በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትክክለኛ መንፈሳዊ እሴቶችን ከየት ማግኘት ትችላለህ?

ትክክለኛ መንፈሳዊ እሴቶችን ከየት ማግኘት ትችላለህ?

ትክክለኛ መንፈሳዊ እሴቶችን ከየት ማግኘት ትችላለህ?

ሩዶልፍ “አንድን ሃይማኖት የምትቀበለው ከአያት ከቅድመ አያት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ነው በሚል ብቻ ከሆነ ከ2, 000 ዓመት በፊት የጥንት አባቶቻችን ይከተሉት የነበረውን የሴልቲክ ሃይማኖት ለምን አትይዝም?” ሲል በምጸት ጠየቀው። ከእርሱ በዕድሜ የሚያንሰው አድማጩ ይህን ሲሰማ ሳቅ አለ።

ሩዶልፍ በመቀጠል እንዲህ አለው:- “እኔ ግን የላቀ ቦታ የምሰጠው ከአምላክ ጋር ላለኝ ዝምድና ነው። በአሥር ብሎም በመቶ ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት የኖሩ ቤተሰቦቼ አንድን ሃይማኖት ስለተከተሉ ብቻ የእነርሱን ሃይማኖት የግድ መቀበል አለብህ በሚለው አመለካከት ፈጽሞ አልስማማም።” ሩዶልፍ ጉዳዩን በጥንቃቄ አመዛዝኗል፤ ሃይማኖት እንዲያው በውርስ የሚገኝ ነገር እንደሆነ አድርጎ አልተመለከተውም።

በዛሬው ጊዜ ብዙዎች የወላጆቻቸውን ሃይማኖት የሚከተሉ ቢሆኑም ሃይማኖትን ከወላጅ ወደ ልጅ በውርስ ማስተላለፍ እየቀነሰ መጥቷል። ሆኖም አንድ ሰው የወላጆቹን ሃይማኖት መከተሉ ሁልጊዜ ትክክል ነውን? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላል?

ሙሴን የተካው ኢያሱ 40 ዓመታት በምድረ በዳ ከቆዩ በኋላ ለእስራኤላውያን እንዲህ ሲል ምርጫ አቀረበላቸው:- “እግዚአብሔርንም ማምለክ ክፉ መስሎ ቢታ​ያችሁ፣ አባቶቻችሁ በወንዝ ማዶ ሳሉ ያመለኩአቸውን አማልክት ወይም በምድራቸው ያላ​ችሁባቸውን የአሞራውያንን አማልክት ታመልኩ እንደ ሆነ፣ የም​ታመልኩትን ዛሬ ምረጡ፣ እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን።”​—⁠ኢያሱ 24:15

ኢያሱ አባቶች ሲል ከጠቀሳቸው መካከል አንዱ በዚያን ዘመን ከኤፍራጥስ ወንዝ በስተምሥራቅ በምትገኘው በዑር ከተማ ይኖር የነበረው የአብርሃም አባት ታራ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ታራ ሌሎች አማልክትን ያመልክ እንደነበረ ከመግለጽ በስተቀር እምብዛም የሚለው ነገር የለም። (ኢያሱ 24:​2) ልጁ አብርሃም የአምላክን ዓላማ በተመለከተ የተሟላ እውቀት ባይኖረውም ይሖዋ የሰጠውን ትእዛዝ ተቀብሎ የትውልድ ከተማውን በፈቃደኝነት ለቅቆ ወጥቷል። አዎን፣ አብርሃም ከአባቱ የተለየ ሃይማኖት ለመከተል መርጧል። እንዲህ በማድረጉ አምላክ ቃል የገባለትን በረከት ለመውረስና በብዙ ሃይማኖቶች ዘንድ ‘በአምላክ ለሚያምኑ ሁሉ አባት እንደሆነ’ ተደርጎ ለመታየት በቅቷል።​—⁠ሮሜ 4:​11

መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ አያት የሆነችው ሩት በአንድ ወቅት የወሰደችው እርምጃ ጥሩ እንደነበር ይተርካል። ሩት እስራኤላዊ ባል የነበራት ሞአባዊት ስትሆን ባልዋ ከሞተ በኋላ በፊትዋ ሁለት ምርጫ ተደቅኖ ነበር:- አንድም እዚያው በአገሯ መኖር አሊያም ከአማትዋ ጋር ወደ እስራኤል መመለስ። ሩት ወላጆቿ ከሚከተሉት የጣዖት አምልኮ ይልቅ የይሖዋ አምልኮ የላቀ ብልጫ እንዳለው በመገንዘብዋ ለአማቷ “ሕዝብሽ ሕዝቤ፣ አምላክሽም አምላኬ ይሆናል” በማለት ነግራታለች።​—⁠ሩት 1:16, 17

ዲክሲዮኔር ደ ላ ቢብል የተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ በያዘው ከፍተኛ ቁም ነገር ላይ ሐሳብ ሲሰጥ “ለእስራኤላውያን ጥላቻ ካላቸውና በእነርሱም ዘንድ የተ​ጠሉ ከሆኑ ከአሕዛብ ወገን የመጣች አንዲት ሴት . . . ለይሖዋ ሕዝብና አምልኮ ካሳየችው ፍቅር የተነሳ በመለኮታዊ ጣልቃ ገብነት የቅዱሱ የንጉሥ ዳዊት ቅድመ አያት ለመሆን እንዴት እንደበቃች” ይህ ታሪክ ያሳያል ሲል ገልጿል። ሩት ከወላጆቿ የተለየ ሃይማኖት ከመከተል ወደኋላ አላለችም። እንዲህ ዓይነት ውሳኔ በማድረግዋም አምላክ ባርኳታል።

የክርስትናን አጀማመር የሚዘግበው ታሪክ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የቅድመ አያቶቻቸውን ሃይማኖት የተዉበትን ምክንያት ይበልጥ ግልጽ በሆነ መንገድ ያቀርባል። ሐዋርያው ጴጥሮስ እጅግ አሳማኝ በሆነ መንገድ ባቀረበው ንግግር ላይ አድማጮቹ ከኃጢአታቸው ንስሐ በመግባትና በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በመጠመቅ ‘ከዚህ ጠማማ ትውልድ እንዲድኑ’ ነግሯቸዋል። (ሥራ 2:​37-41) ክርስቲያኖችን ያሳድድ የነበረው አይሁዳዊው ሳውል ያደረገው ለውጥ በዚህ ረገድ ጉልህ ምሳሌ ተደርጎ ሊጠቀስ ይችላል። ሳውል ወደ ደማስቆ በመሄድ ላይ እያለ ክርስቶስን በራእይ ተመልክቶ የክርስትናን እምነት ከተቀበለ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ በሚል ስም ይጠራ ጀመር።​—⁠ሥራ 9:​1-9

ከጥንት ክርስቲያኖች መካከል አብዛኞቹ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ወደ ክርስትና የመጡ አይደሉም። ይሁንና ሁሉም የአይሁድን እምነት ወይም የተለያዩ የጣዖት አምልኮዎችን መተው ነበረባቸው። ክርስትናን የተቀበሉ ሰዎች ይህን እርምጃ የወሰዱት አብዛኛውን ጊዜ የኢየሱስን መሲሕነት በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቷቸው የተሟላ እውቀት ካገኙ በኋላ ነበር። (ሥራ 8:​26-40፤ 13:​16-43፤ 17:​22-34) እነዚህ የጥንት ክርስቲያኖች በሕይወታቸው ውስጥ ለውጥ ማድረግ እንዳለባቸው በግልጽ ተገንዝበዋል። ጥሪው የቀረበው ለአይሁዳውያንና ለሌሎች ወገኖች ቢሆንም ዋናው መልእክት ግን ተመሳሳይ ነበር። አምላክን ለማስደሰት አዲስ የተቋቋመውን የአምልኮ ሥርዓት ይኸውም ክርስትናን መቀበል የግድ አስፈላጊ ነበር።

በእኛም ፊት የቀረበ ምርጫ

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የአይሁድ እምነትን፣ የንጉሠ ነገሥት አምልኮን፣ የጣዖት አምልኮን የመሳሰሉ ከቤተሰብ የተወረሱ ሃይማኖቶችን ትቶ አይሁዶችም ሆኑ ሮማውያን የሚጠሉትን ሃይማኖት መከተል ድፍረት የሚጠይቅ መሆኑ አይካድም። ይህን ምርጫ ያደረጉ ክርስቲያኖች ብዙም ሳይቆይ መራራ ስደት ደርሶባቸዋል። በክሌርሞ ፌራን የካቶሊክ ቄስ የሆኑት ሂፖሊት ሲሞ ቬኽ ኡን ፍራንስ ፓዬን? (ፈረንሳይ ወደ ጣዖት አምልኮ እየተመለሰች ይሆን?) በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዳስቀመጡት ዛሬም “አብዛኛው ሕዝብ ከሚከተለው አቋም የተለየ እርምጃ መውሰድ” ተመሳሳይ ድፍረት ይጠይቃል። የትችት ዒላማ ከሆነ ከአንድ አናሳ ሃይማኖታዊ ቡድን ማለትም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መቀራረብ ድፍረት ይጠይቃል።

ፈረንሳይ ውስጥ በባስቲያ ከተማ የሚኖረው ፖል የተባለው ወጣት ከልጅነቱ ጀምሮ የካቶሊክ እምነት ተከታይ ነበር። ቤተ ክርስቲያኒቱ ለካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅት ገቢ ማሰባሰቢያ በምታካሂደው ኬክ መሸጥን በመሳሰሉ ተግባሮች አልፎ አልፎ ይሳተፍ ነበር። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የተሻለ ግንዛቤ ለማግኘት በመፈለጉ የይሖዋ ምሥክሮች እንዲያስጠኑት ተስማማ። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ እየተማረ ያለው ነገር ዘላቂ ጥቅም እንደሚያስገኝለት ተገነዘበ። ከዚህም የተነሳ ፖል የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች ተቀብሎ የይሖዋ ምሥክር ሆነ። ወላጆቹ ምርጫውን ያከበሩለት በመሆኑ በመካከላቸው ያለው የጠበቀ የቤተሰብ ዝምድና እንዳለ ሊቀጥል ችሏል።

በደቡባዊ ፈረንሳይ የምትኖረው አሚሊ ቤተሰቦቿ የይሖዋ ምሥክሮች ሲሆኑ እምነቱ በቤተሰቡ ውስጥ የአራት ትውልድ ዕድሜ አስቆጥሯል። የወላጆቿን ሃይማኖት ለመከተል የመረጠችው ለምንድን ነው? እንዲህ ትላለች:- “ወላጆቻችሁ ወይም አያቶቻችሁ የይሖዋ ምሥክር ስለሆኑ አሊያም ስለነበሩ ብቻ የይሖዋ ምሥክር አትሆኑም። ሆኖም ‘ይህን ሃይማኖት የምከተለው የወላጆቼ ሃይማኖት ስለሆነ ሳይሆን ስለማምንበት ነው’ የሚል ውሳኔ ላይ የምትደርሱበት ቀን ይመጣል።” እንደ ሌሎች በርካታ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች ሁሉ አሚሊም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተው ጠንካራ እምነቷ ዓላማ ያለው ሕይወት እንድትመራ ያስቻላት ከመሆኑም በላይ የእውነተኛ ደስታ ምንጭ እንደሆነላት ተገንዝባለች።

አምላክ ያወጣቸውን መመሪያዎች መከተል ያለብን ለምንድን ነው?

የምሳሌ መጽሐፍ ምዕራፍ 6 ቁጥር 20 አምላክን ማስደሰት ለሚፈልጉ ሰዎች “ልጄ ሆይ፣ የአባትህን ትእዛዝ ጠብቅ፣ የእናትህንም ሕግ አትተው” የሚል ማበረታቻ ይሰጣል። እንዲህ ያለው ምክር ወጣቶች የአምላክን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች በጭፍን ከመታዘዝ ይልቅ እምነታቸውን እንዲያሳድጉና ከእርሱ ጋር በግል ዝምድና እንዲመሠርቱ ያበረታታቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹ ‘ሁሉን እንዲፈትኑ’ ማለትም የተማሩት ትምህርት ከአምላክ ቃልና ከፈቃዱ ጋር የሚስማማ መሆኑን እንዲያረጋግጡና በዚያም መሠረት እርምጃ እንዲወስዱ ነግሯቸዋል።​—⁠1 ተሰሎንቄ 5:​21

ወጣትም ሆኑ ጎልማሳ ከስድስት ሚልዮን በላይ የሚሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች ወላጆቻቸው የእምነቱ ተከታዮች ሆኑም አልሆኑ እንዲህ ያለውን እርምጃ ወስደዋል። መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ በማጥናታቸው የሕይወትን ዓላማ በተመለከተ ለነበሯቸው ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ያገኙ ሲሆን አምላክ ለሰው ልጆች ያለውን ፈቃድም በግልጽ ተረድተዋል። ይህን እውቀት ካገኙ በኋላ አምላክ ያወጣቸውን መመሪያዎች ተቀብለው የእርሱን ፈቃድ ለመፈጸም አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ያደርጋሉ።

ይህን መጽሔት አዘውትረህ የምታነብ ሆንክም አልሆንክ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን መንፈሳዊ እሴቶች እንድትመረምር የሚያቀርቡልህን ግብዣ ለምን አትቀበልም። በዚህም መንገድ ‘ይሖዋ ቸር መሆኑን መቅመስና ማየት’ የምትችል ከመሆኑም በላይ የምታገኘውን እውቀት በተግባር በማዋል የዘላለም ሕይወት ማግኘት ትችላለህ።​—⁠መዝሙር 34:​8፤ ዮሐንስ 17:​3

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በፈረንሳይ የሚኖር አራት ትውልድ የይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰብ

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሩት ቅድመ አያቶቿ ካመለኳቸው አማልክት ይልቅ ይሖዋን ለማገልገል መርጣለች