሰነ ጊዜ ፊቱ በማብራቱ ብቻ ሳይሆን እስራኤላውያን ይሖዋን እንዲያውቁና እንዲያገለግሉት ለመርዳት ባደረገው ጥረትም ጭምር ነው።

14. ኢየሱስ የአምላክን ክብር የተመለከተው እንዴት ነው? ምን ማድረግስ ያስደስተው ነበር?

14 ኢየሱስ አጽናፈ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ጀምሮ ሕልቆ መሳፍርት ለሌላቸው ዘመናት በሰማይ የአምላክን ክብር ፊት ለፊት ሲመለከት ኖሯል። (ምሳሌ 8:22, 30) አባትና ልጅ ይህን ሁሉ ጊዜ አብረው ማሳለፋቸው በመካከላቸው ጥልቅ ፍቅር እንዲመሠረት አድርጓል። ይሖዋ አምላክ የፍጥረት ሁሉ በኩር የሆነውን ልጁን በጥልቅ እንደሚወደውና እንደሚያፈቅረው ገልጿል። ኢየሱስም በምላሹ ሕይወት ለሰጠው አምላክ ያለውን ወሰን የለሽ ፍቅር ገልጿል። (ዮሐንስ 14:31፤ 17:24) በአባትና ልጅ መካከል ፍጹም ፍቅር ነበረ። ልክ እንደ ሙሴ ሁሉ ኢየሱስም በሚያስተምረው ነገር የይሖዋን ክብር ማንጸባረቅ ያስደስተው ነበር።

15. ክርስቲያኖች ስለ አምላክ ክብር እንደሚያስቡ የሚያሳዩት እንዴት ነው?

15 እንደ ሙሴና እንደ ኢየሱስ ሁሉ በዚህ ዘመን የሚኖሩ የአምላክ ምድራዊ አገልጋዮችም ስለ ይሖዋ ክብር ማሰብ ያስደስታቸዋል። ክብራማውን ምሥራች ለመቀበል ፈቃደኞች ናቸው። ሐዋርያው ጳውሎስ “አንድ ሰው [ፈቃዱን ለማድረግ] ወደ ጌታ ዘወር ሲል መሸፈኛው ይወገዳል” ብሏል። (2 ቆሮንቶስ 3:16) የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ስለምንፈልግ መጽሐፍ ቅዱስን እናጠናለን። የይሖዋ ልጅና የተቀባ ንጉሥ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት ላይ የተንጸባረቀውን ክብር የምናደንቅ ከመሆኑም በላይ እርሱን ለመምሰል እንጥራለን። እንደ ሙሴና እንደ ኢየሱስ ስለምናመልከው የተከበረ አምላክ ለሌሎች የማስተማር አገልግሎት ተሰጥቶናል።

16. እውነትን በማወቃችን የተባረክነው እንዴት ነው?

16 ኢየሱስ “አባት ሆይ፤ ይህን ከጥበበኞችና ከዐዋቂዎች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ” በማለት ጸልዮ ነበር። (ማቴዎስ 11:25) ይሖዋ ልበ ቅንና ትሑት ለሆኑ ሰዎች ዓላማውንና ባሕርዩን ይገልጽላቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 1:26-28) አምላካችን ጥበቃ የሚያደርግልን ከመሆኑም በላይ አስደሳች ሕይወት በመምራት ራሳችንን እንድንጠቅም ያስተምረናል። ይሖዋ እርሱን ይበልጥ እንድናውቀው ያደረገልንን በርካታ ዝግጅቶች በማድነቅ ወደ እርሱ ለመቅረብ ያሉንን አጋጣሚዎች ሁሉ እንጠቀምባቸው።

17. የይሖዋን ባሕርያት ይበልጥ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?

17 ጳውሎስ በመንፈስ ለተቀቡት ክርስቲያኖች “ባልተሸፈነ ፊት የጌታን ክብር እንደ መስተዋት እያንጸባረቅን፣ የእርሱን መልክ እንድንመስል ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን” በማለት ጽፎ ነበር። (2 ቆሮንቶስ 3:18) ተስፋችን በሰማይም ይሁን በምድር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለሰፈሩት የይሖዋ ባሕርያትና ስለማንነቱ ይበልጥ ባወቅን መጠን እርሱን እየመሰልን እንሄዳለን። ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት፣ አገልግሎትና ትምህርቶች በአድናቆት ባሰላሰልን መጠን የይሖዋን ባሕርያት የበለጠ እናንጸባርቃለን። የእርሱን ክብር ማንጸባረቅ ለምንፈልገው አምላክ ውዳሴ ልናመጣ እንደምንችል ማወቁ ምንኛ የሚያስደስት ነው!

ታስታውሳለህ?

• እስራኤላውያን ሙሴ የአምላክን ክብር ሲያንጸባርቅ ለመመልከት የፈሩት ለምን ነበር?

• በመጀመሪያው መቶ ዘመን ምሥራቹ “የተከደነው” በየትኞቹ መንገዶች ነበር? ዛሬስ?

• የይሖዋን ክብር ማንጸባረቅ የምንችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እስራኤላውያን የሙሴን ፊት ትኩር ብለው ማየት አልቻሉም ነበር

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እንደ ጳውሎስ ሁሉ በአንድ ወቅት የአምላክን እውነት ይቃወሙ የነበሩ ብዙዎች አሁን እያገለገሉት ነው

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ አገልጋዮች የአምላክን ክብር ማንጸባረቅ ያስደስታቸዋል