ለመጽሐፍ ቅዱስ ትኩረት በመስጠታቸው አድናቆት አተረፉ
ለመጽሐፍ ቅዱስ ትኩረት በመስጠታቸው አድናቆት አተረፉ
በደቡብ ኢጣሊያ የምትኖረውና የይሖዋ ምሥክር የሆነችው ማሪአና የተባለች የ18 ዓመት ወጣት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን የምታጠናቅቅበት ዓመት ላይ ደርሳለች። የምትማረው ሌሎች ወጣት ምሥክሮች በሚማሩበት ትምህርት ቤት ውስጥ ነው።
ማሪአና እንዲህ ስትል ጽፋለች:- “ከጥቂት ዓመታት ወዲህ አንዳንዶቻችን በእረፍት ሰዓታችን የዕለቱን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ቅዱሳን ጽሑፎችን በየዕለቱ መመርመር ከተባለው ቡክሌት እናነባለን። ይህንን ማድረግ የምንችልበት ብቸኛው ቦታ በመምህራን ማረፊያ ክፍል አጠገብ በሚገኘው በአንዱ መተላለፊያ ነበር። ቦታው በጣም ጸጥታ የሰፈነበት አይደለም። አብዛኞቹ አስተማሪዎች ሲተላለፉ ያዩናል፤ አንዳንዶቹም ምን እንደምንሠራ ቆም ብለው ይመለከቱናል። ይህ አጋጣሚም ለጥያቄዎቻቸው መልስ ለመስጠት አስችሎናል። በየቀኑ በአማካይ አንድ አስተማሪ ከእኛ ጋር ይወያያል። በርከት ያሉ አስተማሪዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ የተመሠረተውን ውይይታችንን ያዳመጡ ሲሆን እኛ የይሖዋ ምሥክሮች ለመንፈሳዊ ነገሮች የምንሰጠውን ትኩረት በተመለከተ አድናቆታቸውን ገልጸውልናል። በአንድ ወቅት ምክትል ዳይሬክተሩ ውይይታችንን በመምህራኑ ማረፊያ ክፍል ውስጥ እንድናደርግ ጋብዞን ነበር።
“አስተማሪዬ በዕለት ጥቅሱ ላይ የምንወያይበትን ቦታ ከተመለከተ በኋላ ውይይቱን ይበልጥ ጸጥታ በሰፈነበት አንድ ክፍል ውስጥ ማድረግ እንችል እንደሆነ ዳይሬክተሩን ጠየቀው። ዳይሬክተሩ የፈቀደልን ሲሆን አስተማሪዬም በክፍሉ ተማሪዎች ፊት ግሩም ምሳሌ በመሆናችን አመስግኖናል። ሁላችንም ይሖዋ ይህን ትልቅ መብት ስለሰጠን ደስተኞች ነን።”