በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የደም ቅድስናን ለማክበር የተደረገ እርዳታ

የደም ቅድስናን ለማክበር የተደረገ እርዳታ

የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት

የደም ቅድስናን ለማክበር የተደረገ እርዳታ

በምድር ዙሪያ የሚኖሩ የይሖዋ አገልጋዮች ከደም ቅድስና ጋር በተያያዘ የአምላክን መመሪያ በማክበር ታማኝነታቸውን አሳይተዋል። (ሥራ 15:​28, 29) በዚህ ረገድ ታማኝና ልባም ባሪያ ለመላው ክርስቲያናዊ የወንድማማች ማኅበር እርዳታ ሲያበረክት ቆይቷል። (ማቴዎስ 24:​45-47) በፊሊፒንስ የተገኙትን ውጤቶች እስቲ እንመልከት።

የፊሊፒንስ ቅርንጫፍ ቢሮ የሚከተለውን ሪፖርት ልኳል:- “በ1990 ከብሩክሊን ቤቴል የተላኩ ተወካዮች በፊሊፒንስ አንድ ሴሚናር እንደሚያካሂዱ ተነግሮን ነበር። ኮሪያን፣ ታይዋንንና ሆንግ ኮንግን ጨምሮ ከበርካታ የእስያ ቅርንጫፍ ቢሮዎች የተወከሉ ወንድሞች በሴሚናሩ ላይ እንዲገኙ ተጋብዘው ነበር። የሴሚናሩ ዓላማ ወንድሞች በየአገራቸው ባሉት ቅርንጫፍ ቢሮዎች የሆስፒታል መረጃ አገልግሎት ማቋቋም እንዲችሉ ለመርዳትና የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎችን ለማደራጀት ነበር። በፊሊፒንስ የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎች በመጀመሪያ በአራት ትላልቅ ከተሞች ተቋቋሙ።” የኮሚቴዎቹ ተግባር ደምን በተመለከተ ካለን ክርስቲያናዊ አቋም ጋር የሚስማማ ሕክምና ለመስጠት ፈቃደኛ የሆኑ ዶክተሮችን ማፈላለግ ነበር። በተጨማሪም ከደም ጋር በተያያዘ ችግሮች በሚነሱበት ጊዜ ለወንድሞች እርዳታ ይሰጣሉ።

ሬሜሂዮ በባጊዮ ከተማ በተቋቋመው የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ ውስጥ እንዲያገለግል ተመርጦ ነበር። በጊዜ ሂደት ዶክተሮች ኮሚቴው የሚሰጠው አገልግሎት ያለውን ጠቀሜታ እየተገነዘቡ መጡ። ሬሜሂዮ የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴው ከበርካታ ዶክተሮች ጋር ባደረገው አንድ ስብሰባ ላይ ዶክተሮቹ ደም አንወስድም የሚሉ የይሖዋ ምሥክሮችን እንዴት መርዳት እንዳለባቸው ጠይቀው እንደነበር ያስታውሳል። ሬሜሂዮ እንዲህ ይላል:- “ዶክተሮቹ ጥያቄ መጠየቅ ጀመሩ፤ ይሁን እንጂ ጥያቄዎቹ ጠለቅ ያለ የሕክምና እውቀት ስለሚጠይቁ መልስ መስጠት ከአቅሜ በላይ ሆኖብኝ ነበር።” ይህን ፈታኝ ሁኔታ ለመወጣት እንዲረዳው ወደ ይሖዋ ጸለየ። ቀጥሎ ስለተፈጸመው ሁኔታ ሲናገር እንዲህ ይላል:- “ጥያቄ ሲቀርብ ሌሎች ዶክተሮች እጃቸውን አውጥተው ተመሳሳይ ሁኔታ ባጋጠማቸው ጊዜ ምን እንዳደረጉ ማብራሪያ ይሰጡ ነበር።” የጥያቄና መልሱ ክፍለ ጊዜ ለሁለት ሰዓት ያህል የዘለቀ ስለነበር ሬሜሂዮ እርዳታ በማግኘቱ ተደስቷል።

በአሁኑ ወቅት በመላው አገሪቱ በድምሩ 77 የሚያህሉ ወንድሞችን ያቀፉ 21 ኮሚቴዎች ይገኛሉ። የይሖዋ ምሥክር የሆነው ዳኒሎ የሕክምና ዶክተር ሲሆን “ዶክተሮች የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ታካሚዎቻቸው ፍቅራዊ አሳቢነት የሚያሳያቸው የአንድ ድርጅት ድጋፍ እንዳላቸው ተገንዝበዋል” በማለት ተናግሯል። አንድ የሕክምና ባለሞያ መጀመሪያ ላይ ለአንድ ወንድም ያለ ደም ቀዶ ሕክምና ለመስጠት ቢያቅማማም ወንድም ግን በአቋሙ ጸና። በመጨረሻ ቀዶ ሕክምናው ተካሄዶ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቀቀ። የሆስፒታል መረጃ አገልግሎት የላከው ሪፖርት እንዲህ ይላል:- “ወንድም በፍጥነት ማገገሙ ዶክተሩን በጣም ስላስገረመው ‘ከተፈጸመው ሁኔታ በመነሳት የእናንተ አባል የሆነ ማንኛውም ሰው ያለ ደም ተመሳሳይ ቀዶ ሕክምና ማድረግ የሚያስፈልገው ከሆነ ለመርዳት ዝግጁ ነኝ’ በማለት ተናግሯል።”