ለሰው ልጅ ችግሮች ዋነኛው መንስኤ ሃይማኖት ነው?
ለሰው ልጅ ችግሮች ዋነኛው መንስኤ ሃይማኖት ነው?
“ሃይማኖት ግጭትን ባያበረታታ እንኳ የሰውን ኅሊና የሚያደነዝዝ ዕፅ ከመሆኑም በላይ ሰዎች በሕልም ዓለም እንዲኖሩ የሚያደርግ ነው። . . . ሰዎች ጠባብ አስተሳሰብ እንዲኖራቸው፣ አጉል እምነት እንዲከተሉ፣ ጥላቻ እንዲያድርባቸውና በፍርሃት እንዲዋጡ ያደርጋል።” ይህን የጻፉት የቀድሞው የሜቶዲስት ሚስዮናዊ ሲሆኑ “እነዚህ አስተያየቶች ትክክለኛ ናቸው። መጥፎም ጥሩም ሃይማኖት አለ” ሲሉ አክለው ተናግረዋል።—ስታርት ዩር ኦውን ሪሊጅን
አንዳንዶች ‘ይህ ተገቢ ያልሆነ ትችት ነው’ ሊሉ ይችላሉ። ይሁንና የታሪክን ሐቅ ማን ሊክድ ይችላል? “ለአምላክ የሚቀርብ አምልኮና አገልግሎት” እንደሆነ ተደርጎ የሚታየው ሃይማኖት በአብዛኛው ያስመዘገበው ታሪክ እጅግ አሳዛኝ ነው። የሰው ልጆች መንፈሳዊ እውቀት እንዲያገኙና ለመልካም ተግባር እንዲነሳሱ ሊያደርግ ሲገባ ግጭትን፣ ጽንፈኝነትንና ጥላቻን የሚያስፋፋ ሆኗል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው?
አታላይ ‘የብርሃን መልአክ’
መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ግልጽ መልስ ይሰጣል። ሰይጣን ዲያብሎስ ራሱን ‘የብርሃን መልአክ’ አድርጎ በማቅረብ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የአምላክን ሳይሆን የእርሱን ትምህርቶች እንዲከተሉ አድርጓል። (2 ቆሮንቶስ 11:14) ሐዋርያው ዮሐንስ ‘ዓለም በሞላው በክፉው ተይዟል’ ብሎ በመጻፍ ሰይጣን በብዙዎች ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር አመልክቷል። (1 ዮሐንስ 5:19) ዮሐንስ፣ ሰይጣን ‘ዓለሙን ሁሉ በማሳት ላይ እንዳለ’ ተገንዝቦ ነበር።—ራእይ 12:9
ይህስ ምን አስከትሏል? ሰይጣን ከላይ ሲታዩ ቅዱስ የሚመስሉ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን አቋቁሟል። “ሃይማኖታዊ መልክ” ያላቸው ቢሆኑም የሚያፈሩት መጥፎ ፍሬ እውነተኛ ማንነታቸውን የሚያሳይ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:5 አ.መ.ት፤ ማቴዎስ 7:15-20) ሃይማኖት ለሰው ልጅ ችግሮች መፍትሔ ከማስገኘት ይልቅ እሱ ራሱ የችግሩ አንድ አካል ሆኗል።
ይህ የተሳሳተ ወይም የተጋነነ አመለካከት ነው ብለህ ለመደምደም አትቸኩል። ብዙውን ጊዜ ሰዎች መታለላቸውን እንኳን ሳያውቁ እንደሚታለሉ አትዘንጋ። ሐዋርያው ጳውሎስ “አሕዛብ የሚሠዉት ለአጋንንት . . . እንጂ ለእግዚአብሔር” አይደለም ሲል የተናገረው ቃል ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው። (1 ቆሮንቶስ 10:20) እነዚህ ሰዎች አጋንንትን እያመለኩ እንዳሉ ቢያውቁ በጣም እንደሚደነግጡ የታወቀ ነው። አንድ ጥሩ አምላክ ወይም አማልክት እያመለኩ እንዳሉ አድርገው ያስቡ የነበረ ቢሆንም ከሰይጣን ጋር በማበር የሰውን ዘር በማሳሳት ላይ ባሉ ‘በሰማያዊ ሥፍራ በሚገኙ ክፉ መንፈሳውያን ሠራዊት’ ተታልለዋል።—ኤፌሶን 6:12
ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ዮሐንስ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ችላ ያሉ ስመ ክርስቲያኖችን በማታለልና በማሳሳት ረገድ ሰይጣን ምን ያህል እንደተሳካለት እንመልከት።—1 ቆሮንቶስ 10:12
ኢየሱስ ያስተማረው ከአምላክ ያገኘውን ትምህርት ነው
ኢየሱስ ክርስቶስ “ትምህርቴስ ከላከኝ ነው እንጂ ከእኔ አይደለም” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 7:16) አዎን፣ ኢየሱስ ያስተማረው ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ያገኘውን ትምህርት ነው። በመሆኑም ትምህርቶቹ በአድማጮቹ ላይ በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ነበሩ። ‘የሰውን ኅሊና የሚያደነዝዙ ወይም በሕልም ዓለም እንዲኖሩ የሚያደርጉ’ አልነበሩም። ከዚህ ይልቅ የኢየሱስ ትምህርቶች በዲያብሎስ ማታለያ ‘ልቦናው የጨለመው’ ዓለም ከሚያስተምራቸው የተሳሳቱ ሃይማኖታዊ ትምህርቶችና ሰብዓዊ ፍልስፍናዎች ሰዎችን ነፃ የሚያወጡ ናቸው።—ኤፌሶን 4:18፤ ማቴዎስ 15:14፤ ዮሐንስ 8:31, 32
እውነተኛ ክርስቲያኖች ተለይተው የሚታወቁት እንዲሁ በአምላክ እንደሚያምኑ በመናገራቸው ብቻ ሳይሆን የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ፍሬ የሆኑትን ግሩም ባሕርያት በማፍራታቸው ነው። (ገላትያ 5:22, 23፤ ያዕቆብ 1:22፤ 2:26) ከእነዚህ ባሕርያት መካከል ከሁሉ የላቀውና የእውነተኛ ክርስትና መለያ የሆነው ፍቅር ነው።—ዮሐንስ 13:34, 35
ይሁን እንጂ ኢየሱስም ሆነ ሐዋርያቱ የክርስቲያን ጉባኤ መጀመሪያ ሲመሠረት የነበረውን ሁኔታ እንደያዘ ይቀጥላል ብለው እንዳልጠበቁ ልብ በል። እውነተኛው ሃይማኖት ለተወሰነ ጊዜ በክህደት ትምህርት ተውጦ እንደሚቆይ ተገንዝበው ነበር።
እውነተኛው ሃይማኖት ለተወሰነ ጊዜ ተሰውሮ ቆየ
ኢየሱስ ስለ ስንዴውና ስለ እንክርዳዱ በተናገረው ምሳሌ ላይ እውነተኛው ሃይማኖት ለተወሰነ ጊዜ ተሰውሮ እንደሚቆይ ተንብዮአል። በማቴዎስ 13:24-30, 36-43 ላይ ያለውን ዘገባ አውጥተህ አንብብ። ኢየሱስ በአንድ እርሻ ላይ “መልካም ዘር” ማለትም ስንዴ የዘራ ሲሆን ይህም የመጀመሪያው ክርስቲያን ጉባኤ አባላት የሆኑትን ታማኝ ደቀ መዛሙርቱን ያመለክታል። “ጠላት” የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ ከጊዜ በኋላ መጥቶ በስንዴው ማሳ ላይ “እንክርዳድ” እንደሚዘራ አስጠንቅቋል። እዚህ ላይ የተጠቀሰው “እንክርዳድ” ኢየሱስን እንደሚከተሉ ቢናገሩም እንኳ ትምህርቶቹን የማይቀበሉ ሰዎችን ያመለክታል።
የኢየሱስ ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ‘ከእግዚአብሔር ቃል’ ይልቅ ሰዎች የሚያስተምሯቸውን የተዛቡ ትምህርቶች የመረጡ ‘በእንክርዳድ’ የተመሰሉ ግለሰቦች ብቅ አሉ። (ኤርምያስ 8:8, 9፤ የሐዋርያት ሥራ ) በዚህም ሳቢያ የተጣመመ የሐሰት ክርስትና በዓለም መድረክ ላይ ብቅ አለ። ይህ የሐሰት ክርስትና ‘በሚያታልል የክፋት ሥራ’ በተበከለው ብልሹ የቀሳውስት ቡድን የሚመራ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ቡድን “ዐመፀኛ” በማለት ይጠራዋል። ( 20:29, 302 ተሰሎንቄ 2:6-10 አ.መ.ት) ኢየሱስ ይህ ሁኔታ “በዓለም መጨረሻ” እንደሚለወጥ አስቀድሞ ተናግሯል። በስንዴ የተመሰሉት ክርስቲያኖች አንድ ላይ እንዲሰበሰቡ የሚደረግ ሲሆን ‘እንክርዳዱ’ ግን ይቃጠላል።
ባለፉት “መቶ ዘመናት ለተፈጸሙት አረመኔያዊ ድርጊቶች” እና ሕዝበ ክርስትናን ለዋጠው መንፈሳዊ ጨለማ ተጠያቂው ይህ የሐሰት ክርስትና ነው። ከዚያን ጊዜ አንስቶ በሃይማኖት ስም የተፈጸሙትን ወራዳና ኢሰብዓዊ ድርጊቶች አስቀድሞ በማስተዋል ሐዋርያው ጴጥሮስ “በእነርሱም [ክርስቲያን ነን በሚሉ ሰዎች] ጠንቅ የእውነት መንገድ ይሰደባል” ሲል በትክክል ተንብዮአል።—2 ጴጥሮስ 2:1, 2
“ቁጣንና ጥላቻን የሚቀሰቅስ”
ሃይማኖት መጥፎ ስም እንዲያተርፍ ያደረገችው ሕዝበ ክርስትና ብቻ እንዳልሆነች የታወቀ ነው። ‘አክራሪ ሃይማኖታዊ ቡድኖችን’ እንደ ምሳሌ መውሰድ እንችላለን። መነኩሲት የነበሩት ካረን አርምስትሮንግ እንዲህ ያሉት ቡድኖች የሚፈጠሩት “ዋና ዋና ሃይማኖታዊ ልማዶችን” መሠረት በማድረግ እንደሆነ ተናግረዋል። እንደ እርሳቸው አባባል ከሆነ ማንኛውም ሃይማኖት የሚመዘንበት ትልቁ መመዘኛ ተከታዮቹ “በተግባር የሚገለጽ ርኅራኄ” እንዲያሳዩ ማድረግ ይችላል ወይስ አይችልም የሚለው ነው። አክራሪ ሃይማኖቶች በዚህ ረገድ ያስመዘገቡት ታሪክ ምን ይመስላል? አርምስትሮንግ “የአይሁድ፣ የክርስትናም ሆነ የእስልምና ጽንፈኝነት ቁጣንና ጥላቻን የሚቀሰቅስ ከሆነ ይህን መመዘኛ ሊያሟላ አይችልም” ሲሉ ጽፈዋል። (ዘ ባትል ፎር ጎድ—ፈንደሜንታሊዝም ኢን ጁዳይዝም፣ ክርስቲያኒቲ ኤንድ ኢስላም) ይሁን እንጂ ይህን መመዘኛ ሳያሟሉ የቀሩትና ‘ቁጣንና ጥላቻን የሚቀሰቅሱት’ “አክራሪ” የሆኑት ሃይማኖቶች ብቻ ናቸው? ሌሎች ሃይማኖቶችም ይህን መመዘኛ ሳያሟሉ እንደቀሩ ታሪክ ይመሠክራል።
እንዲያውም ሰይጣን ቁጣ፣ ጥላቻና ማብቂያ የሌለው ደም መፋሰስ መለያው የሆነ ዓለም አቀፍ የሐሰት ሃይማኖት ግዛት አቋቁሟል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን የሐሰት ሃይማኖት ግዛት “ታላቂቱ ባቢሎን . . . የምድር ርኵሰት እናት” በማለት የሚጠራው ከመሆኑም በላይ አውሬ መሰል በሆነ የፖለቲካ ሥርዓት ላይ በተቀመጠች አንዲት ጋለሞታ ተመስሏል። ይህች ጋለሞታ ‘በምድርም ለታረዱ ሁሉ ደም’ ተጠያቂ ሆና እንደተገኘች ማስተዋል ይገባል።—ራእይ 17:4–6፤ 18:24
ያልተታለሉ ሰዎች አሉ
ይሁን እንጂ ታሪክ እንደሚያሳየው ያልተታለሉ ሰዎችም አሉ። ሜልቪን ብራግ የጨለማው ዘመን በመባል በሚታወቀው ወቅት እንኳ ሳይቀር “በዙሪያቸው ያሉት አብዛኞቹ ሰዎች ክፉ ሆነው ሳለ መልካም ያደርጉ የነበሩ በርካታ ጥሩ ሰዎች ነበሩ” ሲሉ ተናግረዋል። እውነተኛ ክርስቲያኖች አምላክን “በመንፈስና በእውነት” ማምለካቸውን ቀጥለዋል። (ዮሐንስ 4:21-24) “ወታደራዊ ኃይሎችን በመደገፍ” ግልሙትና ከፈጸመው ዓለም አቀፍ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ገለልተኞች ነበሩ። ታሪክ “ሰይጣን በቤተ ክርስቲያንና በመንግሥት መካከል የፈጠረውን ጥምረት የናዝሬቱ ኢየሱስ ከፈጠረው ማንኛውም ዓይነት ጥምረት ይበልጥ ጠንካራ” እንደሆነ አድርጎ የሚገልጽ ሲሆን እውነተኛ ክርስቲያኖች ግን በዚህ ጥምረት ውስጥ እጃቸውን ከማስገባት ተቆጥበዋል።—ቱ ታውዘንድ ይርስ—ዘ ሰከንድ ሚሊኒየም:- ፍሮም ሜዲቫል ክሪስተንደም ቱ ግሎባል ክርስቲያኒቲ
ከቅርብ ዘመናት ወዲህ ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮች በሰዎች ላይ በጎ ተጽዕኖ በማሳደር ረገድ ተጠቃሽ ናቸው። የሚያምኑበትም ሆነ የሚያደርጉት ነገር አምላክ በመንፈሱ ባስጻፈው በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሙሉ በሙሉ የተመሠረተ በመሆኑ ከማንኛውም የሐሰት ሃይማኖት እድፍ ራሳቸውን መጠበቅ ችለዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) በተጨማሪም በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት ክርስቲያኖች ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮችም ኢየሱስ ተከታዮቹ የዚህ ‘ዓለም ክፍል እንዳይሆኑ’ የሰጠውን ትእዛዝ ታዝዘዋል። (ዮሐንስ 15:17-19፤ 17:14-16) ለምሳሌ ያህል በናዚ ዘመን በጀርመን የነበሩ የይሖዋ ምሥክሮች ክርስቲያናዊ አቋማቸውን ለማላላት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው በናዚ ርዕዮተ ዓለም ተቀባይነት ሳያገኙ ቀርተዋል። በዚህ አቋማቸው የተነሣ በሂትለር ዘንድ ከፍተኛ ጥላቻ አትርፈዋል። አንድ የመማሪያ መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “የይሖዋ ምሥክሮች . . . በምንም ዓይነት ሁኔታ ሥር የጦር መሣሪያ መታጠቅ ተገቢ እንዳልሆነ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ስለሚከተሉ በሠራዊቱ ውስጥ ለማገልገልም ሆነ ከናዚዎች ጋር ለመተባበር ፈቃደኞች ሳይሆኑ ቀርተዋል። በዚህም የተነሳ የኤስ ኤስ ወታደሮች የይሖዋ ምሥክሮችን ቤተሰቦች እስር ቤት አጉረዋል። [በጀርመን] ከነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ተገድለዋል።”—ጀርመን—1918-45
እርግጥ ነው፣ የተለያዩ ሃይማኖቶች አባላት የሆኑ አንዳንድ ደፋር ሰዎችም በእምነታቸው ምክንያት መከራ ደርሶባቸዋል። ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክሮችን ልዩ የሚያደርጋቸው በቡድን ደረጃ አንድ አቋም መውሰዳቸው ነው። አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ያላንዳች ማወላወል ታዘዋል።—የሐዋርያት ሥራ 5:29፤ ማርቆስ 12:17
የችግሩ መንስኤ
ስለዚህ ሃይማኖት ለሰው ልጅ ችግሮች መንስኤ ነው የሚለው አባባል ተቀባይነት የሚኖረው በተወሰነ ደረጃ ነው። ለዚህ ተጠያቂው የሐሰት ሃይማኖት ነው። ይሁንና አምላክ በቅርቡ የሐሰት ሃይማኖትን ሙሉ በሙሉ ጠራርጎ ለማጥፋት ዓላማ አለው። (ራእይ 17:16, 17፤ 18:21) ጽድቅንና ፍትሕን ለሚወዱ ሁሉ የሚከተለውን ትእዛዝ ሰጥቷል:- “ሕዝቤ ሆይ፣ በኃጢአትዋ እንዳትተባበሩ ከመቅሠፍትዋም እንዳትቀበሉ ከእርስዋ [የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ከሆነችው ከታላቂቱ ባቢሎን] ዘንድ ውጡ፤ ኃጢአትዋ እስከ ሰማይ ድረስ ደርሶአልና፣ እግዚአብሔርም ዓመፃዋን አሰበ።” (ራእይ 18:4, 5) አዎን፣ አምላክ ‘ግጭቶችን የሚያባብስና ኅሊናን የሚያደነዝዝ እንዲሁም ሰዎች በሕልም ዓለም እንዲኖሩ፣ ጠባብ አስተሳሰብ እንዲኖራቸው፣ አጉል እምነት እንዲከተሉ፣ ጥላቻ እንዲያድርባቸውና በፍርሃት እንዲዋጡ የሚያደርግ’ ሃይማኖትን በእጅጉ ይጠላል!
እስከዚያው ድረስ ግን አምላክ እውነትን የሚወዱ ሰዎችን ንጹሕና ትክክለኛ ወደሆነው ሃይማኖት እየሰበሰበ ነው። ይህ ሃይማኖት አፍቃሪ፣ ፍትሐዊና ርኅሩኅ የሆነው ፈጣሪ ያወጣቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶችና የሚያስተምራቸውን ትምህርቶች አጥብቆ ይከተላል። (ሚክያስ 4:1, 2፤ ሶፎንያስ 3:8, 9፤ ማቴዎስ 13:30) አንተም የዚህ ሃይማኖት አባል መሆን ትችላለህ። ንጹሕና ትክክለኛ የሆነውን ሃይማኖት ለይተህ ማወቅ የምትችልበትን መንገድ በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ማግኘት የምትፈልግ ከሆነ ለዚህ መጽሔት አዘጋጆች መጻፍ ወይም የይሖዋ ምሥክሮችን ቀርበህ ማነጋገር ትችላለህ።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከተለያየ ዘርና የኑሮ ደረጃ የተውጣጡ ሰዎች ንጹሕና ትክክለኛ በሆነው ሃይማኖት ውስጥ ደስታ አግኝተዋል