ይሖዋ ፍቅራዊ ደግነቱ ብዙ ነው
ይሖዋ ፍቅራዊ ደግነቱ ብዙ ነው
“ይሖዋ . . . ፍቅራዊ ደግነቱ ብዙ ነው።”—መዝሙር 145:8 NW
1. አምላክ ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር ምን ያህል ነው?
“እግዚአብሔር ፍቅር ነው።” (1 ዮሐንስ 4:8) ይህ ልብን ደስ የሚያሰኝ አባባል የይሖዋ አገዛዝ በፍቅር ላይ የተመሠረተ መሆኑን ያሳያል። ለእርሱ የማይታዘዙ ሰዎች እንኳን በፍቅር ተነሳስቶ ከሰጠን ዝናብና ፀሐይ ተጠቃሚ መሆናቸው ይህን ያረጋግጣል። (ማቴዎስ 5:44, 45) ይሖዋ መላውን የሰው ዘር ስለሚወድድ ጠላቶቹ እንኳን ንስሐ ገብተው ወደ እርሱ ሊመለሱና የዘላለም ሕይወት ሊያገኙ ይችላሉ። (ዮሐንስ 3:16) ይሁን እንጂ እርሱን የሚወድዱ ሰዎች ጽድቅ በሰፈነበት አዲስ ምድር ውስጥ የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ከስህተታቸው የማይታረሙትን ክፉ ሰዎች በቅርቡ ጠራርጎ ያጠፋቸዋል።—መዝሙር 37:9-11, 29፤ 2 ጴጥሮስ 3:13
2. ይሖዋ ራሳቸውን ለወሰኑ አገልጋዮቹ ምን ዓይነት ፍቅር ያሳያል?
2 ይሖዋ ለእውነተኛ አምላኪዎቹ ያለው ፍቅር ጥልቅ እና ዘላለማዊ ነው። ይህ ፍቅር “ፍቅራዊ ደግነት” ወይም “ዘላለማዊ ፍቅር” ተብለው በተተረጎሙት የዕብራይስጥ ቃላት ተገልጿል። የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት ለይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት ከፍተኛ አድናቆት ነበረው። ከግል ተሞክሮው በመነሳት እንዲሁም አምላክ ከሌሎች ጋር በነበረው ግንኙነት ላይ በማሰላሰል “ይሖዋ . . . ፍቅራዊ ደግነቱ [ወይም “ዘላለማዊ ፍቅሩ”] ብዙ ነው” በማለት በሙሉ ልብ መዘመር ችሏል።—መዝሙር 145:8 NW
የአምላክን ታማኝ አገልጋዮች ለይቶ ማወቅ
3, 4. (ሀ) መዝሙር 145 የይሖዋን ታማኝ አገልጋዮች ለይተን ለማወቅ የሚረዳን እንዴት ነው? (ለ) ታማኝ አገልጋዮቹ አምላክን ‘የሚባርኩት’ እንዴት ነው?
3 የነቢዩ ሳሙኤል እናት የነበረችው ሐና ይሖዋ አምላክን በሚመለከት “የቅዱሳኑን [“የታማኞቹን፣” NW] እግር ይጠብቃል” በማለት ተናግራለች። (1 ሳሙኤል 2:9) ‘ታማኞቹ’ የተባሉት እነማን ናቸው? ንጉሥ ዳዊት መልሱን ይሰጠናል። ስለ ይሖዋ ግሩም ባሕርያት በአድናቆት ከተናገረ በኋላ “ቅዱሳንህም [“ታማኞችህ፣” NW] ይባርኩሃል” ብሏል። (መዝሙር 145:10) ሰዎች እንዴት አምላክን ሊባርኩ ይችላሉ? ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። በዋነኝነት እርሱን በማወደስ ወይም ስለ እርሱ በአድናቆት በመናገር ነው።
4 ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች በአንደበታቸው ተጠቅመው እርሱን የሚያወድሱ በመሆናቸው ተለይተው ይታወቃሉ። በማኅበራዊ ግብዣዎችም ሆነ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ዋነኛ የጭውውታቸው ርዕስ ምንድን ነው? የይሖዋ መንግሥት እንደሆነ ግልጽ ነው! ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች “የመንግሥትህን ክብር ይናገራሉ፣ ኃይልህንም ይነጋገራሉ” በማለት የዘመረውን የዳዊትን ስሜት ይጋራሉ።—መዝሙር 145:11
5. ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹ የሚያቀርቡለትን ውዳሴ እንደሚሰማ እንዴት እናውቃለን?
5 ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹ ለሚያቀርቡለት ውዳሴ ትኩረት ይሰጣል? አዎን፣ የሚሉትን ትኩረት ሰጥቶ ያዳምጣል። ሚልክያስ በጊዜያችን ስለሚኖረው እውነተኛ አምልኮ ትንቢት ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን የሚፈሩ እርስ በእርሳቸው ተነጋገሩ፤ እግዚአብሔርም አደመጠ፣ ሰማም፣ እግዚአብሔርንም ለሚፈሩ ስሙንም ለሚያስቡ የመታሰቢያ መጽሐፍ በፊቱ ተጻፈ።” (ሚልክያስ 3:16) ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹ ሲያወድሱት መስማት በጣም የሚያስደስተው ሲሆን ምንጊዜም አይረሳቸውም።
6. የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች በየትኛው ሥራቸው ተለይተው ይታወቃሉ?
6 የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች በሚያገኙት አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅመው እውነተኛውን አምላክ ለማያመልኩ ሰዎች በድፍረት በመስበካቸውም ተለይተው ይታወቃሉ። አዎን፣ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ‘ለሰው ልጆች ኃይሉን የመንግሥቱንም ግርማ ክብር ያስታውቃሉ።’ (መዝሙር 145:12) አንተስ በምታገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለሰዎች ስለ ይሖዋ መንግሥት ትናገራለህ? የይሖዋ መንግሥት በቅርቡ ከሚጠፉት ሰብዓዊ መንግሥታት በተቃራኒ ዘላለማዊ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 1:17) ሰዎች ስለ ይሖዋ ዘላለማዊ መንግሥት አውቀው ከእርሱ ጎን መሰለፋቸው በጣም አጣዳፊ ነው። ዳዊት “መንግሥትህ የዘላለም መንግሥት ናት፣ ግዛትህም ለልጅ ልጅ ነው” በማለት ዘምሯል።—መዝሙር 145:13
7, 8. በ1914 ምን ተፈጸመ? በአሁኑ ወቅት አምላክ በልጁ በኩል እየገዛ እንደሆነ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?
7 ከ1914 ጀምሮ ስለ ይሖዋ መንግሥት እንድንሰብክ የሚገፋፋን ተጨማሪ ምክንያት አግኝተናል። በዚያ ዓመት አምላክ በሰማይ መሲሐዊውን መንግሥት በማቋቋም የዳዊት ልጅ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ንጉሥ አድርጎ ሾሞታል። በዚህም ይሖዋ የዳዊት መንግሥት ለዘላለም ጸንቶ እንደሚኖር የገባውን ቃል ፈጽሟል።—2 ሳሙኤል 7:12, 13፤ ሉቃስ 1:32, 33
8 ኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሣዊ ሥልጣኑን መያዙን የሚያሳዩት ምልክቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ በስፋት እየተፈጸሙ መሆናቸው ይሖዋ በልጁ በኩል እየገዛ እንዳለ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። ከእነዚህ ምልክቶች መካከል ዋነኛው ኢየሱስ “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” በማለት የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች እንደሚያከናውኑት የተናገረው ሥራ ነው። (ማቴዎስ 24:3-14) የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች በዚህ ትንቢት አፈጻጸም ላይ በቅንዓት እየተካፈሉ በመሆናቸው ከስድስት ሚሊዮን የሚበልጡ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች በዚህ የማይደገም ታላቅ ሥራ የመሳተፍ አጋጣሚ አግኝተዋል። የአምላክ መንግሥት ተቃዋሚዎች በሙሉ በቅርቡ ተጠራርገው ይጠፋሉ።—ራእይ 11:15, 18
ከይሖዋ ሉዓላዊነት ጥቅም ማግኘት
9, 10. በይሖዋና በሰብዓዊ መሪዎች መካከል ያለው ልዩነት ምን ይመስላል?
9 ራሳችንን ለአምላክ የወሰንን ክርስቲያኖች ከሆንን ሉዓላዊ ጌታ ከሆነው ከይሖዋ ጋር የመሠረትነው ዝምድና ብዙ ጥቅሞች ያስገኝልናል። (መዝሙር 71:5፤ 116:12) ለምሳሌ ያህል አምላክን ስለምንፈራና ጽድቅን ስለምናደርግ ሞገሱን የምናገኝ ከመሆኑም በላይ በመንፈሳዊ ወደ እርሱ እንቀርባለን። (ሥራ 10:34, 35፤ ያዕቆብ 4:8) በአንጻሩ ግን ሰብዓዊ መሪዎች ብዙውን ጊዜ ሲቀራረቡ የሚታዩት ከጦር አዛዦች፣ ከሀብታም ነጋዴዎች ወይም የስፖርትና የመዝናኛው ዓለም ኮከቦችን ከመሳሰሉት ስመ ጥር ሰዎች ጋር ነው። ሶዌታን የተሰኘው በአፍሪካ የሚታተም አንድ ጋዜጣ አንድ ታዋቂ የመንግሥት ባለ ሥልጣን በአገሩ ውስጥ በድህነት የተጠቃን አካባቢ አስመልተው የተናገሩትን በመጥቀስ እንዲህ ብሏል:- “ብዙዎቻችን ወደ እነዚህ አካባቢዎች መሄድ የማንፈልግበት ምክንያት ይገባኛል። እንዲህ ያለ ሁኔታ መኖሩን ማስታወስ ስለማንፈልግ ብቻ ነው። ሕሊናችንን እረፍት ስለሚነሳውና ሰዎች በድህነት ሲማቅቁ እኛ ውድ መኪናዎች የምናሽከረክር መሆናችን ስለሚያሳፍረን ነው።”
10 እርግጥ ለዜጎቻቸው ደኅንነት ከልብ የሚያስቡ አንዳንድ ሰብዓዊ መሪዎች እንዳሉ አይካድም። ቢሆንም በጣም ጥሩ ሰው ነው የሚባለው መሪ እንኳን ዜጎቹን በቅርብ አያውቃቸውም። ለእያንዳንዱ ዜጋ ከልብ የሚያስብና ችግር ሲያጋጥማቸው ለሁሉም በቶሎ የሚደርስላቸው መሪ ይኖር ይሆን? ብለን እንጠይቅ ይሆናል። አዎን አለ። ዳዊት “እግዚአብሔር የተፍገመገሙትን ሁሉ ይደግፋቸዋል፣ የወደቁትንም ያነሣቸዋል” በማለት ጽፏል።—መዝሙር 145:14
11. የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ምን ዓይነት መከራዎች ይደርሱባቸዋል? ማንስ ይረዳቸዋል?
11 የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ፍጹም ስላልሆኑና “በክፉው” በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ባለው ዓለም ውስጥ ስለሚኖሩ ብዙ መከራና ሥቃይ ይደርስባቸዋል። (1 ዮሐንስ 5:19፤ መዝሙር 34:19) ክርስቲያኖች ስደት ያጋጥማቸዋል። አንዳንዶች በከባድ ሕመም ይሰቃያሉ ወይም የሚወዱትን ሰው በሞት በማጣታቸው ምክንያት በእጅጉ ያዝናሉ። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች የሚፈጽሟቸው ስህተቶች ተስፋ ቆርጠው አንገታቸውን እንዲደፉ ሊያደርጓቸው ይችላሉ። ይሁን እንጂ ምንም ዓይነት መከራ ቢደርስባቸው ይሖዋ ለእያንዳንዳቸው መጽናናትን ሊሰጣቸውና በመንፈሳዊ ሊያበረታቸው ምንጊዜም ዝግጁ ነው። ንጉሡ ኢየሱስ ክርስቶስም ለታማኝ ተገዥዎቹ ይህንን ዓይነት ፍቅራዊ አሳቢነት ያሳያል።—መዝሙር 72:12-14
በጊዜው የሚቀርብ ምግብ
12, 13. ይሖዋ ‘ሕይወት ላለው ሁሉ’ የሚያስፈልገውን የሚያሟላው እስከ ምን ድረስ ነው?
12 ይሖዋ በፍቅራዊ ደግነቱ ተነሳስቶ አገልጋዮቹ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ያሟላላቸዋል። ይህም ገንቢ ምግብ አትረፍርፎ ማቅረብን ይጨምራል። ንጉሥ ዳዊት:- “የሁሉ ዓይን አንተን ተስፋ ያደርጋል፤ አንተም ምግባቸውን በየጊዜው ትሰጣቸዋለህ። አንተ እጅህን ትከፍታለህ፣ ሕይወት ላለውም ሁሉ መልካምን ታጠግባለህ” በማለት ተናግሯል። (መዝሙር 145:15, 16) በችግር ጊዜያት እንኳን ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹ ‘የዕለት እንጀራቸውን’ ማግኘት እንዲችሉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይችላል።—ሉቃስ 11:3፤ 12:29, 30
13 ዳዊት ‘ሕይወት ያለው ሁሉ’ እንደሚጠግብ ተናግሯል። ይህ እንስሳትንም ይጨምራል። በየብስም ሆነ በባሕር ላይ የሚበቅሉት ዕጽዋት ባይኖሩ ኖሮ የውኃ ውስጥ ፍጥረታት፣ አእዋፋትና በምድር ላይ የሚኖሩ እንስሳት የሚተነፍሱት ኦክስጅንም ሆነ የሚመገቡት ምግብ አይኖራቸውም ነበር። (መዝሙር 104:14) ይሁን እንጂ ይሖዋ ለሁሉም የሚያስፈልጋቸውን ነገር ያሟላላቸዋል።
14, 15. በጊዜያችን መንፈሳዊ ምግብ እየቀረበ ያለው እንዴት ነው?
14 ሰዎች ከእንስሳት በተቃራኒ መንፈሳዊ ፍላጎት አላቸው። (ማቴዎስ 5:3 NW) ይሖዋ ለታማኝ አገልጋዮቹ ይህን ፍላጎታቸውን አትረፍርፎ ያሟላላቸዋል። ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት “ታማኝና ልባም ባሪያ” ለተከታዮቹ መንፈሳዊ ‘ምግብ በጊዜው’ እንደሚያቀርብላቸው ቃል ገብቶ ነበር። (ማቴዎስ 24:45) በዛሬው ጊዜ ይህ ባሪያ በመንፈስ የተቀቡትን የ144,000ዎቹን ቀሪ አባላት ያመለክታል። ይሖዋ በእነርሱ በኩል የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ አቅርቦልናል።
15 ለምሳሌ ያህል ከይሖዋ ሕዝቦች መካከል አብዛኞቹ በራሳቸው ቋንቋ አዲስና ትክክለኛ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በማግኘታቸው በእጅጉ ተጠቅመዋል። የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉምን በገዛ ቋንቋ ማግኘት ምንኛ መታደል ነው! ከዚህም በላይ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ማጥኛ ጽሑፎች ከ300 በሚበልጡ ቋንቋዎች ተዘጋጅተዋል። በምድር ዙሪያ የሚገኙ እውነተኛ የይሖዋ አምላኪዎች ይህን ሁሉ መንፈሳዊ ምግብ በማግኘታቸው ተባርከዋል። ለዚህ ሁሉ መመስገን ያለበት ማን ነው? ከይሖዋ አምላክ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም። ይሖዋ በፍቅራዊ ደግነቱ ተነሳስቶ ታማኙ ባሪያ መንፈሳዊ ‘ምግብ በጊዜው’ ማቅረብ የሚችልበትን ዝግጅት አመቻችቷል። በእነዚህ ዝግጅቶች አማካኝነት በጊዜያችን ባለው መንፈሳዊ ገነት ውስጥ የሚገኙ ‘ሕይወት ያላቸው ሁሉ’ ፍላጎታቸው ይሟላላቸዋል። በተጨማሪም የይሖዋ አገልጋዮች በቅርቡ ምድር ወደ ገነትነት ተለውጣ ለማየት ባላቸው ተስፋ ይደሰታሉ!—ሉቃስ 23:42, 43
16, 17. (ሀ) የይሖዋ ሕዝቦች መንፈሳዊ ምግብ በጊዜው እንደሚቀርብላቸው የሚያሳዩ ምሳሌዎችን ጥቀስ። (ለ) መዝሙር 145 የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ሰይጣን ያነሳውን አከራካሪ ጥያቄ በሚመለከት የሚሰማቸውን ስሜት የሚገልጸው እንዴት ነው?
16 የይሖዋ ሕዝቦች መንፈሳዊ ምግብ በጊዜው እንደሚቀርብላቸው የሚያሳይ አንድ ግሩም ምሳሌ እንመልከት። በ1939 በአውሮፓ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጀምሮ ነበር። በዚያው ዓመት በኅዳር 1 የመጠበቂያ ግንብ እትም ላይ “ገለልተኝነት” የሚል ርዕስ ወጥቶ ነበር። በርዕሱ ውስጥ በቀረበው ግልጽ ትምህርት መሠረት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ከጦርነቱ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ጥብቅ የገለልተኝነት አቋም መያዝ እንዳለባቸው ተገንዝበው ነበር። ይህ አቋማቸው ለስድስት ዓመታት በዘለቀው ጦርነት በሁለቱም ጎራዎች የተሰለፉትን መንግሥታት አስቆጥቷል። የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች በሥራቸው ላይ እገዳ ቢጣልባቸውና ስደት ቢደርስባቸውም የመንግሥቱን ምሥራች መስበካቸውን አላቋረጡም። ከ1939 እስከ 1946 ድረስ ባሉት ዓመታት 157 በመቶ የሚያህል አስገራሚ ጭማሪ አግኝተዋል። በተጨማሪም በጦርነቱ ወቅት የገለልተኝነት አቋማቸውን በመጠበቅ ያስመዘገቡት ታሪክ አሁንም ድረስ ሰዎች እውነተኛውን ሃይማኖት ለይተው እንዲያውቁ ይረዳል።—ኢሳይያስ 2:2-4
17 ይሖዋ የሚያቀርበው መንፈሳዊ ምግብ ወቅቱን የጠበቀ ብቻ ሳይሆን በጣም የሚያረካ ነው። መንግሥታት በተፋፋመ ፍልሚያ ላይ በነበሩበት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የይሖዋ ሕዝቦች ግን ከራሳቸው መዳን በእጅጉ በሚልቅ ነገር ላይ እንዲያተኩሩ ማበረታቻ ተሰጥቷቸው ነበር። ይሖዋ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ዋነኛው አከራካሪ ጉዳይ የእርሱ ሉዓላዊነት መሆኑን እንዲገነዘቡ አስቻላቸው። እያንዳንዱ የይሖዋ ምሥክር ታማኝነቱን በመጠበቅ፣ የይሖዋን ሉዓላዊነት በማረጋገጥና የዲያብሎስን ሐሰተኝነት በማጋለጥ ረገድ የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት ማወቁ ምንኛ የሚያስደስት ነው! (ምሳሌ 27:11) የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች በይሖዋ እና በአገዛዙ ላይ ነቀፌታ ከሰነዘረው ከሰይጣን በተቃራኒ “እግዚአብሔር በመንገዱ ሁሉ ጻድቅ” መሆኑን በስፋት ማወጃቸውን ይቀጥላሉ።—መዝሙር 145:17
18. ገንቢ መንፈሳዊ ምግብ በጊዜው እየቀረበ እንዳለ የሚያሳይ የቅርብ ጊዜ ምሳሌ ጥቀስ።
18 የአምላክ ሕዝቦች ገንቢ መንፈሳዊ ምግብ በጊዜው እንደሚቀርብላቸው የሚያሳየው ሌላው ምሳሌ “ቀናተኛ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች” በሚል ጭብጥ በ2002/03 በዓለም ዙሪያ በተደረጉት በመቶዎች የሚቆጠሩ የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ የወጣው ወደ ይሖዋ ቅረቡ (እንግሊዝኛ) የተሰኘው መጽሐፍ ነው። “በታማኝና ልባም ባሪያ” ተዘጋጅቶ በይሖዋ ምሥክሮች የታተመው ይህ መጽሐፍ በመዝሙር 145 ላይ የተጠቀሱትን ጨምሮ በይሖዋ አምላክ ድንቅ ባሕርያት ላይ ያተኩራል። ይህ ግሩም መጽሐፍ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ወደ እርሱ ይበልጥ እንዲቀርቡ በመርዳት ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት አያጠራጥርም።
ወደ ይሖዋ ይበልጥ የምንቀርብበት ጊዜ
19. የትኛው ወሳኝ ወቅት እየቀረበ ነው? ንጹሕ አቋማችንን ጠብቀን ይህን ጊዜ ለማለፍ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
19 በይሖዋ ሉዓላዊነት ላይ የተነሳው ጥያቄ እልባት የሚያገኝበት ወሳኝ ወቅት በጣም እየቀረበ ነው። በሕዝቅኤል ምዕራፍ 38 ላይ ‘የማጎጉ ጎግ’ ማለትም ሰይጣን እንደሚያከናውናቸው የተነገሩት ትንቢቶች በቅርቡ ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ። ይህም በይሖዋ ሕዝቦች ላይ የሚሰነዘረውን ዓለም አቀፋዊ ጥቃት ይጨምራል። ሰይጣን በዚህ ጥቃት አማካኝነት የአምላክን ታማኝ አገልጋዮች ንጹሕ አቋም ለማላላት የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል። በመሆኑም የይሖዋ አምላኪዎች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ወደ ይሖዋ ከልብ መጸለይና ለእርዳታ መጮህ ይኖርባቸዋል። ለአምላክ ያላቸው አምልኮታዊ ፍርሃትና ፍቅር በከንቱ ይቀራል? በፍጹም! ምክንያቱም መዝሙር 145:18-20 እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔር ለሚጠሩት ሁሉ፣ በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው። ለሚፈሩት ምኞታቸውን ያደርጋል፣ ልመናቸውንም ይሰማል ያድናቸዋልም። እግዚአብሔር የሚወድዱትን ሁሉ ይጠብቃል፤ ኃጢአተኞችንም ሁሉ ያጠፋል።”
20. በቅርቡ የመዝሙር 145:18-20 ቃላት እውነተኝነት የሚረጋገጠው እንዴት ነው?
20 ይሖዋ ክፉዎችን በሙሉ ጠራርጎ በሚያጠፋበት ጊዜ በእርግጥም በቅርብ እንዳለ ማወቅና የማዳን ኃይሉንም መመልከት ምንኛ የሚያስደስት ይሆናል! በቅርቡ በሚመጣው በዚህ ወሳኝ ወቅት ላይ ይሖዋ የሚያዳምጠው ‘በእውነት የሚጠሩትን’ ብቻ ነው። የግብዞችን ጩኸት ፈጽሞ አይሰማም። ክፉ ሰዎች ባለቀ ሰዓት ላይ የይሖዋን ስም መጥራታቸው ምንም እንደማይፈይድላቸው የአምላክ ቃል በግልጽ ያሳያል።—ምሳሌ 1:28, 29፤ ሚክያስ 3:4፤ ሉቃስ 13:24, 25
21. የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች መለኮታዊውን ስም መጠቀም እንደሚያስደስታቸው የሚያሳዩት እንዴት ነው?
21 ይሖዋን የሚፈሩ ሁሉ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እርሱን ‘በእውነት መጥራት’ ያለባቸው አሁን ነው። ታማኝ አገልጋዮቹ በጸሎታቸውና በስብሰባዎቻቸው ላይ በሚሰጧቸው ሐሳቦች ስሙን መጠቀም ያስደስታቸዋል። በግል ጭውውቶቻቸውም መለኮታዊውን ስም ይጠቀማሉ። እንዲሁም ለሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት ሲመሰክሩ የይሖዋን ስም ከመጠቀም ወደ ኋላ አይሉም።—ሮሜ 10:10, 13-15
22. ዓለማዊ ዝንባሌዎችና ፍላጎቶች እንዳይጋቡብን መታገላችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
22 በተጨማሪም ከይሖዋ ጋር ከመሠረትነው የቀረበ ዝምድና ለመጠቀም ፍቅረ ነዋይን፣ ተገቢ ያልሆነ መዝናኛን፣ ይቅር ባይ አለመሆንን ወይም ለተቸገሩ አሳቢነት አለማሳየትን የመሳሰሉ በመንፈሳዊነታችን ላይ ጎጂ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ዝንባሌዎች እንዳይጋቡብን መታገላችን በጣም አስፈላጊ ነው። (1 ዮሐንስ 2:15-17፤ 3:15-17) በጊዜው ማስተካከያ ካላደረግን እንደነዚህ ያሉት በመንፈሳዊ ጎጂ የሆኑ ባሕርያትና ልማዶች ከባድ ኃጢአት ወደ መፈጸም ሊመሩንና የይሖዋን ሞገስ ሊያሳጡን ይችላሉ። (1 ዮሐንስ 2:1, 2፤ 3:6) ይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት የሚያሳየን ለእርሱ ታማኝ ሆነን ስንቀጥል ብቻ እንደሆነ ማስታወሳችን አስተዋይነት ነው።—2 ሳሙኤል 22:26 አ.መ.ት
23. የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ሁሉ ምን ግሩም ተስፋ ይጠብቃቸዋል?
23 እንግዲያው ሐሳባችን የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች በሚጠብቃቸው ታላቅ ተስፋ ላይ እንዲያተኩር እናድርግ። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ይሖዋን ‘ቀኑን ሙሉ ለዘላለም’ ከፍ ከፍ ከሚያደርጉት፣ ከሚባርኩትና ከሚያወድሱት መካከል የመገኘት ግሩም ተስፋ ይኖረናል። (መዝሙር 145:1, 2) እንግዲያው ‘የዘላለም ሕይወትን’ በተስፋ ስንጠባበቅ ‘በእግዚአብሔር ፍቅር ውስጥ ራሳችንን እንጠብቅ።’ (ይሁዳ 20, 21) ሰማያዊው አባታችን ለሚወድዱት ሁሉ ከሚያሳየው ፍቅራዊ ደግነቱና ከሌሎቹም ግሩም ባሕርያቱ እየተጠቀምን ስንሄድ ዳዊት በመዝሙር 145 የመጨረሻ ቁጥር ላይ እንደሚከተለው ሲል የገለጸው ዓይነት ስሜት ይኑረን:- “አፌ የእግዚአብሔርን ምስጋና ይናገራል፤ ሥጋም ሁሉ ለዘላለም ዓለም የተቀደሰውን ስሙን ይባርክ።”
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• መዝሙር 145 የአምላክን ታማኝ አገልጋዮች ለይተን ለማወቅ የሚያስችለን እንዴት ነው?
• ይሖዋ ‘ሕይወት ላለው ሁሉ’ የሚያስፈልገውን የሚያሟላው እንዴት ነው?
• ወደ ይሖዋ መቅረብ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ስለ ታላላቅ ሥራዎቹ መወያየት ያስደስታቸዋል
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋ አገልጋዮች ሰዎች ስለ መንግሥቱ ግርማ እንዲያውቁ በድፍረት ይረዳሉ
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እንስሳት፦ Parque de la Naturaleza de Cabárceno
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ ‘ሕይወት ላለው ሁሉ’ ምግብ ይሰጣል
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ እንዲረዳቸው በጸሎት ለሚለምኑት ታማኝ አገልጋዮቹ ኃይልና መመሪያ ይሰጣቸዋል