ለሚደርሱብን ችግሮች ተወቃሹ አምላክ ነው?
ለሚደርሱብን ችግሮች ተወቃሹ አምላክ ነው?
ሜሪየን የደረሰች ሴት ልጅዋ በአንጎሏ ላይ ከባድ ጉዳት በደረሰባት ጊዜ አብዛኞቻችን ችግር ሲደርስብን እንደምናደርገው እርሷም እርዳታ ለማግኘት ወደ አምላክ ጸለየች። a ሜሪየን “በሕይወቴ ሙሉ እንደዚያን ጊዜ ረዳት የለሽነትና ብቸኝነት ተሰምቶኝ አያውቅም” ብላለች። ከጊዜ በኋላ የልጅዋ ጤንነት እያሽቆለቆለ ሲሄድ ሜሪየን በአምላክ ላይ ጥርጣሬ አደረባት። “ይህ የደረሰብኝ ለምንድን ነው?” የሚል ጥያቄ በአእምሮዋ ይመላለስ ጀመር። አፍቃሪና አሳቢ የሆነ አምላክ ለምን እንደተዋት ሊገባት አልቻለም።
ሜሪየን የደረሰባት ዓይነት ሁኔታ ብዙ ጊዜ ያጋጥማል። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ብዙ ሰዎች ችግር ሲደርስባቸው አምላክ እንደተዋቸው ተሰምቷቸዋል። የልጅ ልጅዋ የተገደለባት ሊሳ “‘አምላክ ይህ እንዲደርስ የፈቀደው ለምንድን ነው?’ የሚለው ጥያቄ አሁንም ድረስ ይረብሸኛል” ብላለች። “በአምላክ ላይ የነበረኝ እምነት ሙሉ በሙሉ ባይጠፋም እንደቀድሞው ግን አይደለም።” በተመሳሳይም ሕፃን ልጅዋ የተገደለባት አንዲት ሴት “አምላክ ከደረሰብኝ ሐዘን አላጽናናኝም። ምንም ዓይነት አሳቢነትም ሆነ ርኅራኄ አላሳየኝም። መቼም ቢሆን አምላክን ይቅር አልለውም” በማለት ተናግራለች።
ሌሎች ደግሞ በዓለም ላይ የሚፈጸሙ ነገሮችን ሲመለከቱ በአምላክ ላይ ምሬት ያድርባቸዋል። በድህነት የሚማቅቁና በረሃብ የሚሠቃዩ ሰዎች፣ በጦርነት ምክንያት መድረሻ ያጡ ስደተኞች፣ በኤድስ ወላጆቻቸውን የተነጠቁ በርካታ ሕፃናት እንዲሁም በሌሎች በሽታዎች የተለከፉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መመልከት የተለመደ ሆኗል። እነዚህንና እነዚህን የመሰሉ ችግሮችን ለማስወገድ ምንም እርምጃ ባለመውሰዱ ብዙዎች አምላክን ይወቅሱታል።
እውነታው ሲታይ ግን የሰው ልጆችን ቁም ስቅላቸውን ለሚያሳዩአቸው ችግሮች ተወቃሹ አምላክ አይደለም። እንዲያውም አምላክ በሰብዓዊው ቤተሰብ ላይ የሚደርሰውን መከራ በቅርቡ ያስወግደዋል ብለን እንድናምን የሚያደርጉን አሳማኝ ምክንያቶች አሉ። አምላክ በጥልቅ እንደሚያስብልን ለማወቅ የሚቀጥለውን ርዕስ እንድታነብ እንጋብዝሃለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ስሞቹ ተቀይረዋል።