በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የማያዳላው አምላካችንን ይሖዋን ምሰሉ

የማያዳላው አምላካችንን ይሖዋን ምሰሉ

የማያዳላው አምላካችንን ይሖዋን ምሰሉ

“እግዚአብሔር ለሰው ፊት አያደላም።”​—⁠ሮሜ 2:11

1, 2. (ሀ) ይሖዋ በጥቅሉ ከነዓናውያንን በሚመለከት የነበረው ዓላማ ምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ያደረገው ምን ነበር? ይህስ ምን ጥያቄዎች ያስነሳል?

 ዜው በ1473 ከዘአበ ሲሆን በሞዓብ ሜዳ ላይ የሰፈሩት እስራኤላውያን ሙሴ የሚነግራቸውን በጥሞና እያዳመጡ ነው። ከዮርዳኖስ ወንዝ ማዶ አስቸጋሪ ሁኔታ ይጠብቃቸዋል። ይሖዋ በእነርሱ አማካኝነት በተስፋይቱ ምድር ውስጥ የሚገኙትን ሰባቱን ኃያላን ብሔራት ለማጥፋት ዓላማ እንዳለው ሙሴ አሳወቃቸው። “አምላክህ እግዚአብሔርም በእጅህ አሳልፎ በሰጣቸው በመታሃቸውም ጊዜ፣ ፈጽመህ አጥፋቸው” በማለት ሙሴ የተናገራቸው ቃላት ከፍተኛ ማበረታቻ ሰጥቷቸዋል። እስራኤላውያን ከእነዚህ ብሔራት ጋር ቃል ኪዳን እንዲገቡም ሆነ ምህረት እንዲያሳዩአቸው አልተፈቀደላቸውም።​—⁠ዘዳግም 1:1፤ 7:1, 2

2 ሆኖም ይሖዋ እስራኤላውያን ጥቃት ከሰነዘሩበት ከመጀመሪያው ከተማ አንድ ቤተሰብ በሕይወት እንዲተርፍ አድርጓል። እንዲሁም በሌሎች አራት ከተሞች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችም የአምላክን ጥበቃ አግኝተዋል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? እነዚህ ከነዓናውያን በሕይወት የተረፉበት አስገራሚ ሁኔታ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረናል? እርሱን መምሰል የምንችለውስ እንዴት ነው?

የይሖዋን ዝና ሰምተው እርምጃ ወሰዱ

3, 4. እስራኤላውያን ስለተቀዳጁት ድል የተሰማው ወሬ በከነዓን በሚኖሩ ሰዎች ላይ ምን ተጽእኖ አሳድሯል?

3 እስራኤላውያን ተስፋይቱን ምድር ከመውረሳቸው በፊት በምድረ በዳ በቆዩባቸው 40 ዓመታት ይሖዋ ይጠብቃቸውና ይዋጋላቸው ነበር። በተስፋይቱ ምድር ደቡባዊ ክፍል እስራኤላውያን ከከነዓናዊው ንጉሥ ከዓራድ ጋር ጦርነት ገጠሙ። (ዘኍልቍ 21:​1-3) ከዚያም በኤዶም ምድር ዳርቻ አድርገው ወደ ሰሜን በማቅናት ከሙት ባሕር በስተ ሰሜን ምሥራቅ ወደሚገኘው ምድር ተጓዙ። ቀደም ሲል ሞዓባውያን ይኖሩበት የነበረው ይህ ቦታ በዚህ ወቅት በአሞራውያን ተይዞ ነበር። አሞራዊው ንጉሥ ሴዎን እስራኤላውያንን በግዛቱ እንዳያልፉ ከለከላቸው። በዚህም ምክንያት እስራኤላውያን ከአርኖን ሸለቆ በስተ ሰሜን በሚገኘው በያሀጽ ከንጉሥ ሴዎን ጋር ውጊያ የገጠሙ ሲሆን ንጉሡም ተገደለ። (ዘኍልቍ 21:23, 24፤ ዘዳግም 2:30-33) ከዚህ በስተ ሰሜን ደግሞ ዐግ የተባለ ንጉሥ በባሳን በሚኖሩ አሞራውያን ላይ ይገዛ ነበር። ምንም እንኳ ዐግ ግዙፍ ቁመና የነበረው ቢሆንም ይሖዋን የሚቋቋምበት አቅም ስላልነበረው በኤድራይ ተገደለ። (ዘኍልቍ 21:33-35፤ ዘዳግም 3:1-3, 11) ስለ እነዚህ ድሎች የተሰራጨው ወሬ እስራኤላውያን ከግብጽ ስለወጡበት ሁኔታ ከሚናገሩት ታሪኮች ጋር ተዳምሮ በከነዓን ምድር በሚኖሩ ሰዎች ላይ ከባድ ፍርሃት አሳድሮባቸዋል። a

4 እስራኤላውያን የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግረው ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ከነዓን ምድር ከገቡ በኋላ በጌልገላ ሰፈሩ። (ኢያሱ 4:9-19) ከዚህ ብዙም ሳይርቅ በቅጥር የተከበበችው የኢያሪኮ ከተማ ትገኛለች። ከነዓናዊቷ ረዓብ ስለ ይሖዋ ድንቅ ሥራዎች የሰማችው ነገር በእምነት እርምጃ እንድትወስድ አነሳሳት። በዚህም ምክንያት ይሖዋ ኢያሪኮ እንድትጠፋ ሲያደርግ እርሷንና በቤትዋ የነበሩትን ሰዎች አድኗቸዋል።​—⁠ኢያሱ 2:1-13፤ 6:17, 18፤ ያዕቆብ 2:25

5. ገባዖናውያን ብልሃት እንዲጠቀሙ ያነሳሳቸው ምንድን ነው?

5 ከዚያም እስራኤላውያን በዮርዳኖስ ወንዝ አቅራቢያ ከሚገኘው ዝቅተኛ ቦታ ተነስተው በተስፋይቱ ምድር መሃል ወደሚገኘው ተራራማ አካባቢ አመሩ። ኢያሱ በይሖዋ መመሪያ መሠረት የደፈጣ ውጊያ ስልት በመጠቀም የጋይን ከተማ አጠፋት። (ኢያሱ ምዕራፍ 8) በርካታ የከነዓናውያን ነገሥታት ድል እያደረገ በመገስገስ ላይ ስላለው ሕዝብ ወሬ በመስማታቸው ግንባር ፈጥረው ለጦርነት ተዘጋጁ። (ኢያሱ 9:1, 2) የኤዊያውያን ከተማ የሆነችው የገባዖን ነዋሪዎች ግን የወሰዱት እርምጃ ከዚህ የተለየ ነበር። ኢያሱ 9:4 “እነርሱ ደግሞ ተንኰል አደረጉ” በማለት ይናገራል። እነርሱም እንደ ረዓብ፣ ይሖዋ ሕዝቡን ከግብጽ በማውጣትና ሴዎንንና ዐግን በማጥፋት ያደረገውን ማዳን ሰምተው ነበር። (ኢያሱ 9:6-10) ገባዖናውያኑ ከዚህ ሕዝብ ጋር ውጊያ መግጠሙ እንደማያዋጣ ገብቷቸዋል። ስለዚህ በአቅራቢያቸው የነበሩትን ከፊራ፣ ብኤሮትና ቂርያትይዓሪም የተባሉ ሦስት ከተሞችንና ገባዖንን የሚወክሉ ሰዎችን ከሩቅ አገር እንደመጡ አስመስለው በጌልገላ ወደሚገኘው ወደ ኢያሱ ላኩ። የፈጠሩት ዘዴ ተሳካላቸውና ኢያሱ እንደማያጠፋቸው ቃል ገባላቸው። ከሦስት ቀን በኋላ ኢያሱና ሕዝቡ መታለላቸውን አወቁ። ቢሆንም ቃል ኪዳን የገቡት በይሖዋ ስም ስለነበር ቃላቸውን ለማክበር ተገደዱ። (ኢያሱ 9:16-19) ይሖዋስ ጉዳዩን ተቀበለው?

6. ኢያሱ ከገባዖናውያን ጋር ለገባው ቃል ኪዳን ይሖዋ የሰጠው ምላሽ ምን ነበር?

6 ገባዖናውያኑ ለእስራኤላውያን አልፎ ተርፎም በመገናኛው ድንኳን ለሚገኘው “ለእግዚአብሔር መሠዊያ” እንጨት ቆራጮችና ውኃ ቀጂዎች እንዲሆኑ ተደርገዋል። (ኢያሱ 9:21-27) በተጨማሪም አምስት የአሞራውያን ነገሥታትና ሠራዊቶቻቸው ገባዖናውያንን ለመውጋት ሲነሱ ይሖዋ በተአምራዊ ሁኔታ አድኗቸዋል። በጦርነቱ ኢያሱና ሠራዊቱ ከገደሏቸው ይልቅ በበረዶ ድንጋይ የሞቱት ይበልጡ ነበር። እንዲያውም ኢያሱ ጠላቶቻቸውን ጠራርገው ማጥፋት ይችሉ ዘንድ ፀሐይና ጨረቃ እንዲቆሙ ያቀረበውን ልመና ይሖዋ ሰምቷል። ኢያሱ “እግዚአብሔር ለእስራኤል ይዋጋ ነበርና እግዚአብሔር የሰውን ቃል የሰማበት እንደዚያ ያለ ቀን ከዚያም በፊት ከዚያም በኋላ አልነበረም” በማለት ተናግሯል።​—⁠ኢያሱ 10:1-14

7. በአንዳንድ ከነዓናውያን ሁኔታ ተፈጻሚነት ያገኘው ጴጥሮስ የገለጸው እውነታ ምንድን ነው?

7 ከነዓናዊቷ ረዓብና ቤተሰቧ እንዲሁም ገባዖናውያን ይሖዋን በመፍራት ተገቢውን እርምጃ ወስደዋል። የእነርሱ ታሪክ ከጊዜ በኋላ ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጴጥሮስ “እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደ ሆነ” የተናገረውን ሐሳብ እውነተኝነት በግልጽ ያሳያል።​—⁠ሥራ 10:34, 35

ይሖዋ ከአብርሃምና ከእስራኤላውያን ጋር የነበረው ግንኙነት

8, 9. ይሖዋ ከአብርሃምና ከእስራኤል ብሔር ጋር በነበረው ግንኙነት የማያዳላ አምላክ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

8 ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ አምላክ ለአብርሃምና ለዘሩ ያሳየውን የማይገባ ደግነት በተመለከተ ጽፏል። አብርሃም ‘የእግዚአብሔር ወዳጅ’ ለመሆን ያስቻለው የነበረው እምነት እንጂ የትውልድ ሐረጉ አልነበረም። (ያዕቆብ 2:23) አብርሃም ያሳየው እምነትና ለይሖዋ የነበረው ፍቅር ለዘሮቹ በረከት አስገኝቶላቸዋል። (2 ዜና መዋዕል 20:7) ይሖዋ “በእውነት በረከትን እባርክሃለሁ፣ ዘርህንም እንደ ሰማይ ከዋክብትና በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ አበዛዋለሁ” በማለት ቃል ገብቶለት ነበር። ይሁን እንጂ ከዚያ በመቀጠል “የምድር አሕዛብ ሁሉም በዘርህ ይባረካሉ” እንዳለው ልብ በል።​—⁠ዘፍጥረት 22:17, 18፤ ሮሜ 4:1-8

9 ይሖዋ ከእስራኤላውያን ጋር የነበረው ግንኙነት የሚያዳላ አምላክ መሆኑን ሳይሆን የሚታዘዙትን ሰዎች እንዴት እንደሚባርካቸው ያሳያል። ይህም ታማኝ ለሆኑት አገልጋዮቹ ታማኝ ፍቅሩን እንዴት እንደሚገልጽላቸው የሚያሳይ ምሳሌ ነው። እስራኤላውያን ለይሖዋ “የተመረጠ ርስት” ቢሆኑም እንኳ ሌሎች ሕዝቦች የአምላክን ደግነት የማግኘት አጋጣሚ የላቸውም ማለት አይደለም። (ዘጸአት 19:5፤ ዘዳግም 7:6-8) እርግጥ ነው፣ ይሖዋ እስራኤላውያንን ከግብጽ ባርነት ነጻ ካወጣቸው በኋላ “እኔ ከምድር ወገን ሁሉ እናንተን ብቻችሁን አውቄአችኋለሁ” ብሏቸዋል። ይሁን እንጂ ይሖዋ በነቢዩ አሞጽና በሌሎች ነቢያት አማካኝነት ‘ለአሕዛብ ሁሉ’ ግሩም ተስፋ ዘርግቶላቸዋል።​—⁠አሞጽ 3:2፤ 9:11, 12፤ ኢሳይያስ 2:​2-4

ኢየሱስ​—⁠የማያዳላው መምህር

10. ኢየሱስ አድልዎ ባለማሳየት ረገድ አባቱን የኮረጀው እንዴት ነው?

10 የአባቱ ፍጹም ነጸብራቅ የነበረው ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት የማያዳላውን ይሖዋን ኮርጆዋል። (ዕብራውያን 1:3) ኢየሱስ በወቅቱ በዋነኝነት ትኩረት ያደረገው ‘ከእስራኤል ቤት የጠፉትን በጎች’ ለማግኘት ነበር። ይሁን እንጂ በአንድ የውኃ ጉድጓድ አጠገብ ላገኛት ሳምራዊት ምስክርነት ከመስጠት ወደ ኋላ አላለም። (ማቴዎስ 15:24፤ ዮሐንስ 4:7-30) እንዲሁም አንድ ከአሕዛብ ወገን የሆነ የመቶ አለቃ ያቀረበለትን ልመና ሰምቶ ተአምር ፈጽሟል። (ሉቃስ 7:1-10) ይህ ለአምላክ ሕዝቦች ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ሰዎችም ፍቅሩን በተግባር እንደገለጸ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትም ምሥራቹን በሰፊው ሰብከዋል። የይሖዋን በረከት ለማግኘት መሥፈርቱ የልብ ዝንባሌ እንጂ የዘር ሐረግ አለመሆኑ በግልጽ ታይቷል። እውነትን የተራቡ ትሁትና ልበ ቅን ሰዎች ለመንግሥቱ ምሥራች አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተዋል። በአንጻሩ ደግሞ ኩሩና ትዕቢተኛ የነበሩ ሰዎች ለኢየሱስና ለመልእክቱ ንቀት አሳይተው ነበር። ኢየሱስ “የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ፣ ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግናለሁ፤ አዎን አባት ሆይ፣ ፈቃድህ በፊትህ እንዲህ ሆኖአል” በማለት ተናግሯል። (ሉቃስ 10:21) በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መንገድ መሆኑን ስለምንገነዘብ ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ፍቅርና እምነት በማሳየት ከአድልዎ እንርቃለን።

11. በመጀመሪያው መቶ ዘመን በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ አድልዎ አልነበረም ማለት የሚቻለው እንዴት ነው?

11 በመጀመሪያው መቶ ዘመን በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ አይሁዳውያንም ሆኑ አሕዛብ እኩል ቦታ ነበራቸው። ጳውሎስ “በጎ ሥራ ለሚያደርጉ ሁሉ ምስጋናና ክብር ሰላምም ይሆንላቸዋል፣ አስቀድሞ ለአይሁዳዊ ደግሞም ለግሪክ ሰው። እግዚአብሔር ለሰው ፊት አያደላምና።” b (ሮሜ 2:10, 11) ከይሖዋ የማይገባ ደግነት ተጠቃሚ መሆናቸው የተመካው በዘር ሐረጋቸው ላይ ሳይሆን ስለ ይሖዋና በልጁ በኢየሱስ ቤዛ አማካኝነት ስለተከፈተላቸው ተስፋ ሲማሩ በሚሰጡት ምላሽ ላይ ነው። (ዮሐንስ 3:​16, 36) ጳውሎስ “በግልጥ አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ አይደለምና፣ በግልጥ በሥጋ የሚደረግ መገረዝም መገረዝ አይደለምና፤ ዳሩ ግን በስውር አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ ነው፣ መገረዝም በመንፈስ የሚደረግ የልብ መገረዝ ነው እንጂ በመጽሐፍ አይደለም” በማለት ጽፏል። ከዚያም “አይሁዳዊ” (“የይሁዳ ወገን” ማለት ሲሆን የተመሰገነ ወይም የተወደሰ የሚል ትርጉም አለው) የሚለውን ቃል ፍቺ በመጠቀም “የእርሱ ምስጋና ከእግዚአብሔር ነው እንጂ ከሰው አይደለም” በማለት ተናግሯል። (ሮሜ 2:28, 29) ይሖዋ የሚያመሰግነው ያለ አድልዎ ነው። እኛስ?

12. ራእይ 7:9 ምን ተስፋ ይሰጣል? ለእነማን?

12 ከጊዜ በኋላ ሐዋርያው ዮሐንስ በአንድ መንፈሳዊ ብሔር የተመሰሉትን “ከእስራኤል ልጆች ነገድ ሁሉ የታተሙ” 144, 000 ታማኝ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በራእይ ተመልክቶ ነበር። ከዚህ በኋላ ዮሐንስ ‘ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነጭ ልብስ ለብሰው የዘንባባንም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆመው’ ተመለከተ። (ራእይ 7:4, 9) ስለሆነም ዛሬ ባለው ክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ከተለያየ ዘር ወይም ቋንቋ የመጡ ሰዎች ይገኛሉ። እነዚህ ሰዎች ‘ታላቁን መከራ’ በሕይወት የማለፍና በአዲሱ ዓለም ውስጥ ‘ከሕይወት ውኃ ምንጭ’ የመጠጣት ተስፋ አላቸው።​—⁠ራእይ 7:14-17

አድልዎ አለማድረግ የሚያስገኘው መልካም ውጤት

13-15. (ሀ) የዘርና የባህል ልዩነቶችን ማስወገድ የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ሞቅ ያለ የወዳጅነት ስሜት ማሳየት የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች የሚያጎሉ ምሳሌዎችን ጥቀስ።

13 አንድ ጥሩ አባት ልጆቹን የሚያውቃቸውን ያህል ይሖዋም ያውቀናል። እኛም ለሌሎች ባሕልና አስተዳደግ ትኩረት በመስጠት በተሻለ ሁኔታ ስናውቃቸው በመካከላችን ላለው ልዩነት ብዙም ቦታ አንሰጠውም። የዘር ልዩነት የሚፈጥረው እንቅፋት ተወግዶ በመካከላችን ያለው የወዳጅነትና የፍቅር መንፈስ እየጠነከረ ይሄዳል። አንድነታችንም ይበልጥ ይጎለብታል። (1 ቆሮንቶስ 9:19-23) በውጭ አገር ተመድበው የሚያገለግሉ ሚስዮናውያን ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ይሆኑናል። በተመደቡበት አገር ለሚኖሩት ሰዎች ትኩረት የሚሰጡ ሲሆን በዚህም ምክንያት ከጉባኤው አባላት ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ይመሠርታሉ።​—⁠ፊልጵስዩስ 2:4

14 አድልዎ አለማድረግ የሚያስገኘው መልካም ውጤት በብዙ አገሮች ውስጥ በግልጽ ይታያል። ከኢትዮጵያ የመጣው አክሊሉ የእንግሊዝ ዋና ከተማ በሆነችው በለንደን ሲኖር ብቸኝነት ይሰማው ነበር። አክሊሉ በበርካታ ታላላቅ የአውሮፓ ከተሞች ውስጥ እንደሚታየው ሁሉ በለንደንም ከሌሎች አገሮች የመጡ ሰዎችን እንደሚያገልሉ የተሰማው ሲሆን ይህም የብቸኝነት ስሜቱን አባባሰበት። በይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ በሚደረገው ስብሰባ ላይ ሲገኝ ግን ያጋጠመው ሁኔታ በጣም የተለየ ነበር! እዚያ ሞቅ ያለ አቀባበል ያደረጉለት ሲሆን ብዙም ሳይቆይ የባይተዋርነት ስሜቱ ተወገደለት። በአጭር ጊዜ ውስጥ ለፈጣሪው ያለው አድናቆት እየጨመረ ሄደ። ብዙም ሳይቆይ በሚኖርበት አካባቢ የመንግሥቱን ምሥራች ለሌሎች ለማካፈል በሚያስችሉት አጋጣሚዎች መጠቀም ጀመረ። አንድ ቀን አብሮት የሚያገለግለው ወንድም ምን ግቦች እንዳሉት ሲጠይቀው እርሱ በሚናገረው በአማርኛ ቋንቋ የሚካሄድ ጉባኤ ተቋቁሞ የማየት ምኞት እንዳለው ነገረው። አክሊሉ የሚሰበሰብበት የእንግሊዝኛ ጉባኤ ሽማግሌዎች ይህን ሲሰሙ በአማርኛ ቋንቋ የሕዝብ ንግግር እንዲሰጥ ወዲያውኑ ዝግጅት አደረጉ። በርካታ የውጭ አገር ሰዎችና የአገሪቱ ተወላጆች በብሪታንያ ለመጀመሪያ ጊዜ በአማርኛ ቋንቋ በሚካሄደው በዚህ ስብሰባ እንዲካፈሉ የቀረበላቸውን ግብዣ ተቀብለው በስብሰባው ላይ ተገኙ። በዛሬው ጊዜ በአካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ሌሎች ሰዎች አንድ ላይ የሚሰበሰቡበት ጠንካራ ጉባኤ ተመሥርቷል። በዚያ የሚገኙ ብዙዎች ከይሖዋ ጎን ከመቆምና ይህንንም በክርስቲያናዊ የውኃ ጥምቀት ከማሳየት ምንም ነገር ሊያግዳቸው እንደማይችል ተገንዝበዋል።​—⁠ሥራ 8:26-36

15 የሰዎች ባሕርይና አስተዳደግ በእጅጉ ይለያያል። ይህ የአንዱ የበላይነት ወይም የሌላው የበታችነት የሚለካበት ሳይሆን በሰዎች መካከል የሚታይ ተራ ልዩነት ነው። በማልታ ደሴት ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ አገልጋዮች ሲጠመቁ በዚያ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ደስታቸውን ሞቅ ባለ መንፈስ የገለጹ ሲሆን ከብሪታንያ የመጡ ወንድሞች ደግሞ የደስታ እምባ በማንባት ስሜታቸውን ገልጸዋል። በማልታ ያሉትም ሆነ ከብሪታንያ የመጡት ወንድሞች ደስታቸውን የገለጹበት መንገድ የተለያየ ቢሆንም ለይሖዋ ያላቸው ጠንካራ ፍቅር በመካከላቸው ያለውን ክርስቲያናዊ አንድነት አጠናክሮታል።​—⁠መዝሙር 133:1፤ ቆላስይስ 3:14

መሠረተ ቢስ ጥላቻን ማስወገድ

16-18. በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የዘር ጥላቻን እንዴት ማስወገድ እንደሚቻል የሚያሳይ አንድ ተሞክሮ ተናገር።

16 ለይሖዋ እና ለክርስቲያን ወንድሞቻችን ያለን ፍቅር እያደገ ሲሄድ ለሌሎች ባለን አመለካከት ረገድ ይሖዋን ይበልጥ መኮረጅ እንችላለን። ከዚህ በፊት ለአንድ ዓይነት ብሔር፣ ዘር ወይም ባሕል መሠረተ ቢስ ጥላቻ ከነበረን ይህን ዝንባሌ ማስወገድ እንችላለን። ለምሳሌ ያህል የአልበርትን ሁኔታ ተመልከት። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የብሪታንያ የጦር ሠራዊት አባል የነበረው አልበርት በ1942 ሲንጋፖር በጃፓን ስትያዝ ተማረከ። ከዚያም የካዋይ ወንዝ ድልድይ ተብሎ በሚጠራው ቦታ አቅራቢያ በባቡር ሐዲድ ግንባታ ላይ በመሥራት ሦስት ዓመት ገደማ አሳለፈ። ጦርነቱ አብቅቶ ከእስር ሲፈታ 32 ኪሎ ግራም ብቻ ይመዝን የነበረ ሲሆን አገጩና አፍንጫው ላይ ስብራት ደርሶበት እንዲሁም በተቅማጥ፣ በቆዳ በሽታና በወባ ተይዞ ነበር። አብረውት የነበሩት በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞች የከፋ ሁኔታ የደረሰባቸው ከመሆኑም በላይ ብዙዎቹም ለሞት ተዳርገዋል። አልበርት ባየውና በደረሰበት ግፍና ጭካኔ የተነሳ በጣም ስለተመረረ በ1945 ወደ አገሩ ከተመለሰ በኋላ ስለ አምላክም ሆነ ስለ ሃይማኖት እንዲነሳበት አይፈልግም ነበር።

17 የአልበርት ባለቤት አይሪን ከጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክር ሆነች። አልበርት እሷን ለማስደሰት ሲል በአካባቢው በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ለጥቂት ጊዜ ተገኘ። የሙሉ ጊዜ አገልጋይ የሆነ ፖል የተባለ ወጣት ወንድም መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠና ሐሳብ አቀረበለት። አልበርት ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ ለሰዎች ያለው አመለካከት በልባቸው ሁኔታ ላይ የተመካ መሆኑን ተገነዘበ። ከዚያም ራሱን ለይሖዋ ወሰነና ተጠመቀ።

18 ከዚያ በኋላ ፖል ወደ ለንደን ተዛወረና ጃፓንኛ ተምሮ በጃፓንኛ ቋንቋ በሚካሄድ ጉባኤ መሰብሰብ ጀመረ። ፖል ከጃፓን የመጡ አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮችን ቀድሞ ወደነበረበት ጉባኤ ይዞ የመምጣት ሐሳብ እንዳለው ሲነግራቸው በጉባኤው ያሉት ወንድሞች አልበርት ለዚህ አገር ሰዎች ያለው ጥላቻ ትዝ አላቸው። አልበርት ወደ ብሪታንያ ከመጣበት ጊዜ አንስቶ የጃፓን ተወላጅ የሆኑ ሰዎችን ይርቅ ስለነበር ወንድሞች በዚህ ጊዜ ምን ያደርግ ይሆን ብለው አሰቡ። ሆኖም ሁኔታው ሊያሳስባቸው አይገባም ነበር። ምክንያቱም አልበርት እንግዶቹን የተቀበላቸው ሞቅ ባለ ወንድማዊ ፍቅር ነበር።​—⁠1 ጴጥሮስ 3:8, 9

ፍቅራችሁን አስፉ

19. አድልዎ የማድረግ ዝንባሌ ካለን ሐዋርያው ጳውሎስ የሰጠው የትኛው ምክር ሊረዳን ይችላል?

19 ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “ማድላት . . . መልካም አይደለም” ሲል ጽፏል። (ምሳሌ 28:21) በደንብ ከምናውቃቸው ሰዎች ጋር መቀራረብ አይከብደንም። አንዳንድ ጊዜ ግን እምብዛም ለማናውቃቸው ሰዎች ያን ያህል ትኩረት አንሰጣቸው ይሆናል። አንድ የይሖዋ አገልጋይ እንዲህ ዓይነት አድልዎ ማሳየቱ ተገቢ አይደለም። በእርግጥም ሁላችንም ጳውሎስ ፍቅራችሁን ‘አስፉ’ በማለት የሰጠውን የማያሻማ ምክር መከተል ይኖርብናል። አዎን፣ የተለያየ ዘርና ቋንቋ ላላቸው የእምነት ባልንጀሮቻችን ፍቅር ልናሳያቸው ይገባል።​—⁠2 ቆሮንቶስ 6:13

20. የማያዳላውን አምላካችንን ይሖዋን መኮረጅ ያለብን በየትኞቹ የሕይወት ዘርፎች ነው?

20 የሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮችም ሆንን በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያለን ከአድልዎ መራቃችን በአንድ እረኛ ሥር ያለን አንድ መንጋ ለመሆን ያስችለናል። (ኤፌሶን 4:4, 5, 16) የማያዳላውን አምላካችንን ይሖዋን ለመኮረጅ የምናደርገው ጥረት በሁሉም የሕይወት ዘርፎች ማለትም በክርስቲያናዊ አገልግሎት እንዲሁም በቤተሰብና በጉባኤ ውስጥ ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ይጠቅመናል። እንዴት? የሚቀጥለው የጥናት ርዕስ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጣል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ከጊዜ በኋላ የይሖዋ ዝና በቅዱስ መዝሙሮች ውስጥ በተደጋጋሚ ተጠቅሷል።​—⁠መዝሙር 135:8-11፤ 136:11-20

b በዚህ አገባቡ “ግሪካዊ” የሚለው ቃል አሕዛብን በጠቅላላ ያመለክታል።​—⁠በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ጥራዝ 1 ገጽ 1004 ተመልከት።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

የረዓብና የገባዖናውያን ታሪክ ይሖዋ የማያዳላ አምላክ መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው?

ኢየሱስ በማስተማር ሥራው አድልዎ እንደማያደርግ ያሳየው እንዴት ነው?

ማንኛውንም መሠረተ ቢስ የሆነ የዘር ወይም የባሕል ጥላቻ ለማስወገድ የሚረዳን ምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እስራኤላውያን የከነዓንን ምድር ድል እያደረጉ መቆጣጠር ጀመሩ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ለአንዲት ሳምራዊት ከመመስከር ወደ ኋላ አላለም

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በብሪታንያ በአማርኛ ቋንቋ የተካሄደ ሕዝባዊ ስብሰባ

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አልበርት ለይሖዋ ያለው ፍቅር የዘር ጥላቻን እንዲያስወግድ ረድቶታል