አምላክ ስለ አንተ ያስባል
አምላክ ስለ አንተ ያስባል
አንድ ከባድ ችግር አጋጥሞን ዙሪያ ገባው ሲጨልምብን አምላክ እንዲረዳን በጸሎት መለመን ያለ ነገር ነው። ደግሞም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው እርሱ “ታላቅ ነው፤ እጅግ ኀያልም ነው፤ ለጥበቡም ወሰን የለውም።” (መዝሙር 147:5) ችግሮቻችንን መቋቋም እንድንችል ከእርሱ የተሻለ ሊረዳን የሚችል የለም። ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ “ልባችሁን በፊቱ አፍስሱ” የሚል ግብዣ አቅርቦልናል። (መዝሙር 62:8) ይህ ከሆነ ታዲያ በጣም ብዙ ሰዎች አምላክ ለጸሎታቸው ምላሽ እንደማይሰጥ የሚሰማቸው ለምንድን ነው? አምላክ አያስብላቸውም ማለት ነው?
አምላክ ነገሮችን ለማስተካከል ጣልቃ እንዳልገባ ሲሰማህ እርሱን ለመውቀስ ከመቸኮል ይልቅ መለስ ብለህ ትንሽ ልጅ የነበርክበትን ጊዜ አስታውስ። ወላጆችህ የጠየቅኸውን ሁሉ ሊሰጡህ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው እንደማይወዱህ ተሰምቶህ ያውቃል? ብዙ ልጆች እንደዚህ ይሰማቸዋል። ሆኖም እያደግህ ስትሄድ ወላጆችህ ለአንተ ያላቸውን ፍቅር የሚያሳይ ብዙ ነገር እንዳደረጉልህና ለአንድ ልጅ የጠየቀውን ሁሉ መስጠት ወላጆች ለልጆቻቸው ያላቸው ፍቅር መለኪያ እንዳልሆነ ተገንዝበሃል።
በተመሳሳይም ይሖዋ ለጸሎታችን ሁልጊዜ እኛ በምንፈልገው መንገድ ምላሽ ስላልሰጠን ትቶናል ማለት አይደለም። እንዲያውም እንደሚያስብልን በብዙ መንገዶች እያሳየን ነው።
‘የምንኖረው በእርሱ ነው’
በመጀመሪያ ደረጃ “የምንኖረውና የምንንቀሳቀሰው፣ ያለነውም” በአምላክ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 17:28) ይሖዋ ሕይወት የሰጠን ስለሚያፈቅረንና ስለሚያስብልን እንደሆነ አያጠራጥርም!
ከዚህም በላይ ይሖዋ በሕይወት ለመኖር የሚያስፈልጉንን ነገሮች ሰጥቶናል። መጽሐፍ ቅዱስ “ከምድር ምግብን ታወጣ ዘንድ፣ ለእንስሳት ሣርን፣ ለሰው ልጆች ሥራ ዕፀዋትን ታበቅላለህ” ይላል። (መዝሙር 104:14) ለነገሩ ፈጣሪያችን መሠረታዊ ፍላጎታችንን በማሟላት ብቻ አልተወሰነም። በደግነት ተነሳስቶ ‘ዝናብን ከሰማይ እንዲሁም ፍሬያማ ወቅቶችን ሰጥቶናል፤ ልባችንን በመብልና በደስታ ያረካል።’—የሐዋርያት ሥራ 14:17
ያም ሆኖ አንዳንዶች ‘አምላክ ይህን ያህል የሚወደን ከሆነ ስንሠቃይ ዝም ብሎ የሚመለከተው ለምንድን ነው?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። የዚህ ጥያቄ መልስ ምን እንደሆነ ታውቃለህ?
ተወቃሹ አምላክ ነው?
ብዙውን ጊዜ ሰዎችን ለችግር የሚያጋልጣቸው የራሳቸው አካሄድ ነው። ለአብነት ያህል፣ ለአደጋ በሚያጋልጡ ተግባራት መካፈል ጉዳት እንደሚያስከትል በደንብ ይታወቃል። ያም ሆኖ ሰዎች የጾታ ብልግና ከመፈጸም፣ የአልኮል መጠጥንና ሌሎች ዕፆችን አላግባብ ከመውሰድ፣ ትንባሆ ከማጨስ፣ አደገኛ በሆኑ ስፖርቶች ከመካፈል፣ መኪና በከፍተኛ ፍጥነት ከማሽከርከርና እነዚህን ከመሳሰሉ ነገሮች አልተቆጠቡም። እንደዚህ ያለው ለአደጋ የሚያጋልጥ አካሄድ በሰዎች ላይ መከራ ቢያስከትል ተወቃሹ ማን ነው? አምላክ ወይስ ጥበብ የጎደለው ጎዳና የተከተለው ሰው? በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የአምላክ ቃል “አትታለሉ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ያንኑ ያጭዳል” ይላል።—ገላትያ 6:7
ሰዎች በራሳቸው ላይ ከሚያመጡት መከራ በተጨማሪ አብዛኛውን ጊዜ ሌሎችን የሚጎዳ ነገር ያደርጋሉ። አንድ አገር በሌሎች ላይ ጦርነት ቢያውጅ በዚህ ምክንያት ለሚደርሰው መከራ ተጠያቂው አምላክ ሊሆን እንደማይችል ግልጽ ነው። ወንጀለኞች በፈጸሙት ጥቃት የተነሳ ለሚደርሰው ጉዳት ወይም ሞት ተወቃሹ አምላክ ነው? በፍጹም ሊሆን አይችልም! አንድ አምባገነን መሪ ዜጎቹን ቢጨቁን፣ ቢያሠቃይና ቢገድል አምላክ ሊወቀስ ይገባዋል? አምላክን ተጠያቂ ማድረጉ ምክንያታዊ አይሆንም።—መክብብ 8:9
በድህነት ስለሚማቅቁት ወይም በረሃብ ስለሚሠቃዩት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል? ተወቃሹ መዝሙር 10:2, 3፤ 145:16) ረሃብና ድህነት እንዲስፋፋ ምክንያት የሆነው አምላክ አትረፍርፎ የሰጠን ምግብ ለሁሉም ሰው እኩል አለመዳረሱ ነው። የሰው ልጅ ራስ ወዳድነት ደግሞ ችግሩ እንዳይወገድ እንቅፋት ሆኗል።
አምላክ ነው? በፍጹም። ምድራችን ሁሉንም ሰው ለመመገብ ከሚያስፈልገው በላይ ምግብ ትሰጣለች። (የችግሩ ሥረ መሠረት
በዕድሜ መግፋት ምክንያት አንድ ሰው ቢታመም ወይም ቢሞት ተወቃሹ ማን ነው? ለዚህም ቢሆን ተጠያቂው አምላክ አይደለም ቢባል ትገረም ይሆን? አምላክ ሰዎችን ሲፈጥር እንዲያረጁና እንዲሞቱ ዓላማው አልነበረም።
ይሖዋ የመጀመሪያዎቹን ሰብዓዊ ባልና ሚስት በኤደን ሲያስቀምጣቸው ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ነበራቸው። ሆኖም የምድር ነዋሪዎች የተደረገላቸውን ነገር እንዲያደንቁ ይፈልግ ነበር። ስለዚህ የወደፊት ሕይወታቸው በአንድ ሁኔታ ላይ የተመካ እንዲሆን አደረገ። አዳምና ሔዋን በገነት ውስጥ መኖር የሚችሉት አፍቃሪ ለሆነው ፈጣሪያቸው እስከታዘዙ ድረስ ብቻ ነበር።—ዘፍጥረት 2:17፤ 3:2, 3, 17-23
የሚያሳዝነው አዳምና ሔዋን በአምላክ ላይ ዓመፁ። ሔዋን ሰይጣን ዲያብሎስን ለመስማት የመረጠች ሲሆን እርሱም አምላክ አንድ ጥሩ ነገር እንዳስቀረባት አድርጎ በተዘዋዋሪ በመናገር ዋሻት። በዚህም ምክንያት የራሷን መንገድ ተከትላ “መልካምና ክፉን በማወቅ፣ እንደ እግዚአብሔር [ለመሆን]” ሞከረች። አዳምም ከእርሷ ጋር በዓመፅዋ ተባበረ።—ዘፍጥረት 3:5, 6
አዳምና ሔዋን በዚህ መንገድ ኃጢአት ሲሠሩ የዘላለም ሕይወት የሚገባቸው ሰዎች እንዳልሆኑ አሳይተዋል። ኃጢአት የሚያስከትለውን ከባድ መዘዝ የቀመሱ ሲሆን ዓመታት ሲያልፉ አቅም እያጡ ሄዱና በመጨረሻም ሞቱ። (ዘፍጥረት 5:5) ይሁን እንጂ በአምላክ ላይ ማመፃቸው ያስከተለው መዘዝ በዚህ አላበቃም። አዳምና ሔዋን በሠሩት ኃጢአት ምክንያት ዛሬም ድረስ እየተሠቃየን ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ኀጢአት በአንድ ሰው [በአዳም] በኩል ወደ ዓለም እንደ ገባ ሁሉ፣ ሞትም በኀጢአት በኩል ገብቶአል፤ በዚሁ መንገድ ሞት ወደ ሰዎች ሁሉ መጣ፤ ምክንያቱም ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል።” (ሮሜ 5:12) አዎን፣ በአዳምና ሔዋን ዓመፅ ምክንያት ኃጢአትና ሞት እንደ ቀሳፊ በሽታ ለመላው የሰው ዘር ተዳረሰ።
አምላክ እንደሚያስብልን የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ
ይህ ሲባል የሰው ልጆች ምንም ተስፋ የላቸውም ማለት ነው? በፍጹም፤ አምላክ እንደሚያስብልን የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ አለን። ከፍተኛ ዋጋ ቢጠይቅበትም የሰውን ዘር ከኃጢአትና ከሞት ለመዋጀት ዝግጅት አድርጓል። የሰው ልጆችን ለመዋጀት የተከፈለው ዋጋ ኢየሱስ ለእኛ ሲል በፈቃደኝነት ያቀረበው ፍጹም ሕይወቱ ነው። (ሮሜ 3:24) በመሆኑም ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአልና።” (ዮሐንስ 3:16) ተወዳዳሪ የሌለው ይህ ፍቅራዊ ዝግጅት ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ እንድናገኝ አስችሎናል። ጳውሎስ ለሮሜ ክርስቲያኖች “በአንዱ የጽድቅ ሥራ ለሰው ሁሉ ሕይወትን የሚሰጥ ጽድቅ ተገኘ” ሲል ጽፏል።—ሮሜ 5:18
አምላክ በቀጠረው ጊዜ መከራንና ሞትን ከምድራችን ላይ እንደሚያስወግድ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። በምትኩ በራእይ መጽሐፍ ላይ የተገለጸው ሁኔታ ይሠፍናል:- “እነሆ፤ የእግዚአብሔር ማደሪያ በሰዎች መካከል ነው፤ እርሱ ከእነርሱ ጋር ይኖራል፤ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ፤ እግዚአብሔር ራሱም ከእነርሱ ጋር ይኖራል፤ አምላካቸውም ይሆናል። እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም፤ የቀድሞው ሥርዐት ዐልፎአልና።” (ራእይ 21:3, 4) ‘ይህ ሲፈጸም እኔ በሕይወት አልኖርም’ ብለህ ታስብ ይሆናል። ሆኖም በሕይወት እያለህም ሊፈጸም ይችላል። ደግሞም ብትሞት እንኳ አምላክ በትንሣኤ ያስነሳሃል። (ዮሐንስ 5:28, 29) አምላክ ለእኛ ያለው ዓላማ ይህ ነው፤ ደግሞም ይፈጸማል። አምላክ ለሰው ዘር አያስብም ብሎ መናገር ከእውነታው ምን ያህል የራቀ ይሆናል!
“ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ”
አምላክ በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰውን ሥቃይ ለማስወገድ ዘላቂ መፍትሔ እንዳዘጋጀ ማወቁ የሚያጽናና ነው። ሆኖም በአሁኑ ጊዜ ችግሮች ሲደርሱብንስ? የምንወደው ሰው ቢሞትብን ወይም ልጃችን ቢታመምብን ምን ማድረግ እንችላለን? አምላክ በሽታንና ሞትን ለማስወገድ የወሰነው ጊዜ ገና አልደረሰም። መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ ነገሮች እስኪወገዱ ትንሽ መጠበቅ እንዳለብን ያሳያል። ያም ሆኖ ይሖዋ ያለ እርዳታ አልተወንም። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ፤ እርሱም ወደ እናንተ ይቀርባል” ብሏል። (ያዕቆብ 4:8) በእርግጥም ፈጣሪያችን ከእርሱ ጋር የቀረበ ዝምድና እንድንመሠርት ጋብዞናል፤ ከአምላክ ጋር የቀረበ ዝምድና ያላቸው ሰዎች በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ቢገጥማቸው እንኳ የእርሱ ድጋፍ ምንጊዜም አይለያቸውም።
ይሁን እንጂ ወደ አምላክ የምንቀርበው እንዴት ነው? ንጉሥ ዳዊት ከሦስት ሺህ ዓመታት በፊት “እግዚአብሔር ሆይ፣ . . . በተቀደሰው ኰረብታህስ ማን መኖር ይችላል?” በማለት ተመሳሳይ ጥያቄ አንስቶ ነበር። (መዝሙር 15:1) ዳዊት ራሱ ያነሳውን ጥያቄ ሲመልስ “አካሄዱ ንጹሕ የሆነ፣ ጽድቅን የሚያደርግ፤ ከልቡ እውነትን የሚናገር፤ በምላሱ የማይሸነግል፤ በባልንጀራው ላይ ክፉ የማይሠራ” ብሏል። (መዝሙር 15:2, 3) በሌላ አባባል ይሖዋ የሚቀበለው ከአዳምና ሔዋን በተለየ መልኩ እርሱን የሚታዘዙ ሰዎችን ነው። ፈቃዱን ወደሚያደርጉ ሰዎች ይቀርባል።—ዘዳግም 6:24, 25፤ 1 ዮሐንስ 5:3
የአምላክን ፈቃድ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ‘በእግዚአብሔር በአዳኛችን ፊት ደስ የሚያሰኘውን’ ነገር በማወቅና ይህንንም ተግባራዊ በማድረግ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 2:3) ይህም ከአምላክ ቃል ከመጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ እውቀት ማግኘትን ይጨምራል። (ዮሐንስ 17:3፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) መጽሐፍ ቅዱስን ላይ ላዩን ማንበብ ብቻውን በቂ አይደለም። በመጀመሪያው መቶ ዘመን በቤሪያ የነበሩት የጳውሎስን ስብከት የሰሙ አይሁዳውያን የተዉትን ምሳሌ መኮረጅ ያስፈልገናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለ እነርሱ “ነገሩ እንደዚህ ይሆንን እያሉ መጻሕፍትን በየዕለቱ በመመርመር ቃሉን በታላቅ ጉጉት ተቀብለዋል” የሚል ሐሳብ እናገኛለን።—የሐዋርያት ሥራ 17:11
ዛሬም በተመሳሳይ መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቅ ማጥናታችን በአምላክ ላይ ያለንን እምነት ያጠናክረዋል እንዲሁም ከእርሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ለመመሥረት ያስችለናል። (ዕብራውያን 11:6) ከዚህም በላይ ይሖዋ ትክክለኛ ዝንባሌ ላላቸው ሰዎች ሁሉ ስለ ጊዜያዊው ብቻ ሳይሆን ስለ ዘላለማዊው ጥቅማቸው እንደሚያስብ ማወቃችንም ይጠቅመናል።
እስቲ ከአምላክ ጋር የቀረበ ዝምድና የመሠረቱ ክርስቲያኖች የሚሉትን እንስማ። የ16 ዓመቷ ዳኒዬል “ይሖዋን በጣም እወደዋለሁ፤ እንዳመሰግነው የሚገፋፉኝ
በርካታ ነገሮች አድርጎልኛል” ብላለች። “እርሱን ከልባቸው የሚወድዱና በቃሉ መሠረት እንድመላለስ ያሠለጠኑኝ አፍቃሪ ወላጆች ሰጥቶኛል።” በኡራጓይ የሚኖር አንድ ክርስቲያን “ይሖዋ ስላሳየን የማይገባን ደግነትና ስለ ወዳጅነቱ ሳስብ እርሱን ለማመስገን እገፋፋለሁ፤ ልቤም በአድናቆት ስሜት ይሞላል” ብሏል። አምላክ ትናንሽ ልጆችም ወደ እርሱ እንዲቀርቡ ይፈልጋል። የሰባት ዓመት ልጅ የሆነችው ጋብሪኤላ እንዲህ ብላለች:- “በዓለም ላይ ካለ ከማንኛውም ነገር አስበልጬ አምላክን እወደዋለሁ! የራሴ መጽሐፍ ቅዱስ አለኝ። ስለ አምላክና ስለ ልጁ መማር ያስደስተኛል።”ዛሬ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች “ለእኔ ግን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ይሻለኛል” በማለት ከተናገረው መዝሙራዊ ጋር ሙሉ በሙሉ ይስማማሉ። (መዝሙር 73:28) በአሁኑ ጊዜ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች መቋቋም እንዲችሉ እርዳታ አግኝተዋል፤ እንዲሁም በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር የተረጋገጠ ተስፋ አላቸው። (1 ጢሞቴዎስ 4:8) አንተም ‘ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ’ ለምን አትሞክርም? ደግሞም ‘እርሱ ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም’ የሚል ማረጋገጫ ተሰጥቶናል። (የሐዋርያት ሥራ 17:27) በእርግጥም አምላክ ስለ አንተ ያስባል!
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ እንደሚያስብልን በብዙ መንገዶች አሳይቷል
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ትናንሽ ልጆች እንኳ ወደ አምላክ መቅረብ ይችላሉ
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ ችግሮች ሲደርሱብን መቋቋም እንድንችል ይረዳናል። የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ደግሞ በሽታና ሞትን ያስወግዳል