በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወጣቶች—ይሖዋ ያደረጋችሁትን ሥራ አይረሳም!

ወጣቶች—ይሖዋ ያደረጋችሁትን ሥራ አይረሳም!

ወጣቶች—⁠ይሖዋ ያደረጋችሁትን ሥራ አይረሳም!

“እግዚአብሔር፣ ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ እስከ አሁንም ስለምታገለግሉአቸው፣ ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለምና።”—⁠ዕብራውያን 6:10

1. የዕብራውያን መልእክትና የሚልክያስ ትንቢት ይሖዋ አገልግሎትህን እንደማይረሳ የሚያሳዩት እንዴት ነው?

 ለአንድ ጓደኛህ መልካም ነገር አድርገህለት ሳያመሰግንህ የቀረበት ጊዜ አለ? በደግነት ተነሳስተህ ያደረግኸው ነገር ያንን ያህል ግምት ሳይሰጠው ቢቀር ይባስ ብሎም ከነአካቴው ቢረሳ በሁኔታው በጣም መጎዳትህ አይቀርም። ሆኖም ለይሖዋ የምናቀርበው የሙሉ ነፍስ አገልግሎት ፈጽሞ አይረሳም! መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር፣ ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ እስከ አሁንም ስለምታገለግሉአቸው፣ ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለምና” በማለት ይናገራል። (ዕብራውያን 6:​10) ይህ ምን አንድምታ እንዳለው ተመልከት። ይሖዋ እርሱን ለማገልገል ያደረግኸውንና ወደፊት የምታደርገውን የሚረሳ ከሆነ ድርጊቱን እንደ ዓመፅ በሌላ አነጋገር እንደ ኃጢአት ይቆጥረዋል። በእርግጥም ውለታ የማይረሳ አምላክ ነው!​—⁠ሚልክያስ 3:​10

2. ይሖዋን ማገልገል ልዩ መብት የሆነው ለምንድን ነው?

2 አመስጋኝ የሆነውን አምላክ የማምለክና የማገልገል ልዩ መብት አለህ። ከስድስት ቢልዮን የዓለም ሕዝብ መካከል ልክ እንደ አንተው ይሖዋን የሚያገለግሉት ስድስት ሚልዮን ብቻ መሆናቸው በራሱ ይህን መብት ልዩ ያደርገዋል። ከዚህም በላይ ምሥራቹን ሰምተህ መቀበልህ ይሖዋ በግል እንደሚያስብልህ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። ደግሞም ኢየሱስ “የላከኝ አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም” ብሏል። (ዮሐንስ 6:44) አዎን፣ ሰዎች ከክርስቶስ መሥዋዕት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በግለሰብ ደረጃ ይረዳቸዋል።

ላገኘኸው ታላቅ መብት አመስጋኝ ሁን

3. የቆሬ ልጆች ላገኙት ይሖዋን የማገልገል መብት የተሰማቸውን አድናቆት የገለጹት እንዴት ነው?

3 በፊተኛው ርዕስ ላይ እንደተብራራው የይሖዋን ልብ ደስ የማሰኘት ልዩ አጋጣሚ አለህ። (ምሳሌ 27:​11) ይህ ከፍ አድርገህ ልትመለከተው የሚገባ መብት ነው። የቆሬ ልጆች በመንፈስ አነሳሽነት ከጻፏቸው መዝሙሮች ውስጥ በአንዱ ላይ ይሖዋን የማገልገል መብታቸውን ከፍ አድርገው እንደሚመለከቱት ገልጸዋል። እንዲህ በማለት ዘምረዋል:- “ከአእላፍ ይልቅ በአደባባዮችህ አንዲት ቀን ትሻላለች፤ በኀጥአን ድንኳኖች ከመቀመጥ ይልቅ፣ በእግዚአብሔር ቤት እጣል ዘንድ መረጥሁ።”​—⁠መዝሙር 84:​10

4. (ሀ) አንዳንዶች የይሖዋ አምልኮ ነጻነታቸውን እንደሚገድብባቸው የሚሰማቸው ለምን ሊሆን ይችላል? (ለ) ይሖዋ አገልጋዮቹ የሚያደርጉትን ተመልክቶ ወሮታ ለመክፈል እንደሚፈልግ ያሳየው እንዴት ነው?

4 በሰማይ የሚኖረውን አባትህን ለማገልገል ላገኘኸው መብት አንተስ እንዲህ ዓይነት ስሜት አለህ? ለይሖዋ የምታቀርበው አምልኮ አልፎ አልፎ ነጻነትህን የገደበብህ ሆኖ ሊሰማህ እንደሚችል አይካድም። ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ተስማምቶ መኖር በተወሰነ መጠን ጥቅምህን መሥዋዕት ማድረግን እንደሚጠይቅብህ እሙን ነው። ይሁን እንጂ ይሖዋ የሚፈልግብህን ነገር ማድረግህ ውሎ አድሮ ጥቅሙ ለአንተው ነው። (መዝሙር 1:​1-3) ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ ጥረትህን አይቶ ላሳየኸው ታማኝነት አድናቆቱን ይገልጻል። ጳውሎስ፣ ይሖዋ ‘ለሚፈልጉት ዋጋ የሚሰጥ’ አምላክ መሆኑን መጻፉ የተገባ ነው። (ዕብራውያን 11:6) ይሖዋ ብድራትህን ለመክፈል አጋጣሚዎችን ይጠባበቃል። በጥንቷ እስራኤል የኖረ አንድ ጻድቅ ነቢይ “እግዚአብሔር ልቡ በእርሱ ዘንድ ፍጹም የሆነውን ያጸና ዘንድ ዓይኖቹ በምድር ሁሉ ይመለከታሉና” ሲል ተናግሯል።​—⁠2 ዜና መዋዕል 16:9

5. (ሀ) ልብህ በይሖዋ ዘንድ ፍጹም መሆኑን ማሳየት የምትችልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ የትኛው ነው? (ለ) ለሌሎች ስለ እምነትህ መናገር ከባድ መስሎ የሚታየው ለምንድን ነው?

5 ልብህ በይሖዋ ዘንድ ፍጹም መሆኑን ማሳየት የምትችልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ለሌሎች ስለ እርሱ መናገር ነው። ለትምህርት ቤትህ ልጆች ስለ እምነትህ ለመናገር አጋጣሚ አግኝተህ ታውቃለህ? መጀመሪያ ላይ እንዲህ ማድረጉ የሚያስጨንቅ ሊመስልና ገና ስታስበው ፍርሃት ፍርሃት ሊልህ ይችላል። ‘ቢስቁብኝስ? የማይታወቅ ሃይማኖት እንደምከተል አድርገው ቢያስቡስ?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ኢየሱስ የመንግሥቱን መልእክት መስማት የማይፈልጉ ሰዎች እንደሚኖሩ ተናግሯል። (ዮሐንስ 15:​20) ሆኖም ሰው ሁሉ ያፌዝብሃል ወይም አይሰማህም ማለት አይደለም። እንዲያውም በርካታ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች ሰሚ ጆሮ ያገኙ ከመሆኑም በላይ ላመኑበት ነገር ጥብቅ በመሆናቸው በእኩዮቻቸው ዘንድ ታላቅ አክብሮት አትርፈዋል።

“ይሖዋ ይረዳችኋል”

6, 7. (ሀ) አንዲት የ17 ዓመት ወጣት አብረዋት ለሚማሩ ልጆች መመስከር የቻለችው እንዴት ነው? (ለ) ከጄኒፈር ተሞክሮ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

6 ይሁንና ስለ እምነትህ ለመናገር ድፍረት ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው? ሰዎች ስለ ሃይማኖትህ ሲጠይቁህ በግልጽ ለመናገር ለምን ከአሁኑ ቁርጥ ውሳኔ አታደርግም? የ17 ዓመቷ ጄኒፈር ያጋጠማትን ተመልከት። “ትምህርት ቤት ውስጥ ምሳ እየበላሁ ነበር። አብረውኝ የተቀመጡ ልጆች ስለ ሃይማኖት ያወሩ ነበር። በዚህ ጊዜ አንደኛዋ ሃይማኖቴ ምን እንደሆነ ጠየቀችኝ።” ጄኒፈር መልስ መስጠት ፈርታ ይሆን? “ምን ዓይነት ምላሽ እንደሚሰጡኝ እርግጠኛ ስላልነበርኩ ፍርሃት ተሰምቶኝ ነበር” በማለት ሳትሸሽግ ተናግራለች። ታዲያ ምን አደረገች? “የይሖዋ ምሥክር መሆኔን ነገርኳቸው። መጀመሪያ ላይ ያልጠበቁት ነገር ሆነባቸው። የይሖዋ ምሥክሮች ለየት ያሉ ሰዎች ናቸው የሚል ስሜት የነበራቸው ይመስላል። በዚህም ምክንያት አንዳንድ ጥያቄዎችን ይጠይቁኝ ጀመር። ይህም የነበራቸውን የተሳሳተ አመለካከት እንዲያስተካክሉ ለመርዳት አጋጣሚ ከፈተልኝ። ከዚያን ዕለት ወዲህ አንዳንዶቹ ልጆች አልፎ አልፎ ጥያቄ ይጠይቁኛል።”

7 ጄኒፈር ስለ እምነቷ ለመናገር ባገኘችው አጋጣሚ በመጠቀሟ ተቆጭታ ይሆን? በፍጹም! እንዲህ ትላለች:- “ከልጆቹ ከተለየሁ በኋላ ስለ እምነቴ በመናገሬ ከፍተኛ ደስታ ተሰማኝ። አሁን እነዚያ ልጆች ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የተሻለ ግንዛቤ አግኝተዋል።” ጄኒፈር ለሌሎች ወጣቶች የምትሰጠው ሐሳብ አላት:- “አብረዋችሁ ለሚማሩ ልጆች ወይም ለአስተማሪዎቻችሁ መመስከር ከከበዳችሁ አጭር ጸሎት አቅርቡ። ይሖዋ ይረዳችኋል። ምሥክርነት ለመስጠት ባገኛችሁት አጋጣሚ በጥሩ ሁኔታ በመጠቀማችሁ ደስታ ይሰማችኋል።”​—⁠1 ጴጥሮስ 3:​15

8. (ሀ) ነህምያ ያልተጠበቀ ሁኔታ ባጋጠመው ጊዜ ጸሎት ማቅረቡ የጠቀመው እንዴት ነው? (ለ) ለይሖዋ በልብህ አጭር ጸሎት እንድታቀርብ የሚያስገድዱህ በትምህርት ቤት ሊያጋጥሙህ የሚችሉት አንዳንድ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?

8 ስለ እምነትህ ለመናገር አጋጣሚ በምታገኝበት ጊዜ ወደ ይሖዋ ‘አጭር ጸሎት ማቅረብ’ ጥሩ እንደሆነ ጄኒፈር የተናገረችውን ሐሳብ ልብ በል። የፋርስ ንጉሥ የአርጤክስስ ጠጅ አሳላፊ የነበረው ነህምያ ያልጠበቀው ሁኔታ ባጋጠመው ጊዜ ያደረገው ልክ እንደዚህ ነው። ነህምያ አይሁዳውያን ስለነበሩበት አሳዛኝ ሁኔታ እንዲሁም የኢየሩሳሌም ግንብና በሮች ፈራርሰው እንደቀሩ ሲነገረው የተሰማው ሐዘን ፊቱ ላይ ይነበብ ነበር። ንጉሡ፣ ነህምያ መጨነቁን አይቶ ምን እንዳጋጠመው ጠየቀው። ነህምያ መልስ ከመስጠቱ በፊት መመሪያ ለማግኘት ጸለየ። ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ የፈረሰችውን ከተማ ለመገንባት የሚደረገውን ሥራ ለማገዝ ፈቃድ እንዲሰጠው በድፍረት ጠየቀ። አርጤክስስ ያቀረበውን ጥያቄ ተቀበለ። (ነህምያ 2:​1-8) ከዚህ ምን ትምህርት ታገኛለህ? እምነትህን በሚመለከት ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስችል አጋጣሚ ስታገኝ ፍርሃት ከተሰማህ በልብህ ከመጸለይ ወደኋላ አትበል። ጴጥሮስ “[ይሖዋ] ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት” ሲል ጽፏል።​—⁠1 ጴጥሮስ 5:7፤ መዝሙር 55:22

‘መልስ ለመስጠት የተዘጋጃችሁ ሁኑ’

9. የ13 ዓመቷ ልያ የወጣቶች ጥያቄ የተባለውን መጽሐፍ 23 ቅጂዎች ማበርከት የቻለችው እንዴት ነው?

9 አሁን ደግሞ ሌላ ተሞክሮ ተመልከት። የ13 ዓመቷ ልያ ትምህርት ቤት ውስጥ በምሳ ዕረፍት ላይ ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች  a የተባለውን መጽሐፍ እያነበበች ነበር። “በዚህ ጊዜ በርከት ያሉ ልጆች ያዩኝ የነበረ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ መጥተው ከበቡኝና መጽሐፉ ስለ ምን እንደሚናገር ይጠይቁኝ ጀመር።” በዚሁ ቀን አራት ልጆች የወጣቶች ጥያቄ የተባለውን መጽሐፍ እንድታመጣላቸው ጠየቋት። አራቱ ልጆች መጽሐፉን ለሌሎች በማሳየታቸው እነዚህም የመጽሐፉን ቅጂ ለማግኘት ፈለጉ። ልያ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ለትምህርት ቤቷ ልጆችና ለጓደኞቻቸው የዚህን መጽሐፍ 23 ቅጂዎች አበረከተች። ልጆቹ ስለ መጽሐፉ መጥተው ሲጠይቋት ልያ ለመናገር ፈርታ ነበርን? አዎን፣ ፈርታለች! “መጀመሪያ ላይ ፈርቼ ነበር። ከጸለይኩ በኋላ ግን ይሖዋ ከእኔ ጋር እንደሆነ ተሰማኝ” ስትል ተናግራለች።

10, 11. አንዲት እስራኤላዊት ወጣት የሶርያ የጦር አዛዥ ስለ ይሖዋ እንዲያውቅ የረዳችው እንዴት ነው? እርሱስ ምን ዓይነት ለውጥ አድርጓል?

10 የልያ ተሞክሮ ወደ ሶርያ በምርኮ የተወሰደችው እስራኤላዊት ወጣት ያጋጠማትን ሁኔታ ያስታውስህ ይሆናል። የሶርያ የጦር አዛዥ የነበረው ንዕማን የሥጋ ደዌ ይዞት ነበር። የንዕማን ሚስት ልጅቷን ማነጋገር ጀምራ ሳይሆን አይቀርም እስራኤላዊቷ ልጃገረድ “ጌታዬ በሰማርያ ካለው ከነቢዩ ፊት ቢደርስ ኖሮ ከለምጹ በፈወሰው ነበር” በማለት ስለ እምነቷ ለመናገር ግሩም አጋጣሚ አገኘች።​—⁠2 ነገሥት 5:​1-3

11 ይህች ወጣት ባሳየችው ድፍረት የተነሳ ንዕማን “ከእስራኤል ዘንድ በቀር በምድር ሁሉ አምላክ እንደሌለ” መገንዘብ ችሏል። ከዚህም በላይ “ከእግዚአብሔር በቀር ለሌሎች አማልክት የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ሌላ መሥዋዕት” ላለማቅረብ ቁርጥ ውሳኔ አድርጓል። (2 ነገሥት 5:15-17) ይሖዋ ይህች ወጣት ያሳየችውን ድፍረት እንደባረከላት ምንም ጥርጥር የለውም። በዛሬው ጊዜ ያሉ ወጣቶች የሚያደርጉትንም ጥረት እንዲሁ ይባርካል። ልያ ይህን በራስዋ ተሞክሮ አይታለች። መጽሐፉን የወሰዱ አንዳንድ ልጆች ከጊዜ በኋላ መጽሐፉ ጥሩ የሥነ ምግባር መመሪያ እንደሆናቸው ነግረዋታል። ልያ “ሌሎች ስለ ይሖዋ እንዲያውቁና የባሕርይ ለውጥ እንዲያደርጉ በመርዳቴ ደስታ ተሰምቶኛል” ስትል ተናግራለች።

12. ለእምነትህ ጥብቅና ለመቆም ድፍረት ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?

12 አንተም ጄኒፈርና ልያ ያጋጠማቸው ዓይነት ተሞክሮ ማግኘት ትችላለህ። ክርስቲያን እንደመሆንህ መጠን ጴጥሮስ “በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁአችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፣ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን” ሲል የሰጠውን ምክር ምንጊዜም ከመከተል ወደኋላ አትበል። (1 ጴጥሮስ 3:15) ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? ይሖዋ “በፍጹም ድፍረት” መስበክ እንዲችሉ እንዲረዳቸው የጸለዩትን የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖችን ምሳሌ ተከተል። (ሥራ 4:​29 አ.መ.ት ) ከዚያም ስለ እምነትህ ለሌሎች በድፍረት ተናገር። አስደሳች ውጤት የምታገኝ ከመሆኑም በላይ የይሖዋን ልብ ደስ ታሰኛለህ።

ቪዲዮዎችና የቤት ሥራዎች

13. አንዳንድ ወጣቶች ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስችሉ የትኞቹን አጋጣሚዎች ተጠቅመዋል? (በገጽ 20 እና 21 ላይ ያሉትን ሣጥኖች ተመልከት።)

13 ብዙ ወጣቶች የቪዲዮ ክሮችን በመጠቀም አብረዋቸው ለሚማሩ ልጆች ወይም ለአስተማሪዎቻቸው ስለ እምነታቸው ምሥክርነት ሰጥተዋል። አንዳንድ ጊዜም የተሰጣቸው የቤት ሥራ ይሖዋን ለማወደስ የሚያስችል ጥሩ አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። ለምሳሌ ያህል የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ ሁለት የ15 ዓመት ወጣት ወንዶች የታሪክ መምህራቸው በዓለም ላይ ካሉት ሃይማኖቶች መካከል በአንዱ ላይ ጽሑፍ እንዲያዘጋጁ የቤት ሥራ ሰጣቸው። ሁለቱ ልጆች የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ተጠቅመው የይሖዋ ምሥክሮችን ሃይማኖት በተመለከተ ጽሑፍ ለማዘጋጀት ተስማሙ። b ከዚህም በተጨማሪ የሥራ ውጤታቸውን በተመለከተ የአምስት ደቂቃ የቃል ሪፖርት ማቅረብ ነበረባቸው። ሪፖርቱን ካቀረቡ በኋላ መምህሩና ተማሪዎቹ ብዙ ጥያቄዎች ስላቀረቡላቸው ለተጨማሪ 20 ደቂቃ ስለ እምነታቸው ለመናገር የሚያስችል አጋጣሚ አገኙ። ከዚህ በኋላ የክፍሉ ተማሪዎች ለበርካታ ሳምንታት ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ጥያቄ መጠየቃቸውን ቀጥለዋል።

14, 15. (ሀ) ሰውን መፍራት ወጥመድ የሚሆነው እንዴት ነው? (ለ) በልበ ሙሉነት ስለ እምነትህ ለሌሎች እንድትናገር የሚያስችልህ ምንድን ነው?

14 ከላይ የቀረቡት ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት የይሖዋ ምሥክር እንደመሆንህ መጠን ለሌሎች ስለ እምነትህ መናገርህ ከፍተኛ በረከት ሊያስገኝልህ ይችላል። ሰውን መፍራት ሌሎች ይሖዋን እንዲያውቁ በመርዳት መብትህ ከመጠቀም እንዲያግድህ አትፍቀድ። መጽሐፍ ቅዱስ “ሰውን መፍራት ወጥመድ ያመጣል፤ በእግዚአብሔር የሚታመን ግን እርሱ ይጠበቃል” ይላል።​—⁠ምሳሌ 29:25

15 ክርስቲያን ወጣት እንደመሆንህ መጠን ሌሎች እኩዮችህ ያላገኙት በዓይነቱ ልዩ የሆነ ነገር እንዳለህ አትዘንጋ። ይህም በአሁኑ ጊዜ ከሁሉ የተሻለ ሕይወት ወደፊት ደግሞ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 4:​8) ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ሰዎች ባመዛኙ ግድየለሾችና ስለ ኑሮ ብቻ የሚጨነቁ እንደሆኑ ታስብ ይሆናል፤ የሚያስገርመው ግን አንድ ጥናት እንዳሳየው ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው ወጣቶች መካከል ግማሽ ያህል የሚሆኑት ሃይማኖታቸውን በቁም ነገር ይመለከታሉ፣ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ደግሞ ሃይማኖት በሕይወታቸው ውስጥ “ትልቅ ሚና እንዳለው” ተናግረዋል። በሌሎች በርካታ የዓለም ክፍሎችም ሁኔታው ተመሳሳይ እንደሚሆን ይገመታል። በመሆኑም በትምህርት ቤትህ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የምትናገረውን ለማዳመጥ ደስተኞች ሊሆኑ ይችላሉ።

ወደ ይሖዋ ቅረብ

16. ስለ ይሖዋ ለሌሎች ከመናገር በተጨማሪ እርሱን ለማስደሰት ምን ማድረግ ያስፈልጋል?

16 እርግጥ ነው፣ የይሖዋን ልብ ደስ ማሰኘት ስለ እርሱ ከመናገር የበለጠ ነገር ማድረግን ይጠይቃል። ሕይወትህን እርሱ ካወጣቸው መሥፈርቶች ጋር ማስማማትም ይኖርብሃል። ሐዋርያው ዮሐንስ “ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም” ሲል ጽፏል። (1 ዮሐንስ 5:3) ወደ ይሖዋ በመቅረብ የዚህን አባባል እውነተኝነት ማየት ትችላለህ። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

17. ወደ ይሖዋ መቅረብ የምትችለው እንዴት ነው?

17 መጽሐፍ ቅዱስንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ለማንበብ ጊዜ መድብ። ስለ ይሖዋ ባወቅህ መጠን እርሱን መታዘዝና ስለ እርሱ ለሌሎች መናገር ይበልጥ ቀላል ይሆንልሃል። ኢየሱስ “በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፉ ይናገራልና መልካም ሰው ከልብ መልካም መዝገብ መልካሙን ያወጣል” ሲል ተናግሯል። (ሉቃስ 6:45) በመሆኑም ልብህን በመልካም ነገሮች ሙላ። በዚህ ረገድ ለምን የተለያዩ ግቦች አታወጣም? እንዲያውም በሚቀጥለው ሳምንት ለጉባኤ ስብሰባዎች የምታደርገውን ዝግጅት ማሻሻል ትችላለህ። ቀጣዩ ግብህ ደግሞ አጠር ያለ ሆኖም የታሰበበት ሐሳብ መስጠት ሊሆን ይችላል። ከዚህም በላይ የተማርካቸውን ነገሮች ተግባራዊ ማድረግ በጣም አስፈላጊ መሆኑ አያጠያይቅም።​—⁠ፊልጵስዩስ 4:​9

18. አንዳንድ ጊዜ ተቃውሞ ቢያጋጥምህም እንኳ ስለ ምን ነገር እርግጠኛ መሆን ትችላለህ?

18 ይሖዋን በማገልገላችን የምናገኛቸው በረከቶች ዘላቂ አልፎ ተርፎም ዘላለማዊ ናቸው። የይሖዋ ምሥክር በመሆንህ አልፎ አልፎ ተቃውሞ ወይም ፌዝ ሊያጋጥምህ እንደሚችል አይካድም። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሙሴ “ብድራቱን ትኵር ብሎ ተመልክቶአልና” ብሎ የሚናገረውን አስብ። (ዕብራውያን 11:24-26) አንተም ስለ እርሱ ለመማርና ለሌሎች ለመናገር የምታደርገውን ጥረት አይቶ ይሖዋ ብድራቱን እንደሚከፍልህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። በእርግጥም ‘ያደረግኸውን ሥራ ለስሙም ያሳየኸውን ፍቅር ፈጽሞ አይረሳም።’​—⁠ዕብራውያን 6:​10

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

b በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

ታስታውሳለህን?

• ይሖዋ የምታቀርበውን አገልግሎት ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት እርግጠኛ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?

• አንዳንዶች ትምህርት ቤት ውስጥ ለመመስከር ውጤታማ ሆነው ያገኟቸው ዘዴዎች የትኞቹ ናቸው?

• አብረውህ ለሚማሩ ልጆች ለመመስከር ድፍረት ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?

• ወደ ይሖዋ መቅረብ የምትችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ትንንሽ ልጆችም እንኳ ይሖዋን ያወድሳሉ!

ትንንሽ ልጆችም እንኳ ትምህርት ቤት ውስጥ ምሥክርነት መስጠት ችለዋል። እነዚህን ተሞክሮዎች ተመልከት።

የአምስተኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው የአሥር ዓመቷ አምበር በምትገኝበት ክፍል ውስጥ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ናዚዎች በአይሁዶች ላይ ስላደረሱት ጥቃት የሚገልጽ መጽሐፍ እየተነበበ ነበር። አምበር ፐርፕል ትራያንግልስ የተባለውን ቪዲዮ ለአስተማሪዋ ለመስጠት አሰበች። አስተማሪዋ የይሖዋ ምሥክሮችም የናዚ አገዛዝ የጥቃት ሰለባዎች እንደነበሩ ስታውቅ በጣም ተገረመች። አስተማሪዋ ቪዲዮው በክፍል ውስጥ እንዲታይ አደረገች።

የስምንት ዓመቷ አሌክሳ በገና በዓል ላይ መሳተፍ የማትፈልግበትን ምክንያት የሚገልጽ ደብዳቤ ለክፍሏ ተማሪዎች ጻፈች። አስተማሪዋ በደብዳቤው በጣም ከመገረሟ የተነሳ አሌክሳ በክፍሏና በሌሎች ሁለት ክፍሎች ውስጥ ለሚገኙ ተማሪዎች ደብዳቤውን እንድታነብብ አደረገች! ደብዳቤው በመደምደሚያው ላይ እንዲህ ይላል:- “ከእኔ የተለየ እምነት ያላቸውን ሰዎች በአክብሮት መያዝ እንደሚገባኝ ወላጆቼ አስተምረውኛል። እኔም በገና በዓል ላለመካፈል ያደረግሁትን ውሳኔ ስለምታከብሩልኝ ላመሰግናችሁ እወዳለሁ።”

ኤሪክ አንደኛ ክፍል እንደገባ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ የተባለውን መጽሐፍ ወደ ትምህርት ቤት ይዞ ሄዶ መጽሐፉን ለክፍሉ ተማሪዎች ለማሳየት እንዲፈቀድለት ጠየቀ። አስተማሪዋ “እንዲያውም ለክፍሉ ተማሪዎች አንድ ታሪክ ብታነብላቸው ጥሩ ይመስለኛል” ስትል ነገረችው። በዚህ መሠረት ኤሪክ አንድ ታሪክ ካነበበላቸው በኋላ መጽሐፉን ማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ እጃቸውን እንዲያወጡ ጠየቀ። አስተማሪዋና አሥራ ሰባት ልጆች እጃቸውን አወጡ! ኤሪክ ልዩ የአገልግሎት ክልል እንዳለው ይሰማዋል።

የዘጠኝ ዓመቷ ዊትኒ የይሖዋ ምሥክሮችና ትምህርት (እንግሊዝኛ) የተባለው ብሮሹር በመኖሩ በጣም ደስተኛ ነች። c እንዲህ በማለት ተናግራለች:- “እስከዛሬ ድረስ በየዓመቱ ብሮሹሩን ለአስተማሪዎቼ የምትሰጣቸው እናቴ ነበረች። ዘንድሮ ግን እኔ ራሴ ሰጠኋቸው። በዚህ ብሮሹር አማካኝነት ‘ለሳምንቱ ምርጥ ተማሪ’ የሚሰጠውን ሽልማት ለማግኘት በቅቻለሁ።”

[የግርጌ ማስታወሻ]

c ከላይ የተጠቀሱት ጽሑፎችና ቪዲዮ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ ናቸው።

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

አንዳንዶች ስለ እምነታቸው ለመናገር የተጠቀሙባቸው ዘዴዎች

አንዳንዶች ክፍል ውስጥ የሚያቀርቡት ሪፖርት ወይም የቤት ሥራ ሲሰጣቸው ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስችል ርዕስ መርጠዋል

በርካታ ወጣቶች ክፍል ውስጥ እየተማሩት ካለው ርዕስ ጋር ዝምድና ያለው ቪዲዮ ወይም ሌላ ጽሑፍ ለአስተማሪያቸው ሰጥተዋል

አንዳንድ ወጣቶች በእረፍት ሰዓታቸው መጽሐፍ ቅዱስ ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች በሚያነቡበት ጊዜ ሌሎች ወጣቶች ቀርበው ጥያቄዎች ጠይቀዋቸዋል

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ተሞክሮ ያላቸው ወንድሞችና እህቶች ወጣቶች ይሖዋን እንዲያገለግሉ ሊያሰለጥኗቸው ይችላሉ