የይሖዋን ልብ ደስ ያሰኙ ሴቶች
የይሖዋን ልብ ደስ ያሰኙ ሴቶች
“እግዚአብሔር እንደ ሥራሽ ይስጥሽ፤ . . . በእግዚአብሔር ዘንድ ደመወዝሽ ፍጹም ይሁን።”—ሩት 2:12
1, 2. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ የይሖዋን ልብ ደስ ያሰኙ ሴቶችን ታሪክ መመርመራችን እንዴት ይጠቅመናል?
ሁለት ሴቶች ለአምላክ ከነበራቸው ፍርሐት የተነሳ የፈርዖኑን ትእዛዝ ሳይፈጽሙ ቀሩ። አንዲት ጋለሞታ በእምነት በመገፋፋት ሕይወቷን አደጋ ላይ ጥላ ሁለት እስራኤላውያን ሰላዮችን አዳነች። አንዲት ሴት አስጊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ማስተዋልና ትሕትና በማሳየቷ የብዙዎችን ሕይወት ለማትረፍ ከመቻሏም በላይ ይሖዋ የቀባው ንጉሥ ደም ከማፍሰስ እንዲመለስ አደረገችው። አንዲት መበለት በይሖዋ አምላክ ላይ የነበራት እምነትና እንግዳ ተቀባይ መሆኗ የቀራትን ምግብ አሟጥጣ ለአንድ የአምላክ ነቢይ እንድትሰጥ አነሳሳት። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱት የይሖዋን ልብ ደስ ካሰኙ በርካታ ሴቶች መካከል እነዚህ ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው።
2 ይሖዋ ለእነዚህ ሴቶች ከነበረው አመለካከትና ከሰጣቸው በረከት መመልከት እንደሚቻለው ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ለግለሰቡ ፆታ ሳይሆን ለመንፈሳዊ ባሕርያቱ ነው። ለውጫዊ ነገሮች የላቀ ቦታ በሚሰጠው በዚህ ዓለም ውስጥ አንድ ሰው ለመንፈሳዊነቱ ቅድሚያ መስጠት ፈታኝ ሊሆንበት ይችላል። ሆኖም ይህንን ፈታኝ ሁኔታ መወጣት ይቻላል። በዛሬው ጊዜ በአምላክ ሕዝቦች መካከል ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሴቶች ይህንን በተግባር አሳይተዋል። እንደነዚህ ያሉት ክርስቲያን ሴቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት አምላክን የሚፈሩ ሴቶች ያሳዩትን እምነት፣ አስተዋይነት፣ እንግዳ ተቀባይነትና ሌሎች መልካም ባሕርያት ይኮርጃሉ። ክርስቲያን ወንዶችም ቢሆኑ በጥንት ዘመን የኖሩ በአርዓያነታቸው የሚጠቀሱ ሴቶች ያሳዩትን ግሩም ባሕርይ መኮረጅ እንደሚፈልጉ የታወቀ ነው። ይህን በተሟላ መልኩ ማድረግ የምንችልበትን መንገድ ለማየት በመግቢያው ላይ ስለተጠቀሱት ሴቶች መጽሐፍ ቅዱስ የያዘውን ዘገባ በዝርዝር እንመልከት።—ሮሜ 15:4፤ ያዕቆብ 4:8
የፈርዖንን ትእዛዝ ገሸሽ ያደረጉ ሴቶች
3, 4. (ሀ) ፈርዖን ወንድ እስራኤላውያን ሕፃናት ሲያዋልዱ ወዲያው እንዲገድሏቸው የሰጣቸውን ትእዛዝ ሲፓራና ፉሐ ሳይፈጽሙ የቀሩት ለምን ነበር? (ለ) ሁለቱ አዋላጆች ላሳዩት ድፍረትና አምላካዊ ፍርሃት ይሖዋ ወሮታ የከፈላቸው እንዴት ነው?
3 ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በኑረምበርግ፣ ጀርመን በተሰየመው ችሎት ፊት በጅምላ ጭፍጨፋ ተከስሰው የቀረቡ ብዙ ሰዎች ታዝዘን ያደረግነው ነው በማለት ለሠሩት ወንጀል ሰበብ ለማቅረብ ሞክረው ነበር። እስቲ እነዚህን ግለሰቦች በጥንቷ ግብጽ በአንድ በስም ያልተጠቀሰ አምባገነን ፈርዖን የግዛት ዘመን ከኖሩት ሲፓራና ፉሐ የተባሉ እስራኤላውያን አዋላጆች ጋር እናወዳድራቸው። ፈርዖን በከፍተኛ ፍጥነት እየበዙ የመጡትን እስራኤላውያን በመፍራቱ ወንድ እስራኤላዊ ሲወለድ እንዲገድሉት ሁለቱን አዋላጆች አዘዛቸው። ይህ ጭካኔ የተሞላበት ትእዛዝ ሲሰጣቸው ምን አደረጉ? ‘የግብፅ ንጉሥም እንዳዘዛቸው አላደረጉም፣ ወንዶቹን ሕፃናትም አዳኑአቸው።’ እነዚህ ሴቶች ለሰው ፍርሃት ያልተሸነፉት ለምን ነበር? ‘እግዚአብሔርን ስለፈሩ’ ነው።—ዘጸአት 1:15, 17፤ ዘፍጥረት 9:6
4 በእርግጥም አዋላጆቹ በይሖዋ ታምነዋል፤ እርሱም በምላሹ ከፈርዖን ቁጣ በመሰወር “ጋሻ” ሆኖላቸዋል። (2 ሳሙኤል 22:31፤ ዘጸአት 1:18-20) ሆኖም ይሖዋ የከፈላቸው ወሮታ ይህ ብቻ አልነበረም። ሲፓራና ፉሐ የራሳቸው ቤተሰብ እንዲኖራቸው በማድረግ ባርኳቸዋል። ከዚያም አልፎ የእነዚህ ሴቶች ስምና ያከናወኑት ተግባር በመንፈስ አነሳሽነት ባስጻፈው ቃሉ ውስጥ ሰፍሮ መጪው ትውልድ እንዲያነብበው በማድረግ አክብሯቸዋል። በአንጻሩ ግን የፈርዖኑ ስም በጊዜ ሂደት ተረስቶ ቀርቷል።—ዘጸአት 1:21፤ 1 ሳሙኤል 2:30ለ፤ ምሳሌ 10:7
5. በዛሬው ጊዜ ያሉ በርካታ ክርስቲያን ሴቶች የሲፓራና የፉሐ ዓይነት አቋም እንዳላቸው ያሳዩት እንዴት ነው? ይሖዋስ ወሮታ የሚከፍላቸው እንዴት ነው?
5 ዛሬስ እንደ ሲፓራና ፉሐ ያሉ ሴቶች ይኖሩ ይሆን? በሚገባ! በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ እንደነዚህ ያሉ ሴቶች ‘የንጉሥ አዋጅ’ ሕይወት አድን የሆነው መልእክት እንዳይሰበክ በከለከለባቸው አገሮች ውስጥ ነፃነታቸውን አልፎ ተርፎም ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው በድፍረት ይሰብካሉ። (ዕብራውያን 11:23፤ ሥራ 5:28, 29) እንደነዚህ ያሉት ደፋር ሴቶች ለአምላክ እና ለሰዎች ካላቸው ፍቅር የተነሳ ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን የምሥራች ከመስበክ ማንም እንዲያግዳቸው አይፈቅዱም። በዚህም ምክንያት በርካታ ክርስቲያን ሴቶች ተቃውሞንና ስደትን መቋቋም አስፈልጓቸዋል። (ማርቆስ 12:30, 31፤ 13:9-13) ይሖዋ ሲፓራና ፉሐ ያደረጉትን እንደተመለከተ ሁሉ እነዚህ ጎበዝና ደፋር እህቶች የሚያከናውኑትን ተግባርም በሚገባ ያውቃል፤ እስከ መጨረሻው በታማኝነት ከጸኑ ደግሞ ስማቸው “በሕይወት መጽሐፍ” እንዲሰፍር በማድረግ ለእነርሱ ያለውን ፍቅር ያሳያል።—ፊልጵስዩስ 4:3፤ ማቴዎስ 24:13
በፊት ጋለሞታ የነበረች ሴት የይሖዋን ልብ ደስ አሰኘች
6, 7. (ሀ) ረዓብ ስለ ይሖዋና ስለ ሕዝቦቹ ምን የምታውቀው ነገር ነበር? ይህስ ምን እንድታደርግ አነሳስቷታል? (ለ) ረዓብ በአምላክ ቃል ውስጥ በክብር የተገለጸችው እንዴት ነው?
6 በ1473 ከዘአበ ረዓብ የተባለች አንዲት ጋለሞታ የከነዓናውያን ከተማ በሆነችው በኢያሪኮ ትኖር ነበር። ረዓብ በወቅቱ የሚፈጸሙትን ክንውኖች ጠንቅቃ ታውቅ እንደነበረ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ሁለት እስራኤላውያን ሰላዮች እርሷ ቤት ለማደር በመጡ ጊዜ ከ40 ዓመታት በፊት እስራኤላውያን በተዓምራዊ መንገድ ከግብጽ ስለወጡበት ሁኔታ በዝርዝር ልትነግራቸው ችላለች! እንዲሁም ከጥቂት ጊዜ በፊት እስራኤላውያን ሴዎንና ዐግ በተባሉት የአሞራውያን ነገሥታት ላይ ስለተቀዳጁት ድል ታውቅ ነበር። ይህንን ማወቋ ምን ዓይነት ስሜት እንዳሳደረባት ተመልከት። ለሰላዮቹ “እግዚአብሔር ምድሪቱን እንደ ሰጣችሁ . . . አወቅሁ። . . . አምላካችሁም እግዚአብሔር በላይ በሰማይ በታችም በምድር እርሱ አምላክ ነውና” ብላቸዋለች። (ኢያሱ 2:1, 9-11) አዎን፣ ረዓብ ስለ ይሖዋና ለእስራኤላውያን ብሎ ስላደረጋቸው ተዓምራት የሰማቻቸው ነገሮች አዎንታዊ ምላሽ እንድትሰጥና በእርሱ ላይ እምነት እንድታሳድር አነሳስቷታል።—ሮሜ 10:10
7 ረዓብ እምነቷ ለተግባር ስላነሳሳት እስራኤላውያኑን ሰላዮች “በሰላም” ተቀብላቸዋለች። ከዚህም በላይ እስራኤላውያን በኢያሪኮ ላይ ጥቃት በሚሰነዝሩበት ጊዜ ሕይወቷን ለማትረፍ ምን ማድረግ እንዳለባት ሰላዮቹ የሰጧትን መመሪያ ታዝዛለች። (ዕብራውያን 11:31፤ ኢያሱ 2:18-21) ረዓብ ያከናወነቻቸው የእምነት ሥራዎች የይሖዋን ልብ ደስ እንዳሰኙት ምንም ጥርጥር የለውም። በመሆኑም ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ የአምላክ ወዳጅ ከተባለው ከአብርሃም ጋር ስሟን በመጥቀስ ክርስቲያኖች ምሳሌነቷን እንዲከተሉ በይሖዋ መንፈስ ተነሳስቶ ጽፏል። ያዕቆብ “እንደዚሁም ጋለሞታይቱ ረዓብ ደግሞ መልእክተኞቹን ተቀብላ በሌላ መንገድ በሰደደቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን?” ብሏል።—ያዕቆብ 2:25
8. ረዓብ ላሳየችው እምነትና ታዛዥነት ይሖዋ የባረካት እንዴት ነው?
8 ይሖዋ ረዓብን በበርካታ መንገዶች ባርኳታል። በመጀመሪያ ደረጃ፣ እርሷንም ሆነ በቤቷ የተጠለሉትን ሰዎች ሁሉ ይኸውም ‘የአባትዋን ቤተሰብና [“የእርሷ የሆኑትን፣” አ.መ.ት] ሁሉ’ ተዓምራዊ በሆነ መንገድ አድኗቸዋል። ከዚያም እነዚህ ሰዎች እንደ አገሩ ሕዝብ ሆነው “በእስራኤል መካከል” እንዲቀመጡ ፈቀደላቸው። (ኢያሱ 2:13፤ 6:22-25፤ ዘሌዋውያን 19:33, 34) የይሖዋ በረከት ግን በዚህ አላበቃም። የኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ አያት የመሆን ክብርም ሰጥቷታል። በአንድ ወቅት ጣዖት አምላኪ ለነበረች ከነዓናዊት የተደረገ እንዴት ያለ ታላቅ የፍቅራዊ ደግነት መግለጫ ነው! a—መዝሙር 130:3, 4
9. ይሖዋ ለረዓብና በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩ አንዳንድ ክርስቲያን ሴቶች የነበረው አመለካከት በዛሬው ጊዜ ላሉ እህቶች ማበረታቻ የሚሆናቸው እንዴት ነው?
9 እንደ ረዓብ ሁሉ ከመጀመሪያው መቶ ዘመን አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ አንዳንድ ክርስቲያን ሴቶች አምላክን ለማስደሰት ሲሉ ሥነ ምግባር የጎደለው አኗኗራቸውን ትተዋል። (1 ቆሮንቶስ 6:9-11) ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ የሥነ ምግባር ብልግና በጣም በተስፋፋባትና ትክክል እንደሆነ ተደርጎ ይታይ በነበረባት በጥንቷ ከነዓን ከነበረው ሁኔታ ጋር በሚመሳሰል አካባቢ እንዳደጉ ምንም ጥርጥር የለውም። ሆኖም ትክክለኛ በሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ላይ የተመሠረተ እምነት በማዳበራቸው አኗኗራቸውን ለመለወጥ ተገፋፍተዋል። (ሮሜ 10:17) በዚህም የተነሳ እነዚህ ሴቶችም “እግዚአብሔር አምላካቸው ተብሎ ሊጠራ በእነርሱ አያፍርም” ሊባልላቸው ይችላል። (ዕብራውያን 11:16) በእርግጥም ከፍተኛ ክብር ተሰጥቷቸዋል!
አስተዋይ በመሆኗ የተባረከች ሴት
10, 11. አቢግያ እርምጃ እንድትወስድ ያነሳሳት በናባልና በዳዊት መካከል የተፈጠረው የትኛው ሁኔታ ነው?
10 በጥንት ዘመን ይኖሩ የነበሩ በርካታ ታማኝ ሴቶች ከፍተኛ ማስተዋል በማሳየታቸው በይሖዋ ሕዝቦች ዘንድ እንደ ውድ ሀብት ታይተዋል። ከእነዚህ ሴቶች አንዷ ባለጸጋ የሆነው እስራኤላዊ ባለርስት ሚስት የሆነችው አቢግያ ናት። አቢግያ ያሳየችው ማስተዋል የብዙዎችን ሕይወት ከማትረፉም በላይ የወደፊቱን የእስራኤል ንጉሥ፣ ዳዊትን በደም ዕዳ ተጠያቂ ከመሆን ጠብቆታል። የአቢግያን ታሪክ አንደኛ ሳሙኤል ምዕራፍ 25 ላይ ማንበብ ትችላለህ።
11 በታሪኩ መጀመሪያ ላይ ዳዊትና ተከታዮቹ የናባል መንጋ በተሰማራበት አካባቢ ሰፍረው የነበሩ ሲሆን በደግነት ተነሳስተው የዚህን እስራኤላዊ ወንድማቸውን መንጎች አለምንም ክፍያ ቀን ከሌት ጠብቀውለታል። ዳዊት ስንቅ እያለቀበት ሲሄድ ምግብ እንዲሰጠው ለመጠየቅ አሥር ሰዎችን ወደ ናባል ሰደደ። ናባል ዳዊት ላደረገለት ነገር አመስጋኝነቱን ለመግለጽና ይሖዋ የቀባውን ሰው ለማክበር ግሩም አጋጣሚ ተዘርግቶለታል። ሆኖም ናባል የፈጸመው ተቃራኒውን ነበር። በቁጣ በመደንፋት ዳዊትን የዘለፈው ከመሆኑም በላይ መልእክተኞቹን ባዶ እጃቸውን ሰደዳቸው። ዳዊት ይህንን ሲሰማ 400 የታጠቁ ወንዶች አዘጋጀና አጸፋውን ለመመለስ ተነሳ። አቢግያ ባሏ የሰጠውን መጥፎ ምላሽ ስታውቅ የዳዊትን ቁጣ ለማብረድ በርከት ያለ ስንቅ አስቀድማ በመላክ ፈጣንና ማስተዋል የተሞላበት እርምጃ ወሰደች። ከዚያም እርሷ ራሷ ወደ ዳዊት ሄደች።—ቁጥር 2-20
12, 13. (ሀ) አቢግያ አስተዋይ እንዲሁም ለይሖዋና እርሱ ለቀባው ሰው ታማኝ መሆኗን ያሳየችው እንዴት ነው? (ለ) አቢግያ ወደ ቤት ስትመለስ ምን አደረገች? በመጨረሻስ ምን አጋጠማት?
12 አቢግያ ከዳዊት ጋር ስትገናኝ ምሕረት እንዲያደርግላቸው በትሕትና በመለመን ይሖዋ ለቀባው ሰው ያላትን ጥልቅ አክብሮት አሳይታለች። “የእግዚአብሔርን ጦርነት ስለምትዋጋ እግዚአብሔር በእውነት ለጌታዬ የታመነ ቤት ይሠራል” ካለችው በኋላ ይሖዋ በእስራኤል ላይ ዳዊትን መሪ እንደሚያደርገው ተናገረች። (ከቁጥር 28-30) በዚሁ ጊዜ አቢግያ ከፍተኛ ድፍረት በማሳየት ዳዊት ያደረበትን የበቀል ስሜት ካልተቆጣጠረው የደም ባለዕዳ እንደሚሆን ነገረችው። (ቁጥር 26, 31) የአቢግያ ትሕትና፣ ጥልቅ አክብሮትና ቀና አስተሳሰብ ዳዊት ወደ አእምሮው እንዲመለስ ረዳው። ዳዊት እንዲህ በማለት መለሰላት:- “ዛሬ እኔን ለመገናኘት አንቺን የሰደደ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን። ወደ ደም እንዳልሄድ፣ በእጄም በቀል እንዳላደርግ ዛሬ የከለከለኝ አእምሮሽ የተመሰገነ ይሁን፣ አንቺም የተመሰገንሽ ሁኚ።”—ቁጥር 32, 33
13 አቢግያ ወደ ቤት ስትመለስ ለዳዊት ስላደረገችው ስጦታ ለባሏ በግልጽ ልትነግረው ፈለገች። ይሁን እንጂ ቤቷ ስትደርስ ናባል “እጅግ ሰክሮ” ነበር። ስለዚህ ስካሩ እስኪበርድለት ጠብቃ ጉዳዩን ነገረችው። ናባል ምን ተሰማው? በጣም ከመደንገጡ የተነሳ ሰውነቱ በድን ሆነ። ከአሥር ቀናት በኋላ አምላክ ቀስፎ ገደለው። ዳዊት የናባልን መሞት ሲሰማ ከልብ የሚያደንቃትንና በጥልቅ የሚያከብራትን አቢግያን ለጋብቻ ጠየቃት። አቢግያም የዳዊትን ጥያቄ ተቀበለች።—ከቁጥር 34-42
አቢግያን መምሰል ትችላላችሁ?
14. የትኞቹን የአቢግያ ባሕርያት ይበልጥ ማዳበር እንፈልጋለን?
14 ወንዶችም ሆናችሁ ሴቶች አቢግያ ላይ ያስተዋላችሁት ይበልጥ ማዳበር የምትፈልጉት ባሕርይ አለ? ምናልባት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሟችሁ ይበልጥ አርቆ አሳቢነትና ማስተዋል የተሞላበት እርምጃ መውሰድ ትፈልጉ ይሆናል። ወይም አብረዋችሁ ያሉት ሰዎች በተቆጡበት ሰዓት በሰከነና ምክንያታዊነት በሚንጸባረቅበት መንገድ መናገር ትፈልጉ ይሆናል። ከሆነ ለምን ስለጉዳዩ ለይሖዋ አትጸልዩም? ‘በእምነት ለሚለምኑት’ ሁሉ ጥበብ፣ ማስተዋልና እውቀት ለመስጠት ቃል ገብቷል።—ያዕቆብ 1:5, 6፤ ምሳሌ 2:1-6, 10, 11
15. ክርስቲያን ሴቶች የአቢግያን ዓይነት ባሕርያት ማንጸባረቅ የሚኖርባቸው በተለይ የትኞቹ ሁኔታዎች ሲያጋጥሟቸው ነው?
15 በተለይ ደግሞ ለመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች እምብዛም ወይም እስከጭራሹ ምንም ትኩረት የማይሰጥ ባል ያላት ሴት እንደነዚህ ያሉት ግሩም ባሕርያት ያስፈልጓታል። ምናልባት ባለቤትሽ ከልክ በላይ ይጠጣ ይሆናል። ብዙዎች የሚስቶቻቸውን የዋህነት፣ ጥልቅ አክብሮትና መልካም አኗኗር በማየት እንደተለወጡ ሁሉ እንደነዚህ ዓይነት ባሎችም አንድ ቀን ሊለወጡ ይችላሉ።—1 ጴጥሮስ 3:1, 2, 4
16. አንዲት ክርስቲያን እህት በቤት ውስጥ ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥማት ከይሖዋ ጋር ያላትን ዝምድና ከማንኛውም ነገር በላይ ከፍ አድርጋ እንደምትመለከት የምታሳየው እንዴት ነው?
16 በቤት ውስጥ ምንም ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ መቋቋም ቢኖርብሽ የይሖዋን እርዳታ ማግኘት እንደምትችዪ አስታውሺ። (1 ጴጥሮስ 3:12) እንግዲያው ራስሽን በመንፈሳዊ ለማጠናከር ጥረት አድርጊ። ይሖዋ ጥበብና የልብ ሰላም እንዲሰጥሽ ጸልዪ። አዎን፣ አዘውትረሽ መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት፣ በጸሎት፣ በማሰላሰልና ከክርስቲያን ባልንጀሮችሽ ጋር በመሰብሰብ ወደ ይሖዋ ይበልጥ ቅረቢ። አቢግያ ባሏ መንፈሳዊ ሰው አለመሆኑ ለይሖዋ ባላት ፍቅርና እርሱ ለቀባው አገልጋዩ በነበራት አመለካከት ላይ ተጽዕኖ አላሳደረም። በጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶች በመመራት እርምጃ ወስዳለች። ባልየው ምሳሌ የሚሆን የአምላክ አገልጋይ በሆነበት ቤተሰብ ውስጥም እንኳ አንዲት ክርስቲያን ሚስት የራሷን መንፈሳዊነት ለመገንባትና ለመጠበቅ ትጋት ማሳየት እንዳለባት ትገነዘባለች። ባለቤቷ በመንፈሳዊም ሆነ በሰብዓዊ ሁኔታ እርሷን የመንከባከብ ኃላፊነት እንዳለበት እሙን ነው። ያም ቢሆን ግን “በፍርሐትና በመንቀጥቀጥ” መዳኗን የመፈጸሙ ኃላፊነት የሚወድቀው በራሷ ላይ ነው።—ፊልጵስዩስ 2:12፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:8
“የነቢይን ዋጋ” አገኘች
17, 18. (ሀ) በሰራፕታ የነበረችው መበለት ምን ለየት ያለ የእምነት ፈተና አጋጠማት? (ለ) መበለቷ ለኤልያስ ጥያቄ ምን ምላሽ ሰጠች? ይሖዋስ ለዚህ አድራጎቷ ወሮታ የከፈላት እንዴት ነው?
17 ይሖዋ በነቢዩ ኤልያስ ዘመን ለአንዲት ድሃ መበለት ያደረገው እንክብካቤ እውነተኛውን አምልኮ ለመደገፍ ራሳቸውንና ንብረታቸውን ለሚሰጡ ሰዎች ጥልቅ አድናቆት እንዳለው ያሳያል። በኤልያስ ዘመን ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ድርቅ ተከስቶ ስለነበር በሰራፕታ የምትኖረውን መበለትና ትንሹን ልጅዋን ጨምሮ ብዙዎች ለረሃብ ተጋልጠው ነበር። የነበራቸው ምግብ በሙሉ ተሟጥጦ ለአንድ ጊዜ ብቻ የሚሆን ሲቀራቸው ነቢዩ ኤልያስ በእንግድነት ወደ እነርሱ መጣ። ነቢዩ ፈጽሞ ያልተጠበቀ ጥያቄ አቀረበ። ሴትየዋ የነበረችበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ቢያውቅም የቀረቻትን ዘይትና ዱቄት አሟጥጣ “ታናሽ እንጎቻ” እንድትጋግርለት ጠየቃት። ሆኖም አክሎ እንዲህ አላት:- “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና:- በምድር ላይ እግዚአብሔር ዝናብ እስከሚሰጥበት ቀን ድረስ፣ ዱቄቱ ከማድጋ አይጨረስም፣ ዘይቱም ከማሰሮው አይጐድልም።”—1 ነገሥት 17:8-14
18 እንደዚህ ያለ ያልተለመደ ጥያቄ ቢቀርብልሽ ምን ታደርጊ ነበር? በሰራፕታ የነበረችው መበለት ኤልያስ የይሖዋ ነቢይ እንደሆነ ስለተገነዘበች መሆን አለበት “እንደ ኤልያስ ቃል አደረገች።” ይሖዋ መበለቷ ላሳየችው የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ምን ምላሽ ሰጠ? በረሃቡ ዘመን ሴትየዋን፣ ልጅዋንና ኤልያስን ተዓምራዊ በሆነ መንገድ መግቧቸዋል። (1 ነገሥት 17:15, 16) አዎን፣ በሰራፕታ የነበረችው መበለት እስራኤላዊት ባትሆንም ይሖዋ “የነቢይን ዋጋ” ሰጥቷታል። (ማቴዎስ 10:41) የአምላክ ልጅም ይህቺን መበለት በትውልድ አገሩ በናዝሬት ለነበሩት እምነት የለሽ ሰዎች እንደ ምሳሌ አድርጎ በመጥቀስ አክብሯታል።—ሉቃስ 4:24-26
19. በዛሬው ጊዜ ያሉ በርካታ ክርስቲያን ሴቶች በሰራፕታ የነበረችው መበለት ዓይነት መንፈስ የሚያሳዩት እንዴት ነው? ይሖዋስ ስለ እነዚህ ሴቶች ምን ይሰማዋል?
19 ዛሬም በርካታ ክርስቲያን ሴቶች የሰራፕታዋ መበለት ዓይነት ዝንባሌ ያሳያሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አብዛኞቹ ኑሯቸው ዝቅተኛ የሆነና የሚያስተዳድሩት ቤተሰብ ያላቸው ለጋስ ክርስቲያን እህቶች ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችንና ሚስቶቻቸውን ተቀብለው ያስተናግዳሉ። ሌሎች ደግሞ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮችን ቤታቸው ይጋብዛሉ፣ ችግረኞችን ይረዳሉ ወይም በሌሎች መንገዶች የመንግሥቱን ሥራ ለመደገፍ ራሳቸውንና ገንዘባቸውን ይሰጣሉ። (ሉቃስ 21:4) ይሖዋ እንደነዚህ ያሉ መሥዋዕቶችን ይመለከታል? ያለምንም ጥርጥር! “እግዚአብሔር፣ ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ እስከ አሁንም ስለምታገለግሉአቸው፣ ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለምና።”—ዕብራውያን 6:10
20. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የሚብራራው ምንድን ነው?
20 በመጀመሪያው መቶ ዘመን አምላክን የሚፈሩ በርካታ ሴቶች ኢየሱስንና ሐዋርያቱን የማገልገል መብት አግኝተው ነበር። በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እነዚህ ሴቶች የይሖዋን ልብ እንዴት እንዳስደሰቱ እንመለከታለን። በተጨማሪም በአስቸጋሪ ጊዜያትም እንኳ ይሖዋን በሙሉ ልባቸው የሚያገለግሉ በዘመናችን ያሉ ሴቶችን ምሳሌ እናያለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በማቴዎስ ዘገባ መሠረት በኢየሱስ የትውልድ ሐረግ ዝርዝር ውስጥ በስም የተጠቀሱት አራት ሴቶች ሲሆኑ እነርሱም ትዕማር፣ ረዓብ፣ ሩትና ማርያም ናቸው። አራቱም ሴቶች በአምላክ ቃል ውስጥ ከፍ ተደርገው ተገልጸዋል። —ማቴዎስ 1:3, 5, 16
ለክለሳ ያህል
• ከዚህ ቀጥሎ የቀረቡት ሴቶች የይሖዋን ልብ ደስ ያሰኙት እንዴት ነው?
• ሲፓራና ፉሐ
• ረዓብ
• አቢግያ
• በሰራፕታ የነበረችው መበለት
• እነዚህ ሴቶች በተዉት ምሳሌ ላይ ማሰላሰላችን በግለሰብ ደረጃ የሚጠቅመን እንዴት ነው? አብራራ።
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በርካታ ታማኝ ሴቶች ‘የንጉሥን አዋጅ’ ሳይፈሩ አምላክን አገልግለዋል
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ረዓብ እምነት በማሳየት ረገድ ግሩም ምሳሌ የሆነችው እንዴት ነው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አቢግያ ካሳየቻቸው ባሕርያት መካከል የትኞቹን መኮረጅ ትፈልጋላችሁ?
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዛሬው ጊዜ ያሉ በርካታ ክርስቲያን ሴቶች በሰራፕታ የነበረችው መበለት ያሳየችው ዓይነት መንፈስ ያንጸባርቃሉ